የጌታ ራት ስንት ጊዜ መከበር አለበት?
ገና፣ ፋሲካ፣ “የቅዱሳን” በዓሎች። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ብዙ በዓላት ያከብራሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ስንት በዓላት እንዲያከብሩ እንዳዘዛቸው ታውቃለህን? አንድ በዓል ብቻ ነው። ሌሎቹ በዓላት በሙሉ የክርስትና መሥራች ያዘዛቸው አይደሉም።
ኢየሱስ ያቋቋመው በዓል አንድ ብቻ ከሆነ ይህ በዓል በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው። ክርስቲያኖች ልክ ክርስቶስ ባዘዘው መሠረት ማክበር ይኖርባቸዋል። ይህ ልዩ በዓል ምንድን ነው?
ብቸኛው ክብረ በዓል
ኢየሱስ ይህን በዓል ያስተዋወቀው በሞተበት ቀን ነበር። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በመሆን የአይሁዳውያንን የማለፍ በዓል አከበረ። ከዚያም ለማለፍ በዓል ከተዘጋጀው ያልቦካ ቂጣ አነሣና “ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው” በማለት ቆርሶ ሰጣቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” አለና ሰጣቸው። በተጨማሪም “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ።” (ሉቃስ 22:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:24–26) ይህ በዓል የጌታ ራት ወይም የመታሰቢያው በዓል ይባላል። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲያከብሩት ያዘዛቸው ብቸኛው በዓል ይህ ነው።
ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ይህን በዓል ከሌሎች በዓሎቻቸው ጋር አጣምረው እንደሚያከብሩት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ይህን በዓል የሚያከብሩት ኢየሱስ እንዲከበር ካዘዘበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ነው። በጣም ጉልህ ከሆኑት ልዩነቶች አንዱ በዓሉ የሚከበርባቸው ቀናት ብዛት ነው። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየወሩ፣ አንዳንዶች በየሳምንቱ፣ አንዳንዶች ደግሞ እንዲያውም በየቀኑ ያከብሩታል። ኢየሱስ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሎ ለተከታዮቹ በተናገረበት ጊዜ በዓሉ ይህን ያህል በተደጋጋሚ እንዲከበር ፈልጎ ነበርን? ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል እንደሚከተለው ይላል፦ “ይህን እንደ መታሰቢያዬ አድርጉት።” (1 ቆሮንቶስ 11:24, 25) አንድ የመታሰቢያ በዓል የሚከበረው ስንት ጊዜ ነው? ብዙውን ጊዜ በዓመት አንዴ ነው።
በተጨማሪም ኢየሱስ ይህን በዓል ካስጀመረ በኋላ በአይሁዳውያን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ቀን እንደሞተ አስታውስ።a ይህ ቀን አይሁዳውያን በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ከግብጻውያን እጅ ነፃ መውጣታቸውን የሚያስቡበት የማለፍ ቀን ነበር። በዚያ ጊዜ እስራኤላውያን አቅርበውት የነበረው የበግ መሥዋዕት የይሖዋ መልአክ የግብጽን በኩራት ሁሉ በሚመታበት ጊዜ የአይሁድ በኩራት ከመመታት እንዲድኑ አስችሏል።—ዘጸአት 12:21, 24–27
ይህ ስለነገሩ ያለንን ግንዛቤ የሚያዳብርልን እንዴት ነው? ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 5:7) የኢየሱስ ሞት የሰው ልጆች ታላቅ ደህንነት እንዲያገኙ የሚያስችል ታላቅ የማለፍ መሥዋዕት ነው። ስለሆነም የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ለክርስቲያኖች የአይሁድ የማለፍ በዓል ምትክ ነው።—ዮሐንስ 3:16
የማለፍ በዓል ዓመታዊ በዓል ነበር። ስለዚህ የመታሰቢያውም በዓል በዓመት አንዴ ቢከበር ምክንያታዊ ነው። የማለፍ በዓል ማለትም ኢየሱስ የሞተበት ቀን ሁልጊዜ በአይሁዳውያን የኒሳን ወር በ14ኛው ቀን ላይ ይውላል። ስለዚህ የክርስቶስ ሞት በአይሁዳውያን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን በዓመት አንድ ጊዜ መከበር ይኖርበታል። በ1994 ይህ ቀን የሚውለው ቅዳሜ መጋቢት 26 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይሆናል። ታዲያ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ይህን ቀን ልዩ በዓል አድርገው የማያከብሩት ለምንድን ነው? በአጭሩ ታሪክን መመርመር ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።
አደጋ ላይ የወደቀው ሐዋርያዊ ልማድ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የኢየሱስን ሐዋርያት ይከተሉ የነበሩት ክርስቲያኖች የጌታን ራት ልክ ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ያከብሩ እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ በሁለተኛው መቶ ዘመን አንዳንዶች የጌታ ራት የሚከበርበትን ጊዜ መለወጥ ጀመሩ። የመታሰቢያውን በዓል ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን ሳይሆን በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን (አሁን እሁድ ተብሎ በሚጠራው ቀን) ማክበር ጀመሩ። እንደዚህ የተደረገው ለምን ነበር?
የአይሁዶች ቀን የሚቆጠረው ከምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከሚቀጥለው ቀን አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ያለውን ጊዜ ነበር። ኢየሱስ የሞተው ከሐሙስ ማታ አንስቶ እስከ ዓርብ ማታ ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው ኒሳን 14 ቀን በ33 እዘአ ነው። ከሞት የተነሣው በሦስተኛው ቀን እሁድ ጠዋት ነው። አንዳንዶች የኢየሱስ ሞት ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን ሳይሆን በየዓመቱ በአንድ በተወሰነ የሳምንቱ ቀን ላይ እንዲከበር ፈለጉ። በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞተበት ቀን ይልቅ ከሞት ለተነሣበት ቀን የላቀ ግምት ሰጡ። ስለሆነም እሁድን መረጡ።
ኢየሱስ ከሞት የተነሣበት ቀን ሳይሆን የሞተበት ቀን እንዲከበር አዟል። ዛሬ እኛ በምንጠቀምበት የግሪጎሪያን የቀን አቆጣጠር መሠረት የአይሁድ የማለፍ በዓል የሚውልበት ቀን በየዓመቱ ስለሚለዋወጥ የመታሰቢያውም በዓል በየዓመቱ በተለያየ ቀን ላይ መዋሉ ተገቢ ነው። በመሆኑም ብዙዎች የመጀመሪያውን ሥርዓት አጥብቀው በመያዝ የጌታን ራት በየዓመቱ ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን ማክበራቸውን ቀጠሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ ኳርቶዴሲማንስ ወይም በእንግሊዝኛ “ፎርቲንዘርስ” (“አሥራ አራተኞች”) በሚል ቅጽል ስም ይጠሩ ጀመር።
አንዳንድ ምሁራን እነዚህ “ፎርቲንዘርስ” ተብለው ይጠሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የመጀመሪያውን ሐዋርያዊ ምሳሌ ይከተሉ እንደነበረ ተገንዝበዋል። አንድ የታሪክ ጸሐፊ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ፋሲካን [የጌታ ራት የሚከበርበትን] ቀን በተመለከተ በእስያ የሚገኙ የኳርቶዴሲማን አብያተ ክርስቲያናት ይከተሉት የነበረው ልማድ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የመጣ ነበር። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በ2ተኛው መቶ ዘመን የክርስቶስ ሞት ያስገኘውን ከኃጢአት ነፃ የመሆን አጋጣሚ ኒሳን 14 ቀን ያከብሩ ነበር።”—ስቱዲያ ፓትሪስቲካ ጥራዝ 5፣ 1962፣ ገጽ 8
ክርክሩ እያደገ መጣ
በትንሿ እስያ ይኖሩ የነበሩት ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያዊውን ልማድ ሲከተሉ በሮም ያሉት ግን እሁድን ማክበር ጀመሩ። በ155 እዘአ ገደማ በእስያ የሚገኙ ጉባኤዎች ተወካይ የነበረው የሰምርኔሱ ተወላጅ ፖሊካርፕ በዚህና በሌሎች ችግሮች ላይ ለመወያየት ወደ ሮም ሄዶ ነበር። የሚያሳዝነው ግን በዚህ ጉዳይ ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።
የሊዮንስ ተወላጅ የሆነው ኢረንየስ በአንድ ደብዳቤ ላይ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “[የሮሙ] አነሲተስ ከጌታችን ደቀ መዝሙር ከዮሐንስም ሆነ ያውቃቸው ከነበሩት ሌሎች ሐዋርያት ጋር ለብዙ ጊዜ ሲያከብር የኖረውን አከባበር እንዲለውጥ ፖሊካርፕን ሊያሳምነው አልቻለም። አነሲተስ ከእሱ በፊት የነበሩትን ሽማግሌዎች ልማድ መከተል አለብኝ ስላለ ፖሊካርፕም አነሲተስን ሊያሳምን አልቻለም።” (ዩሲቢየስ ጥራዝ 5 ምዕራፍ 24) የፖሊካርፕ አቋም የተመሠረተው ሐዋርያት በተውት የታመነ ማስረጃ ላይ ሲሆን አነሲተስ ግን በሮም የነበሩትን የቀደሙትን ሽማግሌዎች ልማድ እንደተከተለ ልብ በሉ።
ይህ ክርክር እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ ድረስ በጣም ተጋግሎ ነበር። በ190 እዘአ ገደማ አንድ ቪክቶር የሚባል ሰው የሮም ጳጳስ ሆኖ ተመረጠ። ይህ ሰው የጌታ ራት እሁድ ቀን መከበር ይኖርበታል ብሎ ያምን ነበር። ስለሆነም በተቻለ መጠን የብዙ ሌሎች መሪዎችን ድጋፍ ለማግኘት ፈለገ። ቪክቶር በእስያ የሚገኙ ጉባኤዎች እሁድን ማክበር እንዲጀምሩ ብዙ ግፊት አደረገ።
የኤፌሶኑ ፖሊክራተዝ በትንሿ እስያ ያሉትን ክርስቲያኖች ወክሎ መልስ ሲሰጥ ለዚህ ግፊት እንደማይንበረከክ ገልጿል። እንዲህ አለ፦ “ምንም ዓይነት ለውጥ ሳናደርግ፣ ሳንጨምርም ሆነ ሳንቀንስ ይህን ቀን በትክክል እናከብራለን።” ከዚያም ሐዋርያው ዮሐንስን ጨምሮ ብዙ የታመኑ ማስረጃዎችን ከዘረዘረ በኋላ “እነዚህ ሁሉ ወንጌሉ ከሚለው በምንም መንገድ ፈቀቅ ሳይሉ ፋሲካን በአሥራ አራተኛው ቀን ያከብሩ ነበር” ሲል ገለጸ። በማከልም ፖሊክራተዝ እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች፣ እኔ በበኩሌ . . . ዛቻ አልፈራም። እነዚያ ከእኔ የተሻሉት ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል ብለዋል።”—ዩሲቢየስ ጥራዝ 5 ምዕራፍ 24
ቪክቶር በዚህ መልስ አልተደሰተም። አንድ የታሪክ ዘገባ “በእስያ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ አውግዞ የእሱን ሐሳብ የሚደግፉት አብያተ ክርቲያናት በሙሉ ከተወገዙት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ ሰርኩላር እንዳስተላለፈ” ይገልጻል። ይሁን እንጂ “ይህ ዓይነቱ የችኩልነትና የድፍረት እርምጃ ደጋፊዎቹ በነበሩት አስተዋይና ቅን ሰዎች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። እንዲያውም ብዙዎቹ ፍቅርን፣ አንድነትንና ሰላምን ቢጠብቅ . . . እንደሚሻለው አጥብቀው በመግለጽ ጻፉለት።”—ቢንግሀምስ አንቲኩቲስ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ቸርች ጥራዝ 20 ምዕራፍ 5
ክሕደቱ ድርጅታዊ እውቅና አገኘ
ይህን የመሰለ ጠንካራ ተቃውሞ ቢኖርም በትንሿ እስያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የጌታ ራት መቼ ይከበር በሚለው ጉዳይ ላይ የነበራቸው አቋም ድጋፍ እያጣ መጣ። ሌሎች የተለያዩ አስተሳሰቦችም ብቅ ማለት ጀመሩ። አንዳንዶች ከኒሳን 14 ጀምሮ እስከሚቀጥለው እሁድ ድረስ ያለውን ጊዜ በሙሉ ያከብሩ ጀመር። ሌሎች ደግሞ በየሳምንቱ እሁድ ያከብሩ ነበር።
በ314 እዘአ በተደረገው የአርልስ (ፈረንሳይ) ጉባኤ የሮማ ሥርዓት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማስገደድና ማንኛውንም አማራጭ ለማፈን ተሞከረ። አንዳንድ ኳርቶዴሲማኖች ግን በአቋማቸው ጸኑ። አረማዊ ገዥ የነበረው ቆስጠንጢኖስ በግዛቱ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን ነን ባዮች ሁሉ የሚከፋፍለውን ይህንና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት በ325 እዘአ የአብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ ጉባኤ የሆነውን የኒቅያ ጉባኤ ጠራ። ጉባኤውም በትንሿ እስያ የሚገኙ ሁሉ በሮም ካለው አሠራር ጋር እንዲስማሙ የሚያዝ አንድ አዋጅ አወጣ።
የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ትክክል ስላልሆኑ ከሚቀርቡት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱን ልብ እንበል። በኬ ጄ ሂፍል የተዘጋጀው ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ካውንስልስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ለዚህ ከበዓላት ሁሉ ይበልጥ ቅዱስ ለሆነው በዓል የእነዚያን በአሰቃቂ ዓመፆች የተጨማለቁትንና አእምሮአቸው የታወረውን አይሁዶች ልማድ (የቀን አቆጣጠር) መከተል ተገቢ እንዳልሆነ ተገልጾ ነበር።” (ጥራዝ 1፣ ገጽ 322) እንዲያውም ይህን ዓይነቱን አቋም ይዞ መገኘት “ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ላሳዘነው ምኩራብ ‘አሳፋሪ በሆነ መንገድ እንደመገዛት’” ተደርጎ ይታይ ነበር ሲል በስቱዲያ ፓትሪስቲካ ጥራዝ 4 1961 ገጽ 412 ላይ የተጠቀሰው ጄ ጀስተር ይናገራል።
በአይሁድ ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ምክንያት ነው። የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ኢየሱስ በሞተበት ቀን የሚያከብሩ ክርስቲያኖች የአይሁዳውያንን እምነት እንደሚያስፋፉ ሰዎች ይታዩ ነበር። ኢየሱስ ራሱ አይሁድ እንደነበረና ለዚያ ቀን ልዩ ትርጉም ያሰጠው ሕይወቱን ለሰው ልጆች አሳልፎ የሰጠበት ቀን መሆኑ ተረስቷል። ኳርቶዴሲማንስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደ መናፍቆችና ከፋፋዮች ተደርገው በመታየት ይወገዙና ስደት ይደርስባቸው ጀመር። በ341 እዘአ የተደረገው የአንጾኪያ ጉባኤ መወገዝ እንደሚገባቸው ደነገገ። ያም ሆኖ ግን እስከ 400 እዘአ ድረስ ብዙ የ14ኛው ቀን አክባሪዎች ነበሩ። ከዚያም በኋላ ቢሆን ቁጥራቸው ይነስ እንጂ ፈጽመው አልጠፉም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕዝበ ክርስትና ወደ መጀመሪያው የኢየሱስ አከባበር አልተመለሰችም። ፕሮፌሰር ዊልያም ብራይት ሳይሸሽጉ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “አንድ ልዩ ቀን ማለትም የስቅለት ቀን ክርስቶስ የመጨረሻውን ራት ከበላበት ምሽት አንስቶ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ያሳለፋቸውን ሥቃዮች ለማሰብ ስለዋለ የስቅለትን በዓል ቅዱስ ጳውሎስ ከመሥዋዕታዊው ሞት ጋር ባያያዛቸው ‘የፋሲካ’ በዓል አከባበሮች መወሰን ጊዜው አልፎበታል።”—ዘ ኤጅ ኦቭ ዘ ፋዘርስ (የአበው ዘመን) ጥራዝ፣ 1 ገጽ 102
ዛሬስ?
‘እነዚህ ሁሉ ዓመታት ካለፉ በኋላ የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ጊዜ በእርግጥ ልዩነት ያመጣልን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን፣ ልዩነት ያመጣል። ለውጦቹ የተደረጉት ለሥልጣን ይታገሉ በነበሩ ግትር ሰዎች ነው። ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን ከመታዘዝ ይልቅ የራሳቸውን አመለካከት ተከተሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠው ማስጠንቀቂያ በትክክል ተፈጽሟል፦ “ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፣ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ [በክርስቲያኖች መካከል] እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ።”—ሥራ 20:29, 30
አሁን የሚነሣው የመታዘዝና ያለመታዘዝ ጥያቄ ነው። ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንዲያከብሩት ያቋቋመው በዓል አንድ ብቻ ነው። ይህ በዓል መቼና እንዴት መከበር እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል። ታዲያ ይህን ለመለወጥ መብት ያለው ማን ነው? ቀደም ሲል የነበሩ ኳርቶዴሲማንስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበራቸውን አቋም ከመለወጥ ይልቅ ስደትና ውግዘት መቀበል መርጠዋል።
ዛሬም የኢየሱስን ፍላጎት የሚያከብሩና የሞቱን መታሰቢያ እሱ ባቋቋመው ቀን የሚያከብሩ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ስታውቅ ትገረም ይሆናል። በዚህ ዓመት የይሖዋ ምስክሮች መጋቢት 26 ቅዳሜ ከ12 ሰዓት በኋላ በምድር ዙሪያ በሚገኙት የመንግሥት አዳራሾቻቸው ይሰበሰባሉ። ይህ ጊዜ የኒሳን ወር 14ኛ ቀን የሚጀምርበት ነው። በዚህ ጊዜ ታላቅ ትርጉም ባለው በዚህ በዓል ላይ ኢየሱስ እንዲደረግ ያዘዘውን ያደርጋሉ። የጌታን ራት ለምን አብረሃቸው አታከብርም? አንተም በዚህ በዓል ላይ በመገኘት ለኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ያለህን አክብሮት ልታሳይ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአይሁዶች የመጀመሪያ ወር የሆነው ኒሳን የሚጀምረው አዲስ ጨረቃ ከታየችበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ስለዚህ ኒሳን 14 ሁልጊዜ የሚውለው ሙሉ ጨረቃ ላይ ነው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ውድ የሆነው ቤዛ”
የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርት የላቀ ትርጉም ያለው ነገር ነው። ኢየሱስ ራሱ “የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል ተናግሯል። (ማርቆስ 10:45) በተጨማሪም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” በማለት ገልጿል። (ዮሐንስ 3:16) ቤዛው የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ እንዲያገኙና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው መንገድ ይከፍታል።—ዮሐንስ 5:28, 29
የጌታ ራት በሚከበርበት ጊዜ የሚታወሰው ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ነው። የእሱ መሥዋዕት ብዙ ነገሮችን ያከናውናል። አምላካዊ የሆኑ ወላጆች አስተምረው ያሳደጓትና ለብዙ አሥርተ ዓመታት በአምላክ እውነት ውስጥ የተመላለሰች አንዲት ሴት ለቤዛው ያላትን ምስጋና በሚከተሉት ቃላት ገልጻለች፦
“የመታሰቢያውን በዓል በጉጉት እንጠብቀዋለን። በየዓመቱ ይበልጥ ልዩ በዓል ሆኖ ይታየናል። ከ20 ዓመት በፊት የአባቴ አስከሬን በተቀመጠበት ቤት ውስጥ የምወደውን አባቴን ትኩር ብዬ እየተመለከትሁ ሳለሁ ለቤዛው እውነተኛ የሆነ ልባዊ አድናቆት ሲያድርብኝ ትዝ ይለኛል። ከዚያ በፊት ለእኔ ቤዛው እንዲሁ የአእምሮ እውቀት ብቻ ነበር። ሁሉንም ጥቅሶችና ጥቅሶቹ እንዴት እንደሚብራሩ አውቅ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ውድ ቤዛ አማካኝነት ወደፊት የሚከናወኑልንን ነገሮች በማሰብ ልቤ በደስታ የዘለለው በዚያ የሞት አስከፊነት በጣም በተሰማኝ ጊዜ ነበር።”