አምላክ እውነተኛውን አምልኮ የሚባርክበት ምክንያት
“ሃሌ ሉያ . . . ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው።”—ራእይ 19:1, 2
1. ታላቂቱ ባቢሎን የምትጠፋው እንዴት ነው?
“ታላቂቱ ባቢሎን” በአምላክ ፊት ወድቃለች፤ በቅርቡ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ትጠፋለች። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው ይህችን ዓለም አቀፍ ሃይማኖታዊ አመንዝራ የሚያጠፏት ፖለቲካዊ ውሽሞችዋ ሲሆኑ ጥፋቷ ድንገተኛና ፈጣን ይሆናል። ኢየሱስ ለዮሐንስ የገለጠለት ራእይ የሚከተሉትን ትንቢታዊ ቃላት ይዟል፦ “አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንሥቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል፦ ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም።”—ራእይ 18:2, 21
2. የይሖዋ አገልጋዮች ባቢሎን ስትጠፋ ምን ይሰማቸዋል?
2 በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት የሚያዝኑት የሰይጣን ዓለም አባላት ሲሆኑ ሰማያዊዎቹም ሆኑ ምድራዊዎቹ የአምላክ አገልጋዮች ግን በዚህ ሁኔታ ፈጽሞ አያዝኑም። የአምላክ አገልጋዮች እንደሚከተለው በማለት ወደ አምላክ በደስታ ይጮሃሉ፦ “ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፣ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፣ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው።”—ራእይ 18:9, 10፤ 19:1, 2
እውነተኛው ሃይማኖት ምን ዓይነት ፍሬ ማፍራት አለበት?
3. የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ያስፈልጋቸዋል?
3 ምድር ከሐሰት ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ በምትጸዳበት ጊዜ እንዳለ የሚቀጥለው የትኛው አምልኮ ነው? በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ ከሚመጣው ጥፋት የሚተርፈው የትኛው የሃይማኖት ቡድን እንደሆነ በአሁኑ ጊዜ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ቡድን የትኞቹን የጽድቅ ፍሬዎች ማፍራት አለበት? ይሖዋ የሚቀበለውን እውነተኛ አምልኮ ለይቶ ለማወቅ የሚያገለግሉ ቢያንስ አሥር መስፈርቶች አሉ።—ሚልክያስ 3:18፤ ማቴዎስ 13:43
4. እውነተኛው አምልኮ ሊያሟላው የሚያስፈልገው የመጀመሪያ መስፈርት ምንድን ነው? በዚህ ረገድ ኢየሱስ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
4 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከምንም ነገር በላይ የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ አለባቸው። ኢየሱስ ለአባቱ ሉዓላዊነት ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጥቷል። ይህን ያደረገው ለፖለቲካዊ፣ ለጎሣ፣ ለዘር ወይም ለማኅበራዊ ጉዳይ አልነበረም። ከሁሉም የአይሁድ ፖለቲካዊ ወይም አብዮታዊ ፍላጎቶች ይልቅ የአባቱን መንግሥት አስቀድሟል። ሰይጣን ዓለማዊ ሥልጣን ልስጥህ የሚል ግብዣ ሲያቀርብለት “ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ብሎታል። ይሖዋ በመላው ምድር ላይ እውነተኛ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተረድቶ ነበር። ከዚህ ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ይልቅ የይሖዋን አገዛዝ በማያሻማ መንገድ የሚደግፈው የትኛው ሃይማኖታዊ ቡድን ነው?—ማቴዎስ 4:10፤ መዝሙር 83:18 አዓት
5. (ሀ) እውነተኛ አምላኪዎች የአምላክን ስም እንዴት ሊመለከቱት ይገባል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ለዚህ ስም አክብሮት እንደሚሰጡ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ እውነተኛው አምልኮ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ማድረግና መቀደስ አለበት የሚለው ነው። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ስሙ ይሖዋ (በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ያህዌህ) መሆኑን ለሕዝቦቹ ለእስራኤላውያን ከመግለጹም በተጨማሪ ይህ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሷል። ሌላው ቀርቶ ከዚህ በፊት አዳም፣ ሔዋንና ሌሎች ሰዎች ምንም እንኳ ሁልጊዜ ስሙን በአክብሮት ባይዙትም ስሙ ማን እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፍጥረት 4:1፤ 9:26፤ 22:14፤ ዘጸአት 6:2 አዓት) የሕዝበ ክርስትናም ሆኑ የአይሁድ ተርጓሚዎች ብዙውን ጊዜ መለኮታዊውን ስም ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ቢያወጡትም የይሖዋ ምሥክሮች የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ ለዚህ ስም ተገቢውን ቦታና አክብሮት ሰጥተውታል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለዚህ ስም አክብሮት ሰጥተዋል። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፣ . . . ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እመለሳለሁ፣ የወደቀችውንም የዳዊትን ድንኳን እንደ ገና እሠራታለሁ፣ ፍራሽዋንም እንደ ገና እሠራታለሁ እንደ ገናም አቆማታለሁ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ።”—ሥራ 15:14-17 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ አሞጽ 9:11, 12
6. (ሀ) እውነተኛው አምልኮ ሊያሟላው የሚገባ ሦስተኛ ብቃት ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስና ዳንኤል የመንግሥቱን አገዛዝ ጠበቅ አድርገው የገለጹት እንዴት ነው? (ሉቃስ 17:20, 21)
6 በሦስተኛ ደረጃ፣ እውነተኛው አምልኮ የሰው ልጆች በአገዛዝ በኩል ላሉባቸው ችግሮች ትክክለኛና ተግባራዊ መፍትሄ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን መናገር አለበት። ኢየሱስ ይህ መንግሥት እንዲመጣና የአምላክ አገዛዝ ምድርን እንዲቆጣጠር እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸዋል። ዳንኤል የመጨረሻዎቹን ቀናት በተመለከተ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ በማለት ተንብዮ ነበር፦ “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ . . . እነዚያንም [የዓለም ፖለቲካዊ] መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ለዚህ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጡ በተግባራቸው ያሳዩ እነማን ናቸው? በታላቂቱ ባቢሎን ሥር ያሉ ሃይማኖቶች ናቸው ወይስ የይሖዋ ምሥክሮች?—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:10፤ 24:14
7. እውነተኞቹ አምላኪዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ይመለከቱታል?
7 እውነተኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስፈልጋቸው አራተኛው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ ማመን ነው። እንዲህ ማድረጋቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ የሰው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውጤት አድርገው ለማቅረብ ከሚሞክሩ ተቺዎች ይጠብቃቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ለጢሞቴዎስ እንደጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ ያምናሉ፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”a በዚህ የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማንኛውም የሕይወታቸው ዘርፍ እንደ መመሪያ የሚጠቀሙበት ከመሆኑም በላይ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ የተስፋ ምንጭ አድርገው ይመለከቱታል። —2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ተለይቶ የሚታወቀው ሃይማኖት
8. እውነተኛው አምልኮ የሚፈለግበት አምስተኛ ብቃት ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹን ለይቶ የገለጻቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ የሰጠው መልስ እውነተኛው አምልኮ ተለይቶ የሚታወቅበትን አምስተኛ መለያ ምልክት ያሳውቀናል። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34, 35 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ኢየሱስ ፍቅሩን ያሳየው እንዴት ነው? ሕይወቱን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ልባዊ ፍቅር እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? ዮሐንስ እንዲህ በማለት ምክንያቱን ይነግረናል፦ “ወዳጆች ሆይ፣ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ . . . እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።”—1 ዮሐንስ 4:7, 8
9. እውነተኛ ፍቅር ያሳዩት እነማን ናቸው? እንዴትስ?
9 በጊዜያችን የዘር፣ የብሔር ወይም የጎሣ ጥላቻ ቢኖርም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ያሳዩት እነማን ናቸው? በፍቅር ተገፋፍተው ራሳቸውን ለከባድ መከራ አልፎ ተርፎም ለሞት አሳልፈው የሰጡ እነማን ናቸው? በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ በተፈጸመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ እጃቸውን ያስገቡት የካቶሊክ ቄሶችና ሴት መነኩሴዎች ናቸው ማለት እንችላለንን? በባልካን አገሮች በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት “በጎሣዊ ምንጠራ” እና በሌሎች ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ተግባራት የተካፈሉት የሰርቢያ ኦርቶዶክሶች ወይም የክሮኤሺያ ካቶሊኮች ናቸው? ወይስ ላለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በሰሜን አየርላንድ መናናቅንና ጥላቻን ሲያራግቡ የነበሩት የካቶሊክ ወይም የፕሮቴስታንት ቀሳውስት? የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ባሉ ግጭቶች ውስጥ ተካፍለዋል ተብለው ሊከሰሱ አይችሉም። ክርስቲያናዊ ፍቅራቸውን ወደ ጎን ከመተው ይልቅ በእስር ቤቶችና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ እስከ ሞት ድረስ ተሰቃይተዋል።—ዮሐንስ 15:17
10. እውነተኛ ክርስቲያኖች ገለልተኛ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
10 በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ካለው አምልኮ የሚፈለገው ስድስተኛ መስፈርት ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ መሆን ነው። ክርስቲያኖች ፖለቲካ ውስጥ መግባት የሌለባቸው ለምንድን ነው? ጳውሎስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንዲህ የምናደርግበትን ጠንካራ ምክንያት ገልጸውልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እርስ በርስ መከፋፈልን በሚያስከትለው ፖለቲካና በሌላ በማንኛውም መንገድ ተጠቅሞ የማያምኑትን ሐሳብ የሚያሳውረው ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” እንደሆነ ጽፏል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል” እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ብሏል። በዚህ የተነሳ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ብልሹ በሆነው የሰይጣን ዓለም ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ወይም ሥልጣን በመያዝ ለአምላክ የሚያቀርበውን ንጹሕ አምልኮ አያጎድፍም።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ያዕቆብ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19
11. (ሀ) ክርስቲያኖች ጦርነትን እንዴት ይመለከቱታል? (ለ) እንዲህ ያለ አቋም ለመውሰድ የሚያስችል ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለ? (2 ቆሮንቶስ 10:3-5)
11 ከዚህ በላይ የተገለጹትን ሁለት መስፈርቶች በመመልከት ሰባተኛውን ከወዲሁ ማወቅ ይቻላል። ይኸውም እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት መካፈል የለባቸውም የሚል ነው። እውነተኛው ሃይማኖት በፍቅር ላይ የተመሠረተ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ስለሆነ ይህንን ‘በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞች ማኅበር’ አንዳችም ነገር ሊከፋፍለው ወይም ኃይሉን ሊያዳክመው አይችልም። ኢየሱስ ያስተማረው ፍቅርን እንጂ ጥላቻን አይደለም፤ ሰላምን እንጂ ጦርነትን አይደለም። (1 ጴጥሮስ 5:9፤ ማቴዎስ 26:51, 52) ቃየን አቤልን እንዲገድለው ያነሳሳው “ክፉው” ሰይጣን በሰው ልጆች መካከል ጥላቻ መዝራትና ሰዎችን በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በጎሣ በመከፋፈል ግጭት መፍጠሩን እንዲሁም ደም ማፋሰሱን ቀጥሏል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅባቸውም ‘ጦርነት አይማሩም።’ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውን ማጭድ ለማድረግ ቀጥቅጠዋል።’ ከአምላክ መንፈስ የሚገኘውን የሰላም ፍሬ አፍርተዋል።—1 ዮሐንስ 3:10-12፤ ኢሳይያስ 2:2-4፤ ገላትያ 5:22, 23
አምላክ ንጹሕ ምግባር ያላቸውንና ያልተበከለ ትምህርት የሚያስተምሩትን ይባርካል
12. (ሀ) ስምንተኛው ብቃት ምንድን ነው? ሆኖም የትኞቹን ሃይማኖታዊ ክፍፍሎች መጥቀስ ትችላለህ? (ለ) ጳውሎስ ይህንን ስምንተኛ ብቃት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
12 ክርስቲያናዊ አንድነት ከእውነተኛው አምልኮ የሚፈለግ ስምንተኛው መስፈርት ነው። ሆኖም የሕዝበ ክርስትና ከፋፋይ ሃይማኖቶች እንዲህ ለማድረግ አያስችሉም። ብዙዎቹ ዋና ተደርገው የሚታዩ ሃይማኖቶች እርስ በርሳቸው እየተከፋፈሉ በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እየተፈጠሩ ሲሆን ይህም ውዥንብር ፈጥሯል። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘውን የባብፕቲስት ሃይማኖት ተመልከት። ይህ ሃይማኖት በሰሜን ባፕቲስት (የአሜሪካ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን)፣ በደቡብ ባፕቲስት (የደቡብ ባፕቲስት እምነት) እና በሌሎች በደርዘን በሚቆጠሩ የባፕቲስት እምነቶች ተከፋፍሏል። (ወርልድ ክርስቲያን ኢንሳይክሎፔድያ ገጽ 714) አብዛኞቹን ክፍፍሎች ያስከተለው የመሠረተ ትምህርት ወይም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ልዩነት ነው (ለምሳሌ ፕሪስቢቴሪያን፣ ኤፒስኮፖሊያን እና ኮንግርጌሽናል።) እንደ ቡድሂዝም፣ እስልምና ወይም ሂንዱኢዝም የመሳሰሉትም ከሕዝበ ክርስትና ውጪ የሆኑ ሃይማኖቶች እርስ በርስ ተከፋፍለዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የመከራቸው ምንድን ነው? “ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11
13, 14. (ሀ) ‘ቅዱስ መሆን’ ምን ይጠይቃል? (ለ) እውነተኛው አምልኮ ንጹሕ እንደሆነ የሚቀጥለው እንዴት ነው?
13 በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖት ሊያሟላው የሚገባ ዘጠነኛ መስፈርት ምንድን ነው? በዘሌዋውያን 11:45 ላይ “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” የሚል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተጠቅሷል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህንን ብቃት ደግሞታል።—1 ጴጥሮስ 1:15 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
14 ቅዱስ መሆን ያስፈልጋል ሲባል ምን ይጠይቃል? የይሖዋ አምላኪዎች በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆን አለባቸው። (2 ጴጥሮስ 3:14) የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት መናቃቸውን በተግባራቸው ለሚያሳዩ ንስሐ ለማይገቡና አውቀው ኃጢአት ለሚሠሩ ሰዎች ቦታ የለም። (ዕብራውያን 6:4-6) ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤ ንጹሕና ቅዱስ እንዲሆን ይፈልጋል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አንዱ መንገድ ጉባኤውን የሚበክሉ ሰዎችን ማስወገድ ነው።—1 ቆሮንቶስ 5:9-13
15, 16. ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ምን ለውጥ አድርገዋል?
15 ብዙዎች የክርስትናን እውነት ከማወቃቸው በፊት ወራዳ የሆነ፣ ደስታን በማሳደድ ላይ የተመሠረተና ራስ ወዳድነት የሚያጠቃው ሕይወት ይመሩ ነበር። ሆኖም ስለ ክርስቶስ የሚናገረው እውነት ለወጣቸውና ኃጢአታቸው ይቅር ተባለላቸው። ጳውሎስ እንዲህ በማለት በጻፈ ጊዜ ይህንን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል፦ “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 6:9-11 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
16 ይሖዋ ቀደም ሲል ከነበራቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አኗኗር ንስሐ ገብተው፣ አካሄዳቸውን የለወጡና ክርስቶስንና እርሱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች በሐቀኝነት የሚከተሉ ሰዎችን እንደሚቀበል አያጠራጥርም። እነዚህ ሰዎች ሌሎችን እንደ ራሳቸው አድርገው ይወድዳሉ። ይህንንም ሳያቋርጡ በአገልግሎቱ በመካፈል ሕይወት የሚያስገኘውን መልእክት ለሚሰሙ ሁሉ በመናገርና በሌሎች የተለያዩ መንገዶች ያሳያሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:5
‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’
17. እውነተኛው ሃይማኖት ሊያሟላው የሚገባ አሥረኛ ብቃት ምንድን ነው? ምሳሌዎች ስጥ።
17 ይሖዋ በመንፈስና በእውነት ከሚያመልኩት ሰዎች የሚጠይቀው አሥረኛ መስፈርት አለ። ይኸውም ያልተበከለ ትምህርት ነው። (ዮሐንስ 4:23, 24) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 8:32) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው እውነት እንደ ነፍስ አለመሞት፣ የሲኦል እሳትና መንጽሔ ከመሳሰሉት አምላክን የማያስከብሩ ትምህርቶች ነፃ አውጥቶናል። (መክብብ 9:5, 6, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4, 20) ከባቢሎን ከመነጨው ምሥጢራዊው የሕዝበ ክርስትና “ቅዱስ ሥላሴ” አላቆናል። (ዘዳግም 4:35፤ 6:4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:27, 28) ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች ከታዘዙ አፍቃሪ፣ አሳቢ፣ ደግና መሐሪ ይሆናሉ። እውነተኛው ክርስትና መናፍቃን በሚል ሰበብ ሰዎችን እንዳስጨፈጨፉት እንደ ቶማስ ደ ቶርኩማዳ የመሳሰሉ ሰዎች ወይም የመስቀል ጦርነትን እንደቆሰቆሱት በጥላቻ የተሞሉ ጳጳሶች በቀልን አያነሳሳም። ታላቂቱ ባቢሎን ግን በመላው የሰው ዘር ታሪክ ከናምሩድ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህንን የመሰለ ፍሬ አፍርታለች።—ዘፍጥረት 10:8, 9
ለየት ያለ ስም
18. (ሀ) እውነተኛው ሃይማኖት ሊያሟላቸው የሚገባውን አሥር ብቃቶች የሚያሟሉት እነማን ናቸው? እንዴትስ? (ለ) ከፊታችን የሚጠብቀንን ተስፋ ለመጨበጥ በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ አለብን?
18 በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ከእውነተኛው አምልኮ የሚፈለጉ አሥር መስፈርቶች የሚያሟሉ እነማን ናቸው? በሌሎች ዘንድ በንጹሕ አቋማቸውና በሰላማዊነታቸው የሚታወቁት እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ‘የዚህ ዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ በዓለም ዙሪያ ይታወቃል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14, 16፤ 18:36) የይሖዋ ሕዝቦች በይሖዋ ስም በመጠራትና ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቱ ታማኝ ምሥክር እንደሆነ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን ሞገስ አግኝተዋል። ስሙ ከሚወክለው ነገር ጋር ተስማምቶ መኖር የሚጠይቅብንን ኃላፊነቶች ልብ በማለት ይህንን ቅዱስ ስም ተሸክመናል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ከፊታችን እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ተዘርግቶልናል! ይኸውም ታዛዥና በአንድነት የተሳሰረ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባል የመሆን እንዲሁም ተመልሳ ገነት በምትሆነው ይህችው ምድር ላይ የአጽናፈ ዓለሙን ልዑል የማምለክ ተስፋ አለን። ይህንን በረከት ለማግኘት እንድንችል በማያሻማ ሁኔታ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን መሰለፋችንንና የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በደስታ መሸከማችንን እንቀጥል። ምክንያቱም “ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸው”!—ራእይ 19:2፤ ኢሳይያስ 43:10-12፤ ሕዝቅኤል 3:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመው በአምላክ መንፈስ መሪነት አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያ ቋንቋዎች በተለያየ መንገድ እንደተረዷቸው ሊያንጸባርቁ ይችላሉ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የይሖዋ አገልጋዮች የታላቂቱን ባቢሎን ጥፋት እንዴት ይመለከቱታል?
◻ እውነተኛው አምልኮ ሊያሟላቸው የሚገቡ ቁልፍ መስፈርቶች የትኞቹ ናቸው?
◻ እውነት ነፃ ያወጣህ እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ምን ልዩ ሞገስ አግኝተናል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ወንጌል ይሰብካሉ እንዲሁም ያስተምራሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ከፖለቲካና ከጦርነት ገለልተኛ ናቸው
[ምንጭ]
አውሮፕላን፦ Courtesy of the Ministry of Defense, London