የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 7/15 ገጽ 3-5
  • ይሖዋ ማን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ማን ነው?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከግብጽ አማልክት የላቀ
  • የሕዝቡን ሕይወት የሚጠብቅ
  • ከተሞክሮ የሚገኙ ትምህርቶች
  • ‘ያህ ድነቴ ሆነልኝ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ሙሴና አሮን ፈርዖንን አነጋገሩት
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • ሙሴ እና አሮን የአምላክን ቃል በድፍረት አውጀዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 7/15 ገጽ 3-5

ይሖዋ ማን ነው?

“ይሖዋ ማን ነው?” ከ3,500 ዓመታት በፊት ኩሩው የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ይህን ጥያቄ ጠይቆ ነበር። እብሪተኛነት “ይሖዋን አላውቅም” በማለት አክሎ እንዲናገር የገፋፋው ይመስላል። በዚያን ጊዜ በፈርዖን ፊት ቆመው የነበሩት ሁለት ሰዎች ግን ይሖዋ ማን እንደሆነ ያውቁ ነበር። እነርሱም ከእስራኤል ከሌዊ ነገድ የመጡ ሥጋዊ ወንድማማቾች የሆኑት ሙሴና አሮን ነበሩ። ሃይማኖታዊ በዓል እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን ወደ ምድረበዳ እንዲሰዳቸው የግብጽን ገዥ እንዲጠይቁ ይሖዋ ልኳቸው ነበር። — ዘጸአት 5:​1, 2 አዓት

ፈርዖን ለጥያቄው መልስ አልፈለገም። በእርሱ ሥልጣን ሥር ካህናት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐሰት አማልክት አምልኮ ያራምዱ ነበር። ፈርዖን ራሱ እንደ አምላክ ተደርጎ ይታይ ነበር! የግብጻውያን አፈ ታሪክ ፈርዖን ራ የተባለው የፀሐይ አምላክ ልጅ እንደሆነና የጭልፊት ራስ የነበረው ሆረስ የተባለው አምላክ ከሞተ በኋላ በአዲስ መልክ ፈርዖን ሆኖ እንደመጣ ይናገራል። ፈርዖን “ኃያል አምላክ” እና “ዘላለማዊ” በሚሉትና በመሳሰሉት የማዕረግ ስሞች ይጠራ ነበር። ስለዚህ “ቃሉን እሰማ ዘንድ . . . ይሖዋ ማን ነው?” ብሎ በንቀት መጠየቁ አያስደንቅም።

ሙሴና አሮን ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት አላስፈለጋቸውም። በዚያ ወቅት በግብጽ ባርነት ይሠቃዩ የነበሩት እስራኤላውያን የሚያመልኩት አምላክ ይሖዋ መሆኑን ፈርዖን ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ፈርዖንና የግብጽ ሕዝብ በሙሉ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ እንደሆነ የሚማሩበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ ስሙንና አምላክነቱን በምድር ላይ ለሚገኝ ለእያንዳንዱ ሰው ያሳውቃል። (ሕዝቅኤል 36:​23) ስለዚህ ይሖዋ አምላክ በጥንቷ ግብጽ ስሙን እንዴት በሰፊው እንዳሳወቀ በመመርመር ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

ከግብጽ አማልክት የላቀ

ፈርዖን በዕብሪተኝነት ይሖዋ ማን እንደሆነ በጠየቀ ጊዜ ያ ሁሉ መዘዝ ይመጣል ብሎ አላሰበም ነበር። ይሖዋ ራሱ በግብጽ ላይ አሥር መቅሰፍቶችን በመላክ ምላሽ ሰጥቶታል። እነዚህ መቅሰፍቶች ለሐገሪቱ ብቻ የታሰቡ አልነበሩም። በግብጽ አማልክትም ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።

መቅሰፍቶቹ ይሖዋ ከግብጻውያን አማልክት የላቀ መሆኑን አሳይተዋል። (ዘጸአት 12:​12፤ ዘኁልቁ 33:​4) ይሖዋ የአባይን ወንዝና በግብጽ የሚገኘውን ውኃ በሙሉ ወደ ደም በለወጠው ጊዜ የነበረውን ሁካታ ገምት! በዚህ ተአምር አማካኝነት ፈርዖንና ሕዝቡ ይሖዋ ሄፕ ከተባለው የአባይ ወንዝ አምላክ የላቀ መሆኑን ተረድተዋል። እንዲሁም አንዳንድ የዓሣ ዘሮች ይመለኩ ስለነበር በአባይ ወንዝ የሚገኙ ዓሦች መሞታቸው ለግብጻውያን ሃይማኖት ታላቅ ሽንፈት ነበር። — ዘጸአት 7:​19–21

ቀጥሎ ይሖዋ በግብጽ ላይ የእንቁራሪቶች መቅሰፍት ሰደደ። ይህም የእንቁራሪት አምላክ የሆነችው ሄክት ዋጋ የሌላት መሆኗን አሳየ። (ዘጸአት 8:​5–14) ትቢያውን ወደ ቅማል የለወጠው ሦስተኛው መቅሰፍት ይህን የይሖዋን ተአምር መልሶ መፈጸም ያቃታቸውን አስማተኞች ግራ አጋብቶአቸዋል። “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” በማለት ጮኹ። (ዘጸአት 8:​16–19) የአስማት ምንጭ ነው እየተባለ ይወደስ የነበረው ቶዝ የተባለው የግብጻውያን አምላክም እነዚህን አውቃለሁ ባዮች ሊረዳቸው አልቻ⁠ለም።

ፈርዖን ይሖዋ ማን እንደሆነ እየተገነዘበ ነው። ይሖዋ ዓላማውን በሙሴ በኩል ማሳወቅ ከዚያም በግብጻውያን ላይ ተአምራዊ መቅሰፍቶችን በመላክ መፈጸም የሚችል አምላክ ነው። እንዲሁም ይሖዋ እነዚያን መቅሰፍቶች እንደፈቃዱ ማምጣትና ማቆም ይችላል። ይሁን እንጂ ፈርዖን ይህን ማወቁ ይሖዋ ያዘዘውን እሺ ብሎ እንዲፈጽም ሊገፋፋው አልቻለም። በዚህ ፈንታ ትዕቢተኛው የግብጽ ገዥ በእልህ ይሖዋን መቃወሙን ቀጠለ።

በአራተኛው መቅሰፍት ላይ ዝንቦች አገሪቱን አጠፉ፣ ቤቶችን ወረሩ፤ እንዲሁም ሹ የተባለው አምላክና አይሲስ የተባለችው የሰማይ አምላክ አምሳል የሆኑለትን በግብፃውያን ይመለክ የነበረውን አየር ሳይሸፍኑት አይቀሩም። እነዚህን ነፍሳት ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የዝንብ መንጋ”፣ “የሚናከስ ዝንብ” ወይም “ጢንዚዛ” ተብሎ ተተርጉሟል። (አዓት፤ ሰፕቱጀንት፤ ያንግ ) ወራሪዎቹ ነፍሳት ጥቁር ጢንዚዛዎች ከሆኑ ግብጻውያን እንደ ቅዱስ አድርገው በሚያዩአቸው ነፍሳት ተመተዋል ማለት ነው። ሕዝቡም ሳይጨፈልቃቸው መራመድ አይችልም ነበር። ያም ሆነ ይህ መቅሰፍቱ ፈርዖንን ስለ ይሖዋ አንድ አዲስ ነገር አስተምሮታል። የግብጽ አማልክት አምላኪዎቻቸውን ከዝንብ መንጋ መከላከል ሲሳናቸው ይሖዋ ግን ሕዝቡን መጠበቅ ችሏል። በዚህና በተከታዮቹ መቅሰፍቶች ግብጻውያን እንጂ እስራኤላውያን አልተጠቁም። — ዘጸአት 8:​20–24

አምስተኛው መቅሰፍት በግብጻውያን ከብቶች ላይ የደረሰ ቸነፈር ነበር። ይህ መቅሰፍት ሀቶርን፣ አፒስንና የላም ቅርጽ ያላትን ነት የተባለችውን አምላክ አዋርዷል። (ዘጸአት 9:​1–7) ስድስተኛው መቅሰፍት በሰውና በእንስሳ ላይ ቡግንጅ ያስከተለ ነበር፤ ይህም የመፈወስ ችሎታ አላቸው እየተባለ በስህተት ይነገርላቸው የነበሩትን ቶት፣ አይሲስ እና ታ የተባሉትን አማልክት ውርደት አልብሷቸዋል። — ዘጸአት 9:​8–11

ሰባተኛው መቅሰፍት እሳት የቀላቀለ የበረዶ ውርጅብኝ ነበር። ይህ መቅሰፍት የመብረቅ ጌታ ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን ረሽፑ የተባለውን አምላክ እና ዝናብንና ነጐድጓድን ይቆጣጠራል የሚባለውን ቶትን አሳፍሯቸዋል። (ዘጸአት 9:​22–26) ስምንተኛው የአንበጣ መቅሰፍት ሰብልን ይጠብቃል ተብሎ ይታሰብ ከነበረው ሚን ተብሎ ከሚጠራው የልምላሜ አምላክ ይሖዋ የላቀ መሆኑን ያሳየ ነበር። (ዘጸአት 10:​12–15) ዘጠነኛው መቅሰፍት በግብጽ ምድር ላይ የሦስት ቀን ጨለማን ያስከተለ ሲሆን እንደ ራ እና ሆረስ ያሉት የግብጻውያን የፀሐይ አማልክት እንዲናቁ አድርጓል። — ዘጸአት 10:​21–23

ዘጠኝ አውዳሚ መቅሰፍቶች ቢደርሱም ፈርዖን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ አሻፈረኝ አለ። አምላክ ለሰውና ለእንስሳ በኩር መሞት ምክንያት የሆነውን አሥረኛ መቅሰፍት ባመጣ ጊዜ የፈርዖን ልበ ደንዳናነት ግብጽን ከፍተኛ ክስረት ላይ ጣላት። ሌላው ቀርቶ እንደ አምላክ ይታይ የነበረው የፈርዖን የበኩር ልጅ እንኳ ሞቷል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘በግብጽ አማልክት ሁሉ ላይ ፍርዱን ፈጽሞባቸዋል።’ — ዘጸአት 12:​12, 29

ይህ ከሆነ በኋላ ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራቸውና “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፣ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፣ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] አገልግሉ፤ እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፣ ሂዱም፣ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ” አላቸው። — ዘጸአት 12:​31, 32

የሕዝቡን ሕይወት የሚጠብቅ

እስራኤላውያን ወጡ፤ ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ፈርዖን በምድረበዳ ያለአንዳች ዓላማ የሚቅበዘበዙ መስሎ ታየው። እርሱና አገልጋዮቹ “እንዳይገዛልን እስራኤልን የለቀቅነው ምን አድርገናል?” ሲሉ ጠየቁ። (ዘጸአት 14:​3–5) ይህን በባርነት ያገለግል የነበረ ሕዝብ ማጣት በግብጽ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ውድቀት ያመጣል።

ፈርዖን ሠራዊቱን ሰበሰበና እስራኤላውያንን እስከ ፊሀሒሮት ድረስ አሳደዳቸው። (ዘጸአት 14:​6–9) ከወታደራዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ እስራኤላውያን በባሕርና በተራሮች ተከበው ስለነበር ሁኔታው ለግብጻውያን የተሻለ ይመስል ነበር። ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመጠበቅ በእነርሱና በግብጻውያን መካከል ደመና በመጋረድ እርምጃ ወሰደ። ግብጻውያን በነበሩበት በኩል “ደመናና ጨለማ ነበረ” ይህም ጥቃት እንዳይሰነዝሩ አግዷቸዋል። በሌላው ወገን ደግሞ ደመናው ብርሃን በመስጠት ለእስራኤላውያን “ሌሊቱን አበራ።” — ዘጸአት 14:​10–20

ግብጻውያን ለመዝረፍና ለማጥፋት ታጥቀው ተነሥተው ነበር፤ ሆኖም ደመናው ይህን እንዳያደርጉ አገዳቸው። (ዘጸአት 15:​9) ደመናው ሲነሣ እንዴት ያለ አስደናቂ ነገር ታየ! ቀይ ባሕር ተከፈለ፤ እስራኤላውያንም በደረቅ መሬት ላይ ወደ ማዶ ተሻገሩ! ፈርዖንና ሠራዊቱ የቀድሞ ባሮቻቸውን ለመያዝና ለመበዝበዝ ቆርጠው በመነሣት በፍጥነት ወደ ባሕሩ ተንጋግተው ገቡ። ይሁን እንጂ ትዕቢተኛው የግብጽ ገዥ ይህን ያደረገው ትምክህቱን በዕብራውያን አምላክ ላይ ጥሎ አይደለም። ይሖዋ መንኰራኩሩ ከሰረገላው እንዲነቃቀል በማድረግ ግብጻውያንን አሸበራቸው። — ዘጸአት 14:​21–25

የግብጽ ኃያላን ሰዎች “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” በማለት ጮሁ። ፈርዖንና ኃያላኑ ይህን የተገነዘቡት ጊዜው ካለፈባቸው በኋላ ነበር። ከአደጋው ነፃ በሆነው በወዲያኛው ዳርቻ ላይ ቆሞ የነበረው ሙሴ እጁን ዘረጋ፤ ውኃው ወደ ቀደሞው ስፍራው ተመለሰና ፈርዖንንና የጦር ሠራዊቱን ሁሉ ገደላቸው። — ዘጸአት 14:​25–28

ከተሞክሮ የሚገኙ ትምህርቶች

እንግዲያው ይሖዋ ማን ነው? ኩሩው ፈርዖን ለዚህ ጥያቄ መልስ አግኝቷል። በግብጽ ላይ የተከሰቱት ሁኔታዎች ይሖዋ ‘ከማይረቡት የአሕዛብ አማልክት’ ፈጽሞ የተለየና እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አረጋግጠዋል። (መዝሙር 96:​4, 5 አዓት) ይሖዋ አስደናቂ በሆነው ኃይሉ ተጠቅሞ ‘ሰማይንና ምድርን ፈጥሯል።’ በተጨማሪም ‘በምልክትና በድንቅ ነገር፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ ሕዝቡን እስራኤልን ከግብጽ ምድር ያወጣ’ ታላቅ ነፃ አውጪ ነው። (ኤርምያስ 32:​17–21) ይህ እርምጃ ይሖዋ ሕዝቡን መጠበቅ እንደሚችል ግሩም አድርጎ ያሳያል!

ፈርዖን እነዚህን ትምህርቶች ከደረሰበት መራራ ተሞክሮ ተምሯል። እንዲያውም የመጨረሻው ትምህርት ሕይወቱን አሳጥቶታል። (መዝሙር 136:​1, 15) “ይሖዋ ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ትሕትናን አሳይቶ ቢሆን ኖሮ እጅግ ጥበበኛ በሆነ ነበር። ከዚያም ይህ ገዥ ከተሰጠው መልስ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ትሑታን የሆኑ ብዙ ሰዎች ይሖዋ ማን እንደሆነ እየተማሩ መሆናቸው ደስ የሚያሰኝ ነው። ይሖዋ ምን ዓይነት ባሕርያት አሉት? ከእኛ የሚፈለግብን ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ስሙ ይሖዋ ለሆነው ብቸኛ አምላክ ያለህን አድናቆት እንዲያሳድግልህ እንመኝልሃለን። — መዝሙር 83:​18 አዓት

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ