የአንባቢያን ጥያቄዎች
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:9 ላይ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ [“ከማንኛውም ሌላ ስም በላይ” አዓት] ያለውን ስም ሰጠው” ብሏል። ይህ አዲስ ስም ምንድን ነው? ኢየሱስ ከይሖዋ የሚያንስ ከሆነ የኢየሱስ ስም ከማንኛውም ሌላ ስም በላይ የሆነው በምን መንገድ ነው?
ፊልጵስዩስ 2:8, 9 እንዲህ ይነበባል፦ “በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው።”
ይህ ጥቅስ ከሌላ ከማንኛውም በላይ የሆነ ስም ያለው ይሖዋ ስለሆነ ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር አንድ አካል መሆን አለበት የሚል ትርጉም የለውም። በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ውስጥ የሚገኘው በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው ኢየሱስ ከፍ ያለ ስሙን ያገኘው ከሞት ከተነሳ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ይህንን ስም አላገኘም ነበር። በሌላ በኩል ይሖዋ ምንጊዜም ታላቅ ሲሆን ያለው ቦታ ፈጽሞ ተለውጦ አያውቅም። ኢየሱስ ከምድራዊ አገልግሎቱ በፊት ከነበረው ስም የሚበልጥ ስም ተቀብሏል የሚለው እውነታ ኢየሱስ ማለት ይሖዋ ማለት እንዳልሆነ ያሳያል። ኢየሱስ ከማንኛውም ሌላ ስም የበለጠ ስም እንደተቀበለ ጳውሎስ ሲናገር ከአምላክ ፍጥረታት ሁሉ የሚበልጥ ስም አለው ማለቱ ነው።
የኢየሱስ ታላቅ ስም ምንድን ነው? ኢሳይያስ 9:6 መልሱን እንድናገኝ ይረዳናል። ይህ ጥቅስ ይመጣል ተብሎ ይጠበቅ ስለነበረው መሲሕ ማለትም ስለ ኢየሱስ ሲናገር “አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” ይላል። እዚህ ላይ የኢየሱስ ‘ስም’ ከከፍተኛ ቦታና ሥልጣን ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። በፊልጵስዩስ 2:9 ላይ ‘ከስምም ሁሉ በላይ [“ከማንኛውም ሌላ ስም በላይ” አዓት] ያለው ስም’ ተብሎ የተጠቀሰውንም የምንረዳው በዚሁ መንገድ ነው። ይሖዋ ለኢየሱስ የሰጠውን ከፍተኛ ሥልጣን በመቀበል ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲንበረከክ ታዟል፤ ይህም ይሖዋ ለማንኛው ፍጡር ከሰጠው ሥልጣን የላቀ ነው። በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ላይ የገባው “ሌላ” የሚለው ቃል የጥቅሱ ምንጭ በሆነው የግሪኩ ጽሑፍ ላይ ባይገኝም የጥቅሱ ስሜት ይህንን ያመለክታል። የኢየሱስ “ስም” የሚበልጠው ከሌላ ከማንኛውም ፍጥረት ስም እንጂ ከራሱ ስም ጭምር አይደለም።
የኢየሱስን ስም ተቀብለን በጉልበታችን በመንበርከክ ታማኝ ከሆኑት መላእክትና ሰዎች ጋር በመተባበራችን ምንኛ ደስተኞች ነን! ይሖዋ ከፍተኛ ቦታ ለሰጠው “ለእግዚአብሔር አብ ክብር” ማለትም ለኢየሱስ ራሳችንን በማስገዛት ይህንን እናደርጋለን።—ፊልጵስዩስ 2:11፤ ማቴዎስ 28:18