የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 2/1 ገጽ 20-25
  • “ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስፔይናዊቷ ሙሽራና የስፔኑ የሥራ ምድብ
  • መባረር
  • የመንፈስ ጭንቀትን መዋጋት
  • እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ተሰጥቶን ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • በይሖዋ አገልግሎት የገጠሙን ያልጠበቅናቸው ነገሮች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በ80 ዓመት ዕድሜ የመኖሪያ ሥፍራ መቀየር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ‘ይሖዋን በተስፋ የሚጠባበቁ ደስተኞች ናቸው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 2/1 ገጽ 20-25

“ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም”

ሮናልድ ቴይለር እንደተናገረው

በ1963 የበጋ ወራት ሕይወቴን ለማትረፍ እየታገልኩ ነበር። በባሕር ዳርቻ እየተጓዝኩ ሳለ አንድ የሚከዳ መሬት ረገጥኩና በድንገት ውኃ ውስጥ ጠለቅኩ። ዋና ስለማልችል ከባሕር ዳርቻው ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ልሰጥም ነበር። ጓደኛዬ ያለሁበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ከማውጣቱ በፊት ብቅ ጥልቅ እያልኩ ብዙ ውኃ ጠጥቼ ነበር። አፉን በአፌ ላይ አድርጎ በመተንፈሱ ከሞት ልተርፍ ችያለሁ።

ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ በሚመስሉበት ጊዜም እንኳ ያለመታከትን አስፈላጊነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተረዳሁት በዚህ ጊዜ አልነበረም። ከልጅነቴ ጀምሮ ለመንፈሳዊ ሕይወቴ መጋደል ነበረብኝ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከክርስትና እውነት ጋር የተዋወቅኩት ተስፋ አስቆራጭ በነበረው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር። ከቦምብ ጥቃት አደጋዎች ለመትረፍ ከለንደን ወደ ሌላ ቦታ ከተወሰዱት በሺህ የሚቆጠሩ ልጆች አንዱ ነበርኩ። በዚያን ወቅት ገና የ12 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ጦርነቱ ይህን ያህል አላስጨነቀኝም ነበር፤ ለእኔ እንደ አንድ ልዩ ገጠመኝ ነበር።

በደቡብ ምዕራብ ኢንግላንድ ዌስተን ሱፐር ሜር የሚገኙ አረጋውያን ባልና ሚስት ይንከባከቡኝ ነበር። ወደ ባልና ሚስቱ ቤት ከመጣሁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዳንድ አቅኚ አገልጋዮች ቤታችን ይመጡ ጀመር። የሃርግሪቭዝ ቤተሰብ ነበሩ፤ አራቱም ማለትም ሬጅ፣ ሜብስ፣ ፓሜላና ቫለሪ ልዩ አቅኚዎች ነበሩ። አሳዳጊ ወላጆቼ እውነትን ተቀበሉ፤ እኔም የአምላክ በገና የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ካጠናሁ በኋላ ይሖዋን ለማገልገል ወሰንኩ። ስድስት ሳምንታት ብቻ እንደቆየሁ በስብከቱ ሥራ እንድካፈል ተጋበዝኩ።

ወደ መስከ አገልገሎት የወጣሁበትን የመጀመሪያ ቀን እስካሁን አስታውሳለሁ። ምንም ዝግጅት ሳይደረግ ጥቂት ቡክሌቶች ተሰጠኝና “በዚያኛው መንገድ በኩል ትሠራለህ” ተብሎ ተነገረኝ። የመጀመሪያ የስብከት ቀኔን ያሳለፍኩትም በዚህ መንገድ ነበር። በዚያን ወቅት ብዙውን ጊዜ ኃይለኛ መልእክቶችን በያዙ የሸክላ ማጫወቻዎች ተጠቅመን እንሰብክ ነበር። የሸክላ ማጫወቻዎችን ይዤ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የተቀዱ ንግግሮችን ማጫወት ስችል በጣም ተደስቼ ነበር። በዚያ መንገድ ማገልገልን እንደ ትልቅ መብት እቆጥረው ነበር።

በትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ እመሠክር ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክት ያላቸውን በርካታ መጻሕፍት ሰብስቤ ለርዕሰ መምህሩ ሳበረክት ትዝ ይለኛል። በ13 ዓመቴ አንድ ትልቅ ስብሰባ በተደረገበት ቦታ አቅራቢያ በሚገኝ የገላ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅኩ። ሌላው በጭራሽ የማልረሳው በጦርነቱ ወቅት የተደረገ ትልቅ ስብሰባ በ1941 በሌይስተር ውስጥ ደ ሞንፎር በተባለ አዳራሽ የተካሄደውን ስብሰባ ነበር። በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ወንድም ራዘርፎርድ ያስተላለፈውን የግል መልእክት የያዘ ልጆች የተሰኘ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ የግል ቅጂ ለመቀበል ወደ መድረኩ ወጥቼ ነበር። በስብሰባው ላይ ለተገኙት ለሁሉም ወጣቶች የተሰጠው ቀስቃሽ ንግግር ይሖዋን ለዘላለም ለማገልገል የነበረኝን ፍላጎት አጠናከረልኝ።

በዚህ ሁኔታ በእውነት ውስጥ በማደግ ከአሳዳጊዎቼ ጋር ሁለት አስደሳች ዓመታትን አሳለፍኩ። ይሁን እንጂ 14 ዓመት ሲሞላኝ ወደ ለንደን ተመልሼ መተዳደሪያ ለማግኘት መሥራት ነበረብኝ። ከቤተሰቤ ጋር እንደገና ብቀላቀልም ከመካከላቸው የኔ ዓይነት እምነት የነበረው ማንም ስላልነበረ በመንፈሳዊ ራሴን መቻል ነበረብኝ። ይሖዋ የሚያስፈልገኝን እርዳታ ወዲያውኑ አደረገልኝ። ለንደን ከደረስኩ ከሦስት ሳምንታት በኋላ በአካባቢው ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ሊወስደኝ ይችል እንደሆነ አባቴን ለማስፈቀድ አንድ ወንድም ወደ ቤቴ መጣ። ያ ወንድም አሁን የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ባር ነበር። እሱም በእነዚያ አስቸጋሪ የአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ መንፈሳዊ “አባቶች” ከሆኑኝ መካከል አንዱ ሆነ።—ማቴዎስ 19:29

በለንደን ከሚገኘው የቤቴል መኖሪያ አጠገብ ባለው በክራቨን ቴራስ አዳራሽ ይሰበሰብ ከነበረው የፓዲንግተን ጉባኤ ጋር መሰብሰብ ጀመርኩ። በመንፈሳዊ ወላጆች የሌሉት ልጅ ስለነበርኩ በዕድሜ የገፋው ቅቡዕ ወንድም “አባባ” ሁምፍሬይስ ልዩ ክትትል እንዲያደርግልኝ ተመደበ። በጉባኤው ውስጥ ከሚያገለግሉ ብዙ ቅቡዕ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብ መቻል በእርግጥም ትልቅ በረከት ነበር። ኢዮናዳብ የምንባለው ምድራዊ ተስፋ ያለን ጥቂቶች ነበርን። እንዲያውም እኔ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት በምካፈልበት ቡድን ውስጥ “ኢዮናዳብ” የነበርኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። ምንም እንኳን ከእኩዮቼ ጋር ብዙ ቅርርብ የነበረኝ ባይሆንም ከጎለመሱ ወንድሞች ጋር የነበረኝ ውድ ወዳጅነት ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሮኛል። ምናልባት ከሁሉ ይበልጥ የጠቀመኝ ይሖዋን ማገልገልን በጭራሽ መተው እንደማይገባ ያገኘሁት ትምህርት ሊሆን ይችላል።

በእነዚያ ወቅቶች ቅዳሜና እሑድን በሙሉ ለስብከቱ ሥራ እናውል ነበር። የድምፅ መሣሪያና የመኪና ባትሪ የተገጠመበት “የድምፅ መኪና” ይባል የነበረ ባለ ሦስት ጎማዎች ብስክሌት እንድይዝ ተመደብኩ። ቅዳሜ ቅዳሜ የሸክላ ቅጂዎችን በመክፈት ጥቂት ሙዚቃዎችን ካሰማን በኋላ ከወንድም ራዘርፎርድ ንግግሮች አንዱን ወደምናጫውትባቸው የተለያዩ የመንገድ ማዕዘኖች በባለ ሦስት ጎማው ብስክሌት እጓዝ ነበር። በተጨማሪም ቅዳሜ ቅዳሜ የመጽሔት መያዣ ቦርሳዎቻችንን ይዘን በመንገድ ላይ እንመሰክር ነበር። እሑድ ደግሞ ከቤት ወደ ቤት ለማገልገልና ቡክሌቶችንና የተጠረዙ መጻሕፍትን ለማበርከት ተወስኖ ነበር።

በዕድሜ ከገፉ ቀናተኛ ወንድሞች ጋር የነበረኝ ቅርርብ አቅኚ የመሆን ፍላጎት ቀሰቀሰብኝ። በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ስለ አቅኚነት የተሰጡ ንግግሮችን ሳዳምጥ ይህ ፍላጎቴ ጨመረ። በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያስከተለው አንዱ ትልቅ ስብሰባ በ1947 በለንደን በኧርል ኮርት አዳራሽ ውስጥ የተካሄደው ስብሰባ ነው። ከሁለት ወራት በኋላ ወደ አቅኚነት አገልገሎት ገባሁ፤ ከዚያ ወዲህም ያ “የአቅኚነት መንፈስ” እንዳይጠፋብኝ ስጥር ቆይቻለሁ። እድገት የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ያገኘሁት ደስታ ትክክለኛ ውሳኔ እንዳደረግሁ አረጋገጠልኝ።

ስፔይናዊቷ ሙሽራና የስፔኑ የሥራ ምድብ

በ1957 እዚያው ፓዲንግተን ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት በማገልገል ላይ ሳለሁ ራፋኤላ የምትባል አንዲት ተወዳጅ ስፔይናዊ እህት ተዋወቅሁ። ከጥቂት ወራት በኋላ ተጋባን። ግባችን አብረን በአቅኚነት ማገልገል ነበር፤ ሆኖም በመጀመሪያ የራፋኤላ ወላጆች ለማግኘት ስለፈለግኩ ወደ ማድሪድ ሄድን። ሕይወቴን የለወጠ ጉብኝት ነበር። በማድሪድ ውስጥ እያለን የስፔይን ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ሬይ ዱዚንበሪ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች በብዛት በሚያስፈልጉበት በስፔይን ውስጥ ለማገልገል እናስብ እንደሆነ ጠየቀኝ።

እንዲህ ያለውን ግብዣ እንዴት አንቀበልም እንላለን? በዚህ መንገድ በ1958 በስፔይን ውስጥ አብረን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን። በዚያን ወቅት አገሪቱ በፍራንኮ ትመራ ነበር፤ ሥራችንም ሕጋዊ እውቅና አልነበረውም፤ ይህም ለስብከቱ ሥራ ከባድ እንቅፋት ነበረ። ከዚህም በተጨማሪ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ከስፓኒሽ ቋንቋ ጋር መታገል ነበረብኝ። አንዳንዴ በጉባኤ ውስጥ ካሉ ወንድሞች ጋር በደንብ መግባባት ሳልችል ስቀር በሚሰማኝ ብስጭት ምክንያት ባለቅስም ይህም ሁኔታ አለመታከትን የሚጠይቅ ነበር።

የበላይ ተመልካቾች በጣም ያስፈልጉ ስለነበር ምንም እንኳ የስፓኒሽ ቋንቋ ባልችልም በወር ውስጥ አንድ አነስተኛ ቡድን መርዳት ጀመርኩ። ሥራው በምሥጢር ይሠራ ስለነበር ከሞላ ጎደል እንደ አነስተኛ ጉባኤ በሚንቀሳቀሱ ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ አስፋፊዎችን ባቀፉ ትናንሽ ቡድኖች ተደራጅተን ነበር። መጀመሪያ ላይ ብዙውን ጊዜ አድማጮች የሚሰጡትን መልስ ስለማልረዳ ስብሰባዎችን መምራት በጣም ያስጨንቀኝ ነበር። ይሁንና ባለቤቴ ኋላ ትቀመጥና ግራ እንደተጋባሁ ከተረዳች መልሱ ትክክል መሆኑን በዘዴ ራሷን በማነቃነቅ ትጠቁመኛለች።

ቋንቋዎችን የመማር የተፈጥሮ ተስጥኦ የለኝም፤ አንዳንዴ ማንኛውንም ነገር ይበልጥ በቀላሉ መሥራት ወደምችልበት ወደ ኢንግላንድ ለመመለስ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ ከመጀመሪያ አንስቶ የስፔይን ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅርና ወዳጅነት ቋንቋውን አለመቻሌ ያሳደረብኝን ብስጭት አካክሶልኛል። ይሖዋ ጊዜዬንና ጉልበቴን ላጠፋላቸው በሚገቡ ልዩ ልዩ መብቶችም ባርኮኛል። በ1958 በኒው ዮርክ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ስፔይንን ወክዬ እንድገኝ ተጋበዝኩ። በ1962 በታንጂየር ወስጥ ሞሮኮ በተባለች ከተማ ከተዘጋጀልን የመንግሥት አገልገሎት ትምህርት ቤት ዋጋው የማይተመን ሥልጠና አገኘሁ።

ከቋንቋ ሌላ ያጋጠመኝ ችግር በፖሊስ እያዛለሁ የሚለው የማያቋርጥ ጭንቀት ነበር። የውጪ አገር ዜጋ እንደመሆኔ መጠን ከተያዝኩ ወዲያውኑ ከአገር እንደምባረር አውቃለሁ። አደጋውን ለመቀነስ ስንል ጥንድ ጥንድ ሆነን እንሠራ ነበር። አንዱ ሲመሠክር ሌላው አደጋ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ይከታተላል። በአፓርታማ ሕንፃ ላይ ብዙውን ጊዜ ከላይ ያሉትን አንድ ወይም ሁለት ቤቶች ካንኳኳን በኋላ ሁለት ወይም ሦስት ሕንፃዎችን እንዘልና ሌላ ሁለት ወይም ሦስት ቤቶችን እናንኳኳለን። መጽሐፍ ቅዱስን በብዛት ከመጠቀማችንም በተጨማሪ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የሚበረከቱ ጥቂት ቡክሌቶችን በካፖርታችን ውስጥ እንሸጉጥ ነበር።

ማድሪድ ውስጥ አንድ ዓመት ካሳለፍን በኋላ አንድም የይሖዋ ምሥክር በሌለባት በደቡብ ምዕራባዊው የስፔይን ክፍል በምትገኘው ቪጎ በምትባል ሰፊ ከተማ ተመደብን። ማኅበሩ ለወር ያህል ጎብኚዎች እንድንመስል አብዛኛውን ጊዜ ባለቤቴ እንድትመሠክር ሐሳብ አቀረበ። ብዙ ጥንቃቄ ብናደርግም ስብከታችን ትኩረት ሳበ። በወር ውስጥ የካቶሊክ ቀሳውስት በሬዲዮ ያወግዙን ጀመር። አንድ ባልና ሚስት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራሉ ሲሉ ምእመናኖቻቸውን አስጠናቀቋቸው፤ በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስ የታገደ ያህል ነበር። አንድ የውጪ አገር ዜጋ የሆነ ሰውና ከእሱ በበለጠ ሰዎችን የምታነጋግረው ስፔናዊት ሚስቱ “በፖሊስ በጥብቅ የሚፈለጉ ባልና ሚስት” ናቸው ተባለ!

ቄሶች ከእነዚህ አደገኛ ባልና ሚስት ጋር መነጋገር ራሱ ወዲያውኑ ለቄስ ካልተናዘዙ በቀር ይቅር ሊባል የማይችል ኃጢአት ነው ሲሉ ደነገጉ። እውነትም ከአንዲት ሴት ጋር አስደሳች ውይይት አድርገን ልንደመድም ስንል ሴትዬዋ ሄዳ መናዘዝ እንዳለባት በትሕትና ገለጸችልን። ከቤቷ ስንወጣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እየተቻኮለች ስትሄድ አየናት።

መባረር

ቪጎ ከገባን ከሁለት ወራት በኋላ ድንገት በፖሊስ ተያዝን። የያዘን ፖሊስ ርኅሩህ ስለነበር ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲወስደን በካቴና አላሰረንም። ጣቢያው ስንደርስ አንድ የምናውቀውን ፊት አየን፤ በቅርቡ የመሠከርንላት ታይፒስት ነበረች። እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረን ስታይ እንደተረበሸች ግልጽ ነበር፤ እንዳልወነጀለችን ለእኛ ለመንገር ተቻኮለች። ሆኖም “የስፔይንን መንፈሳዊ አንድነት” አደጋ ላይ ጥላችኋል ተብለን ተከሰስንና ከስድስት ሳምንታት በኋላ ካገር ተባረርን።

መሰናክል ነበር፤ ይሁንና ለመታከት አልዳዳንም። በአይቤሪያን ባሕረ ገብ ምድር ብዙ የሚሠራ ሥራ ነበር። ለሦስት ወራት በታንጂየር ካገለገልን በኋላ ምንም ባልተሠራበት ጂብራልታር በተባለ ሌላ ክልል ተመደብን። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው አገልግሎታችንን ከፍ አድርገን ከተመለከትነው ማገልገላችንን አናቋርጥም፤ ይህም ሽልማት ያስገኝልናል። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 7, 8) ይህ እውነት መሆኑ በእኛ ሁኔታ ታይቷል። በመሠከርንበት የመጀመሪያው ቤት ለጠቅላላው ቤተሰብ ጥናት ጀመርንላቸው። ብዙም ሳይቆይ እያንዳንዳችን 17 ጥናቶችን መምራት ጀመርን። ያስጠናናቸው ብዙ ግለሰቦች ምሥክሮች ሆኑ፤ በሁለት ዓመታት ውስጥም 25 አስፋፊዎች ያሉበት ጉባኤ ተቋቋመ።

ይሁን እንጂ በቪጎ እንደነበረው ሁሉ ቀሳውስት በእኛ ላይ ማሳደም ጀመሩ። የአንግሊካኑ የጂብራልታር ጳጳስ የፖሊሶቹን አለቃ እነዚህ ሰዎች “የማይፈለጉ” ናቸው ሲል አስጠነቀቀው፤ እያደር ማግባቢያው ውጤት አስገኘ። በጥር 1962 ከጂብራልታር ተባረርን። ቀጥሎ የት እንሄድ ይሆን? አሁንም በስፔይን ውስጥ ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ ስለነበር ቀደም ሲል ፖሊስ የያዘብን መዝገብ በቅርብ አይገኝም ብለን ተስፋ በማድረግ ወደ ስፔይን ተመለስን።

አዲሱ ቤታችን ፀሐያማ ሴቪል ከተማ ውስጥ ሆነ። እዚያም ሬይእና ፓት ኪርኩፕ ከተባሉ ሌሎች አቅኚ ባልና ሚስት ጋር ተቀራርበን መሥራት በመቻላችን ተደሰትን። ምንም እንኳ ሴቪል ግማሽ ሚልዮን ነዋሪዎች ያሉባት ከተማ ብትሆንም የነበሩት አስፋፊዎች 21 ብቻ ስለነበሩ ብዙ የሚሠራ ሥራ ነበር። አሁን እዚያ 1,500 አስፋፊዎች ያሏቸው 15 ጉባኤዎች ይገኛሉ። ከአንድ ዓመት በኋላ አንድ ያላሰብነው አስደሳች ነገር ገጠመን፤ በባርሴሎና አካባቢ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ተጋበዝን።

ሥራችን ሕጋዊ እውቅና ባላገኘበት አገር የክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ መሥራት ትንሽ ለየት የሚል ነበር። በየሳምንቱ በአብዛኛው ጥቂት ብቃት ያላቸው ወንድሞች የሚገኙባቸውን ትናንሽ ቡድኖች እንጎበኛለን። እነዚህ ጠንክረው የሚሠሩ ወንድሞች እኛ ልንሰጣቸው የምንችለው ሥልጠናና ድጋፍ ሁሉ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ሥራ ወደነው ነበር! ጥቂት ምሥክሮች ባሉበት አካባቢ (ያውም ካሉ) ለበርካታ ዓመታት ከሠራን በኋላ ብዙ የተለያዩ ወንድሞችንና እህቶችን ለመጎብኘት በመቻላችን ተደስተናል። ከዚህም በተጨማሪ በባርሴሎና የስብከቱ ሥራ ይበልጥ ቀላል ነው፤ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይፈልጉ ነበር።

የመንፈስ ጭንቀትን መዋጋት

ይሁንና ከስድስት ወራት በኋላ ሕይወቴ ድንገት ተለወጠ። በባሕር ዳርቻ አጠገብ ባሰለፍነው የመጀመሪያ የእረፍት ጊዜያችን ቀደም ሲል የተገለጸው አደጋ ሲያጋጥመኝ አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ሊከሰት ነበር። ለመስጠም ጥቂት ሲቀረኝ ከደረሰብኝ ድንጋጤ በአካላዊ ሁኔታ ወዲያውኑ ማገገም ብችልም አደጋው በነርቮቼ ላይ የማይፋቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።

ለጥቂት ወራት በክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለመቀጠል ከታገልኩ በኋላ በመጨረሻ ለሕክምና ወደ ኢንግላንድ ለመመለስ ተገደድኩ። ከሁለት ዓመታት በኋላ የክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ወደ ቀጠልንበት ወደ ስፔይን ለመመለስ የሚያስችል በቂ ጤንነት አገኘሁ። ሆኖም በዚህ ሥራችን የቀጠልነው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። የባለቤቴ ወላጆች በጠና ታመሙና እነሱን ለማስታመም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን አቆምን።

በ1968 ከባድ የነርቭ ሕመም ሲያጋጥመኝ ኑሮ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። ራፋኤላና እኔ በጭራሽ እንደማልድን ያሰብንበት ጊዜ ነበር። በሌላ መንገድ ቢሆንም እንደገና የሰጠምኩ ያህል ነበር! የመንፈስ ጭንቀቱ በውስጤ አሉታዊ ስሜቶች እንዲያድሩብኝ ከማድረጉም በላይ ኃይሌን አሟጠጠብኝ። በጣም ይደክመኝ ስለነበር ያለማቋረጥ ለማረፍ ተገደድኩ። ያን ጊዜ ሁሉም ወንድሞች ችግሬን አልተረዱም፤ ሆኖም ይሖዋ ይረዳው እንደነበር አውቃለሁ። የተጨነቁ ሰዎችን ችግር የሚገነዘቡትንና እርዳታ የሚለግሱትን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት አስደሳች ርዕሶች ማንበብ ትልቅ እርካታ አምጥቶልኛል።

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሁሉ ባለቤቴ የማያቋርጥ የብርታት ምንጭ ሆናልኝ ነበር። በእርግጥም ችግሮችን በአንድነት መቋቋም የጋብቻን ማሰሪያ ያጠነክራል። የራፋኤላ ወላጆች ሞቱና ከ12 ዓመታት በኋላ ጤንነቴ ስለተሻሻለ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መመለስ እንደምንችል ተሰማን። በ1981 እንደገና በክልል ሥራ እንድናገለግል መጋበዛችን ያላሰብነው አስደሳች ነገር ነበር።

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሎት ስናገለግል ከነበረበት ጊዜ ወዲህ በስፔይን ውስጥ ብዙ ቲኦክራሲያዊ ለውጦች ተካሂደዋል። አሁን የስብከቱ ሥራ በነፃነት የሚካሄድ ስለሆነ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ራሴን ማስተካከል ነበረብኝ። ሆኖም እንደገና በክልል የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ትልቅ መብት ነበር። አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያሉም በአቅኚነት መቀጠላችን ችግር ያጋጠማቸውን አቅኚዎች ለማበረታታት አስችሎናል። አብዛኛውን ጊዜም ሌሎች አቅኚ እንዲሆኑ ለመርዳት ችለናል።

በማድሪድና በባርሴሎና ውስጥ ለ11 ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ካገለገልን በኋላ የጤና ችግር ሥራችንን እንደገና እንድንለውጥ አድርጎናል። ሽማግሌ በመሆን ማገልገል በምችልባት ሳላማንካ በተባለች ከተማ በልዩ አቅኚነት ተመደብን። በሳላማንካ ያሉ ወንድሞች ጥሩ አቀባበል አደረጉልን። ከአንድ ዓመት በኋላ ጽናታችንን የሚፈትን ሌላ ችግር ገጠመን።

ራፋኤላ ባልታወቀ ምክንያት በጣም ገረጣችና ምርመራ ሲደረግ የአንጀት ካንሰር እንደያዛት ተረጋገጠ። አሁን እኔ በርትቼ የምችለውን ያህል ባለቤቴን መርዳት አለብኝ። መጀመሪያ ላይ የተሰማን ስሜት ፍርሃት ያስከተለ ጥርጣሬ ነበር። ራፋኤላ ትተርፍ ይሆን? በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ወቅቶች በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመናችን ለመጽናት ረድቶናል። ራፋኤላ የተደረገላት የቀዶ ሕክምና አመርቂ ስለነበር ተደስቻለሁ፤ ካንሰሩ ዳግመኛ እንዳይነሣባት ተስፋ አደረግን።

በስፔይን ውስጥ ባሳለፍናቸው 36 ዓመታት ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ቢያጋጥሙንም በዚህ መንፈሳዊ እድገት በሚታይበት ዘመን መኖር ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነው። በ1958 የነበረው 800 አስፋፊዎች የነበሩበት ትንሽ ቡድን ዛሬ ከ100,000 በላይ የሆኑ የአስፋፊዎች ሠራዊት ሲሆን ተመልክተናል። ሌሎች እውነትን እንዲቀበሉና በመንፈሳዊ እንዲጎለምሱ በመርዳታችን፣ ባልና ሚስት ሆነን አንድ ላይ በመሥራታችንና ሕይወታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንደተጠቀምንበት ስለሚሰማን ያገኘናቸው ደስታዎች ያጋጠሙንን ችግሮች ያስ ንቃሉ።

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ “ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 4:1) ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስብ እንዳልታክት ያደረጉኝ ብዙ ነገሮች እንዳሉ አምናለሁ። በልጅነቴ ትኩረት ሰጥተው የተከታተሉኝ የታማኝ ቅቡዓን ወንድሞች ምሳሌነት ጥሩ መሠረት ሆኖልኛል። እንደ እኔው ዓይነት ግቦች ያላት የትዳር ጓደኛ ማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ ስጨነቅ ራፋኤላ ታበረታታኝ ነበር፤ እሷ ስትጨነቅ ደግሞ እኔ እንዲሁ አደርግ ነበር። ለዛ ያለው ጨዋታም ትልቅ እሴት ነው። ከወንድሞች ጋር መቀላለድና በራስ ላይ መሳቅ መቻል በሆነ መንገድ ችግሮችን ያቃልላል።

ከሁሉም በላይ ግን ፈተናዎች ሲያጋጥሙን መጽናት የይሖዋን ኃይል ማግኘትን ይጠይቃል። ሁልጊዜ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን እችላለሁ” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት አስታውሳለሁ። ይሖዋ ስለሚረዳን መቼም ቢሆን መታከት የለብንም።—ፊልጵስዩስ 4:13 አዓት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሮናልድና ራፋኤላ ቴይለር በ1958

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በስፔይን ውስጥ በእገዳ ሥር የተካሄደ ስብሰባ (1969)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ