የናሽ ፓፒረስ ጥቅም
አንድን በድሮ ጊዜ የተጻፈ የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ መቼ እንደተጻፈ በትክክል ለማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? በ1948 ዶክተር ጆን ቸ ትረቬር በሙት ባሕር የኢሳይያስ ጥቅሎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩ የተደቀነባቸው ችግር ይህ ነበር። የዕብራይስጡ ፊደላት ቅርጽ ትኩረታቸውን ሳበው። የፊደሎቹ ቅርጽ የሙት ባሕር ጥቅሎችን ዕድሜ ለማወቅ የሚረዳ ቁልፍ ነገር እንደሆነ አወቁ። ግን ከምን ጋር ሊያወዳድሯቸው ይችሉ ይሆን? ከናሽ ፓፒረስ ጽሑፎች ጋር ብቻ ሊያወዳድሯቸው እንደሚችሉ በትክክል ደመደሙ። ለምን? ይህ የድሮ ጽሑፍ ምንድን ነው? ከየትስ መጣ?
የናሽ ፓፒረስ ከዕብራይስጡ ጽሑፍ 24 መስመሮችን የያዙ 7.5 በ12.5 ሴንቲ ሜትር መጠን ያላቸው አራት ቁርጥራጮች ናቸው። ፓፒረሱ ይህን ስሙን ያገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የመሬት ቁፋሮ ጥናት ማኅበር ጸሐፊ የሆኑ ደብልዩ ኤል ናሽ የተባሉ ሰው ከአንድ ግብጻዊ ነጋዴ በ1902 ከገዙት በኋላ ነበር። በቀጣዩ ዓመት በዚያ ማኅበር የሥራ ክንውኖች መዝገብ ውስጥ በኤስ ኤ ኩክ ታተመና በለንደን ላለው የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ መጽሐፍት ቤት ተሰጠ። እስካሁንም እዚያው ይገኛል። የዚህ ፓፒረስ ቁርጥራጭ ጥቅም ከዕድሜው ጋር የተያያዘ ነው። ምሑራን ይህ ፓፒረስ የተጻፈው ከዘአበ በሁለተኛው ወይም በአንደኛው መቶ ዘመን እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ ይህ የዕብራይስጥ ጽሑፍ የያዘ ቅጠል እስከ ዛሬ ከተገኙት ጽሑፎች ሁሉ አንጋፋው ነው ማለት ነው።
ዶክተር ትሬቨር የናሽ ፓፒረስን ባለ ቀለም ስላይድ በፊታቸው ካለው ጥቅል ጋር አወዳደሩት። የእያንዳንዱን ፊደል አጻጻፍና ቅርጽ በጥንቃቄ ተመለከቱ። ያለ ጥርጥር በጣም ተመሳሳዮች ነበሩ። ያም ሆኖ ግን አዲስ የተገኘው የድሮ ጽሑፍ የናሽ ፓፒረስን ያህል የቆየ ዕድሜ ያለው ነው ብሎ ማሰቡ የማይታመን መስሎ ታያቸው። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እሳቸው የደረሱበት አስተሳሰብ ትክክል ሆኖ ተገኘ። የሙት ባሕር የኢሳይያስ ጥቅሎች ከዘአበ በሁለተኛው መቶ ዘመን የተጻፉ ነበሩ!
የናሽ ፓፒረስ ይዘት
በናሽ ፓፒረስ ላይ የተደረገ ምርመራ 24ቱም መስመሮች ከሁለቱም ዳርና ዳር አንድ ቃል ወይም ፊደል የጐደላቸው ስለሆኑ ያልተሟሉ መሆናቸውን ያሳያል። በዘጸአት ምዕራፍ 20 ላይ የሚገኙትን የአሥርቱን ትዕዛዛት ክፍሎችና ከዘዳግም ምዕራፍ 5 እና 6 ውስጥ አንዳንድ ቁጥሮችን ይዟል። ስለዚህ ይህ መደበኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ለልዩ ዓላማ የተዘጋጀ ድብልቅ ጽሑፍ ነው። ለአምላክ ስለሚያቀርበው ሥራ አንድን አይሁዳዊ ለማስታወስ ሲባል የተጻፈ የመመሪያዎች ስብስብ አንድ ክፍል መሆኑ ግልጽ ነው። ሼማ ተብሎ የሚጠራው በዘዳግም 6:4 የሚጀምረው ቅዱስ ጽሑፍ አንድ ክፍል በብዛት ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ይህ ቁጥር እንዲህ ይነበባል፦ “እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አንድ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ነው።”
“ይሖዋ” የሚለውን የአምላክ ስም ከሚወክሉት የሐወሐ ከሚሉት የአማርኛ ፊደላት ጋር ተመሳሳይ ድምፅ የሚሰጡ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (ቴትራግራማተን) በፓፒረሱ የመጨረሻ መሥመር ላይ ባለው በዚህ ቁጥር ውስጥ ሁለት ጊዜ በግልጽ የሚታይ ሲሆን በሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ አምስት ጊዜ ይገኛል። በተጨማሪም የመጀመሪያ ፊደሉ የጎደለው ቴትራግራማተን አንድ ጊዜ ይገኛል።
የሼማ ዓላማ “አምላክ አንድ መሆኑን” ለማጉላት ነበር። በአይሁዳውያን ታልሙድ (በርኮት 19ሀ) መሠረት ኤቻድ (“አንድ”) የተባለው የመደምደሚያው ቃል “እያንዳንዱን ፊደል ጠበቅ በማድረግ ይነበብ ነበር።” (ደብልዩ ኦ ኢ ኦስትርሊ እና ጂ ኤች ቦክስ) ኤቻድ ጎተት ተደርጎ ሲነበብ ሌላ አምላክ የሌለ መሆኑን ያሳያል።
በዛሬው ጊዜ በተለይም በሙት ባሕር በኩል ወደ ኩምራን አቅራቢያ ባሉት ዋሻዎች ውስጥ ከተገኙት ጥቅሎች ውስጥ ናሽ ፓፒረስ በተጻፈበት ጊዜ የተጻፉ ብዙ ጽሑፎች አሉ። ከእነዚህ ጽሑፎች አብዛኞቹ ከዘአበ በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመናት የተጻፉ መሆናቸውን በዝርዝር የተደረጉ ምርምሮች አረጋግጠዋል።a ምንም እንኳን የናሽ ፓፒረስ ከድሮ ጽሑፎች ሁሉ አንጋፋ ጽሑፍ ተደርጎ መታየቱ ያበቃ ቢሆንም አሁንም እንኳን ትልቅ ትኩረት ይስባል። በግብጽ ውስጥ ከተገኙት የድሮ ጽሑፎች ሁሉ አንጋፋው አሁንም እርሱ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 15, 1991 ገጽ 10-13ን ተመልከት።