ሌቦች የማይኖሩበት ዓለም
ነገሩ የተከናወነው በፍጥነት ነበር። አንቶኒዮa በብራዚል በሳኦ ፖውሎ ከሚገኘው ቤቱ በራፍ ሲደርስ አንድ ጥሩ አለባበስ የነበረው ሰው ሽጉጡን አውጥቶ ግንባሩ ላይ ደገነበት። ከዚያም የመኪናውን ቁልፍና ሊብሬውን ተቀብሎ በፍጥነት እየነዳ አመለጠ።
በሪዮ ዲ ጃኔሮ መሣሪያ የታጠቁ አራት ሰዎች ፓውሎ የተባለን አንድ ሰው የአሥር ዓመት ሴት ልጁ እያየች አስገድደው ወሰዱት። እቤት ከደረሱም በኋላ ዘራፊዎቹ ገቡና የሚፈልጉትን ሁሉ በፓውሎ ሁለት መኪናዎች ሞልተው ወሰዱ። ሚስቱንም እንደሚገድሏት በማስፈራራት ከሌላ ቅጥር ሠራተኛ ጋር በመያዣነት አግተው በከተማ ውስጥ ወደሚገኘው የፓውሎ የጌጣጌጥ መጋዘን በመሄድ ውድ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ዘረፉ። በኋላም ሌቦቹ በድንገት ስልክ ደውለው መኪናዎቹን የት እንደተዉአቸው ተናገሩ።
ደክመው ያገኙት ገንዘብና ንብረት ሲዘረፍ እንዴት ቅስም የሚሰብር ነው! ምንም እንኳን አንቶኒዮም ሆነ ፓውሎ እንደዚያ ለማድረግ ባይሞክሩም ሌሎች ግን በሕጋዊ መንገድ ከመጠቀም የበቀል እርምጃ ራሳቸው ይወስዳሉ። ሌቦቹን ይገድላሉ ወይም የራሳቸውን ሕይወት ያጣሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ወጣት ሰዓት ነጥቆ ሊሸሽ ሲሞክር በነገሩ የተናደደችው ብራዚላዊት ሴት ከቦርሳዋ ውስጥ ሽጉጧን አወጣችና ተኩሳ ገደለችው። ውጤቱስ ምን ሆነ? ኦ ኤስታዶ ዴ ኤስ ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ትርዒቱን በዓይናቸው ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች ማንነቷ ያልታወቀችው ሴትዮዋ የወሰደችውን አቋም አሞገሱ፤ ለፖሊሶች የእርሷን ማንነት ለመጠቆምም ፈቃደኞች አልነበሩም።” ምንም እንኳ ክርስቲያኖች ሌባ የማይኖርበትን ዓለም ቢናፍቁም ሴትዮዋ እንዳደረገችው የበቀል እርምጃ አይወስዱም። በቀል የአምላክ በመሆኑ የሚከተሉትን የምሳሌ 24:19, 20 ቃላት ያከብራሉ:- “ስለ ኃጢያተኞች አትቆጣ፣ በክፉዎችም አትቅና። ለኃጢያተኛ የፍጻሜ ተስፋ የለውምና።”
ነገር ግን ጥቃት ቢደርስብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በሪዮ ዲ ጃኔሮ የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ረጋ የማለትን አስፈላጊነት ያሳያል። ሄሎዛ የምትባል አንድ ክርስቲያን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት በአውቶቡስ ተሳፍራ እየተጓዘች ነበር። ሁለት ሰዎች ተጓዦቹን መዝረፍ ጀመሩ። አውቶቡሱ የምትወርድበት ቦታ ላይ ሲደርስ ሄሎዛ የይሖዋ ምስክር እንደሆነችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት እንደምትሄድ ነገረቻቸው። መጽሐፍ ቅዱሷንና የምታስጠናበትን መጽሐፍ አሳየቻቸው። ሌቦቹ ሳይዘርፏት እንድትወርድ ፈቀዱላት። ቀደም ብሎ ግን ሌላ ተሳፋሪ እንዲወርድ አልተፈቀደለትም ነበር። በመጨረሻ ሹፌሩ እንደዚህ ያለ ነገር አይቶ እንደማያውቅ ተናገረ።
ሬጅናም ሁለት መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች መኪናዋ ውስጥ እንድትገባ ሲያዟት ራሷን አረጋግታለች። ሬጅና የራሷን የንቁ! መጽሔት ቅጂ አሳየቻቸውና መሰከረችላቸው። ዘራፊዎቹ ተረብሸው ስለ ነበር ከረሜላ ያስቀመጠችበትን የመኪናውን የውስጥ የዕቃ ማስቀመጫ እንዲከፍቱት ነገረቻቸው። ነገር ግን የመንግሥቱን ዝማሪ ካሴቶች ሲያዩ ያንን ማዳመጥ ጀመሩ። ሁኔታው የወዳጅነት መልክ እየያዘ ስለመጣ ዘራፊዎቹ ሬጅናን የሚረዳት አንድ ደግ ሰው እንደምታገኝ አረጋግጠውላት ጉዳት ሳያደርሱባት ሊለቋት ወሰኑ። አሥር ደቂቃ በእግሯ ከተጓዘች በኋላ አንድ ቤት አገኘች። የቤቱ ባለቤት ግን “ምንም ጉዳት የደረሰብሽ አትመስይም፤ በጣም ተረጋግተሽ ነው የምትታይው” በማለት ተናገረ፤ የነገረችውን ታሪክ ለማመን አልቻለም።
የዘራፊዎች ሰለባ የሆነ ሰው የአካል ጉዳት ባይደርስበትም እንኳ እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚረብሽ ነገር ሲያጋጥም በኋላ ከባድ ውጤት ይኖረዋል። ‘ጥቃቱ የደረሰበት ሰው ስጋት ይሰማዋል፤ የቤተሰብ አባሎቹን ወይም ሊረዱት የሚሞክሩትን የሚጠላ፣ ሌሎችን ማመን የማይችል፣ ነገሮችን ስለማደራጀት ብዙ የሚጨነቅ፣ በዓለም ላይ ፍትሕ እንደሌለ የሚሰማው’ ይሆናል ሲል ኦ ኤስታዶ ኤስ ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በተቃራኒው ግን በይሖዋ አምላክ የሚታመን ሰው ጥቃቱ ቢደርስበትም ያጋጠመውን ነገር በአካልና በስሜት ሳይጎዳ ሊወጣው የሚችልበት አጋጣሚ የላቀ ነው። ነገር ግን ወንጀልም ይሁን የሚያስፈራ ነገር ፈጽሞ አለመኖሩ በረከት ነው ቢባል በዚህ አትስማማምን?
“የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ”
ምንም እንኳ ብዙዎች የስግብግብነት አኗኗር መንገዳቸውን ቢመርጡም ሌቦች ምኞታቸውንና አቋማቸውን እንዲቀይሩ የአምላክ ቃል ረድቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:23) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እውነተኛ የሕይወት ዓላማ በማግኘታቸው “በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል” የሚሉትን ቃላት ይቀበላሉ። (ምሳሌ 16:8) ክላውዲዮ እንዲህ ይላል “ቤተሰቤ በጠቅላላ ምስክሮች ናቸው ማለት ይቻላል። እኔ ግን ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው የሚነግሩኝን እሺ ብዬ ተቀብዬ አላውቅም። በተሰረቀች የፒክአፕ መኪና 2,000 ኪሎ ሜትር የሚያክል ርቀት ከተጓዝኩ በኋላ ስመለስ ብዙ የፖሊስ ፍተሻ ጣቢያዎችን ማለፍ ነበረብኝ። በዚህ መሃል ሕይወቴን መለወጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ከዚህ በፊት ይህንን ለማድረግ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን አልተሳካልኝም። አሁን ግን የይሖዋ ምስክሮች ስለሆኑት ዘመዶቼ በማሰብ እንዴት የተለዩ እንደሆኑ ማሰላሰል ጀመርኩ። እርካታና ደስታ ሰላም አላቸው።” በመጨረሻም ክላውዲዮ የአምላክን ቃል ማጥናት ጀመረና ዕጽ መውሰዱን በማቆም እንዲሁም የቀድሞ ጓደኞቹን በመተው ክርስቲያን የአምላክ አገልጋይ ሆነ።
አሁንም ሌሎች “ዓመፅን ተስፋ አታድርጉ፣ ቅሚያንም አትተማመኑ” የሚሉትን ቃላት ይታዘዛሉ። (መዝሙር 62:10) የዕፅ ሱሰኛና በስውር ዕፅ የሚሸጥ የነበረው ጆሲ በዘረፋ ወቅት ሰው ለመግደል ሞክረሃል ተብሎ ታሥሮ ፍርዱን ከጨረሰ በኋላ ከእኅቱ ባል ጋር ባደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጠቀመ። የዕፅ ሱሰኝነቱንና ሻጭነቱን በማቆም አሁን ቀናተኛ ምስክር ሆኗል።
ሆኖም አዲስ ሰውነት በቅጽበት ወይም በተአምር አይመጣም። በዕፅ ሱሰኝነትና በስርቆት ውስጥ ተጠላልፎ የነበረው ኦስካር እንዲህ ይላል:- “ብዙውን ጊዜ ከእንባዬ ብዛት ወለሉ ትንሽ ሐይቅ እስኪመስል ድረስ ምርር ብዬ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር።” አዎን፣ ትጋት ከተሞላበት የአምላክ ቃል ጥናት በተጓዳኝ የማያቋርጥ ልባዊ ጸሎት ያስፈልጋል። በሚከተሉት የጸሎት ባሕርይ ያላቸው ቃላት ውስጥ የተንጸባረቀውን ጥበብ አስተውል “ከንቱነትንና ሐሰተኝነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፣ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም:- እግዚአብሔር ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፣ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።” — ምሳሌ 30:8, 9
የራስን ጥቅም የማሳደድ ፍላጎት በእውነተኛ ፍቅር ሊተካ ይገባል:- “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም።” (ኤፌሶን 4:28) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ዘንድ ከነበረው ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ዛሬም ቀደም ብሎ ‘ሌቦች ወይም ስግብግቦች’ የነበሩትን ነገር ግን ንስሐ የገቡትን ሰዎች ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛ አማካኝነት ምሕረት በማሳየት ይቅር ይላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9–11) ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ዓይነት ቢሆን አኗኗራችንን መለወጥ መቻላችንና የአምላክን ሞገስ ማግኘታችን እንዴት የሚያጽናና ነው! — ዮሐንስ 3:16
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት
ሌቦች የማይኖሩበትን ዓለም እስቲ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ብዙ ገንዘብ የሚያስወጡ እንደ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ፓሊስና ወኅኒ ቤት የመሳሰሉት ሕግ አስከባሪዎች አያስፈልጉም! አንዱ የሌላውን ስብዕናና ንብረቱን የሚያከብርበት የበለጸገ ዓለም ይሆናል! ይህ የማይታመን ይመስል ይሆን? አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ዓመፃን ሁሉ ወደ ፍጻሜው ያመጣዋልን? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ለመሆኑና የሚናገራቸው ትንቢቶችም እምነት የሚጣለባቸው እንደሆኑ የሚያሳዩትን ማስረጃዎች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። አንድ ለውጥ ከፊታችን እንደሚጠብቀን ልትተማመን የሚያስችልህ ጠንካራ መሠረት ታገኛለህ። ጽድቅን ለሚያፈቅሩ ሁሉ ቃል የተገባላቸውን እፎይታ እንዳያመጣ አምላክን ሊያግደው የሚችል የለም። “በክፉዎች ላይ አትቅና፣ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና።” (መዝሙር 37:1, 2) ከረዥም ጊዜ በፊት የተጻፉት እነዚህ ቃላት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማሉ።
የአምላክ መንግሥት ተስፋ የለሽነትንና ጥርጣሬን የሚፈጥሩትን ስቃይና ዓመፅን ወደ ፍጻሜያቸው ታመጣለች። ማንም ሰው ለስርቆት የሚገፋፋው ችግር አይኖርበትም። “በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።” የሚለው ትንቢት ማረጋገጫ ይሆነናል። (መዝሙር 72:16) በእርግጥም በምትመጣዋ ገነት እውነተኛውን አምላክ የሚያውቁትንና የሚያመልኩትን የሰው ዘሮች ሰላም የሚረብሽ ምንም ነገር አይኖርም። — ኢሳይያስ 32:18
ይህ የዚህን ዓለም የስግብግብነት መንገዶች በመቋቋም የሚገኝ እንዴት ያለ ሽልማት ነው! ምሳሌ 11:19 “በጽድቅ የሚጸና በሕይወት ይኖራል፤ ክፋትን የሚከተል ግን ለሞቱ ነው” ይላል። አዎን፣ ክፉዎች ከጠፉ በኋላ ማንም ሰው ስለ ሕይወቱ ወይም ስለ ንብረቱ የሚሰጋበት ምክንያት አይኖረውም። መዝሙር 37:11 “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” የሚል ተስፋ ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስርቆትን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይበጃል?
በቤት ውስጥ ስትሆን፤ በቤትህ ውስጥም ሆንክ ከቤት ውጭ ሌቦች ሊመጡ ስለሚችሉ ቤትህን መዝጋትና መቆለፍ አለብህ። የጉዳዩ ባለሞያዎች በሩ ላይ የማስጠንቀቂያ ደወል አድርጉ ወይም ውሻ አሳድጉ በማለት ይመክራሉ። ከቤት ለሽርሽር ርቀህ የምትሄድ ከሆነ ለምታምነው ጎረቤትህ ንገረው። ዘራፊዎች የሚወስዱት እርምጃ ፈጣንና ድንገተኛ ሊሆን ስለሚችል ከተሸበሩም እቅዳቸውን ወዲያው ሊለውጡ ስለሚችሉ ረጋ በል። ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ከሆንክ ራስህን አስተዋውቅና ምስክርነት ለመስጠት ሞክር። ወዳጅነት ልትፈጥርና እንዲያዝኑልህ ልታደርግ ትችል ይሆናል። አካላዊ ጥቃት እስካልደረሰብህ ድረስ ምንም ነገር ለማድረግ አትሞክር።
በሕዝብ መሐል ስትሆን ወይም በመንገድ ላይ ስትሄድ፤ የሚከተልህ ሰው መኖሩን ለማስተዋል ንቁ ሁን። በእግረኞች መንገድ መሃል መሃሉን ሂድ፤ ጨለማ በሆነና ጭር ባለ መንገድ አትሂድ። የገንዘብ ቦርሳህን ወይም ውድ የሆኑ እቃዎችህን ደበቅ አድርገህ ያዝ። አንድ ቦታ እንደምትሄድ ለማስመሰል ፈጠን ፈጠን እያልክ ተራመድ። ውድ የሆኑ ልብሶችን ወይም ትኩረት የሚስቡ ጌጣጌጦችን አታድርግ። ሁኔታው የማያስተማምን ከሆነ ገበያ ከሌላ ሰው ጋር ሂድ፤ የሚያስፈልግህን ገንዘብ ብቻ ያዝ፤ በልብስህ የተለያዩ ኪሶች ውስጥ ወይም በሌሎች ቦታዎች ከፋፍለህ አስቀምጠው።
በመኪና ውስጥ ስትሆን፤ ባለህበት አካባቢ ‘መኪናህ ውስጥ እያለህ የሚደረግ ጠለፋ’ የተለመደ ከሆነ መኪናህን አቁመህ ውስጥ አትቀመጥ። ከሥራ ስትመጣና ስትሄድ መንገድህን ቀያይር። ረጅም ሊሆን ቢችልም እንኳ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነውን መንገድ ምረጥ። መኪናህን ከማቆምህ በፊት በአካባቢው የሚያጠራጥር ሁኔታ እንዳለና እንደሌለ አረጋግጥ። ጭር ባለ አካባቢ የመኪናህን እቃ ማስቀመጫ ክፍት አትተው። ውድ የሆኑ እቃዎችን በመኪና ውስጥ እየታዩ ጥለህ አትሄድ። ቁልፍ ያለው ሰንሰለት ወይም ሌባን ለመከላከል የሚያገለግሉ ሌሎች መሣሪያዎች ተራ ሌቦችን አይጋብዙም።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብን አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ።” — ማቴዎስ 6:19, 20