የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 12/15 ገጽ 23-25
  • ወደ ኢየሱስ መጸለይ ይገባሃልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወደ ኢየሱስ መጸለይ ይገባሃልን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጸሎት ምንድን ነው?
  • ኢየሱስ ያለውን ቦታ አንደምንቀበል በጸሎታችን ማሳየት
  • በኢየሱስ ስም ‘የሚጠሩት’ እንዴት ነው?
  • ኢየሱስ ሊያደርግልን እንደሚችል
  • ኢየሱስን የምታከብረው እንዴት ነው?
  • ተሰሚነት ያላቸው ጸሎቶች
  • አምላክ ስለሚሰማቸው ጸሎቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና አጠናክር
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • ወደ አምላክ የመጸለይ ውድ መብት
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
  • በጸሎት አማካኝነት ከአምላክ ጋር መቀራረብ
    አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 12/15 ገጽ 23-25

ወደ ኢየሱስ መጸለይ ይገባሃልን?

አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጸለይ ይገባል ብለው ያስባሉ። ጀርመን ውስጥ ብዙዎች ልጆች ሳሉ ምግብ ከመመገባቸው በፊት እጃቸውን በማጣመር ኢየሱስን ማመስገን እንዳለባቸው ከወላጆቻቸው ተምረዋል።

እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በሰማይ ከፍተኛ ቦታ እንደያዘ ይገልጻል። ሆኖም ይህ ማለት ወደ እሱ መጸለይ አለብን ማለት ነውን? ለኢየሱስ ካላቸው ፍቅር የተነሣ ወደ እሱ ከሚጸልዩት አንዱ ትሆን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ራሱ ስለ እነዚህ ጸሎቶች ምን ይሰማዋል?

መጀመሪያ ነገር ይሖዋ አምላክ “ጸሎት ሰሚ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚናገር እነዚህ ጥያቄዎች ከነአካቴው ለምን ተነሡ? ስለዚህ እንደ እስራኤላውያን ያሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ሁሉን ወደሚችለው ወደ ይሖዋ አምላክ ብቻ መጸለያቸው ምንም አያስደንቅም።—መዝሙር 5:1, 2 (የ1980 ትርጉም)፤ 65:2

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ወደ ምድር ሲመጣ ነገሮች ተለወጡ እንዴ? በፍጹም፤ በዚያን ጊዜም ቢሆን ጸሎቶች የሚቀርቡት ወደ ይሖዋ ነበር። ኢየሱስ ራሱ በምድር በነበረበት ወቅት በተደጋጋሚ ወደ ሰማያዊ አባቱ ይጸልይ ነበር፤ ሌሎችም እንደዚህ እንዲያደርጉ አስተምሯል። በዓለም ላይ ከፍተኛ ታዋቂነት ካላቸው ጸሎቶች አንዱ የሆነውን አንዳንድ ጊዜ የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ ተብሎ የሚጠራው ሞዴል የሚሆነንን ጸሎት እስቲ አስብ። ኢየሱስ ወደ እሱ እንድንጸልይ አላስተማረንም፤ የሚከተለውን ሞዴል ሰጥቶናል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።”—ማቴዎስ 6:6, 9፤ 26:39, 42

አሁን ጸሎት ምን እንደሆነ በመመርመር ርዕሱን ይበልጥ በቅርብ እንመልከተው።

ጸሎት ምንድን ነው?

እያንዳንዱ ጸሎት የአምልኮ ሥርዓት አንዱ ክፍል ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ በማለት ይህን ያረጋግጣል፦ “ጸሎት ግለሰቡ ለአምላክ ማደሩን የሚገልጽበት፣ ምስጋና፣ ኑዛዜ ወይም ምልጃ የሚያቀርብበት የአምልኮ ሥርዓት አንዱ ክፍል ነው።”

በአንድ ወቅት ላይ ኢየሱስ፦ “ለጌታህ [ለይሖዋ አዓት ] ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ብሏል። ኢየሱስ አምልኮን በተመለከተ አንድ መሠረታዊ እውነትን በጥብቅ ተከትሏል። አምልኮ (ጸሎትንም ይጨምራል) ወደ አባቱ ይሖዋ አምላክ ብቻ መቅረብ እንዳለበት አጥብቆ ተናግሯል።—ሉቃስ 4:8፤ 6:12

ኢየሱስ ያለውን ቦታ አንደምንቀበል በጸሎታችን ማሳየት

ኢየሱስ ለሰው ልጆች መሥዋዕታዊ ቤዛ በመሆን ሞቶ አምላክ ካስነሣው በኋላ ከፍተኛ ቦታ ይዟል። ልትገምት እንደምትችለው ይህ ሁሉ ተቀባይነት ባለው ጸሎት ረገድ ለውጥ አምጥቷል። በምን መንገድ?

ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ ቦታ በጸሎት ላይ ያስከተለውን ትልቅ ለውጥ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።”—ፊልጵስዩስ 2:9–11

‘ጉልበት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከካል ’ ማለት ወደ ኢየሱስ እንጸልያለን ማለት ነውን? በፍጹም አይደለም። እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል “የሚንበረከኩትን አንድ የሚያደርጋቸውን ሁሉንም በአምልኮ የሚያስተባብራቸውን ስም (πᾶν γόνυ) ያመለክታል። ኢየሱስ የተቀበለው ስም ሁሉንም በአንድነት እንዲያከብሩት ያንቀሳቅሳቸዋል።” (ኤ ግራመር ኦቭ ዘ ኢድየም ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት በጂ ቢ ዊነር እንደተጻፈው።) እርግጥ ጸሎት ተቀባይነት እንዲያገኝ ከተፈለገ “በኢየሱስ ስም” መቅረብ አለበት፤ ይሁን እንጂ ጸሎት ወደ ይሖዋ አምላክ መቅረብ ያለበት ሲሆን ለእሱ ክብር የሚያመጣ መሆን ይኖርበታል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ፦ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ” ብሏል።—ፊልጵስዩስ 4:6

መንገድ ወደ አንድ መድረሻ እንደሚወስድ ሁሉ ኢየሱስ ሁሉን ወደሚችለው አምላክ የሚወስድ “መንገድ” ነው። ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ሲል ሐዋርያትን አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:6 ) እንግዲያውስ ጸሎታችንን በኢየሱስ በኩል ወደ አምላክ እንጂ በቀጥታ ወደ ራሱ ወደ ኢየሱስ ማቅረብ የለብንም።a

‘ይሁንና ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስም ሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስን ከምድር ሆነው እንዳነጋገሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገር የለምን?’ በማለት አንዳንዶች ይጠይቁ ይሆናል። ይህ እውነት ነው። ሆኖም እስጢፋኖስም ሆነ ዮሐንስ ኢየሱስን በራእይ አይተው በቀጥታ ስላነጋገሩት እነዚህ ጊዜያት ጸሎትን የሚያመለክቱ አልነበሩም። (ሥራ 7:56, 59፤ ራእይ 1:17–19፤ 22:20) ከአምላክ ጋርም እንኳን እንዲሁ መነጋገር ብቻ ጸሎት እንዳልሆነ አትዘንጋ። አዳምና ሔዋን በኤደን ውስጥ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ አምላክ ሲፈርድባቸው ለከባድ ኃጢአታቸው ሰበብ በማቅረብ ከአምላክ ጋር ተነጋግረዋል። በዚህ መንገድ ከአምላክ ጋር ያደረጉት ንግግር ጸሎት አልነበረም። (ዘፍጥረት 3:8–19) ስለዚህ እስጢፋኖስ ወይም ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር ያደረጉትን ንግግር ለኢየሱስ መጸለይ እንደሚገባን እንደ ማስረጃ አድርጎ መጥቀስ ትክክል አይሆንም።

በኢየሱስ ስም ‘የሚጠሩት’ እንዴት ነው?

አሁንም ቢሆን ወደ ኢየሱስ መጸለይ ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው የሚል ጥርጣሬ በአእምሮህ ውስጥ ይጉላላልን? አንዲት ሴት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ጽፋለች፦ “የሚያሳዝነው እስከ አሁን የቀድሞ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ አልጸለዩም ብዬ ለማመን የሚያበቃ ማስረጃ አላገኘሁም።” በ1 ቆሮንቶስ 1:2 ላይ የተጠቀሱትን “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት በአእምሮዋ ይዛ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ሰው “ከሚጠሩት” የሚለው አነጋገር መጀመሪያ የተጻፈበት ቋንቋ ከጸሎት የተለየ ነገር ማለት ሊሆን እንደሚችል መታወስ አለበት።

የክርስቶስ ስም በየስፍራው ‘የተጠራው’ እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተከታዮች በስሙ ብዙ ተአምራትን በማድረግ እሱ መሲሕና “የዓለም መድኃኒት” መሆኑን በይፋ ማሳወቃቸው ነበር። (1 ዮሐንስ 4:14፤ ሥራ 3:6፤ 19:5) በዚህ ምክንያት ዘ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል ሐረጉን ሲገልጽ “የጌታችንን ስም መጥራት . . . ማለት ወደ እሱ ከመጸለይ ይልቅ ጌትነቱን በሰው ፊት ማሳወቅ ማለት ነው” ብሏል።

በተጨማሪም ክርስቶስን መቀበልና በፈሰሰው ደሙ ማመንም “የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሚጠራበት” መንገድ አንዱ ነው። (ሥራ 10:43ን ከ22:16 ጋር አወዳድር።) በእሱ በኩል ወደ አምላክ ስንጸልይም የኢየሱስን ስም ቃል በቃል እንጠራለን። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ስም መጥራት እንደምንችል ቢጠቁምም ወደ ኢየሱስ መጸለይ እንዳለብን አያመለክትም።—ኤፌሶን 5:20፤ ቆላስይስ 3:17

ኢየሱስ ሊያደርግልን እንደሚችል

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ሲል በግልጽ ቃል ገብቶ ነበር። ይህ ወደ እሱ መጸለይን ይጠይቃልን? አይጠይቅም። ልመናው የሚቀርበው ወደ ይሖዋ ነው፤ ግን በኢየሱስ ስም መሆን አለበት። (ዮሐንስ 14:13, 14፤ 15:16) ልጁ ኢየሱስ ከፍተኛ ኃይሉንና ሥልጣኑን እኛን ለመጥቀም አንዲጠቀምበት አምላክን እንለምናለን።

ኢየሱስ በዘመናችን ካሉት ተከታዮቹ ጋር ግንኙነት የሚያደርገው እንዴት ነው? ጳውሎስ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ የገለጸበት መንገድ እንደ ምሳሌ ሊያገለግል ይችላል። ጉባኤውን በአካል ኢየሱስን ደግሞ በራስ መስሎታል። “ራስ” የሆነው ኢየሱስ የመንፈሳዊ አካሉ ክፍሎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ “በመገጣጠሚያና በጅማት” በኩል ወይም ጉባኤውን መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብና ለመምራት በሚጠቀምባቸው መንገዶችና ዝግጅቶች አማካይነት ያሟላላቸዋል። (ቆላስይስ 2:19 የ1980 ትርጉም) በተመሳሳይ መንገድ በዘመናችን ኢየሱስ ጉባኤውን ለመምራት አስፈላጊ ሲሆንም ለማረም “ስጦታ የሆኑ ወንዶችን” ወይም መንፈሳዊ ብቃት ባላቸው ወንዶች ይጠቀማል። የጉባኤው አባላት በቀጥታ ወደ ኢየሱስ የሚቀርቡበት ወይም ወደ እሱ የሚጸልዩበት ዝግጅት የለም፤ ይሁን እንጂ የኢየሱስ አባት ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ የግድ መጸለይ እንዳለባቸው እሙን ነው።—ኤፌሶን 4:8–12 አዓት

ኢየሱስን የምታከብረው እንዴት ነው?

የሰው ዘሮችን መዳን በተመለከተ ኢየሱስ እንዴት ያለ ቁልፍ ቦታ ይዟል! ሐዋርያው ጴጥሮስ በአድናቆት ሲናገር፦ “መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” ብሏል። (ሥራ 4:12) የኢየሱስ ስም ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ትገነዘባለህን?

ኢየሱስን ራሱን በጸሎት አለማነጋገራችን ቦታውን ዝቅ ማድረጋችን አይደለም። ከዚህ ይልቅ በስሙ ስንጸልይ ኢየሱስ ይከበራል። በተጨማሪም ልጆች ታዛዥ በመሆን ወላጆቻቸውን እንደሚያከብሩ ሁሉ ትእዛዞቹን በተለይም እርስ በርስ ስለ መዋደድ የሚናገረውን አዲሱን ትእዛዝ በመከተል ኢየሱስ ክርስቶስን እናከብራለን።—ዮሐንስ 5:23፤ 13:34

ተሰሚነት ያላቸው ጸሎቶች

ተሰሚነት ያላቸውን ጸሎቶች ለማቅረብ ትፈልጋለህን? እንግዲያው ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ ይህንንም በኢየሱስ ስም አቅርብ። የአምላክን ፈቃድ እወቅ፤ ጸሎቶችህም ይህን እውቀት የሚያንጸባርቁ ይሁኑ። (1 ዮሐንስ 3:21,22፤ 5:14) በሚከተሉት የመዝሙር 66:20 (የ1980 ትርጉም) ቃላት ተበረታታ፦ “ጸሎቴን ስላልናቀና ዘላለማዊ ፍቅሩን ስላልነፈገኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።”

ከላይ እንደተመለከትነው ጸሎት ሁሉን ለሚችለው አምላክ ብቻ የሚቀርብ አንዱ የአምልኮ ክፍል ነው። ጸሎቶቻችንን ሁሉ ወደ ይሖዋ አምላክ በማቅረብ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለን እንድንጸልይ ኢየሱስ የሰጠንን መመሪያ እንደምንከተል እናሳያለን።—ማቴዎስ 6:9

[የግርጌ ማስታወሻ]

a አንዳንዶች ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ በማመን ወደ ኢየሱስ ይጸልዩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ እሱ ራሱ አባቱን ይሖዋን አምልኳል። (ዮሐንስ 20:17) ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ