የአንባብያን ጥያቄዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ‘አባት ስለ ሌለው ወንድ ልጅ’ [አዓት] ደጋግሞ መጥቀሱ ለሴት ልጆች እንደማያስብ ያመለክታልን?
በጭራሽ አያመለክትም።
የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አምላክ ወላጅ ለሌላቸው ልጆች እንደሚያስብ በሚያሳዩ ብዙ ጥቅሶች ላይ ‘አባት የሌለው ልጅ’ በሚለው ሐረግ ይጠቀማል። አምላክ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች እንደሚያስብ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ላይ በግልጽ አመልክቷል።
ለምሳሌ አምላክ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን [አባት የሌለውን ልጅ አዓት] አታስጨንቁአቸው። ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ፤ ቁጣዬም ይጸናባችኋል፣ በሰይፍም አስገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁም መበለት፣ ልጆቻችሁም ድሀ አደጎች [አባት የሌላቸው ልጆች አዓት] ይሆናሉ።” (ዘጸአት 22:22–24) “አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፣ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፣ በፍርድ የማያደላ፣ መማለጃም የማይቀበል ነውና . . . ለድሀ አደጉና [አባት ለሌለው ልጅና አዓት] ለመበለቲቱ ይፈርዳል።”—ዘዳግም 10:17, 18 [በ1954 በታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር 16, 18]፤ 14:29፤ 24:17፤ 27:19
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በእነዚህ ጥቅሶች ላይ “አባት የለሽ ሕፃን” ወይም “አባትና እናት የሞቱባቸው” በማለት ወንዶችም ሴቶችም ልጆች እንዲጠቃለሉ አድርገዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት አተረጓጎሞች በውስጠ ታዋቂነት የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል (ያትሆህም) የሚያስተላልፈውን ተባዕታይ ጾታ ይተዉታል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ግን “አባት የሌለው ልጅ (ወንድ ልጆች)” በሚለው ትክክለኛ ትርጉም ይጠቀማል። ለምሳሌ በመዝሙር 68:5 ላይ “በቅዱስ ማደሪያው ያለው አምላክ አባት ለሌላቸው ወንድ ልጆች አባት፣ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው” ይላል። በተመሳሳይ ሁኔታ በመዝሙር 68:11 ላይ በውስጠ ታዋቂነት የገባው የዕብራይስጡ ቃል አነስታይ ጾታን እንደሚያመለክት በመገንዘብ “ምሥራቹን የሚናገሩ ሴቶች ትልቅ ሠራዊት ናቸው” ተብሎ ተተርጉሟል።a
ምንም እንኳን ያትሆህም የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ዋና ትርጉሙ “አባት የሌለው ልጅ” ቢሆንም ወላጅ ለሌላቸው ሴት ልጆች አሳቢ አለመሆንን እንደሚያሳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። እዚህ ላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ጥቅሶች የአምላክ ሕዝቦች ለባልቴቶች ማለትም ለሴቶች እንዲያስቡ ማበረታቻ እንደተሰጣቸው ያሳያሉ። (መዝሙር 146:9፤ ኢሳይያስ 1:17፤ ኤርምያስ 22:3፤ ዘካርያስ 7:9, 10፤ ሚልክያስ 3:5) አምላክ አባታቸው የሞተባቸው የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች የርስት ድርሻ እንዲያገኙ ስለተፈረደላቸው ፍርድ የሚገልጸው ታሪክ በሕጉ ውስጥ እንዲጨመር አድርጓል። ያ ደንብ ተመሳሳይ ለሆኑ ሌሎች ሁኔታዎችም ቋሚ ሕግ ሆኗል። በዚህም መንገድ አባት የሌላቸውን ሴቶች ልጆች መብት አስከብሯል።—ዘኁልቁ 27:1–8
ኢየሱስ ለሕፃናት ባሳየው ደግነት የጾታ ልዩነት አላደረገም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ የሚል ቃል እናነባለን፦ “እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። ኢየሱስ ግን አይቶ ተቆጣና፦ ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና። እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው። አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።”—ማርቆስ 10:13–16
እዚህ ላይ “ሕፃናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ወንድነትን ወይም ሴትነትን የማያመለክት ግዑዝ ጾታ ነው። አንድ የታወቀ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት ይህ ቃል “ለወንዶችም ለሴቶችም የሚያገለግል” ነበረ ብሏል። ኢየሱስ ይሖዋ ለልጆች ሁሉ ማለትም ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ልጆች ያለውን ተመሳሳይ ስሜት ማንጸባረቁ ነበር። (ዕብራውያን 1:3፤ ከዘዳግም 16:14 ጋር አወዳድር፤ ማርቆስ 5:35, 38–42) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለው ‘አባት ለሌላቸው ልጆች’ [አዓት] እንክብካቤ ስለማድረግ የተሰጠው ምክር አንዱን ወይም ሁለቱንም ወላጆች ላጡ ልጆች ሁሉ ምን ያህል አሳቢዎች መሆን እንደሚገባን የሚያሳይ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በአይሁዶች ታናክ ላይ እንዲህ ይነበባል፦ “ጌታ ትዕዛዝ ሰጠ፤ ዜናውን የሚያደርሱ ሴቶች እጅግ ብዙ ናቸው።”