ዓለም በፍርሃት የተዋጠው ለምንድን ነው?
በፍርሃት ተውጦ መኖር የሚፈልግ ማን ነው? ጤናማ የሆነ ማንኛውም ሰው ሕይወቱንም ሆነ ንብረቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሳያጋጥመው ደህንነቱ ተጠብቆ መኖር ይፈልጋል። በመሆኑም ብዙዎች ወንጀል በከፍተኛ መጠን የሚፈጸምባቸውን ቦታዎች ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ። ሆኖም ፍርሃት የሚያሳድሩ ነገሮች በየትኛውም ስፍራ አሉ።
በኑክሌር መሣሪያዎች ሳቢያ የሚመጡት አደጋዎች የሰው ዘር ለጥፋት ሊዳረግ ይችላል የሚል ፍርሃት ፈጥረዋል። በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣው ዓመፅ ፍርሃትን ያስፋፋል። ብዙዎች ኤድስ የሰውን ሕይወት በመቅጠፍ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የዘመኑ ወረርሽኝ ይሆናል የሚል ፍርሃት አድሮባቸዋል። የአካባቢያችን የተፈጥሮ ገጽታ መውደምም ፍርሃት ካሳደሩት ሌሎች ነገሮች መካከል አንዱ ነው። እነዚህ ፍራቻዎች ለየት ያለ ትርጉም አላቸውን? ወደፊት እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት በማይኖርበት ዓለም ውስጥ እንኖራለን ብለን ተስፋ ማድረግስ እንችል ይሆን?
በዓለም ዙሪያ ያለው ፍርሃት ትልቅ ትርጉም አለው
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቅድሚያ ከተነገረው አንፃር ሲታይ በዛሬው ጊዜ የተስፋፋው ፍርሃት ትልቅ ትርጉም አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻዎቹን ቀኖች አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ ፍርሃትን የሚያሳድሩ ሁኔታዎችን ጠቅሷል። እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል።” ኢየሱስ ስለ “ዓመፃም ብዛት” ተናግሯል። ከ1914 ጀምሮ የተከሰቱት ተወዳዳሪ የሌላቸው ጦርነቶች፣ ረሀብ፣ የምድር መናወጥና ዓመፅ ታላቅ ፍርሃትን አስከትለዋል። የብዙ ሰዎችንም ሕይወት ለሞት ዳርገዋል።—ማቴዎስ 24:7–14
ሌላው ቀርቶ የሰዎች ዝንባሌ እንኳ በዛሬው ጊዜ ላለው ፍርሃት ምክንያት ሆኗል። በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–4 ላይ እንዲህ የሚሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ትንቢታዊ ቃላት እናነባለን፦ “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች በእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ተከበን የምንኖር በመሆኑ ከፍተኛ ፍርሃት መኖሩ አያስደንቅም!
ይህ ዓለም መጠበቅ የሚችለው ነገር
ኢየሱስ ይህን ወቅት በኖህ ዘመን ከነበረው ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ጋር አወዳድሮታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባ እንዲህ በማለት ስለሚናገር በዚያ ወቅት ከፍተኛ ፍርሃት እንደነበረ ምንም አያጠራጥርም፦ “ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።” በመሆኑም “እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና።” (ዘፍጥረት 6:11, 13) ያ ክፉ ዓለም እጅግ ዓመፀኛ ስለነበረ አምላክ በዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ አጠፋው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ጻድቁን ኖህንና ቤተሰቡን ስላፈቀራቸው ከጥፋቱ አዳናቸው።—2 ጴጥሮስ 2:5
እንግዲያው በአሁኑ ጊዜ ያለው የኃይል እርምጃ የተጠናወተው ዓለም ምን ነገር ሊጠብቅ ይችላል? አምላክ ስለ ሌሎች ደህንነት ባለማሰብ የሚፈጸመውን ዓመፅ ይጠላዋል። ይህም በመዝሙራዊው ቃላት ላይ በግልጽ ተንጸባረቋል፦ “እግዚአብሔር ጻድቅንና ኀጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል።” (መዝሙር 11:5) ይሖዋ በኖህ ዘመን የነበረውን ዓመፀኛ ዓለም አጥፍቶታል። እንግዲያው አስፈሪ በሆነ ዓመፅ የተጥለቀለቀውን ይህን ዓለም አምላክ ያጠፋዋል ብለን መጠበቅ አይኖርብንምን?
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመለኮታዊ አነሣሽነት ስለ ክርስቶስ መገኘት ለመናገርና በአሁኑ ጊዜ ያለው ክፉ ዓለም ስለሚደርስበት ከፍተኛ ጥፋት ትንቢት ለመጻፍ ችሏል። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።” ከዚያ በኋላ ጴጥሮስ በሰው ዘር ላይ የሚገዛውን ፍጽምና የጎደለው አገዛዝ ለማመልከት “ሰማያት” የሚለውን ቃልና ኃጢአተኛውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ለማመልከት “ምድር” የሚል ቃል ተጠቅሟል። “ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደነበሩ ወደው አያስተውሉምና” አለ፤ “በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።”—2 ጴጥሮስ 3:3–7
ጳውሎስም ይህንኑ አቅጣጫ በመከተል ክርስቶስና ኃያላን መላእክቱ ‘እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን እንደሚበቀሉና እነዚህ ሰዎች በዘላለም ጥፋት እንደሚቀጡ’ አመልክቷል። (2 ተሰሎንቄ 1:6–9) የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ሕዝቦች “በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር” እንደሚሰበሰቡ ይናገራል፤ እንዲሁም ይሖዋ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ’ ያረጋግጥልናል።—ራእይ 11:18፤ 16:14–16
የፍርሃት ሳይሆን የደስታ ጊዜ ነው
ጻድቅ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ዓለም በቅድሚያ በተናገረው ነገር በፍርሃት ከመርበድበድ ይልቅ የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው። ይሖዋ በቅርቡ ይህን ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜ ያመጣዋል፤ ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው ጽድቅን ለሚያፈቅሩ ሰዎች ጥቅም ነው። በአሁኑ ጊዜ ያለው የነገሮች ሥርዓት በመለኮታዊ ኃይል ከተደመደመ በኋላ ቀጥሎ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? ይኼማ ምን ጥያቄ አለው፤ ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲጸልዩላት ያስተማራቸው ሰማያዊት የአምላክ መንግሥት የምታስተዳድረው አዲስ ሥርዓት ከተፍ ይላል! ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሲሆን ምን ለውጦች ይከናወናሉ ብሎ መጠበቅ ይቻላል?
ጦርነትና ጦርነት ያስከተለው ታላቅ ፍርሃት ያከትማሉ። መዝሙር 46:9 እንዲህ ይላል፦ “[ይሖዋ አምላክ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።” ከዚያም “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ሚክያስ 4:4
ገዳይ የሆኑ በሽታዎች ፍርሃት ማሳደራቸውና ሕይወትን መቅጠፋቸው ያበቃለት ነገር ይሆናል። መለኮታዊው ተስፋ “በዚያም የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም” ይላል። (ኢሳይያስ 33:24) እንዴት ያለ የሚያስደስት ነገር ነው!
በወንጀልና በዓመፅ ሳቢያ የሚከሰተው ፍርሃትም ጊዜ ያለፈበት ነገር ይሆናል። መዝሙር 37:10, 11 እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣል፦ “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”
በዛሬው ጊዜ ያለው ፍርሃት በእውነተኛ ሰላምና ደህንነት ሊተካ የሚችለው እንዴት ነው? በአንድ ጻድቅ መንግሥት ይኸውም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ነው። ያለንበትን ጊዜ አስመልክቶ ዳንኤል 2:44 እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” ይሖዋ የሾመው ንጉሥ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አምላክ ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ሊነግሥ ይገባዋል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:25) የኢየሱስ የሺህ ዓመት የግዛት ዘመን ምድር ለዘላለም ደስተኛ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ገነት እንድትሆን አምላክ መጀመሪያ የነበረው ዓላማ ግቡን እንዲመታ ያደርጋል።—ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 20:6፤ 21:1–5
በገነቲቷ ምድር ላይ አንድ ጤናማ ፍርሃት ይኖራል። እርሱም “እግዚአብሔርን መፍራት” ነው። (ምሳሌ 1:7) እንዲያውም ይህ ፍርሃት ፍቅራዊ ደግነቱንና ጥሩነቱን ስለምናደንቅ አምላክን ላለማሳዘን በመፈለግ ጥልቅ የሆነ አክብሮትና አድናቆት ማሳየት ማለት ስለሆነ አሁንም እንኳን ቢሆን ሊኖረን የሚገባ ነገር ነው። ይህ ፍርሃት በይሖዋ ላይ የማያወላውል እምነት ማሳደርንና ለእርሱ በታማኝነት መታዘዝን የሚጠይቅ ነው።—መዝሙር 2:11፤ 115:11
አስፈሪ ክስተቶች ይህ ዘመን የመጨረሻው ዘመን እንደሆነ ለይተው ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ አምላክን እንደምናፈቅረው ካስመሠከርን ከመፍራት ይልቅ መደሰት እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በመለኮታዊ ኃይል አማካኝነት ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው የሚመጣበት ጊዜ በደጅ መቅረቡን ያሳያሉ። ይህ ዓለም ይሖዋ አምላክ ቃል በገባው ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይተካል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በቅርቡ ጤናማ ያልሆነ ፍርሃት የማይኖርበት ዓለም እንደሚመጣ ምንም አያጠራጥርም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአንዲት መጽሔት ኃይል
ቶማሽ የሚባል አንድ ፖላንዳዊ ወጣት ሕገ ወጥ ድርጊት በመፈጸሙ ከአገር ይሰደዳል። ለስድስት ወራት መኪና እየለመነ፣ በየመንገዱ በድንኳን እያደረና ሥራ እየቀያየረ በአውሮፓ ውስጥ ካንዱ አገር ወደ ሌላው ሲዘዋወር ይከርማል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮው ውስጥ ይጉላላ ነበር።
አንድ ቀን በፖላንድ ቋንቋ የተዘጋጀች አንዲት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በተሰጠችው ጊዜ ቶማሽ ጥያቄው ተመለሰለት። መጽሔቷን ደጋግሞ አነበባት። ይህች መጽሔት እሱ ሲፈልገው የነበረውን እውነት እንደያዘች ተገነዘበ። ቶማሽ እንደገና መኪና እየለመነ 200 ኪሎ ሜትር አቋርጦ በጀርመን አገር በዜልተርስ ታውኑስ ወደሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ ሄደ። ሰኞ ዕለት ማታ እዚያ እንደደረሰ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቱን አውጥቶ “ይህች መጽሔት ስለያዘችው ነገር ይበልጥ የሚያብራራልኝ ሰው እፈልጋለሁ። ማድረግ የሚያስፈልገኝ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
የዚያን ዕለት ማታ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከቶማሽ ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውይይት በማድረግ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ነገሩት። ቶማሽ ይበልጥ ለመማር ከመጓጓቱ የተነሣ በዚያ ሳምንት በየቀኑ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እየሄደ መጽሐፍ ቅዱስንና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አጠና።
ቶማሽ ፖላንድ ውስጥ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ቢያውቅም ወደዚያው ለመመለስ ወሰነ። ስለዚህ ዓርብ ዕለት በሴለተርስ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በመጣ በአራት ቀኑ ወደ አገሩ ለመመለስ ጉዞ ጀመረ። ፖላንድ እንደደረሰም እዚያ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። ቶማሽ ፈጣን መሻሻል አደረገና እየተማረ ስላለው ነገር ለሌሎች በቅንዓት መናገር ጀመረ። ጥቅምት 1993፣ ሴለተርስ ከደረሰ ከአራት ወር በኋላ የይሖዋ ምሥክር በመሆን ተጠመቀ።
አንዲት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ይህን ወጣት የሕይወትን ዓላማ እንዲመረምር ረዳችው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥት ውስጥ፣ ዓለም በፍጹም ዳግመኛ በፍርሃት አይዋጥም