የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ሙሴ እና አሮን የአምላክን ቃል በድፍረት አውጀዋል
ትዕይንቱን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፦ የሰማንያ ዓመቱ ሙሴና ወንድሙ አሮን በምድር ላይ እጅግ ኃያል በነበረው በግብፁ ፈርዖን ፊት ቆመዋል። ግብፃውያን ይህን ሰው የሚመለከቱት የአማልክቶቻቸው ወኪል እንደሆነ ብቻ አድርገው አይደለም። እርሱ ራሱ አምላክ ነው ብለው ያምኑ ነበር። የጭልፊት ጭንቅላት የነበረው አምላክ ማለትም ሆረስ በቀጥታ በፈርዖን ተመስሎ እንደመጣ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ሆረስ ከአይሲስና ከኦሲሪስ ጋር በመሆን በግብፃውያን ወንድና ሴት አማልክት ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን ሥላሴ መሥርቶ ነበር።
ፈርዖን ፊት የቀረበ ማንኛውም ሰው በፈርዖን ዘውድ መካከል የተሠራውን የሚያስፈራ የእፉኝት ጭንቅላት ምስል መመልከቱ የማይቀር ነው። ይህ እፉኝት እሳት በመትፋት ማንኛውንም የፈርዖን ጠላት ሊያጠፋ እንደሚችል ይታመን ነበር። ሙሴና አሮን አንድ ለየት ያለ ጥያቄ ይዘው እንደ አምላክ ይታይ በነበረው ንጉሥ ፊት ቀረቡ። ጥያቄው ፈርዖን በባርነት ሥር የነበሩትን እስራኤላውያን ነፃ እንዲለቃቸውና ለአምላካቸው ለይሖዋ በዓል እንዲያደርጉ ነበር።—ዘጸአት 5:1
ፈርዖን እሺ እንደማይል ይሖዋ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ስለዚህ ፈርዖን “ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፣ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም” በማለት አሻፈረኝ ማለቱ ሙሴንና አሮንን አላስደነቃቸውም። (ዘጸአት 4:21፤ 5:2) በዚህ የተነሳ መድረኩ ለአንድ አስደናቂ ግጥሚያ ተዘጋጀ። ሙሴና አሮን ለሁለተኛ ጊዜ ፈርዖን ፊት ሲቀርቡ እውነተኛውንና ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ወክለው እንደቀረቡ የሚያሳይ የሚያስደነግጥ ማስረጃ ለፈርዖን አሳዩ።
አንድ ተአምር ተፈጸመ
አሮን ይሖዋ ባዘዘው መሠረት አንድ ተአምር ፈጸመ። ይህም ተአምር ይሖዋ በግብፅ አማልክት ላይ የበላይ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። በትሩን በፈርዖን ፊት ሲጥለው ወዲያውኑ ትልቅ እባብ ሆነ! ፈርዖን በዚህ ተአምር ግራ በመጋባት መተተኛ ካህናቱን ጠራቸው።a እነዚህ ሰዎች በበትሮቻቸው ተጠቅመው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር መሥራት ችለው ነበር፤ ይህንን ያደረጉት በአጋንንት ኃይል በመጠቀም ነው።
ፈርዖንና ካህናቱ በድል አድራጊነት ቢፈነድቁም ለጊዜው ነበር። የአሮን እባብ እባቦቻቸውን አንድ በአንድ ሲውጥ ፊታቸው ላይ ምን እንደሚነበብ በዓይነ ኅሊናህ ተመልከት! እዚያ የተገኙት ሁሉ የግብፃውያን አማልክት እውነተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር እንደማይተካከሉ ለመገንዘብ ችለዋል።—ዘጸአት 7:8–13 አዓት
ፈርዖን ይህ ከተፈጸመ በኋላም ሐሳቡን አልለወጠም። ፈርዖን “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፣ ከሕዝቤም መካከል ውጡ ሂዱም፣ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ” በማለት ለሙሴና ለአሮን የነገራቸው አምላክ አሥር ኃይለኛ መዓቶች ወይም መቅሰፍቶች በግብፅ ላይ ካወረደ በኋላ ነበር።—ዘጸአት 12:31
ለእኛ የሚሆኑ ትምህርቶች
ሙሴና አሮን ኃያል በሆነው በግብፁ ፈርዖን ፊት ለመቅረብ ያስቻላቸው ምን ነበር? ሙሴ መጀመሪያ ላይ ‘ኮልታፋና አጥርቶ መናገር የማይችል’ እንደሆነ በመናገር በችሎታው እንደማይተማመን ገልጾ ነበር። ይሖዋ እንደሚረዳው ካረጋገጠለት በኋላ እንኳ “ጌታ ሆይ፣ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ” በማለት ለምኗል። በሌላ አባባል አምላክ ሌላ ሰው እንዲልክ አጥብቆ ጠይቆ ነበር። (ዘጸአት 4:10, 13) ሆኖም ይሖዋ ሥራውን ለመፈጸም የሚያስችለውን ጥበብና ጥንካሬ በመስጠት ትሑት በነበረው ሙሴ ተጠቅሟል።—ዘኁልቁ 12:3
በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አምላክና የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ የተሰጣቸውን ትእዛዝ እያከናወኑ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህንን ተልእኮ ከግቡ በማድረስ ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ጥሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ሊኖረንና ያለንን ማንኛውንም ችሎታ በተሻለ ሁኔታ ልንጠቀምበት ይገባናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13–16) በጉድለቶቻችን ላይ ከማተኮር ይልቅ አምላክ የሚሰጠንን ማንኛውንም ሥራ በእምነት እንቀበል። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገንን ብቃትና ብርታት ይሰጠናል።—2 ቆሮንቶስ 3:5, 6፤ ፊልጵስዩስ 4:13
ሙሴ ከሰውም ሆነ ከአጋንንት ተቃውሞ ይደርስበት ስለነበረ መለኮታዊ ድጋፍ አስፈልጎት ነበር። በዚህ የተነሳ “እይ፣ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ” በማለት ይሖዋ ቃል ገብቶለታል። (ዘጸአት 7:1) አዎን፣ ሙሴ መለኮታዊ ድጋፍና ሥልጣን ነበረው። የይሖዋ መንፈስ በሙሴ ላይ ስለነበረ ፈርዖንን ወይም የዚህን ትዕቢተኛ መሪ ጠባቂዎች የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረውም።
እኛም አገልግሎታችንን ለመፈጸም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም ፈጣን ኃይል ላይ መመካት አለብን። (ዮሐንስ 14:26፤ 15:26, 27) መለኮታዊ ድጋፍ ስላለን መዝሙራዊው “በእግዚአብሔር ታመንሁ፣ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?” በማለት የዘመረውን መዝሙር ማስተጋባት እንችላለን።—መዝሙር 56:11
ይሖዋ ሩኅሩኅ ስለሆነ ሙሴ ሥራውን እንዲወጣ ብቻውን አልተወውም። ከዚህ ይልቅ “ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን . . . ከፈርዖን ጋር ይናገራል” ብሎታል። (ዘጸአት 7:1, 2) ይሖዋ ለሙሴ የአቅሙን ያህል ሥራ በመስጠት አፍቃሪ መሆኑን አሳይቷል!
አምላክ የልዑሉ ይሖዋ ምሥክር በመሆናቸው ምክንያት የሚደርሱባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተቀብለው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ያቀፈ ማኅበር ሰጥቶናል። (1 ጴጥሮስ 5:9) እንቅፋቶች ሊያጋጥሙን ቢችሉም የአምላክን ቃል በድፍረት እንደተናገሩት እንደ ሙሴና አሮን እንሁን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “መተተኛ ካህናት” ተብሎ የተተሮጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከአጋንንት የሚበልጥ መለኮታዊ ኃይል አለን የሚሉ ጠንቋዮችን ያመለክታል። አጋንንት በእነዚህ ሰዎች ላይ ኃይል ስለሌላቸው አጋንንት እንዲታዘዟቸው ማድረግ ይችላሉ ተብሎ ይታመን ነበር።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሙሴና አሮን ይሖዋን ወክለው በፈርዖን ፊት በድፍረት ቀርበዋል