እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ ተሰጥቶን ነበር
ሪቻርድ ጉንተር እንደተናገረው
ጊዜው መስከረም 1959 ነበር። ጁሊዮ ሲዛር በተባለችው የኢጣሊያ የመንገደኞች መርከብ ተሳፍረን ከኒው ዮርክ ተነስተን ስፔይን ውስጥ ወደምትገኘው ካዲዝ ከተማ ለመድረስ የአትላንቲክን ውቅያኖስ እያቋረጥን ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ከባለቤቴ ሪታ እንዲሁም ባልና ሚስት ከሆኑት ሌሎች ሁለት ሚስዮናውያን ማለትም ከፖል እና ኤቭሊን ሃንደርትማርክ ጋር በዚህ አይቤሪያዊ አገር እንዳገለግል መድቦኛል። እዚያም ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይጠብቁናል። ነገር ግን ወደ ሚስዮናዊነት ሥራ የገባነው እንዴት ነበር?
እኔና ሪታ በኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን በ1950 ተጠመቅን። ብዙም ሳይቆይ አንድ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቁ እጃችን ውስጥ ማስገባት አለብን ብለን ወሰንን። የነበርንበት ጉባኤ የአገልግሎት ክልሉን ሊሸፍኑ የሚችሉ በቂ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት። ስለዚህ የምሥራቹ ሰባኪ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውረን ለማገልገል ራሳችንን የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለብን ተሰማን። በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በ1958 የበጋ ወቅት በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የሚስዮናዊነት አገልግሎት ለመጀመር አመለከትን።
ብዙም ሳይቆይ ወደ መጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንመጣ ተጋበዝን፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ሚስዮናዊ ሆነን ወደ ስፔይን ለመጓዝ ዝግጅት ላይ ነበርን። ጊዜያችን ብዙ ዝግጅቶች በማድረግ ተጣቦና በደስታ ስሜት ተውጠን ስለነበር ምን ተሰጥቶን እንደነበር በዚያን ጊዜ አልተገነዘብንም ነበር። ኢየሱስ እጅግ ውድ የሆነ ዋጋ ስላለው ዕንቁ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 13:45, 46) ምንም እንኳ የኢየሱስ ምሳሌ የእኛን የሚስዮናዊነት አገልግሎት የሚያመለክት ባይሆንም በሚስዮናዊነት እንድናገለግል የተሰጠን ልዩ መብት ለእኛ እንዲህ ካለው ዕንቁ ጋር የሚወዳደር ነበር። ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የነበረንን ይህንን ውድ የአገልግሎት ስጦታ አሁን ይበልጥ እናደንቀዋለን።
የማይረሳ ጊዜ
በዚያን ጊዜ የጊልያድ ትምህርት ቤት ኮርስ የሚካሄደው በኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ በፊንገር ሐይቆች አካባቢ በሚገኝ ውብ ገጠራማ ስፍራ ነበር። እዚያም ከዚህ ዓለም ጉዳዮችና ችግሮች ራሳችንን አግልለን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመጠመድና እውነተኛ በሆነ ክርስቲያናዊ ኅብረት ስድስት ግሩም ወራት አሳለፍን። አብረውን ይማሩ የነበሩት ባልደረቦቻችን አውስትራሊያን፣ ቦሊቪያን፣ እንግሊዝን፣ ግሪክንና ኒው ዚላንድን ጨምሮ ከብዙ የዓለም ክፍሎች የመጡ ነበሩ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የምንመረቅበት ቀን ደረሰ። ነሐሴ 1959 ወደ ተለያዩ ሚስዮናዊ የአገልግሎት ምድቦቻችን ለመሄድ በመርከብ ስንሳፈር የተሰነባበትነው እያለቀስን ነበር። ከአንድ ወር በኋላ የስፔይንን መሬት ረገጥን።
አዲስ ባሕል
ከግዙፉ የጅብራልታር ቋጥኝ አጠገብ ወደሚገኘው ደቡባዊው አልጄሲራስ ወደብ ደረስን። በዚያው ምሽት አራታችንም ማለትም እኔና ሪታ እንዲሁም ሃንደርትማርክና ባለቤቱ በባቡር ወደ ማድሪድ ተጓዝን። በምሥጢር የሚሠራው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ አባላት ከሆኑ ወንድሞች ጋር እስከምንገናኝ ድርስ ሜርካዶር ወደ ተባለ ሆቴል ሄድን። ስፔይን በጄኔራሊስሞ ፍራንሲስኮ ፍራንኮ አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ነበረች። ይህም ማለት በአገሪቱ ሕጋዊ እውቅና የነበረው ሃይማኖት የሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነበር። የትኛውንም ሌላ ሃይማኖት በይፋ መከተል በሕግ የተከለከለ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው የስብከት ሥራ ታግዶ ነበር። ሃይማኖታዊ ስብሰባ ማድረግ እንኳ ተከልክሎ ስለነበር በጊዜው በስፔይን ውስጥ በ30 ጉባኤዎች የሚገኙ ወደ 1,200 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ መሰብሰብ አይችሉም ነበር። በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በድብቅ እንሰበሰብ ነበር።
ስፓኒሽ ቋንቋ መማርና መናገር
መጀመሪያ ፈተና የሆነብን ነገር ቋንቋውን መማር ነበር። በመጀመሪያው ወር በየቀኑ ለ11 ሰዓታት ያህል ስፓኒሽ ቋንቋ በመማር እናሳልፍ ነበር። በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ለ4 ሰዓታት ትምህርት ይሰጠናል፤ ከዚያም ለ7 ሰዓታት በግላችን እናጠናለን። በሚቀጥለው ወር የጠዋቱ ፕሮግራም እንደ ቀድሞው ሲቀጥል የከሰዓት በኋላውን ጊዜ ግን ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው ስብከት ማዋል ጀመርን። ሁኔታውን ልትገምቱ ትችላላችሁ? እኔና ሪታ ቋንቋውን ገና ሳናውቀው ካርድ ላይ በተጻፉ በቃል ባጠናናቸው መግቢያዎች ብቻ ከቤት ወደ ቤት ብቻችንን እንሄድ ነበር።
ቫሌካስ በሚባል ማድሪድ ውስጥ በሚገኝ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ አንድ በር እንዳንኳኳሁ አስታውሳለሁ። ምናልባት የምናገረው እንዳይጠፋኝ ካርዴን በእጄ ይዤ በስፓኒሽ ቋንቋ እንዲህ አልኩ፦ “እንደምን አደሩ? ክርስቲያናዊ ሥራ እየሠራን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል (ጥቅስ አነበብንላቸው።) ይህ ቡክሌት እርስዎም እንዲኖርዎት እንፈልጋለን።” ሴትየዋ ግራ በመጋባት ተመለከተችንና ቡክሌቱን ወሰደችው። ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግላት ወደ ቤት እንድንገባ ጋበዘችንና ገባን፤ እኛ ስንናገር ዝም ብላ ትመለከተን ነበር። በምንችለው ውስን ስፓኒሽ ቋንቋ ተጠቅመን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናት ጀመር፤ በጥናቱ ወቅት ዝም ብላ ታዳምጠናለች እንዲሁም ትመለከተናለች። መጀመሪያ ያነጋገርናት ቀን የተናገርነው ምን እንደሆነ ባይገባትም ዲዮስ (አምላክ) የሚለውን ቃል ሰምታ እንደ ነበር መጨረሻ ላይ ነገረችን፤ እንዲሁም ጥሩ ነገር መሆኑን ለማወቅ ለእርሷ ይህ በቂ እንደ ነበር ገለጸችልን። ከጊዜ በኋላ ሰፋ ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ቀሰመችና ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።
ስፓኒሽ ቋንቋ መማር ፈጽሞ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። በከተማው ውስጥ ስዘዋወር የግሶችን አረባብ አሰላስልባቸዋለሁ። አንድ ሳምንት በቃሌ ያጠናሁትን በሚቀጥለው ሳምንት እረሳዋለሁ! ይህም ተስፋ ያስቆርጠኝ ነበር። ብዙ ጊዜያት ተስፋዬ ወደመሟጠጡ ደረጃ ደርሶ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲህ ያለ የተሰባበረ ስፓኒሽ ቋንቋ እየተናገርኩ በመካከላቸው ግንባር ቀደም ሆኜ ስሠራ የስፔይን ወንድሞች በጣም ታጋሾች መሆን ነበረባቸው። በአንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንድ ወንድም ከመድረክ ሆኜ እንዳነበው በአንድ ወረቀት ላይ በእጅ የተጻፈ ማስታወቂያ ሰጠኝ። የእጅ ጽሑፉን ማንበብ ስላስቸገረኝ “ነገ ወደ ስታዲየሙ ሙሌታስ (ምርኩዛችሁን) ይዛችሁ እንድትመጡ” በማለት አስታወቅሁ። መነበብ የነበረበት ግን “ነገ ወደ ስታዲየሙ ማሌታስ (ጓዛችሁን) ይዛችሁ እንድትመጡ” ተብሎ ነበር። በስብሰባው ላይ የነበሩት ሰዎች ሳቁ፤ እኔም አፈርኩ።
ማድሪድ ውስጥ መጀመሪያ ያጋጠሙን ፈተናዎች
በማድሪድ ያሳለፍናቸው የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት በእኔና በሪታ ስሜት ላይ በጣም ችግር ፈጥረውብን ነበር። አገራችንና ጓደኞቻችን በጣም ይናፍቁን ነበር። ከዩናይትድ ስቴትስ ደብዳቤ በደረሰን ቁጥር ይበልጥ በናፍቆት ባሕር እንዋጥ ነበር። እነዚያ በናፍቆት እንዋጥባቸው የነበሩ ጊዜያት ከባድ ነበሩ፤ ቢሆንም አልፈዋል። አገራችንን፣ ቤተሰባችንንና ጓደኞቻችንን የላቀ ዋጋ ያለውን ውድ ዕንቁ ለማግኘት ስንል ትተናቸዋል። ካለንበት ሁኔታ ጋር መላመድ አስፈልጎን ነበር።
ማድሪድ ውስጥ መኖር የጀመርነው በአንድ አሮጌ አልቤርጎ ውስጥ ነበር። የራሳችን የሆነ ክፍል ነበረን እንዲሁም በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ እናገኛለን። ክፍሏ አነስተኛ ጨለማ ክፍል ስትሆን ፍራሾቹ ከደረቅ ሳር የተሠሩ ናቸው። የወሩ ኪራይ በየወሩ የምናገኘውን አነስተኛ የወጪ መተኪያ ሙሉ በሙሉ ይጨርሰው ነበር። ሁልጊዜ ምሳችንን እኩለ ቀን ላይ እዛው እንበላለን፤ እንዲሁም ቤቱን ያከራየችን ሴት እንዳይቀዘቅዝብን ራታችንን ምድጃ ውስጥ ትታልን ስለምትሄድ ራታችንን አምሽተን እንበላለን። ቢሆንም ቀንና ማታ በእግራችን ስለምንጓዝ በጣም ይርበን ነበር። ከተሰጠን የወጪ መተኪያ ላይ ምንም ገንዘብ ካልተረፈን ካለን ውስን ተቀማጭ ገንዘብ ላይ ወጪ አድርገን መግዛት የምንችለው ርካሽ የሆነ ቸኮላታ ነበር። ይሁን እንጂ የማኅበሩ የዞን የበላይ ተመልካች ከጎበኘን በኋላ ይህ ሁኔታ ወዲያውኑ ተለወጠ። ያለንበትን መጥፎ ሁኔታ ተመለከተና የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ሆኖ የሚያገለግል ትንሽ አፓርታማ መፈለግ እንደምንችል ነገረን። ይህም ኩሽና ውስጥ መሬት ላይ በተቀመጠ ክብ ሳፋ ውስጥ ቆሞ ሰውነትን ከመታጠብ እጅግ የተሻለ ነበር። በዚህ ጊዜ መታጠቢያ፣ ምግብ የምናስቀምጥበት ማቀዝቀዣ እንዲሁም ምግባችንን የምናዘጋጅበት የኤሌክትሪክ ምድጃ ነበረን። ለተደረገልን አሳቢነት በጣም አመስጋኞች ነን።
ማድሪድ ውስጥ ያጋጠሙን ግሩም ተሞክሮዎች
ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው ስብከት የሚከናወነው በጥንቃቄ ነበር። ማድሪድ ውስጥ በየዕለቱ የሚኖረው ትርምስ ጥቅም ነበረው፤ በግርግሩ ውስጥ እንጋረድ ስለነበር በቀላሉ ሰው ዓይን ውስጥ አንገባም። የውጪ አገር ዜጎች መሆናችን እንዳይታወቅ እንደ ሌሎቹ ለመልበስና እነርሱን ለመምሰል እንጥራለን። ከቤት ወደ ቤት ስንሰብክ እንጠቀምበት የነበረው ዘዴ ወደ አንድ መኖሪያ ሕንፃ ውስጥ በመግባት በር እናንኳኳና ከግለሰቡ ጋር ከተነጋገርን በኋላ ሕንጻውን፣ መንገዱንና አካባቢውን ጥሎ መሄድ ነበር። የቤቱ ባለቤት ለፖሊስ ደውሎ ሊነግርብን ስለሚችል ጎረቤት መቆየት ጥበብ አልነበረም። እንዲያውም ምንም እንኳ ፖልና ኤቭሊን ሃንደርትማርክ በዚህ ዘዴ በመጠቀም በኩል ጥንቁቆች የነበሩ ቢሆኑም በ1960 ተይዘው ከአገሪቱ ተባረሩ። ወደ አጎራባቿ ፖርቱጋል ሄደው ፖል በድብቅ በሚሠራው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት እየሠራ ለብዙ ዓመታት አገለገሉ። ፖል በአሁኑ ጊዜ በካሊፎርኒያ ግዛት ሳን ዲያጎ ከተማ ውስጥ የከተማ የበላይ ተመልካች ነው።
ነገር ግን ጎድሎብን የነበረውን ነገር የሚያሟላ ሁኔታ ተፈጽሟል። ፖርቱጋል ተመድበው የነበሩ ስድስት ሚስዮናውያን ከስድስት ወራት በኋላ ፖርቱጋልን ለቀው እንዲወጡ ታዘዙ! ይህም አስደሳች ለውጥ አምጥቷል ምክንያቱም ከእኛ ጋር በአንድ የጊልያድ ኮርስ የተካፈሉት ኤሪክ እና ሄዜል ቤቭሪጅ ፖርቱጋልን ለቀው ወደ ስፔይን እንዲመጡ ተነገራቸው። ስለዚህ የካቲት 1962 እንደገና ወደ ሜርካዶር ሆቴል ሄድን፤ በዚህ ጊዜ የሄድነው ግን ኤሪክና ሄዜል ስለመጡ እነርሱን ለመቀበል ነው።
እኔና ሪታ ከሃይማኖታዊ ግብዝነት ጋር የተያያዘ ተሞክሮ ያጋጠመን ማድሪድ ውስጥ ባሳለፍናቸው በእነዚሁ የመጀመሪያ ዓመታት ነበር። በርናርዶ እና ማሪያ ከተባሉ ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እናጠና ነበር፤ እነዚህ ባልና ሚስት በርናርዶ ሊያገኛቸው በቻለው ውድቅዳቂ የግንባታ ቁሳቁሶች በተሠራች ትንሽ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። እናስጠናቸው የነበረው ማታ አምሽተን ነበር፤ ከጥናቱ በኋላ ዳቦ፣ ወይንና ቺዝ ወይም ያላቸውን ማንኛውንም ነገር ይጋብዙን ነበር። የሚጋብዙን ቺዝ የአሜሪካ ቺዝ እንደሚመስል አስተዋልኩ። አንድ ቀን ማታ ከጥናቱ በኋላ ቺዙ የመጣበትን ጣሳ አመጡት። እላዩ ላይ በትልልቅ የእንግሊዝኛ ፊደላት “ከአሜሪካ ሕዝብ ለስፔይን ሕዝብ የተሰጠ—መሸጥ አይቻልም” ተብሎ ተጽፎበታል። ይህ ድኻ ቤተሰብ ይህንን ቺዝ እንዴት ሊያገኝ ቻለ? መንግሥት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቺዙን ለድሆች እንድታከፋፍል አድርጓል። ነገር ግን ቄሱ ይሸጠው ነበር!
ለወታደሮች የሰጠነው ፍሬያማ ምሥክርነት
ብዙም ሳይቆይ ለእኛና ለሌሎች ብዙ ሰዎች ከፍተኛ በረከት ያስገኘ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። በዩ ኤስ አየር ኃይል የጦር ሰፈር የሚኖር ዎልተር ኪዳሽ የተባለ አንድ ወጣት ሄደን እንድናነጋግር ከቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ደረሰን። የአየር ኃይሉ ማዕከል የሚገኘው ከማድሪድ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኘው ቶሬኾን ነበር። እርሱንና ሚስቱን ሄደን አነጋገርናቸው፤ እዚያም ከእነርሱና የአየር ኃይሉ ባልደረቦች ከሆኑ ከሌሎች ባልና ሚስት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን።
በዚህ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ የአየር ኃይል ሠራተኞች የሆኑ ወደ አምስት የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እመራ ነበር። እርግጥ ሁሉም የሚያጠኑት በእንግሊዝኛ ነበር። ከእነዚህም መካከል ሰባቱ ከጊዜ በኋላ ተጠመቁ፤ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሱ በኋላ ደግሞ ከመካከላቸው አራቱ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆኑ።
በዚህ ወቅት በሥራችን ላይ በተጣለው ዕገዳ የተነሳ መጽሐፎችን፣ መጽሔቶችንና መጽሐፍ ቅዱሶችን ወደ አገሪቱ ውስጥ ለማስገባት የነበሩት መንገዶች በጣም ጥቂት ነበሩ። ቢሆንም በቱሪስቶችና በአንዳንድ አሜሪካውያን ሰዎች አማካይነት ጥቂት ጽሑፎች ይገቡልን ነበር። በምሥጢር የሚሠራውን የጽሑፍ ማከማቻ ሥራ እንዳንቀሳቅስ በቅርንጫፉ ተመደብኩ። የጽሑፍ ማከማቻው የሚገኘው በቫሌካስ ከአንድ የጽሕፈት መሣሪያዎች መደብር ጀርባ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ነበር። የመደብሩ ባለቤት ሚስት የይሖዋ ምሥክር ናት። የመደብሩ ባለቤት የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ለሥራችን አክብሮት ነበረው፤ ከዚህም በላይ ለራሱና ለሥራው በጣም አስጊ ቢሆንም ይህንን በስተጀርባ የሚገኝ ቦታ የታሸጉ ጽሑፎችን ለማዘጋጀትና በመላው አገሪቱ ወደሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ለመላክ እንድገለገልበት ፈቀደልኝ። ይህ ክፍል መጋዘን እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም አቧራማ፣ ዝርክርክ ያለና በካርቶኖች የተሞላ ክፍል ሆኖ መታየት ስለነበረበት በፍጥነት ተገጣጥመው ለሥራ ሊውሉ የሚችሉና ወዲያውኑ ሊደበቁ የሚችሉ መጽሐፍ መደርደሪያዎችንና አንድ ጠረጴዛ መሥራት ነበረብኝ። በቀኑ መጨረሻ ላይ ሁሉም ከመጋዘኑ እስኪወጡ ድረስ እጠብቅ ነበር፤ ከዚያም የታሸጉትን ጽሑፎች ይዤ በፍጥነት እሄድ ነበር።
በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ጉባኤዎች እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ያሉትንና ሌሎችንም መንፈሳዊ ጽሑፎች በማሰራጨቱ ሥራ ላይ መካፈሉ ታላቅ መብት ነበር። እነዚህ ጊዜያት በጣም አስደሳች ጊዜያት ነበሩ።
ሪታ 16 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ደስታ አግኝታለች፤ ከእነርሱም መካከል ግማሽ የሚያክሉት የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ዶሎሬስ ባለባት የልብ ሕመም የተነሳ ቀዝቃዛውን የክረምት ወራት በአልጋ ውስጥ የምታሳልፍ ወጣት ባለትዳር ሴት ናት። በጸደይ ወቅት ከመኝታዋ ተነስታ በመጠኑ መንቀሳቀስ ትችላለች። ዶሎሬስ ጠንካራ እምነት ነበራት፤ ስለዚህም ፈረንሳይ ውስጥ በቱሉዝ ከተማ የሚደረገው የአውራጃ ስብሰባችን ሲደርስ እርሷም ለመሄድ ጓጓች። የልቧ ጤንነት ካለበት አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር ይህንን ማድረጉ ጥበብ እንዳልሆነ ዶክተሩ አስጠነቀቃት። የቤት ልብስና ነጠላ ጫማ አድርጋ ምንም ጓዝ ሳትይዝ ባሏን፣ እናቷን እንዲሁም ሌሎቹን ለመሰናበት ወደ ባቡር ጣቢያ ሄደች። ዓይኖቿ እንባ አቀረሩ፣ ጥለዋት ሲሄዱ ቆማ ለማየት ስላልቻለች ባቡሩ ላይ ተሳፈረችና ወደ ፈረንሳይ ሄደች! ሪታ ይህንን አላወቀችም ነበር። ነገር ግን ስብሰባው ላይ ዶሎሬስን ሞቅ ካለ ፈገግታ ጋር ስትመለከታት ያላሰበችው ነገር ነበር!
አንድ ለየት ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
ይህንን የማድሪድ የአገልግሎት ምድባችንን ታሪክ ስለ ዶን ቤኒግኖ ፍራንኮ “ኤል ፕሮፌሰር” ሳንነግራችሁ መቋጨት አንችልም። የአካባቢው ተወላጅ የሆነ ምሥክር አንድ የተከበሩ ሽማግሌ እንድናነጋግር ወሰደኝ፤ እኝህ ሰው ከሚስታቸው ጋር በአንድ በተጎሳቆለ አፓርታማ ውስጥ ይኖራሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርን። ዓመት ከመንፈቅ ያህል ካጠኑ በኋላ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ጠየቁ።
እኚህ የተከበሩ ሽማግሌ ማለትም ዶን ቤኒግኖ ፍራንኮ በጊዜው በስፔይን አምባ ገነን ገዢ የነበረው የፍራንሲስኮ ፍራንኮ የአጎት ልጅ ናቸው። ዶን ቤኒግኖ ምንጊዜም ነፃነት የሚፈልጉ ሰው ነበሩ ማለት ይቻላል። በስፔይኑ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ሪፑብሊኩን በመደገፍ ጦርነቱን አሸንፈው የካቶሊክ አምባገነናዊ አገዛዝ የመሠረቱትን የአጎታቸውን ልጅ ይቃወሙ ነበር። ዶን ቤኒግኖ ከ1939 ጀምሮ የመሥራት መብታቸውን ተነፍገው በጣም የተጎሳቆለ ኑሮ ይኖሩ ነበር። የስፔይን አምባገነን ገዢ ጄኔራሊሲሞ ፍራንሲስኮ ፍራንኮ ኮዲሎ ያጎት ልጅ የይሖዋ ምሥክር የሆኑት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር።
ያልተጠበቀ ጥሪ
በ1965 የስፔይኑ ቅርንጫፍ ቢሮ ባርሴሎና ውስጥ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወርን እንድናገለግል ጋበዘን። ይህ ማለት በማድሪድ ውስጥ በጣም ቀርበናቸው የነበሩትን እነዚያን አፍቃሪ ወንድሞች በሙሉ ትቶ መሄድ ማለት ነው። አሁን ይህ ለእኔ አዲስ ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን ፈተናም ነበር። ሁልጊዜ ችሎታዬን ስለምጠራጠር ሁኔታው አስፈሪ ነበር። በዚህ የአገልግሎት መስክ ውጤታማ እንድሆን ያስቻለኝ ይሖዋ እንደሆነ አሳምሬ አውቃለሁ።
በእያንዳንዱ ሳምንት አንድ ጉባኤ መጎብኘት ማለት በወንድሞች ቤት መኖር ማለት ነው። ቋሚ መኖሪያ የለንም፤ በየሁለት ሳምንቱ ማለት ይቻላል ከአንዱ ቤት ወደ ሌላ ቤት እንዛወራለን። ይህ በተለይ ለአንዲት ሴት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ባርሴሎና ውስጥ የሚኖሩት ሆሴ እና ሮሰር ኤስኩዴ ለብዙ ተከታታይ ቀናት አብረናቸው እንድንቀመጥ ጠየቁን። ይህም ንብረታችንን የምናስቀምጥበትና እሁድ እሁድ ማታ የምናርፍበት ቋሚ ቦታ ለማግኘት ስላስቻለን እነዚህ ወንድሞች ከፍተኛ ፍቅር አሳይተውናል።
እኔና ሪታ የሚቀጥሉትን አራት ዓመታት በሜዲትራኒያን ባሕር ዳር በምትገኘው ካታሎኒያ ክፍለ ሀገር በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ አሳለፍን። ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ስብሰባዎቻችን የሚደረጉት በድብቅ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲሆን ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው ስብከታችንም የሰዎችን ትኩረት ላለመሳብ በጥንቃቄ ይከናወን ነበር። አንዳንድ ጊዜ በተለይም የወረዳ ስብሰባ ለማድረግ በምንፈልግበት ጊዜ መላው ጉባኤ አንድ ላይ ሆነን እሁድ ዕለት “ለሽርሽር” ወደ ጫካ እንሄድ ነበር።
ሥራቸውንና ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ጉባኤዎች ዘወትር አንድነት ያላቸውና በትጋት የሚሠሩ እንዲሆኑ ለማድረግ ይደክሙ የነበሩትን አያሌ ታማኝ መንፈሳዊ ወንድሞችን ምንጊዜም እናደንቃቸዋለን። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ሥራው ከዋናው ከተማ ውጪ ባሉ ከተማዎች እንዲስፋፋ በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋል። ይህም በ1970 በስፔይን የተጣለው ዕገዳ ከተነሳና የሃይማኖት ነፃነት ከተሰጠ በኋላ ለተገኘው ታላቅ ጭማሪ መሠረት ሆኗል።
የሚስዮናዊነት ሥራችንን ማቋረጥ
በስፔይን ባሳለፍናቸው አሥር ዓመታት አግኝተነው የነበረው ይሖዋን የማገልገል ልዩ በረከት በወላጆቻችን ሁኔታ የተነሳ እክል ገጠመው። በተለያዩ ጊዜያት እናቴንና አባቴን ለመጦር ስንል የአገልግሎት ምድባችንን ለቀን ወደ አገራችን ለመመለስ ምንም ያህል አልቀረንም ነበር። ነገር ግን በወላጆቻችን አቅራቢያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የተነሳ አገልግሎታችንን በስፔይን ለመቀጠል ቻልን። አዎን፣ በእነዚያ ዓመታት በሚስዮናዊነት ሥራ የማገልገል መብት መካፈል የቻልነው የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች በማስቀደሙ ሥራ ከእኛ ጋር የሚካፈሉ የሌሎች ሰዎች እርዳታ ስለታከለበት ነበር።
በመጨረሻ ታኅሣሥ 1968 ላይ እናቴን ለመጦር ስንል ወደ አገራችን ተመለስን። በዚሁ ወር አባቴ አረፈ፤ አሁን እናቴ ብቻዋን ቀረች። በዚህ ጊዜም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል በመጠኑ ነፃ ስለነበርኩ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለማገልገል የአገልግሎት ምድብ ተቀበልን፤ ቢሆንም በዚህ ጊዜ የተሰጠኝ የአገልግሎት ምድብ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር። ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት በስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ ወረዳዎች ውስጥ አገለገልን። ምንም እንኳ እጅግ ውድ የሆነ ዋጋ ያለውን የሚስዮናዊነት ዕንቁ ብናጣም ሌላ ዕንቁ አግኝተን ነበር።
የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና ዓመፅ በሚካሄድበት ቦታ መስበክ
በዚህ ጊዜ ከተማዎች ውስጥ በሚገኙ ወንጀል ባጥለቀለቃቸው ሰፈሮች ውስጥ ከሚኖሩ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጋር እናገለግል ነበር። እንዲያውም በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራችን በመጀመሪያው ሳምንት ብሩክሊን ኒው ዮርክ ውስጥ ሪታ ቦርሳዋን ተቀምታለች።
አንድ ጊዜ እኔና ሪታ ከሌሎች በርከት ያሉ ወንድሞች ጋር ሆነን በኒው ዮርክ ከተማ በአንድ ሌላ ሰፈር ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን ስብከት እያከናወንን ነበር። አንድ መታጠፊያ ላይ ስንደርስ ማንም በማይኖርበት በአንድ ሕንፃ ግድግዳ ላይ ባለ ቀዳዳ ፊት ለፊት ጥቂት ሰዎች ተሰልፈው ተመለከትን። በመንገዱ ላይ ፈጠን ብለን ትንሽ እንደተራመድን አንዱ ወጣት በእግረኛ መንገዱ ላይ ቆሞ ወደ እኛ እንደሚመለከት ልብ አልን። በወዲያኛው መታጠፊያ ላይ ደግሞ ሌላ ወጣት የፖሊስ መኪና መምጣቱን ይጠብቃል። በዕፅ አስተላላፊዎች ገበያ መካካል እየሄድን ነበር! የመጀመሪያው ጠባቂ ደነገጠ፤ ነገር ግን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሲመለከት እፎይ አለ። ሆኖም መጠበቂያ ግንብ መያዜ ብቻ ፖሊስ ላለመሆኔ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም ነበር! ከዚያም በስፓኒሽ ቋንቋ “ሎስ አታላያስ! ሎስ አታላያስ!” (መጠበቂያ ግንቦች! መጠበቂያ ግንቦች!) በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ። እነማን እንደሆንን በመጽሔቱ ስላወቁ ሁሉም ነገር በሰላም አለፈ። በአጠገቡ ሳልፍ “ብዊኖስ ዲአስ፣ ኮሞ ኤስታ?” (እንደምን አደራችሁ?) አልኩኝ። ‘ጸልይልኝ’ ሲል መለሰልኝ።
አስቸጋሪ ውሳኔ
በ1990 ከእናቴ አጠገብ ምንጊዜም መለየት እንደሌለብኝ ግልጽ ሆነ። በተጓዥነት ሥራ ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት አድርገን ነበር፤ ነገር ግን ያገኘነው ማስተዋል ሁለቱንም ኃላፊነቶች በአንድነት መፈጸም እንደማንችል ግልጽ አደረገልን። እናቴ ፍቅራዊ እንክብካቤ እያገኘች ለመሆኗ እርግጠኛ መሆን ፈለግን። ነገር ግን በጣም ውድ አድርገን የምንመለከተውን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ዕንቁ አሁንም መተው ነበረብን። በዓለም ላይ ያለው የከበረ ድንጋይና ይህ ለአንድ ሰው ሊያደርግለት የሚችለው ነገር እንደ ከበረ ድንጋይ ከሚታየው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሚስዮናዊ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ከማገልገል ጋር ሲወዳደር ኢምንት ነው።
እኔና ሪታ አሁን በ60ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ እንገኛለን። በአካባቢው ካለ አንድ የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ ጋር እያገለገልን በመሆናችን በጣም እንረካለን እንዲሁም ደስተኞች ነን። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍናቸውን ዓመታት መለስ ብለን ስንቃኝ፣ ይሖዋ እጅግ ውድ የሆኑ አንዳንድ ዕንቁዎችን በአደራ ስለሰጠን እናመሰግነዋለን።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሪታ ከፖልና ኤቭሊን ሃንደርትማርክ (በስተቀኝ) ጋር ማድሪድ ውስጥ ከኮርማዎች ጋር የሚደረግ ትግል በሚታይበት ሥፍራ ከውጪ በኩል ሆነን
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጫካ ውስጥ “ሽርሽር” ሄደን ባደረግነው ስብሰባ ላይ ጉባኤውን ሳገለግል