አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና በመስጠት አንዱን የሰው መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት
“በጣም ጥሩ ነው!” “ጎሽ፣ በርታ!” ወይም “ጎበዝ፣ እንኮራብሃለን!” የሚል ከልብ የመነጨ የአድናቆት መግለጫ በተለይ ከአንድ ከምታከብረው ሰው ማግኘት በራስ የመተማመን መንፈስን በእጅጉ ያጎለብታል። ሰዎች ለሠሩት ሥራ ዕውቅና ሲያገኙ ይበረታታሉ። የተሻለ ይሠራሉ፤ እንዲሁም ይበልጥ ደስተኞች ይሆናሉ። በእርግጥም፣ ተስማሚ ምግብ ለሰውነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ ሰዎች ለሠሩት ሥራ ተገቢ ዕውቅና መስጠትም ለአእምሮና ለልብ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና መስጠት ተብሎ የተተረጎመውን ሪኮግኒሽን የተባለውን የእንግሊዝኛ ቃል አንድ መዝገበ ቃላት “አንድን ግለሰብ አሳቢነት ወይም ትኩረት ሊቸረው እንደሚገባ አድርጎ መቀበል” እና “አንክሮ ወይም ትኩረት” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ከአክብሮትና ሌላውን ከፍ አድርጎ ከመመልከት ስሜት ጋር የቀረበ ዝምድና አለው፤ እነዚህ ነገሮች በሚገለጹበት ጊዜ ለአንድ ሰው ምክንያታዊ የሆነ ግምት መስጠትንና ያ ሰው ለሠራው ሥራ ሊሰጠው የሚገባውን ዕውቅና መጠን ያመለክታሉ።
አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው
ማመስገን ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ምስጋናን መግለጽ ምክንያታዊና ትክክል ነው። ኢየሱስ ጌታቸው ንብረቱን በአደራ ስለ ሰጣቸው ባሪያዎች በተናገረው ምሳሌ ላይ ልንከተለው የሚገባንን መንገድ ጠቁሞናል። ለቁሳዊ ንብረቱ የተደረገውን ትክክለኛ አያያዝ በማድነቅ “መልካም፣ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 25:19–23) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ይህ መገለጽ ያለበት ምስጋና ቸል ይባላል። ለሰው ሥራ ዕውቅና አለመስጠት ቅስምን ይሰብራል፤ በራስ አነሳሽነት ከመሥራት እንዲታቀቡም ያደርጋል። አዮና በዚህ መንገድ አስቀምጣዋለች፦ “የሠራኸው ሥራ ዕውቅና ሲያገኝ ጠቃሚ እንደሆንክ፣ እንደምትፈለግና እንደምትደነቅ ሆኖ ይሰማሃል። . . . ለሥራ ያነሳሳሃል። ቸል ከተባልክ ግን ተስፋ ትቆርጣለህ፤ እንዲሁም እንደተተውክ ሆኖ ይሰማሃል።” ፓትሪክ “ከዚህ በኋላ ከፍተኛ የጥራትና የምርታማነት ደረጃ ጠብቆ መሥራት ያዳግታል” ሲል አክሎ ተናግሯል። እንግዲያው ለሰው ሥራ ዕውቅና የምንሰጠው እንዴትና መቼ እንደሆነ ማወቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው። ሁላችንም በአካባቢያችን ባሉት ሰዎች ተቀባይነት እንዳለን ማወቅ የሚያስገኘውን የመረጋጋት ስሜት ለማግኘት በጣም እንፈልጋለን። ይህ የሰው ልጅ የሚያስፈልገው መሠረታዊ ነገር ነው።
የምስጋና ቃል፣ ተጨማሪ ሃላፊነት አልፎ ተርፎም ቁሳዊ ስጦታ አቅምህ የሚፈቅድልህን ሁሉ ማድረግህን እንድትቀጥል ያነሳሳሃል። ይህ ነገር ባል፣ ሚስት፣ ልጅ፣ የጉባኤ አባል ወይም የበላይ ተመልካች ሳይል ለሁሉም የሚሠራ ነው። “ለሠራሁት ሥራ ዕውቅና ሳገኝ” ትላለች ማርጋሬት፣ “ደስ ይለኛል፣ ተፈላጊ እንደሆንኩ ይሰማኛል፣ እንዲሁም የተሻለ ለመሥራት ፍላጎት ያድርብኛል።” አንድሩ ከዚህ አባባል ጋር በመስማማት “መንፈሴ ይታደሳል፤ ይበልጥ እንድሠራም ያነሳሳኛል” ብሏል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና ለመስጠትና ለማክበር በጥሞና ማሰብንና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታን ይጠይቃል።
አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና በመስጠት ረገድ የይሖዋን ምሳሌ ተከተል
ለሌሎች ዋጋማነት ዕውቅና በመስጠት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ አምላክ ነው። ለሠሩት ሥራ ዕውቅና ሊሰጣቸው የሚገቡትን ሰዎች አመስግኗቸዋል። እንደ አቤል፣ ሄኖክና ኖኅን የመሰሉ ሰዎች ለሠሩት ሥራ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 4:4፤ 6:8፤ ይሁዳ 14) ዳዊት ላሳየው የላቀ ታማኝነት ይሖዋ አድናቆት ቸሮታል። (2 ሳሙኤል 7:16) ነቢይ ሆኖ በማገልገል ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ያከበረው ሳሙኤል ፍልስጤማውያንን ድል ለማድረግ የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ላቀረበው ጸሎት አፋጣኝ መልስ በሰጠው በአምላክ አክብሮትን አግኝቷል። (1 ሳሙኤል 7:7–13) ለሠራኸው ሥራ እንዲህ ዓይነት መለኮታዊ ዕውቅና ስታገኝ እንደተከበርክ ሆኖ አይሰማህምን?
ምስጋናና አድናቆት ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና ከመስጠት ጋር በጣም የተያያዙ ነገሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የምናመሰግን’ እንድንሆንና ለእኛ ሲባል የተደረገልንን ነገር እንድናደንቅ አጥብቆ ይመክረናል። (ቆላስይስ 3:15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:18) ምንም እንኳ ይህ በተለይ ለይሖዋ አመስጋኝ መሆንን የሚያመለክት ቢሆንም በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮችም የሚሠራ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ተገንዝቦ ነበር። ፌቤን ‘ለብዙዎች ደጋፊ’ እንደሆነች አድርጎ በመመልከትና ጵርስቅላና አቂላም ለእርሱም ሆነ ለሌሎች ‘ነፍሳቸውን ለሞት በማቅረባቸው’ ለሠሩት ሥራ ዕውቅና ሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 16:1–4) ይህን በግልጽ የቀረበ ምስጋና ሲቀበሉ ምን ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸው እንደነበረ እስቲ ገምተው። ጳውሎስም ቢሆን ሌሎች ለሠሩት ሥራ ዕውቅናን፣ አክብሮትንና ማበረታቻን በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ማግኘቱ ጥሩ ነበር። እኛም ለሚገባቸው ሰዎች ለሠሩት ሥራ ተገቢውን ዕውቅና በመስጠት ይሖዋንና አድናቂ የሆኑ አምላኪዎቹን ልንመስል እንችላለን።—ሥራ 20:35
በቤተሰብ ክልል ውስጥ አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅናን መስጠት
“አንድ ሰው ለሠራው ሥራ መጠነኛ ዕውቅና መስጠት ሕይወትን አስደሳች ለማድረግ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም” በማለት ሚሸል የተባለ አንድ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግል ባል ተናግሯል። “ለሠራችሁት ሥራ ዕውቅና የሰጣችሁን ሰው ምናልባትም እስከ መጨረሻው እንድትወዱት ያደርጋችኋል።” ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን ባል ከባድ የሃላፊነት ሸክም ይሸከማል፤ እንዲሁም የቤተሰቡን ደህንነት የሚመለከቱ ትልልቅ ውሳኔዎችን ይወስዳል። ቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊ፣ ቁሳዊና ስሜታዊ ነገሮች ማሟላት አለበት። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) የቤተሰቡ ራስ በመሆን ለሚያከናውነው አምላክ ለሰጠው ሥራ ተገቢ ዕውቅና ሲሰጠውና ሚስቱ “የጠለቀ አክብሮት” ስታሳየው ምንኛ አመስጋኝ ይሆን!—ኤፌሶን 5:33 አዓት
ብዙ ሰው የማያየው የቤት እመቤት የምታከናውነው ሥራ ቸል ሊባል አይገባውም። ዘመናዊው አስተሳሰብ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ሊያጣጥለውና ሊሰጠው የሚገባውን ክብርና ዋጋ ሊነፍገው ይችላል። አምላክን ግን ያስደስተዋል። (ቲቶ 2:4, 5) አንድ አስተዋይ የሆነ ባል በተለይ የተሻለ ሥራ ባከናወነችባቸው የኑሮ ዘርፎች በሙሉ ሚስቱን በማመስገን በራስነት ሥልጣኑ ሥር፣ ለሠራችው ሥራ ይህን የመሰለውን ዕውቅና ቢሰጣት ምንኛ የሚያነቃቃ ነው! (ምሳሌ 31:28) ሮውና ስለ ባሏ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ለሠራሁት ሥራ ሲያመሰግነኝ ለእርሱ መገዛት፣ እርሱን ከፍ አድርጌ መመልከትና ማክበር ይበልጥ ይቀለኛል።”
አሜሪካዊው አስተማሪ ክርስቲያን ቦቪ በአንድ ወቅት “ፀሐይ ለአበቦች አስፈላጊ እንደሆነች ሁሉ ምክንያታዊ የሆነ ምስጋናም ለልጆች አስፈላጊ ነው” ብለው ነበር። አዎን፣ አንድ ትንሽ ልጅ እንኳ ጠቃሚ የቤተሰቡ አባል እንደሆነ እንዲሰማው የሚያደርግ የማያቋርጥ ማበረታቻ ያስፈልገዋል። በአዳዲስ ስሜታዊና አካላዊ ለውጦች በሚታጀቡት የአንድን ሰው የወደፊት ሕይወት በሚቀርጹት የአሥራዎቹ ዓመታት ራስን በራስ የመምራትና ለሠሩት ሥራ ዕውቅና የማግኘት ከፍተኛ ጥማትን ጨምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ስለ ሰውነት አቋም ከመጠን በላይ የመጨነቅ ሁኔታ አለ። በዚህ ጊዜ በተለይ አንድ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ልጅ በወላጆቹ እንደሚወደድ ሊሰማውና ችግሩን በመረዳትና በሰብዓዊ ደግነት ሊያዝ ይገባዋል። ልክ እንደዚሁም በዕድሜ የገፉ ወላጆችና አያቶች በዕድሜ ቢገፉም እንኳ ጠቃሚነታቸውና የሚወደዱ መሆናቸው እንዳልቀረና ‘በእርጅና ዘመን እንዳልተጣሉ’ የሚያስገነዝባቸው ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 71:9፤ ዘሌዋውያን 19:32፤ ምሳሌ 23:22) ለሰው ሥራ ዕውቅና የመስጠትን አስፈላጊነት በተገቢ ሁኔታ ማሟላት በቤተሰብ ክልል ውስጥ የበለጠ ደስታና ስኬትን ያመጣል።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ዕውቅና መስጠት
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላሉ ለሌሎች ልባዊ ትኩረት መኮትኮትና ላደረጓቸው ነገሮችና ጥረቶች በሚገባ አድናቆትን መግለጽ ያለው ዋጋ ይህ ነው የሚባል አይደለም። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች ዳር ላደረሷቸው ነገሮችና ላሳዩአቸው ጥረቶች በማመስገን ክርስቲያን ሽማግሌዎች ቀዳሚ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። “የአድናቆት ቃላት አንድን ሰው ለማበረታታት እንዲሁም እርካታና ደስታ እንዲያገኝ ለማድረግ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የተገነዘብኩት በርከት ያሉ የእረኝነት ጉብኝቶች ከተደረጉልኝ በኋላ ነበር” ስትል ማርጋሬት ተናግራለች። “አንድ ሰው ለሠራው ሥራ አጠቃላይ የሆነ ዕውቅና ሳያገኝ ሲቀር ምን ነገር እንደሚያጣ ተገንዝቤያለሁ።” በጉባኤ ውስጥ ላሉት በሙሉ እውነተኛና ፍቅራዊ የግል ትኩረት እንድናሳይ የሚያደርግ እንዴት ያለ ጥሩ ምክንያት ነው! ያከናወኑትን ጥሩ ሥራ አድንቁላቸው። በደንብ አመስግኗቸው፤ እንዲሁም አበረታቷቸው። በብዙ ጉባኤዎች፣ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ መንፈሳዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለመትከል ጠንክረው የሚሠሩ ነጠላ ወላጆች አሉ። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ልዩ ምስጋና ሊሰጣቸው ይገባል። አፍራሽ ከሆኑት ነገሮች ይልቅ ገንቢ የሆኑትን ጎኖች ጎላ አድርገህ ተመልከት። ሌሎች ለእነርሱ ያለህን ወንድማዊ የመውደድ ስሜት እንዲረዱ አድርግ። እንደምታስብላቸው እንዲገነዘቡ አድርግ። በዚህ መንገድ አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤውን ለመገንባት መሥራት ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 10:8) ግለሰብ አባሎች ለእነርሱ ጠንክረው ለሚሠሩት ለእንዲህ ዓይነቶቹ የታመኑ ሰዎች ተገቢውን ዕውቅናና አክብሮት በመስጠት አጸፋውን ይመልሳሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:17፤ ዕብራውያን 13:17
ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ ሌላ ጎን ወይም የትኩረት አቅጣጫ አለው። ሰዎች ለሠሩት ሥራ ዕውቅና የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ምንም አያጠያይቅም። በኢየሱስ ዘመን ሃይማኖታዊ መሪዎች ይበልጥ ያሳስባቸው የነበረው ነገር ይህ ሆኖ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ረገድ ያላቸውን አመለካከት ማረም አስፈልጎት ነበር። (ማርቆስ 9:33–37፤ ሉቃስ 20:46) ክርስቲያኖች ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት ሊኖራቸው ይገባል። ለሠሩት ሥራ ዕውቅና የማግኘት ፍላጎት ገደቡን ካለፈ ከፍተኛ መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። (ያዕቆብ 3:14–16) ለምሳሌ ያህል አንድ ሽማግሌ ትዕቢት ከተጠናወተውና ለራሱ ያለውን ከፍ ያለ ግምት ሌሎች እንዲቀበሉት መፈለግ ከጀመረ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል!—ሮሜ 12:3
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የነበሩትን መሰል ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል በጥበብ መክሯቸዋል፦ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በእርሳችሁ ከአንጀት ተዋደዱ። አንዳችሁ ለሌላው አክብሮትን በማሳየት ረገድ ቅድሚያውን ውሰዱ።” (ሮሜ 12:10 አዓት ) እነዚህ ቃላት ክርስቶስ የጉባኤው ራስ መሆኑን ሁልጊዜ መገንዘብ ላለባቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይሠራሉ። ለክርስቶስ የበላይ አመራር መገዛት የሚንጸባረቀው በመንፈስ ቅዱስ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና የ“ታማኝና ልባም ባሪያ” የአስተዳደር አካል በሚሰጠው አመራር አማካኝነት የእሱን መመሪያ በመፈለግ ነው።—ማቴዎስ 24:45–47፤ ራእይ 1:16, 20ንና 2:1ን ተመልከት።
ስለዚህ ሽማግሌዎች በሚሰበሰቡበት እንዲሁም የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ የይሖዋን አመራር ለማግኘት በሚጸልዩበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያላቸውን ውሳኔዎች ለመወሰን ጥረት ያደርጋሉ። ክርስቲያናዊ አቅምንና ቦታን የማወቅ ባሕርይ፣ ገርነትና ትሕትና ማንኛውም ሽማግሌ ራሱን ከፍ ከፍ እንዳያደርግ፣ ወንድሞቹን እንዳይጫንና በስብሰባዎች ላይ የእርሱ ሐሳብ ብቻ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ እንዳይሞክር ያግደዋል። (ማቴዎስ 20:25–27፤ ቆላስይስ 3:12) የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ የሽማግሌዎቹ አካል ሊቀ መንበር ከስብሰባው አስቀድሞ እሱን መሰል የሆኑት ሽማግሌዎች ሐሳቦችን እንዲሰነዝሩ ያደርግና በዝርዝር በሰፈረው በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ በጥሞናና በጸሎት ለማሰብ የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲኖር ቀደም ብሎ አጀንዳውን ያዘጋጃል። በሽማግሌዎቹ ስብሰባ ወቅት የሽማግሌዎቹን ሐሳብ በፈለገው መንገድ ለመቅረጽ አይሞክርም፤ ከዚህ ይልቅ ውይይት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይ ‘የመናገር ነጻነታቸውን’ እንዲጠቀሙበት ለማበረታታት ይጥራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:13 አዓት) መሰል ሽማግሌዎችም በበኩላቸው እያንዳንዱ ሽማግሌ የሚሰጣቸውን ሐሳቦች በጥሞና ማዳመጥና የብዙ ዓመታት ክርስቲያናዊ ልምድ ካካበቱት ሽማግሌዎች የጠለቀ ማስተዋል በደስታ ትምህርት መቅሰም ይኖርባቸዋል።—ዘጸአት 18:21, 22
ይሁን እንጂ የበላይ ተመልካቾች ክርስቶስ አንድን ችግር ለመፍታት ወይም አንድ ትልቅ ውሳኔ ለመውሰድ የሚያስፈልጉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመለገስ በሽማግሌዎቹ አካል ውስጥ ባለ በማንኛውም ሽማግሌ ሊጠቀም እንደሚችል ይገነዘባሉ። እያንዳንዱ ሽማግሌ የጉባኤውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ላበረከተው አስተዋጽኦ ተገቢ ዕውቅና ሲሰጠው በሽማግሌዎቹ አካል ውስጥ ጥሩ መንፈስ ይሠርጻል።—ሥራ 15:6–15፤ ፊልጵስዩስ 2:19, 20
ተገቢውን ዕውቅና ለመስጠትና ለማግኘት ትጋ
ለሠሩት ሥራ ዕውቅና ማግኘት ያንጻል። ያበረታታል፤ እንዲሁም ፍቅርን ያነሳሳል። ሜሪ “ተራ እንደሆንን ቢሰማንም እንኳ በራሳችን እንድንተማመን ማበረታቻ ያስፈልገናል” በማለት ተናግራለች። ሌሎች በየዕለቱ ለሚያሳዩአቸው ጥረቶች ከልብ አመስግናቸው። እንዲህ ማድረግህ ሕይወትን የበለጠ ዋጋማና አስደሳች ያደርግላቸዋል። ወላጆች፣ ልጆች፣ የበላይ ተመልካቾችና የክርስቲያን ጉባኤ አባላት፣ በአነጋገራችሁና በምታሳዩት ጠባይ ዕውቅናን ልታገኙ ትችላላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ታታሪ፣ ልከኛና ትሑት ሰዎችን በመደገፍ ይናገራል። (ምሳሌ 11:2፤ 29:23፤ ዕብራውያን 6:1–12) ራስህን ዝቅ በማድረግ የሌሎችን ዋጋማነት መቀበልን ተማር። ከሌሎች ጋር ስትሠራ ስሜቶቻቸውን ግምት ውስጥ አስገባ። ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፣ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፣እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፣ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ”። (1 ጴጥሮስ 3:8) ይህ ለሰዎች ሥራ ዕውቅና መስጠትን ይጠይቃል፤ በዚህም መንገድ ሰው የሚያስፈልገውን አንዱን መሠረታዊ ነገር ማሟላት ይቻላል።