ዕድል ተወስኗል የሚለው እምነት ከአምላክ ፍቅር ጋር ሊስማማ ይችላልን?
“ዕድል ተወስኗል የሚለውን እምነት የምንፈታው አምላክ በእያንዳንዱ ሰው ላይ ማድረግ የሚፈልገውን ነገር የወሰነበት ዘላለማዊ ዕቅድ እንደሆነ አድርገን ነው። ሁሉንም ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ስላልፈጠረ አንዳንዶቹን ለዘላለም ሕይወት ሌሎቹን ደግሞ ለዘላለም ኩነኔ አስቀድሞ ወስኗቸዋል።”
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር የፕሮቴስታንት ተሃድሶ አራማጅ የነበረው ጆን ካልቪን ኢንስቲትዩትስ ኦቭ ዘ ክርስቺያን ሪሊጅን በተባለው መጽሐፉ ላይ ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ሐሳቡን ያብራራው። ይህ አስተሳሰብ አምላክ ሁሉን አዋቂና ፍጡሮቹ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ያወጣውን ዓላማ ተፈጻሚነት ጥያቄ ውስጥ ሊከቱት ወይም ለውጦች እንዲያደርግ ሊያስገድዱት አይችሉም በሚለው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው።
ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገረው በእርግጥ ይህንኑ ነውን? ይበልጥ አንገብጋቢው ደግሞ ይህ ዓይነቱ ማብራሪያ ከአምላክ ባሕርያት በተለይም ከሁሉ የላቀ ባሕርይው ከሆነው ከፍቅሩ ጋር ይስማማልን? የሚለው ጥያቄ ነው።
የወደፊቱን አስቀድሞ መናገር የሚችል አምላክ
አምላክ የወደፊቱን አስቀድሞ መናገር ይችላል። “በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ” በማለት ስለ ራሱ ይናገራል። (ኢሳይያስ 46: 10) አምላክ አስቀድሞ የማወቅና አንድ ነገር ከመፈጸሙ በፊት የመናገር ችሎታ እንዳለው ለማሳየት በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት ሁሉ ትንቢቶቹ ተመዝግበው እንዲቆዩ አድርጓል።
ይህም በመሆኑ በባቢሎኑ ንጉሥ በብልጣሶር ዘመን ነቢዩ ዳንኤል እርስ በእርስ ስለሚቀናቀኑ ሁለት አራዊት ሕልም ባለመ ጊዜ “ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው” በማለት ይሖዋ ፍቺውን ሰጠው። (ዳንኤል 8:20, 21) አምላክ የዓለምን ኃያላን መንግሥታት ቅደም ተከተል ለመግለጽ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን እንደተጠቀመበት ግልጽ ነው። በጊዜው የነበረው የባቢሎን መንግሥት በሜዶ ፋርስ ይተካል፤ ከዚያም ግሪክ ይወርሳል።
ትንቢቶች አንድን ግለሰብ የሚመለከቱም ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ አሳውቋል። (ሚክያስ 5:2) አሁንም አምላክ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን ተጠቅሞበታል። ቢሆንም ይህ ጉዳይ የታወጀበት ልዩ ዓላማ ነበረው። ይህም የመሲሑን ማንነት ለይቶ ማሳወቅ ነው። ይህ ሁኔታ እያንዳንዱን ግለሰብ በተመለከተ ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ትምህርት ተቀባይነት እንዳለው አያሳይም።
ከዚህ በተቃራኒ ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ላለማወቅ የሚመርጥባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ይገልጻሉ። ሰዶምና ገሞራ ከመጥፋታቸው በፊት “እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍጥረት 18:21) አምላክ ጉዳዩን ከመመርመሩ በፊት በእነዚያ ከተሞች ምግባረ ብልሹነት ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበር አስቀድሞ እንዳላወቀ ይህ ጥቅስ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።
አምላክ አንዳንድ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ለማየት የሚችል መሆኑ እውነት ቢሆንም በብዙ ጉዳዮች ላይ አስቀድሞ በማወቅ ችሎታው ላለመጠቀም መርጧል። አምላክ ሁሉን ቻይ ስለሆነ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች እንደፈለጉት ሳይሆን እርሱ እንደፈለገ በችሎታዎቹ የመጠቀም ነፃነት አለው።
ነገሮችን ማስተካከል የሚችል አምላክ
አንዳንዶች ልክ እንደ ካልቪን ሰው በኃጢአት እንደሚወድቅ ከመፈጠሩ በፊት አምላክ ወስኖታል፤ እንዲሁም ከዚህ ውድቀት በፊት ‘የተመረጡትን’ ወስኗቸው ነበር ብለው ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ እንደማያገኙት ሙሉ በሙሉ እያወቀ አምላክ ለአዳምና ሔዋን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማቅረቡ ግብዝነት አይሆንበትምን? ከዚህም በላይ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መለኮታዊ መመሪያዎችን ተከትለው ለዘላለም የመኖር ወይም እነዚህን መመሪያዎች ችላ ብለው የመሞት ምርጫ እንደተሰጣቸው አንድም ቦታ አያስተባብሉም።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 2
ነገር ግን የአዳምና የሔዋን ኃጢአት በእርግጥ የአምላክን ዓላማ አጨናግፎታልን? አላጨናገፈውም፤ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ልክ ኃጢአት እንደሠሩ ሰይጣንንና ወኪሎቹን የሚያጠፋ እንዲሁም በምድር ላይ የተበላሸውን የሚያስተካክል “ዘር” እንደሚያስነሳ አምላክ አስታውቋል። ጥቂት ነፍሳት አንድን አትክልተኛ የተትረፈረፈ ምርት እንዳያመርት ሊያደርጉት እንደማይችሉ ሁሉ የአዳምና የሔዋን አለመታዘዝም አምላክ ምድርን ገነት ከማድረግ አያግደውም።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 3
በኋላም አምላክ ለንጉሥ ዳዊት ዘር የተሰጠና ሌሎች በመንግሥቱ ተባባሪዎች የሚሆኑበት ንጉሣዊ መስተዳድር እንደሚኖር ገለጸ። እነዚህ ሌሎች “የልዑሉ ቅዱሳን” ተብለዋል።—ዳንኤል 7:18፤ 2 ሳሙኤል 7:12፤ 1 ዜና መዋዕል 17:11a
አስቀድሞ መናገር ዕድልን አስቀድሞ መወሰን አይደለም
ሰዎች የትኛውን አቅጣጫ እንደሚከተሉ አምላክ ለማወቅ አልመረጠም የሚለው እውነታ የሰዎች ሠናይና እኩይ ምግባራት ምን ውጤት እንደሚያስከትሉ ከመተንበይ አያግደውም። መኪናዋ ስላለችበት መጥፎ ሁኔታ ለሹፌሩ ማስጠንቀቂያ የሰጠ መካኒክ አደጋ ቢደርስ ተጠያቂ ሊሆን ወይም ዕድሏን አስቀድመህ ወስነሃል ተብሎ ሊከሰስ አይችልም። ልክ እንዲዚሁ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚወስደው እርምጃ ላስከተለው አስከፊ ውጤት ዕድሉን አስቀድመህ ወስነሃል ተብሎ አምላክ ሊከሰስ አይችልም።
ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ዘሮችም ይህ ነገር እውነት ነበር። ቃየን ወንድሙን ከመግደሉ በፊት ይሖዋ በቃየን ፊት ምርጫ አስቀመጠለት። በኃጢአት ላይ ይነግሥ ይሆን ወይስ ኃጢአት በሱ ላይ ይነግሥበት ይሆን? ቃየን መጥፎ ምርጫ እንደሚያደርግና ወንድሙን እንደሚገድለው ይሖዋ አስቀድሞ እንደወሰነ የሚጠቁም ነገር በታሪኩ ላይ አይገኝም።—ዘፍጥረት 4:3–7
ለምሳሌ እስራኤላውያን ከአረማውያን ሕዝቦች ሚስቶችን በመውሰድ ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ዞር ቢሉ ምን እንደሚፈጠር የሙሴ ሕግ አስጠነቅቋቸው ነበር። አስቀድሞ ተነግሮ የነበረው ተከሰተ። በስተርጅናው ጣዖት እንዲያመልክ በባዕድ አገር ሚስቶቹ ተጽዕኖ ከደረሰበት ከንጉሥ ሰሎሞን ምሳሌ ይህን ማየት ይቻላል። (1 ነገሥት 11:7, 8) አዎን፣ አምላክ ሕዝቦቹን አስጠነቀቀ እንጂ የየግላቸው እርምጃ ምን እንደሚሆን አስቀድሞ አልወሰነም።
የተመረጡት ሰዎች በሰማያት ከኢየሱስ ጋር እንደሚነግሡ ቃል የተገባላቸውን ሽልማት እንዳይነጠቁ ከፈለጉ እስከ መጨረሻ እንዲጸኑ ተበረታተዋል። (2 ጴጥሮስ 1:10፤ ራእይ 2:5, 10, 16፤ 3:11) አንዳንድ ቀደምት የሃይማኖት ምሁራን እንደጠየቁት፣ የተመረጡት ሰዎች መጠራት ድሮውኑ የተወሰነ ከሆነ ይህን የመሰሉ ማሳሰቢያዎች ለምን ተሰጡ?
ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው እምነትና የአምላክ ፍቅር
ሰው ‘በእግዚአብሔር መልክ’ የተፈጠረ እንደመሆኑ መጠን ነፃ የመምረጥ መብት ተሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 1:27) ሰዎች አስቀድመው በተሞሉት መሠረት ብቻ እንደሚንቀሳቀሱ ሮቦቶች ሳይሆን በፍቅር ተነሳስተው ለአምላክ አክብሮታቸውን እንዲገልጹና እንዲያገለግሉት ካስፈለገ ነፃ የመምረጥ መብት ያላቸው መሆኑ ወሳኝ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ነፃ ፍጥረታት የሚያሳዩት ፍቅር አምላክ ተገቢ ያልሆኑ ክሶችን ውድቅ ለማድረግ ያስችለዋል። “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” ይላል።—ምሳሌ 27:11
የአምላክ አገልጋዮች ዕድላቸው አስቀድሞ ተወስኗል ወይም የሚንቀሳቀሱት ሁሉ በተሞሉት መሠረት ነው ከተባለ ለፈጣሪያቸው ያላቸው ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆኑ አጠያያቂ ሊሆን አይችልምን? በተጨማሪም አስቀድመው የተወሰኑትን ሰዎች የየራሳቸውን መልካም ሥራ ግምት ውስጥ ሳያስገባ ክብርንና ደስታን ዕጣ ፈንታቸው ማድረጉ የማያዳላ አምላክ ከመሆኑ ጋር አይጻረርምን? ከዚህም በላይ ሌሎች ዘላለማዊ ቅጣት ዕጣቸው ሆኖ አንዳንዶች ይህንን አድሏዊ ስጦታ ሲቀበሉ “የተመረጡት” ከልብ አመስጋኝ ለመሆን አይገፋፉም።—ዘፍጥረት 1:27፤ ኢዮብ 1:8፤ ሥራ 10:34, 35
ወደ መደምደሚያው ስንመጣ፣ ክርስቶስ ለሁሉም የሰው ዘር ምሥራቹን እንዲሰብኩ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። አምላክ የሚድኑትን ሰዎች ቀድሞውኑ መርጦ ከሆነ ክርስቲያኖች በወንጌላዊነቱ ሥራ የሚያሳዩትን ቅንዓት አያቀዘቅዝባቸውምን? የምሥክርነቱንስ ሥራ ትርጉም አልባ አያደርገውምን?
ሰዎች በምላሹ እሱን እንዲወዱት ሊገፋፋቸው የሚችለው ጠንካራ ኃይል ከአምላክ የሚገኘው የማያዳላ ፍቅር ነው። ከሁሉ የላቀው የአምላክ ፍቅር መግለጫ ፍጹም ላልሆነው ኃጢአተኛ የሰው ዘር ልጁን መሥዋዕት ማድረጉ ነው። አምላክ ስለ ልጁ የወደፊት ሁኔታ አስቀድሞ ያወቀበት ልዩ ምክንያት አለው። ነገር ግን ተመልሰው የሚመጡት በኢየሱስ ላይ የተመኩ ተስፋዎች በእርግጥ የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያረጋግጥልናል። ስለዚህ በዚህ ልጅ ላይ እምነት በማሳደር ወደ አምላክ እንቅረብ። ከፈጣሪያችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንድንመሠርት ራሱ ያቀረበልንን ግብዣ በመቀበል አድናቆታችንን እናሳይ። ዛሬ አምላክ ነፃ ምርጫቸውን ለመጠቀምና ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት ለሚፈልጉ ሁሉ ይህንን ጥሪ አቅርቦላቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ “ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ” ስለተዘጋጀ መንግሥት ሲናገር (ማቴዎስ 25:34) ከመጀመሪያው ኃጢአት በኋላ ያለውን ጊዜ ማመልከቱ መሆን አለበት። ሉቃስ 11:50, 51 ‘ዓለም የተፈጠረበትን’ ወይም በቤዛው የሚዋጅ የሰው ልጅ የተገኘበትን ጊዜ ከአቤል ዘመን ጋር ያዛምደዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በቡድን ደረጃ አስቀድመው የተወሰኑ
“አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።” (ሮሜ 8:29, 30) ጳውሎስ “አስቀድሞ የወሰናቸው” ብሎ በዚህ ጥቅስ ላይ የተጠቀመበትን አገላለጽ እንዴት መረዳት አለብን?
ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ የእያንዳንዱ ሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል ብሎ የማያሻማ ሐሳብ መስጠቱ አይደለም። በያዝነው መቶ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ዲክሲዮናር ደ ቴኦሎዢ ካቶሊክ የተባለው መዝገበ ቃላት “እየተስፋፋ የመጣው በካቶሊክ ምሁራን ዘንድ ያለው ሐሳብ የዘላለም ሕይወት ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ፍሬ ነገር አልተብራራም የሚለው ነው” በማለት የጳውሎስን ሐሳብ (ሮሜ ምዕራፍ 9–11) አብራርቷል። ከዚያ በኋላ ተመሳሳይ የመረጃ ምንጭ ኤም ላግራንግን በመጥቀስ እንደተናገረው “ጳውሎስ ያስነሳው ጥያቄ ዕድልን አስቀድሞ ስለ መወሰንና አንድ ነገር ከመፈጸሙ አስቀድሞ ስለ ማወቅ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አይሁዶች እምነት በማጣታቸው ምክንያት አሕዛብ ወደ ክርስትና ጸጋ ስለ መጠራታቸው እየተናገረ ነው። . . . የሚያመለክተው ቡድኖችን፣ አሕዛብን እና ቃል በቃል የተለዩ ግለሰቦች ያልሆኑትን ነው።”—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
በቅርቡ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ምዕራፎች (9–11) በተመለከተ እንዲህ በማለት ተመሳሳይ መደምደሚያ አቅርቧል፦ “የእነዚህ ምዕራፎች ርዕሰ ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ ለክብርም ሆነ ለእምነት አስቀድሞ ስለ መወሰን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባሉት አነጋገሮች በተነሳው ብቸኛ ጥያቄ ረገድ እስራኤል በሰው ዘር መዳን ታሪክ ውስጥ ስለምትጫወተው ሚና የሚናገር ነው።”
የሮሜ ምዕራፍ 8 የመጨረሻ ቁጥሮች በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ ጋር ግንኙነት አላቸው። እነዚህ ቁጥሮች ከሰው ዘር የተውጣጣ አንድ ቡድን ሊደርስበት የሚገባ ብቃቶችን አሟልቶ ከኢየሱስ ጋር እንደሚነግሥ አምላክ አስቀድሞ እንደተመለከተ የሚያስታውሱን ናቸው። ይህ የተከናወነው በግለሰብ ደረጃ ለይቶ አስቀድሞ በመምረጥ አይደለም ምክንያቱም እንዲህ ማድረጉ ከአምላክ ፍቅርና ፍትሕ ጋር ይጻረራል።