ፍርሃት የሚያከትመው መቼ ይሆን?
እውነተኛ ደህንነት የዛሬ 2,000 ዓመት ከኖረ አንድ ሰው ጋር ግንኙነት እንዳለው ብታውቅ ያስገርምሃልን? ኢየሱስ የፍቅርን አስፈላጊነት ለማሳየት የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ምሳሌ ተናግሯል፦ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።” ሁለት መንገደኞች ይህንን የተጠቃ ሰው እንዳላዩ ሆነው ቢያልፉትም አንድ ደግ ሳምራዊ ምሕረት አሳይቶ ነበር። የሆነ ሆኖ በዛሬው ጊዜ በሚፈጸም ወንጀል የተጎዱትን ሰዎች የሚንከባከባቸው ማን ነው? ከፍርሃት የሚገላግለን ምን ነገር ተስፋ ማድረግ እንችላለን?—ሉቃስ 10:30–37
ምንም እንኳ በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም ብዙዎች ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ያለባቸው ሰዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ከባድ የእስር ቅጣቶች ወይም ፖሊሶችን ጥሩ ደሞዝ እየከፈሉ በብዛት ማሰማራት ኃይል የታከለበት ወንጀልን ያስቀር ይሆን? ሕግ አስከባሪ ድርጅቶች በቂ ደህንነት ለማስገኘት ከልብ ቢጥሩም እንኳ አደንዛዥ ዕፅ አለአግባብ መጠቀምን፣ የቡድን ዝርፊያንና ድህነትን የመሳሰሉ ነገሮችን ያጠፋሉ ብለህ በእርግጥ ታምናለህን? ቢሆንም ለጽድቅ ያለን ረሀብና ጥማት ከንቱ መሆን አያስፈልገውም።—ማቴዎስ 5:6
መዝሙር 46:1 “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” ይላል። እነዚህ ቃላት እንዲያው ውብ የሆኑ የግጥም ቃላት ብቻ እንዳልሆኑ ወደፊት እናያለን።
እንደምታውቀው ሰዎች በእርስ በርስ ጦርነቶችና በሽብር ፈጣሪዎች እንደተጨፈጨፉ የዜና ማሰራጫዎች በየቀኑ ሪፖርት ያደርጋሉ። በአንዳንድ የምድር ክፍሎች በወንጀሉ ያልተካፈሉ ወጣቶችን ወይም ወንጀል ሲፈጸም የዓይን ምሥክሮች የሆኑትን መግደል የተለመደ ሆኗል። ሕይወት እንደዚህ በጣም ርካሽ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ላለው ዓመፅ የተለያዩ መነሾዎች ሊኖሩት ቢችሉም እንኳ ችላ ልንለው የማይገባ አንድ ምክንያት አለ።
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው መሠረት ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ (1 ዮሐንስ 5:19) እንዲያውም ሰይጣን ዲያብሎስ ውሸታም ብቻ ሳይሆን “ነፍሰ ገዳይ” እንደሆነም ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋግጧል። (ዮሐንስ 8:44) በተለያዩ መንገዶች በሰው ዘር ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ይህ ኃያል የሆነ መንፈሳዊ ፍጡር በዛሬው ጊዜ ያለውን እየጨመረ የሚሄድ ዓመፅ እያስፋፋ ነው። ራእይ 12:12 “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” ይላል። ደግነቱ ግን ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ‘ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ይተካል።—2 ጴጥሮስ 3:13
ከዚህ አስደናቂ የአዲስ ዓለም ተስፋ በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ምን የሚረዳን ዝግጅት አለ?
ለዚህ ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ለማግኘት ከመመርመራችን በፊት እውነተኛ ክርስቲያኖችም እንኳ ዓመፅ እንደማይደርስባቸው ዋስትና እንደሌላቸው ማስታወሱ ጥሩ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የደረሱበትን አንዳንድ አደጋዎች ገልጾ ነበር። “በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ [በወገኖቹ] በኩል ፍርሃት፣ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረ በዳ ፍርሃት፣ በባሕር ፍርሃት” ነበረበት። (2 ቆሮንቶስ 11:26) ቢሆንም ጳውሎስ ከእነዚህ አደጋዎች አምልጧል። ዛሬም ቢሆን እንደዚሁ ነው፤ ንቁ በመሆን በዛሬው ጊዜም ሥራዎቻችንን በተቻለ መጠን እንደ ወትሮው ማከናወን እንችላለን። ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችን እስቲ እንመርምር።
አንድ ሰው በአደገኛ ሰፈር የሚኖር ከሆነ የሚያሳየው ጥሩ ጠባይ ከለላ ሊሆንለት ይችላል። ምክያቱም ሰዎች ሌሎች የሚያደርጉትን በቅርብ ይመለከታሉ። ምንም እንኳ ዘራፊዎች እቅድ አውጥተው ወንጀሎችን ቢፈጽሙም ብዙዎቹ ራሳቸውን የሚመለከቱት እንደማንኛውም ሰው አድርገው ነው። የሚሠሩትን ነገር ከመንቀፍ ተቆጠብ፤ እንዲሁም ምን እንዳደረጉ ለማወቅ አትሞክር። በዚህ መንገድ የበቀላቸው ዒላማ የመሆንህን አጋጣሚ ልትቀንስ ትችላለህ። ሌቦች ማን አዲስ ነገር እንደገዛ ወይም እነማን ለእረፍት ቤታቸውን ጥለው እንደሚሄዱ ለማወቅ እንደሚሞክሩ አትዘንጋ፤ ስለዚህ ከሰዎች ጋር ስታወራ ምሥጢር የምትቋጥር ሁን።
ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልጋይነታቸው ያተረፉት መልካም ስም በከፍተኛ ደረጃ ጠቅሟቸዋል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሳያዳሉ ለመርዳት ራሳቸውን ለሚያቀርቡ እንዲህ ላሉ ክርስቲያኖች ወንጀለኞች አክብሮት እንዳላቸው በተደጋጋሚ አሳይተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ነፍሰ ገዳዮች ወይም ሌቦች ወይም ደግሞ ‘በሰው ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ’ ስላልሆኑ አስጊዎች አይደሉም።—1 ጴጥሮስ 4:15 የ1980 ትርጉም
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ደህንነት
ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ የተናገረው ‘የዓመፃ ብዛት’ ቢያሳዝነንም ከመጠን በላይ ከመጨነቅ ይልቅ አምላክ ይህንን ክፉ ሥርዓት በቅርቡ ከሥሩ ነቅሎ እንደሚያጠፋው እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ኢየሱስ “ይህ የመንግሥት ወንጌል” በዓለም ዙሪያ እንደሚሰበክ ትንቢት ከመናገሩም በተጨማሪ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” በማለት ተከታዮቹን አስታውሷቸዋል።—ማቴዎስ 24:12–14
እያደቡ ሌሎችን የሚያጠቁ፣ አንዳንድ ጊዜ ለማመን የሚያስቸግር ጭካኔ የሚፈጽሙ ሰዎች እንደሚወገዱ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ምሳሌ 22:22, 23 እንዲህ ይላል፦ “ድሀን በግድ አትበለው ድሀ ነውና፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው፤ እግዚአብሔር የእነርሱን ፍርድ ይፋረድላቸዋልና፣ የቀሙአቸውንም ሰዎች ሕይወት ይቀማልና።” እንደ ዘራፊዎች፣ ነፍሰ ገዳዮችና በጾታ አለአግባብ የሚጠቀሙ የመሳሰሉትን ክፉ አድራጊዎች ይሖዋ ጠራርጎ ያጠፋቸዋል። ከዚህም በላይ የእነዚህ ወንጀሎች ሰለባ የሆኑ ሰዎችን አይዘነጋም። ያጡትን ነገርና ጤንነታቸውን ሙሉ በሙሉ ይመልስላቸዋል።
በእርግጥም ‘ከክፉ ሸሽተው መልካም የሚያደርጉ’ ሰዎች የሚመጣውን ታላቅ መከራ በሕይወት በማለፍ አለዚያም ከሞት በመነሣት የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:27–29) እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሞች የሚገኙት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትነት አማካኝነት ነው። (ዮሐንስ 3:16) ነገር ግን ተመልሳ በምትቋቋመው ገነት ውስጥ ሕይወት ምን ይመስል ይሆን?
በአምላክ መንግሥት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ከልብ የሚያስደስት ይሆናል። “ሕዝቤም በሰላም ማደሪያ በታመነም ቤት በጸጥተኛ ማረፊያ ይቀመጣል” በማለት ይሖዋ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 32:18) የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት በጠቅላላ ጠባያቸውን ያስተካክላሉ። ክፉ ወይም ታማኝ ያልሆነ አንድም ሰው አይኖርም፤ ወይም ደግሞ የትኛውም ሰው የእንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ የጥቃት ሰለባ አይሆንም። ነቢዩ ሚክያስ “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም” ብሏል። (ሚክያስ 4:4፤ ሕዝቅኤል 34:28) በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት አደገኛ ሰፈሮች እንዴት የተለየ ሁኔታ ነው!
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ተጠንቀቅ
ብዙ ወንጀለኞች እንደሙያ አድርገው ሙሉ ጊዜያቸውን ወንጀል በመሥራት ያሳልፋሉ። መሣሪያ የሚደቅንብህ አንድ ሰው ቢሆንም እንኳ የሚሠሩት ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በቡድን ሆነው ሊሆን ይችላል። ወንጀለኛው ወጣት በሆነ መጠን ይበልጥ አደገኛ እንደሚሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። አንዴ እጃቸው ውስጥ ከገባህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ሌባው እንዳይደናገጥ ረጋ በል፤ አለበለዚያ ካለማወቁ የተነሳ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብሎ ሊገድልህ ይችላል። የይሖዋ ምሥክር ከሆንህ የይሖዋ ምሥክር እንደሆንህ ንገረው። ቢሆንም ሌባው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ለማስረከብ አታመንታ። የምትዘገይ ከሆነ የሚደርስብህ አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል። ከሰጠኸው በኋላ መታወቂያ ወረቀቶችን ወይም ለአውቶቡስ የሚሆን ገንዘብ እንዲመልስልህ መጠየቁ ለክፉ እንደማይሰጥ ይሰማህ ይሆናል።
ብዙውን ጊዜ ወንጀለኛው ማን እንደሆነ መረዳት አትችልም። አንዳንድ ሌቦች የዕፅ ሱሰኞች ወይም ወንጀልን ሙያቸው ያደረጉ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ለዕለት ጉርሳቸው ብቻ የሚሆን ለማግኘት የሚፈልጉ ናቸው። በማንኛውም ሁኔታ ብዙ መጠን ያለው ገንዘብ አትያዝ። ጌጣ ጌጦችን፣ የወርቅ ቀለበቶችን ወይም ውድ ሰዓቶችን ከማሳየት ተቆጠብ። ፍርሃት ሳታሳይ እንደወትሮህ ተጓዝ። ለይተህ ለማወቅ እንደምትፈልጋቸው አድርገህ በሰዎች ላይ ዓይንህን አትትከል። መንገድ ላይ ተኩስ ከተከፈተ መሬት ላይ ተኛ፤ ልብሶችህ በኋላ ሊታጠቡ ይችላሉ።—የቀድሞው የሪዮ ዴ ጄኔሮ ፖሊስ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ረጋ በል፤ እንዲሁም ሌባው የሚፈልጋቸውን ነገሮች ስጠው። የምትዘገይ ከሆነ የሚደርስብህ አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል