ጊልያድ ትምህርት ቤት የ100ኛ ክፍል ተመራቂዎቹን ላከ
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የአምላክን መንግሥት በዓለም ዙሪያ ለማወጅ በጊዜያችን እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው። የጊልያድ ትምህርት ቤት ሚስዮናውያንን ማሠልጠን ከጀመረበት ከ1943 ጀምሮ ከዚህ ትምህርት ቤት የተመረቁ ሚስዮናውያን ከ200 በሚበልጡ አገሮች አገልግለዋል። መጋቢት 2, 1996 100ኛውን ክፍል አስመርቋል።
ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት ኒው ዮርክ ፓተርሰን የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከልና አካባቢው ከሁለት ሜትር ከፍታ በላይ በበረዶ ተሸፍኖ ነበር። ስለዚህ በተመረቁበት ዕለት በረዶ መዝነቡ አያስደንቅም። ሆኖም ዋናው አዳራሽ ከመሙላቱም በተጨማሪ በፓተርሰን፣ በዎልኪልና በብሩክሊን ሆነው ፕሮግራሙን ያዳመጡትን ጨምሮ በአጠቃላይ 2, 878 ሰዎች ፕሮግራሙን ለመከታተል ችለዋል።
የአስተዳደር አካል የትምህርት ኮሚቴ አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራስ ሊቀ መንበር ነበር። ወንድም ጃራስ ከብዙ አገሮች ለመጡት እንግዶች ሞቅ ያለ የእንኳን ደህና መጣችሁ ሰላምታ ካቀረበ በኋላ ሁሉም ከመቀመጫቸው ተነስተው መዝሙር ቁጥር 52ን እንዲዘምሩ ጋበዘ። ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ ከተባለው መጽሐፍ “የአባታችን ስም” የተሰኘውን ይህን መዝሙር ሲዘምሩ አዳራሹ ለይሖዋ በሚቀርበው ውዳሴ አስተጋባ። ይህ መዝሙር ያገኘነውን ትምህርት ይሖዋን ለማወደስ ስለመጠቀም ሊቀ መንበሩ ከሰጠው ሐሳብ ጋር ተዳምሮ ለቀሪው ፕሮግራም ድምቀት ሰጥቶት ነበር።
አረጋውያን የሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር
ፕሮግራሙ እንደ ጀመረ ይሖዋን በማገልገል ረጅም ጊዜ ያሳለፉ በርካታ ወንድሞች ለተመራቂዎቹ አጫጭር ንግግሮች አቀረቡ። የዋናው መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆነውና በ1940 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው ሪቻርድ ኤብርሃምሰን “እየተስተካከላችሁ መሄዳችሁን ቀጥሉ” በማለት ተማሪዎቹን አበረታቷቸዋል። ክርስቲያን እንደመሆናቸው መጠን በጊልያድ ያሳለፉትን የአምስት ወር የትምህርት ጊዜ ጨምሮ በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያዎች ያደረጉባቸው የተለያዩ ጊዜያት እንደነበሩ አስታወሳቸው። ታዲያ እየተስተካከሉ መሄድ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
ተናጋሪው በ2 ቆሮንቶስ 13:11 (አዓት) ላይ የሚገኘው የሐዋርያው ጳውሎስ አነጋገር “አንድ ሰው በቀላሉ የማይደረስባቸውን የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ለማሟላት ቀስ በቀስ የሚያደርገውን የእድገት ሂደት፣ ይሖዋ እርሱን ለማስተካከልና ለማረም የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሳያቋርጥ መቀበልና ጥቃቅን ማስተካከያዎችንም ጭምር ማድረግ እንደሚያስፈልገው ያመለክታል” ብሏል። ተመራቂዎቹ ከአገራቸው ውጪ በሚሰጣቸው የአገልግሎት ምድብ ከዚህ በፊት ያላዩአቸው እምነታቸውን የሚፈታተኑ ነገሮች ያጋጥሟቸዋል። አዲስ ቋንቋ መማር፤ ከተለየ ባሕል፣ የኑሮ ሁኔታና ከተለያዩ የአገልግሎት ክልሎች ጋር ራሳቸውን ማስማማት ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም በሚስዮናዊ ቤቶችና በአዲሱ ጉባኤያቸው ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው የተለያየ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሁኔታዎች ባጋጠሟቸው ቁጥር ለመስተካከል ፈቃደኛ በመሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አንድ በአንድ በሥራ ላይ የሚያውሉ ከሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ‘ደስተኛ ሆነው መቀጠል’ ይችላሉ።
በፕሮግራሙ ላይ ከተሳተፉት አምስት የአስተዳደር አካል አባላት አንዱ የሆነው ጆን ባር ከ1 ቆሮንቶስ 4:9 የተወሰደ ጭብጥ ያለው ንግግር አቀረበ። ክርስቲያኖች ለመላእክትና ለሰዎች የቲያትር ተዋንያን መስለው እንደሚታዩ አድማጮቹን አስታወሰ። ከዚያም እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ይህንን ማወቁ በተለይም የሚናገረውና የሚያደርገው ነገር በዓይን በሚታዩትም ሆነ በማይታዩት ተመልካቾቹ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል መገንዘቡ ክርስቲያናዊ ሕይወት የመምራቱን አስፈላጊነት ይበልጥ ያጎላዋል። የጊልያድ ትምህርት ቤት 100ኛ ክፍል ተመራቂዎች የሆናችሁ ውድ ወንድሞችና እህቶች ወደ ተለያዩ አገሮች ስትሄዱ ይህን ጉዳይ ብታስታውሱ ሁላችሁንም በጣም እንደሚጠቅማችሁ አምናለሁ።”
ሚስዮናውያኑ በግ መሰል ለሆኑ ሰዎች እውነትን አሳውቀው ‘አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ እንደሚሆን’ እንዳይዘነጉ ወንድም ባር አርባ ስምንቱን ተማሪዎች አጥብቆ መክሯል። (ሉቃስ 15:10) 1 ቆሮንቶስ 11:10ን በመጥቀስ ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓቶች ያለን ዝንባሌ በዓይናችን የምናያቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ብቻ ሳይሆን በዓይን የማይታዩትን መላእክት እንደሚነካ ተናገረ። ጉዳዩን እንዲህ ሰፋ አድርጎ መመልከቱ እንዴት ጠቃሚ ነው!
ራሱ የጊልያድ ትምህርት ቤት ምሩቅ የሆነው ሌላኛው የአስተዳደር አካል አባል ጌሪት ሎሽ ‘ይሖዋ ለሕዝቡ አጥር እንደሚሆን’ ለማሳየት መዝሙር 125:1, 2፤ ዘካርያስ 2:4, 5 እና መዝሙር 71:21ን (አዓት) የመሳሰሉ ጥቅሶች አብራርቷል። ይሖዋ በማንኛውም ጉዳይ ሕዝቡን ይጠብቃል። አምላክ ይህን ዓይነቱን ጥበቃ የሚያደርገው በታላቁ መከራ ወቅት ብቻ ነውን? ተናጋሪው እንዲህ በማለት መለሰ፦ “አይደለም። ይሖዋ ምን ጊዜም ቢሆን ሕዝቡን የሚጠብቅ ‘የእሳት ቅጥር’ ነው። ከጦርነቱ በኋላ ማለትም በ1919 የመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን የመንግሥቱን ምሥራች በዓለም ዙሪያ ለመስበክ በጣም ጓጉተው ነበር። በሰማይ ያለችው ምሳሌያዊቷ ኢየሩሳሌም ወኪሎች ነበሩ። ይሖዋ በመጨረሻው ዘመን ለእነዚህ ወኪሎቹ መለኮታዊ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቷል። ታዲያ እንቅስቃሴያቸውን ማቆም የሚችለው ማን ነው? ማንም አይችልም።” ይህ ለእነርሱና መለኮታዊውን ፈቃድ በመፈጸሙ ሥራ ከእነርሱ ጋር በቅርብ ለሚተባበሩ ሰዎች ሁሉ እንዴት ያለ ማጽናኛ ነው!
የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ቀደምት አባል የሆነው ዩሊሴስ ግላስ ‘ዓለም አቀፍ በሆነው የይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባላቸው ተስማሚ ሥራ እስከ መጨረሻ ለመቀጠል እንዲጣጣሩ’ ተማሪዎቹን አበረታታቸው። ተስማሚ ሥራ ማለት ከአንድ ሰው ችሎታ ወይም ጠባይ ጋር የሚሄድ ሥራ ወይም ተግባር ማለት ነው። እንዲህ አለ፦ “እናንተ ዕጩ ሚስዮናውያን በይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የሚስማማችሁን ሥራ አግኝታችኋል። አሁንም እንኳ ለዚህ ሥራ ከፍተኛ ዋጋ ብትሰጡትም አሁን ያላችሁበት ሁኔታ ወደፊት በሚስዮናዊነት ለምታሳልፉት ሕይወት ገና መክፈቻው ነው።” ችሎታቸውን ጥሩ አድርገው ለመጠቀም ጥረት ማድረግ እንዲሁም ይሖዋና ድርጅቱ ከሰጧቸው ልዩ የአገልግሎት ምድቦች ጋር ራሳቸውን ማስማማት ያስፈልጋቸዋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የመጨረሻውን ንግግር ያቀረበው ቦሊቪያ ውስጥ ለ17 ዓመታት ያገለገለው የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተዳደር አባል የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ ነው። “አምላክን ትፈትኑታላችሁን?” በማለት ተማሪዎቹን ጠየቃቸው። ይህን ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? እስራኤላውያን አምላክን በተሳሳተ መንገድ ፈትነውታል። (ዘዳግም 6:16) ተናጋሪው “በአምላክ ላይ በማማረር ወይም በማጉረምረም ምናልባትም አንዳንድ ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት እንደሌለን በማሳየት አምላክን መፈተን ስህተት መሆኑ አያጠያይቅም” በማለት ተናገረ። ከዚያም “በምትሄዱበት በአዲሱ የአገልግሎት ምድባችሁ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንዳያድርባችሁ ተከላከሉ” በማለት አጥብቆ አሳሰባቸው። ታዲያ አምላክን መፈተን የምንችልበት ትክክለኛ መንገድ ምንድን ነው? “አምላክን በትክክለኛ መንገድ መፈተን የምንችለው የተናገረውን ካመንንና ያዘዘንን በትክክል ከፈጸምን በኋላ የሚመጣውን ውጤት በእርሱ ላይ በመተው ነው” በማለት ወንድም ሊቨረንስ ተናገረ። በሚልክያስ 3:10 ላይ እንደሰፈረው ይሖዋ “ፈትኑኝ” በማለት ለሕዝቡ ግብዣ አቅርቧል። አሥራታቸውን ሳያሰልሱ ወደ ቤተ መቅደሱ ጎተራ የሚያመጡ ከሆነ ይሖዋ እንደሚባርካቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ተናጋሪው እንዲህ በማለት አሳሰባቸው፦ “እናንተም የሚስዮናዊነት የአገልግሎት ምድባችሁን እንደዚህ ብትመለከቱት ጥሩ ነው። ይሖዋ በሥራችሁ የተሳካላችሁ እንድትሆኑ ስለሚፈልግ ፈትኑት። የአገልግሎት ምድባችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። ምድባችሁ የሚጠይቅባችሁን ማስተካከያዎች አድርጉ። ጽናት ይኑራችሁ። ከዚያም ይሖዋ እንደሚባርካችሁና እንደማይባርካችሁ ተመልከቱ።” ይሖዋን ለሚያመልኩ ሁሉ እንዴት ያለ ግሩም ምክር ነው!
በየተራ የቀረቡት ንግግሮች አብቅተው መዝሙር ከተዘመረ በኋላ አስደሳች የሆኑ ቃለ ምልልሶች በተከታታይ ይቀርቡ ጀመር።
ከመስኩ የተገኙ ተግባራዊ አስተያየቶች
የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተዳደር አዲስ አባል የሆነው ማርክ ኑማር ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ ሳሉ በመስክ አገልግሎት ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች እንዲናገሩ ጋበዛቸው። ተሞክሮዎቹ በአገልግሎት ላይ ቀዳሚ ሆኖ ውይይት መጀመር ጠቃሚ እንደሆነ ከማጉላታቸውም በተጨማሪ ውይይቱን ያዳምጡ የነበሩ ሰዎች ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ ተግባራዊ ነጥቦች አቅርበዋል።
እነዚህኞቹ የጊልያድ ተመራቂዎች በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ከ42 አገሮች ለልዩ ሥልጠና ወደ ፓተርሰን የትምህርት ማዕከል ከመጡ የቅርንጫፍ ቢሮ አባላት ጋር ለመገናኘት መቻላቸው ልዩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ ከብዙ ዓመታት በፊት ከጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቁ ናቸው። በፕሮግራሙ ላይ 3ኛውን፣ 5ኛውን፣ 51ኛውንና 92ኛውን ክፍል እንዲሁም ጀርመን የሚገኘውን የጊልያድ ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ ወክለው ለመጡ ወንድሞች ቃለ መጠየቅ ተደርጎላቸዋል። የሰጡት አስተያየት ምንኛ ጠቃሚ ነበር!
ሚስዮናውያን በአገልግሎት ምድቦቻቸው ያሉ ይሖዋን የሚያወድሱ ሰዎች ከጥቂት ቁጥር ተነስተው በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሲሆኑ በማየታቸው ምን እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። በአንዲስ ተራሮች አጠገብ ተበታትነው ለሚገኙ ነዋሪዎችና የአማዞን ወንዝ በሚነሳበት አካባቢ ላሉ መንደሮች ምሥራቹን በማድረሱ ሥራ ስላደረጉት ተሳትፎ ተናግረዋል። በተጨማሪም ሚስዮናውያኑ በአካባቢው ሰዎች ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች ሳይኖሯቸው ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች እንዴት ይመሰክሩ እንደነበር ተናግረዋል። እነርሱ ራሳቸው አዳዲስ ቋንቋዎችን ለመማር ስላደረጉት ትግልና ተመራቂዎቹ እንደ ቻይንኛ ባሉ ቋንቋዎች ለመመስከርና ንግግር ለመስጠት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብናል ብለው በምክንያታዊነት መጠበቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ከዚህም በላይ ለናሙና የሚሆኑ አቀራረቦችን በስፓንኛ እና በቻይንኛ ቋንቋ በሠርቶ ማሳያ አቅርበዋል። ሚስዮናውያኑ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት ከቋንቋው አልፈው የሰዉን አስተሳሰብ ሲያውቁ እንደሆነ ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። በድሃ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ስለሚመሩት አስቸጋሪ ሕይወት ከተናገሩ በኋላ እንዲህ አሉ፦ “ይህ ዓይነቱ ሕይወት ብዙውን ጊዜ ከጭቆና ጋር ግንኙነት እንዳለው ሚስዮናውያን መገንዘብ አለባቸው። አንድ ሚስዮናዊ እንደ ኢየሱስ የሚሰማው ከሆነ ጥሩ ነው። ኢየሱስ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለነበሩት ሰዎች አዝኖ ነበር።”
መዝሙር ከተዘመረ በኋላ ፕሮግራሙ በመቀጠል የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ኤ ዲ ሽሮደር ንግግር አቀረበ። ወንድም ሽሮደር የጊልያድ ትምህርት ቤት በ1943 ሲከፈት ከመጀመሪያዎቹ አስተማሪዎች አንዱ የመሆን መብት አግኝቶ ነበር። “ይሖዋን እንደ ሉዓላዊ ጌታ ማወደስ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ንግግር ለፕሮግራሙ ተስማሚ መደምደሚያ ነበር። ይሖዋን እንደ ሉዓላዊ ጌታ ማወደስ ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ የሚያሳየው ወንድም ሽሮደር በ24ኛው መዝሙር ላይ ያቀረበው ትኩረት የሚስብ ማብራሪያ በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ አስገርሟቸው ነበር።
ዲፕሎማ ከተሰጠና የመደምደሚያ መዝሙር ከተዘመረ በኋላ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ካርል ክላይን ልብ የሚነካ ጸሎት በማቅረብ ደመደመ። እንዴት ያለ ጠቃሚና መንፈሳዊ ማነቃቂያ የሚያስገኝ ፕሮግራም ነበር!
በምርቃቱ ማግሥት ባሉት ቀናት አርባ ስምንቱ የ100ኛው ክፍል ተመራቂዎች በሚስዮናዊነት ወደ ተመደቡባቸው 17 አገሮች መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሆኖም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገልግሎት መሰማራታቸው አልነበረም። ቀደም ሲልም በሙሉ ጊዜ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ረጅም ጊዜ አሳልፈዋል። ጊልያድ ትምህርት ቤት ሲመዘገቡ ዕድሜያቸው በአማካይ 33 ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደግሞ በአማካይ 11.7 ዓመት አሳልፈዋል። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዓለም አቀፍ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ነበሩ። ሌሎች ደግሞ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግለዋል። አብዛኞቹ ተማሪዎች ከውጭ አገር ሰዎች ጋር ግንኙነት ባለው አንድ ዓይነት አገልግሎት ተካፍለው ያውቃሉ። በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በደሴቶችና በአገራቸው ውስጥ በሚገኙ የውጪ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድኖች አገልግለዋል። አሁን ግን ‘በምናስፈልግበት በማንኛውም የዓለም ክፍል እናገለግላለን’ በማለት በደስታ ለመናገር ከሚችሉ ሌሎች አያሌ ሚስዮናውያን ጋር ተቀላቅለዋል። ሕይወታቸውን ይሖዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ የመጠቀም ልባዊ ምኞት አላቸው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተመራቂዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ፦
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች፦8
የተመደቡባቸው አገሮች፦17
የተማሪዎቹ ብዛት፦48
አማካይ እድሜ፦33.75
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦17.31
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ፦12.06
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት የ100ኛ ክፍል ተመራቂዎች
ቀጥሎ ከፊት ለፊት ከቆሙት ተማሪዎች በመጀመር ከግራ ወደ ቀኝ ስማቸው ተዘርዝሯል።
(1) ሺርሌ ኤም፣ ግሩንድስትረም ኤም፣ ጄናርዲኒ ዲ፣ ጃይሞ ጄ፣ ሾድ ደብልዩ፣ ፌር ፒ፣ ቡካነን ሲ፣ ሮቢንሰን ዲ። (2) ፓይን ሲ፣ ክራኡስ ቢ፣ ራሲኮት ቲ፣ ሃንሰን ኤ፣ ቢትስ ቲ፣ ቤርግ ጄ፣ ጋርሲያ ኤን፣ ፍሌሚንግ ኬ። (3) ዊነሪ ኤል፣ ዊነሪ ኤል፣ ሃርፕስ ሲ፣ ጃይሞ ሲ፣ ቤርግ ቲ፣ ማን ሲ፣ ቤሪያስ ቪ፣ ፋይፈር ሲ። (4) ራንዳል ኤል፣ ጄናርዲኒ ኤስ፣ ክራኡስ ኤች፣ ፍሌሚንግ አር፣ ዳባዲ ኤስ፣ ሺርሌ ቲ፣ ስቴቬንሰን ጂ፣ ቡካነን ቢ። (5) ሮቢንሰን ቲ፣ ጋርሲያ ጄ፣ ሃርፕስ ፒ፣ ራሲኮት ዲ፣ ዳባዲ ኤፍ፣ ፌር ኤም፣ ስቴቬንሰን ጂ፣ ሾድ ዲ። (6) ቢትስ ኤል፣ ፋይፈር ኤ፣ ቤሪዮስ ኤም፣ ፓይን ጄ፣ ማን ኤል፣ ራንዳል ፒ፣ ግሩንድስትረም ጄ፣ ሃንሰን ጂ።