የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 9/1 ገጽ 22-26
  • “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ተቋቋመ
  • የቀሳውስት ተቃውሞ
  • የስብከት እንቅስቃሴያችን
  • የጦርነቱ ዓመታት
  • ጋብቻን በተመለከተ ይሖዋ ያወጣው የአቋም ደረጃ ግልጽ ተደረገ
  • የአገልግሎት መብቶች
  • እውነተኛ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም
  • ኮብላይ ልጅ ነበርኩ
    ንቁ!—2006
  • ባለኝ ረክቼ መኖሬ እንድጸና አስችሎኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • ያገኘሁት ውድ ክርስቲያናዊ ውርስ በይሖዋ ቤት እንዳብብ አስችሎኛል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 9/1 ገጽ 22-26

“ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም”

ሳሙኤል ዲ ላደሱዪ እንደተናገረው

ያለፉትን በርካታ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስታውሳቸውና የተከናወኑትን ነገሮች ስመለከት በጣም ይገርመኛል። ይሖዋ በመላው ዓለም ውስጥ አስደናቂ ነገሮችን በማድረግ ላይ ነው። በ1931 ኢሌሻ በምትባል የናይጄሪያ ከተማ ጥቂት ሆነን መስበክ የጀመርን ሰዎች አሁን 36 ጉባኤዎች ሆነናል። የመጀመሪያዎቹ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች በገቡበት በ1947 በናይጄሪያ ውስጥ የነበሩት ወደ 4,000 የሚጠጉ አስፋፊዎች በአሁኑ ወቅት ከ180,000 በላይ ሆነዋል። በእነዚያ የቀድሞዎቹ ዓመታት አሁን የተገኘው ጭማሪ ይገኛል ብለን ልንጠብቅ ቀርቶ ጨርሶ አላሰብነውም ነበር። ለዚህ አስደናቂ ሥራ አስተዋጽኦ የማበርከት መብት በማግኘቴ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ! እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ልንገራችሁ።

አባቴ ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወረ አነስተኛ የጦር መሣሪያዎችንና ጥይቶችን ይነግድ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜም እቤት አይቀመጥም። እኔ የማውቃቸው ሰባት ሚስቶች ነበሩት፤ ይሁን እንጂ አብረውት የሚኖሩት ሁሉም አልነበሩም። አባቴ የሟቹ ወንድሙ ሚስት የነበረችውን እናቴን አግብቶ ነበር። እርሷ ሁለተኛ ሚስቱ ሆነች፤ እኔ የምኖረውም ከእርሷ ጋር ነበር።

አንድ ቀን አባባ በአቅራቢያችን በሚገኘው መንደር ውስጥ የምትኖረውን የመጀመሪያ ሚስቱን ጠይቆ መጣ። እዚያ በነበረበት ወቅት ግማሽ ወንድሜ ትምህርት ቤት እንደገባ ሰማ። ግማሽ ወንድሜ እንደ እኔ አሥር ዓመቱ ነበር። ስለዚህ አባባ ትምህርት ቤት መግባት እንዳለብኝ ወሰነ። ሦስት ብር ለመጽሐፍ መግዣ፣ ስድስት ብር ደግሞ ለምዝገባ እንዲሆነኝ ብሎ ዘጠኝ ብር ሰጠኝ። ይህ የሆነው በ1924 ነበር።

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ተቋቋመ

ከልጅነቴ ጀምሮ የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ነበረኝ። በትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚሰጥባቸውን ክፍለ ጊዜያት በጣም እወዳቸው ነበር፤ የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ሁልጊዜ ያመሰግኑኝ ነበር። ስለዚህ በ1930 ከሌላ ቦታ የመጣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሰጠው ንግግር አላመለጠኝም፤ እርሱም በኢሌሻ ውስጥ ከሰበኩት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አንዱ ነበር። ከንግግሩ በኋላ በዮሩባ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአምላክ በገና የተባለ መጽሐፍ አንድ ቅጂ አበረከተልኝ።

በሰንበት ትምህርት ቤት ዘወትር እካፈል ነበር። አሁን የአምላክ በገና የተባለውን መጽሐፍ ይዤ መሄድና እዚያ የሚያስተምሯቸውን አንዳንድ መሠረተ ትምህርቶች ለማፍረስ በእርሱ መጠቀም ጀመርኩ። ብዙ ክርክሮች ተፈጠሩ፤ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን ‘አዲስ ትምህርት’ እንዳልከተል ብዙ ጊዜ ያስጠነቅቁኝ ነበር።

በሚቀጥለው ዓመት በመንገድ ላይ በእግሬ እየተንሸራሸርኩ ሳለ ሰዎች ተሰባስበው አንድ ሰው ንግግር ሲያደርግላቸው የሚያዳምጡበት ስፍራ ደረስኩ። ንግግር ያደርግ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነው ጄ አይ ኦዋንፓ ነበር። ሌጎስ ሆኖ የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው ዊሊያም አር ብራውን (ብዙውን ጊዜ ባይብል ብራውን ተብሎ ይጠራል) ወደዚህ እንዲመጣ ልኮት ነበር።a በኢሌሻ ውስጥ የአምላክ በገና የተባለውን መጽሐፍ ለማጥናት አንድ አነስተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ቡድን እንደተቋቋመ ስለተገነዘብኩ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀልኩ።

ገና በ16 ዓመት ዕድሜ ገደማ የምገኝ ተማሪ ስለ ነበርኩ በቡድኑ ውስጥ ከነበሩት ሁሉ ትንሹ እኔ ነበርኩ። በ30ዎቹና ከዚያ በላይ በሆነ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ጋር በጣም መቀራረብ ሊያሳፍረኝ እንዲያውም ሊያስፈራኝ ይገባ ነበር። ሆኖም እነሱ እኔ በመካከላቸው በመገኘቴ በጣም ከመደሰታቸውም በላይ ያበረታቱኝ ነበር። እንደ አባት ሆነውልኝ ነበር።

የቀሳውስት ተቃውሞ

ወዲያውኑ ከቀሳውስት ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዘርብን ጀመር። ቀደም ሲል እርስ በርሳቸው ግጭት የነበራቸው ካቶሊኮች፣ አንግሊካኖችና ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች አሁን እኛን ለመቃወም ግምባር ፈጠሩ። እኛን ተስፋ የሚስቆርጥ እርምጃ ለመውሰድ በአካባቢው ከሚገኙ የጎሣ አለቆች ጋር ሆነው አሤሩ። ለኅብረተሰቡ ጎጂ ናቸው በማለት ፖሊሶችን ልከው መጽሐፎቻችንን ወሰዱብን። ይሁን እንጂ የአውራጃው የፖሊስ አዛዥ መጽሐፎቹን የመውሰድ መብት እንደሌላቸው አስጠነቀቃቸው። ከሁለት ሳምንት በኋላም መጽሐፎቹ ተመለሱልን።

ይህ ከሆነ በኋላ ኦባ ወይም የጎሣ አለቆች አለቃና በከተማዋ ውስጥ በጣም የታወቁ ሌሎች ሰዎች በሚገኙበት ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ተጠራን። በዚያ ወቅት 30 ያህል ነበርን። እነዚያን “አደገኛ” የሚሏቸውን መጻሕፍት እንዳናነብ ሊከለክሉን አስበው ነበር። ለአካባቢው እንግዳ ስለ መሆናችን ጠየቁን፤ ሆኖም ፊታችንን አትኩረው ከተመለከቱ በኋላ “በመካከላቸው አንዳንድ እንግዶች ቢኖሩም ልጆቻችን ናቸው” አሉ። እኛን የሚጎዳንን ሃይማኖት መጻሕፍት ማጥናታችንን እንድንቀጥል እንደማይፈልጉ ነገሩን።

ለእነዚህ ታዋቂ ሰዎች አንዳችም ትኩረት እንዳንሰጥ ተስማምተን ስለ ነበር ምንም ሳንተነፍስ ወደ ቤታችን ተመለስን። አብዛኞቻችን እየተማርን ባለነው ነገር በጣም ስለ ተደሰትን ጥናታችንን ለመቀጠል ወሰንን። ስለዚህ ጥቂቶች ፈርተው ከቡድናችን ውስጥ ራሳቸውን ቢያገሉም ብዙዎቻችን አንድ አናጺ በሚሠራበት ቤት ውስጥ ጥናታችንን ቀጠልን። ጥናቱን የሚመራልን ሰው አልነበረንም። በጸሎት እንጀምርና ተራ በተራ የመጽሐፉን አንቀጾች እናነብ ነበር። ከአንድ ሰዓት ያህል በኋላ እንደገና እንጸልይና ወደ ቤታችን እንመለሳለን። ይሁን እንጂ ስለላ ያካሄዱብን ነበር፤ የጎሣ አለቆችና የሃይማኖት መሪዎች በየሁለት ሳምንቱ እየጠሩን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ጽሑፎች እንዳናጠና ማስጠንቀቃቸውን ቀጠሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ያለችንን ጥቂት እውቀት ተጠቅመን ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት እንሞክር ነበር፤ ብዙዎችም ይቀበሉን ነበር። ቀስ በቀስ ግለሰቦች ከእኛ ጋር መቀላቀላቸውን ቀጠሉ። በጣም ደስተኞች የነበርን ብንሆንም ስለያዝነው ሃይማኖት ብዙም የምናውቀው ነገር አልነበረም።

በ1932 እኛን ለማደራጀት አንድ ወንድም ከሌጎስ መጣ፤ በሚያዝያ ወር “ባይብል” ብራውንም ጭምር መጣ። ወንድም ብራውን ቡድኑ ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች እንዳሉበት ከተገነዘበ በኋላ በጥናታችን ምን ያህል እድገት እያደረግን እንደሆንን ጠየቀን። የምናውቀውን ሁሉ ነገርነው። እርሱም ለጥምቀት ብቁ መሆናችንን ገለጸ።

ወቅቱ በጋ ስለነበር ከኢሌሻ 14 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ አንድ ወንዝ መጓዝ ነበረብን፤ እዚያም ወደ 30 የምንጠጋው ተጠመቅን። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ለመሆን ብቁ እንደሆንን ተሰማንና ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ማገልገል ጀመርን። ይህን እንድናደርግ ባይጠበቅብንም በዚህ ወቅት የምናውቀውን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ጓጉተን ነበር። የሚያጋጥሙንን የሐሰት ትምህርቶች ለማፍረስ የሚያስችሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን ለማግኘት በሚገባ መዘጋጀት ነበረብን። ስለዚህ በስብሰባዎቻችን ላይ የምናውቃቸውን ነገሮች እርስ በርስ በመከፋፈል ስለ መሠረተ ትምህርቶች እንወያይ ነበር።

የስብከት እንቅስቃሴያችን

ከተማዋን በስብከታችን አዳረስን። ሰዎች ቢያሾፉብንና ቢጮሁብንም እኛ ግድ አልነበረንም። ወደፊት ማወቅ የሚያስፈልጉን ብዙ ነገሮች ቢኖሩም እንኳ እውነትን ስላወቅን በጣም ተደስተን ነበር።

እሑድ እሑድ ሁልጊዜ ከቤት ወደ ቤት እንሄድ ነበር። ሰዎች ጥያቄዎችን ሲጠይቁን መልስ ለመስጠት እንሞክራለን። እሑድ ማታ የሕዝብ ንግግር እናቀርባለን። የመንግሥት አዳራሽ ስላልነበረን የምንሰበሰበው ሜዳ ላይ ነበር። ሰዎችን ሰብስበን ንግግር እንሰጣቸውና ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ እንጋብዛቸዋለን። አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ እንሰብክ ነበር።

ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰምተው የማያውቁ ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ቦታዎችም እንሄድ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በብስክሌቶች የምንሄድ ብንሆንም አልፎ አልፎ አውቶቡስ እንኮናተራለን። ወደ አንድ መንደር ስንገባ ከፍ ባለ ድምፅ ጥሩንባ እንነፋለን። ሰፈሩ ሁላ ይሰማናል! ሰዎች ምን እንደተከሰተ ለማወቅ እየተቻኮሉ ይመጣሉ። ከዚያም መልእክታችንን እንነግራቸዋለን። እንደ ጨረስን ሰዎች ጽሑፎቻችንን ለማግኘት ይሻማሉ። በጣም ብዙ ጽሑፎችን እናበረክታለን።

የአምላክን መንግሥት መምጣት በጉጉት እንጠባበቅ ነበር። የ1935 የዓመት መጽሐፍ ሲደርሰን ከወንድሞች አንዱ ለዓመቱ የሚሆነውን ጠቅላላ የዕለት ጥቅስ ፕሮግራም ተመልክቶ “አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት አንድ ዓመት ሙሉ መቆየት አለብን ማለት ነው?” ሲል እንደጠየቀ አስታውሳለሁ።

የጥናት መሪው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “አርማጌዶን ነገ ቢመጣ የዓመት መጽሐፉ ን ማንበብ የምናቆም ይመስልሃል ወንድም?” በማለት ጠየቀው። ወንድም እንደማናቆም ሲናገር የጥናት መሪው “ታዲያ ምን አስጨነቀህ?” አለው። የይሖዋን ቀን በጉጉት እንጠባበቅ ነበር፤ አሁንም ቢሆን እንደዚያው ነን።

የጦርነቱ ዓመታት

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መጽሐፎቻችንን ወደ አገር ውስጥ እንዳናስገባ ታገድን። በኢሌሻ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም ሪችስ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሳያውቅ ለአንድ ፖሊስ አሳየው። ፖሊሱ “ይህን መጽሐፍ ማን ሰጠህ?” ሲል ጠየቀው። ወንድም የራሴ ነው አለ። ፖሊሱ መጽሐፉ የተከለከለ መሆኑን ነገረውና ወደ ፖሊስ ጣቢያው ወስዶ አሰረው።

ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄድኩና አንዳንድ ጥያቄዎችን ከተጠየቅሁ በኋላ ወንድምን ዋስ ሆኜ አስፈታሁት። ከዚያም የተከሰተውን ችግር ለማሳወቅ በሌጎስ ውስጥ ለሚገኘው ለወንድም ብራውን ስልክ ደወልኩለት። መጽሐፎቻችንን እንዳናሰራጭ የሚያግድ ሕግ ስለመኖሩ ጥያቄ አቀረብኩለት። ወንድም ብራውን መጽሐፎቻችንን ወደ አገር ውስጥ እንዳናስገባ እንጂ እንዳናሰራጭ እንዳልታገድን ነገረኝ። ከሦስት ቀናት በኋላ ወንድም ብራውን የተከሰተውን ነገር እንዲያጣራ አንድን ወንድም ከሌጎስ ላከ። ይህ ወንድም በማግስቱ ሁላችንም መጽሔቶችንና መጻሕፍትን ይዘን ለስብከት ሥራ እንድንወጣ ወሰነ።

በተለያዩ አቅጣጫዎች ተበታተንን። ከአንድ ሰዓት ያህል በኋላ አብዛኞቹ ወንድሞች እንደታሰሩ የሚገልጽ ሪፖርት ደረሰኝ። ስለዚህ ሊጎበኘን የመጣው ወንድምና እኔ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሄድን። መጽሐፎቹ አለመታገዳቸውን ለማስረዳት የሰጠነውን ማብራሪያ ፖሊሶች አልተቀበሉም።

የታሰሩት 33 ወንድሞች በኢፈ ወደሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተወሰዱ፤ እኔም አብሬአቸው ሄድኩ። እኛ ወደዚያ ስንወሰድ የተመለከቱ የከተማዋ ሰዎች “ከእንግዲህ ወዲህ አለቀላቸው። እዚህ እንደገና አይመጧትም” አሉ።

ክሱ በናይጄሪያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፊት ቀረበ። መጽሐፎቹና መጽሔቶቹ በሙሉ ታዩ። አቃቤ ሕጉ እነዚህን ሰዎች ለማሰር ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው በማለት የፖሊስ አዛዡን ጠየቁት። የፖሊስ አዛዡ ይህን ያደረግሁት ከአውራጃው ባለ ሥልጣን መመሪያ ተሰጥቶኝ ነው በማለት መልስ ሰጠ። አቃቤ ሕጉ የፖሊስ አዛዡንና እኔን ጨምሮ አራት ተወካዮቻችንን ወደ እንግዳ መቀበያ አዳራሻቸው አስጠሩን።

አቃቤ ሕጉ የአቶ ብራውንን ማንነት ጠየቁን። በሌጎስ ውስጥ የሚገኝ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተወካይ መሆኑን ገለጽንላቸው። እኛን በተመለከተ ከአቶ ብራውን የቴሌግራም መልእክት እንደ ደረሳቸው ነገሩን። በዚያ ቀን የተቀጠረውን ክስ ለሌላ ጊዜ አስተላለፉና ወንድሞች በዋስ እንዲለቀቁ ያቀረብነውን ጥያቄ ተቀበሉ። በሚቀጥለው ቀን ወንድሞችን በነጻ ለቀቋቸውና መጽሐፎቹን እንዲመልሱልን ፖሊሶቹን አዘዙ።

እየዘመርን ወደ ኢሌሻ ተመለስን። ሰዎች እንደገና መጮኽ ጀመሩ፣ በዚህ ወቅት ግን የጮኹት “እንደገና መጡ!” በማለት ነበር።

ጋብቻን በተመለከተ ይሖዋ ያወጣው የአቋም ደረጃ ግልጽ ተደረገ

የመጀመሪያዎቹ ሦስት የጊልያድ ተመራቂዎች ወደ ናይጄሪያ የመጡት በ1947 ነበር። ከእነዚህ ወንድሞች አንዱ የሆነው ቶኒ አትውድ አሁንም በናይጄሪያ ቤቴል ውስጥ በማገልገል ላይ ነው። ከዚያ ጊዜ አንሥቶ የይሖዋ ድርጅት በናይጄሪያ ውስጥ ከፍተኛ ለውጦችን ሲያደርግ ተመልክተናል። ከተደረጉት ትላልቅ ለውጦቹ አንዱ ከአንድ ሚስት በላይ ስለ ማግባት በነበረን አመለካከት ላይ የተደረገው ነበር።

በ1941 ኦላቢሲ ፋሹባን አገባሁ፤ ሌሎች ተጨማሪ ሚስቶችን ማግባት እንደሌለብኝ ለመገንዘብ የሚያስችል በቂ እውቀት ነበረኝ። ይሁን እንጂ በ1947 ሚስዮናውያን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት በጉባኤዎች ውስጥ የተለመደ ነገር ነበር። ከአንድ ሚስት በላይ ያገቡ ወንድሞች ከአንድ ሚስት በላይ ያገቡት ካለማወቅ የተነሣ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። ስለዚህ ሁለት ወይም ሦስት ወይም አራት ወይም አምስት ሚስቶች ካሏቸው አብረዋቸው ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሆኖም ተጨማሪ ሚስት ማግባት የለባቸውም። እንከተለው የነበረው ደንብ ይህ ነበር።

ብዙ ሰዎች በተለይ ደግሞ በኢሌሻ ውስጥ የሚኖር የቼሩቢምና የሴራፊም ማኅበረሰቦች ከእኛ ጋር ለመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። እውነትን የሚያስተምሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው ይሉ ነበር። የምናስተምራቸውን ትምህርቶች ስለተቀበሉ ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ወደ መንግሥት አዳራሽነት ለመለወጥ ፈለጉ። እንዲህ ዓይነቱን ኅብረት ለመፍጠር በትጋት እንሠራ ነበር። እንዲያውም ሽማግሌዎቻቸውን የምናሠለጥንባቸው ማዕከሎች ነበሩን።

በዚያን ጊዜ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን በተመለከተ አዲስ መመሪያ መጣ። በ1947 በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከሚስዮናውያን አንዱ አንድ ንግግር አደረገ። ጥሩ ጠባይንና ልማዶችን በተመለከተ ተናገረ። ከዚያም ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም የሚለውን 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10ን ጠቀሰ። ቀጥሎም “እንዲሁም ከአንድ በላይ ሚስት የሚያገባ ማንኛውም ሰው የአምላክን መንግሥት አይወርስም!” በማለት አከለ። አድማጮች በምጸት “ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡ ሰዎች የአምላክን መንግሥት አይወርሱማ!” ብለው ጮኹ። ክፍፍል ተፈጠረ። የጦርነት ያህል ነበር። ከአዲሶች መካከል ብዙዎች “አምላክ የተመሰገነ ይሁን፣ ገና አዲስ መሆናችን በጀን” በማለት ራሳቸውን አገለሉ።

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ወንድሞች ተጨማሪ ሚስቶቻቸውን በመፍታት ጋብቻቸውን አስተካከሉ። ገንዘብ ይሰጧቸውና ‘ዕድሜሽ ገና ከሆነ ሂጂና ሌላ ባል ፈልጊ። አንቺን በማግባቴ ተሳስቻለሁ። አሁን ግን የአንዲት ሚስት ባል መሆን አለብኝ’ ይሏቸው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ሌላ ችግር ተፈጠረ። አንዳንዶች አንድ ሚስት ለማግባትና ሌሎችን ለመፍታት ከወሰኑ በኋላ ሐሳባቸውን ቀየሩና ከሌሎች ሚስቶቻቸው ውስጥ አንዷን ለመውሰድና ከዚያ ቀደም ያገቧትን ለመፍታት ወሰኑ! ስለዚህ እንደገና ችግር ተፈጠረ።

ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ስለ ‘ልጅነት ሚስት’ በሚናገረው በሚልክያስ 2:14 ላይ የተመሠረተ ተጨማሪ መመሪያ ተሰጠ። መመሪያው ባሎች መጀመሪያ ያገቧትን ሚስት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ ነበር። ጥያቄው በመጨረሻ እልባት ያገኘው በዚህ መንገድ ነበር።

የአገልግሎት መብቶች

በ1947 ማኅበሩ ጉባኤዎችን ማጠናከርና በወረዳዎች ማደራጀት ጀመረ። ‘የወንድሞች አገልጋዮች’ አሁን ደግሞ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ተብለው የሚጠሩትን በእውቀት የበሰሉ ወንድሞች መሾም ፈለጉ። ወንድም ብራውን እንዲህ ዓይነቱን ሹመት ለመቀበል ፈቃደኛ ስለ መሆኔ ጠየቀኝ። የተጠመቅሁት የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ነው አልኩት፤ አክዬም “እንዲያውም ያጠመቅኸኝ አንተ ነህ። አሁን ይሖዋን የበለጠ ማገልገል የምችልበትን አጋጣሚ ሳገኝ እምቢ የምል ይመስልሃል?” በማለት መለስ ኩለት።

በዚያው ዓመት በጥቅምት ወር ከመካከላችን ሰባት የምንሆነው ተጠራንና ወደ ወረዳ ሥራ ከመላካችን በፊት ሥልጠና ተሰጠን። በእነዚያ ጊዜያት ወረዳዎች ሰፋፊ ነበሩ። ጠቅላላ አገሪቱ በሰባት ወረዳዎች ብቻ ተከፋፍላ ነበር። ጉባኤዎች ጥቂት ነበሩ።

የወንድሞች አገልጋዮች በመሆን የምናከናውነው ሥራ በጣም ከባድ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሞቃታማ በሆነው በሐሩር ክልል ውስጥ በሚገኙ ጫካዎች መካከል አቋርጠን በየቀኑ አያሌ ኪሎ ሜትሮች በእግራችን እንጓዛለን። በየሳምንቱ ከአንዱ መንደር ወደ ሌላው መንደር መጓዝ ነበረብን። አንዳንድ ጊዜ እግሮቼ ሲዝሉ ይሰማኛል። አልፎ አልፎ ልሞት የተቃረብኩ ይመስለኛል! ይሁን እንጂ እጅግ የሚስደስቱ ነገሮችም ነበሩ፤ በተለይ እውነትን የያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ስመለከት በጣም እደሰት ነበር። እንዲያውም በሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ በአገሪቱ ያሉት የአስፋፊዎች ቁጥር በአራት እጥፍ አድጓል!

በ1955 በሕመም ምክንያት ወደ ኢሌሻ እንድመለስ እስከተገደድኩበት ጊዜ ድረስ በወረዳ ሥራ አገልግያለሁ፤ እዚያም የከተማ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ቤት መሆኔ ቤተሰቤን በይበልጥ በመንፈሳዊ ለመርዳት አስችሎኛል። በአሁኑ ወቅት ስድስቱም ልጆቼ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው።

እውነተኛ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም

ያለፉትን በርካታ ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከታቸው አመስጋኝ የምሆንባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አሳዛኝ ነገሮች፣ ጭንቀትና በሽታ ቢያጋጥመኝም ብዙ የሚያስደስቱ ነገሮችንም አግኝቻለሁ። እውቀታችንና ማስተዋላችን እየጨመረ የመጣው ከብዙ ዓመታት በኋላ ቢሆንም 1 ቆሮንቶስ 13:8 “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” የሚለው ምን ትርጉም እንዳለው በተሞክሮ ተረድቻለሁ። ይሖዋን ከወደድከውና በአገልግሎቱ ጸንተህ ከቆምህ ችግሮች በሚያጋጥሙህ ወቅት የሚረዳህ ከመሆኑም በተጨማሪ አትረፍርፎ ይባርክሃል።

የእውነት ብርሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ መጥቷል። እውነትን በሰማንበት ወቅት አርማጌዶን በቶሎ ይመጣል ብለን አስበን ነበር፤ የምንችለውን ያህል ለመሥራት የተጣደፍነውም ለዚህ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የሆነው ለጥቅማችን ነው። መዝሙራዊው “በሕይወቴ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት] አመሰግናለሁ፤ በምኖርበት ዘመን ሁሉ ለአምላኬ እዘምራለሁ” ካለው ሐሳብ ጋር የምስማማው ለዚህ ነው።—መዝሙር 146:2

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ወንድም ብራውን ባይብል ብራውን በመባል የታወቀው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መጨረሻው ባለ ሥልጣን አድርጎ የመጥቀስ ልማድ ስለ ነበረው ነው።—“እውነተኛ ወንጌላዊ ያስገኘው መከር” በሚል በመስከረም 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ በገጽ 32 ላይ የወጣውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ሳሙኤል ከሚልተን ሄንሽል ጋር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳሙኤል ከባለቤቱ ከኦላቢሲ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ