ልድያ እንግዳ ተቀባይ የነበረችው የአምላክ አገልጋይ
የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች ከጥንት ጀምሮ በእንግዳ ተቀባይነታቸው የታወቁ ናቸው። (ዘፍጥረት 18:1-8፤ 19:1-3) “እንግዶችን ማፍቀር፣ መውደድ ወይም ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” የሚል ትርጉም ያለው ከቅን ልቦና የሚወጣው ይህ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ዛሬም የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ነው። እንዲያውም አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሊያሟላው የሚገባ ነገር ነው።—ዕብራውያን 13:2፤ 1 ጴጥሮስ 4:9
እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነን ልድያ ነች። ፊልጵስዩስን ለመጎብኘት የመጡትን ክርስቲያን ሚስዮናውያን ‘አጥብቃ በመለመን’ እቤቷ እንዲያርፉ አድርጋለች። (ሥራ 16:15 የ1980 ትርጉም) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ ልድያ የተጠቀሰው በአጭሩ ቢሆንም ስለ እርሷ የተገለጸው ጥቂት ሐሳብ ግን ለእኛ ማበረታቻ ሊሆን ይችላል። በምን መንገድ? ልድያ ማን ናት? ስለ እርሷስ ምን የምናውቀው ነገር አለ?
“የቀይ ሐር ሻጭ”
ልድያ የመቄዶንያ ዋና ከተማ በሆነችው በፊልጵስዩስ ትኖር ነበር። ይሁን እንጂ ትውድ አገሯ ልድያ የተባለ ክፍለ ሃገር ከተማ በሆነችውና በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው በትያጥሮን ነበር። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች “ልድያ” የሚለው ስም ፊልጵስዩስ ከመጣች በኋላ የተሰጣት የቅጽል ስም ነው በማለት ይናገራሉ። በሌላ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠከረላት ሴት “ሳምራዊት ሴት” ተብላ ልትጠራ እንደምትችል ሁሉ እርሷም “ልድያዊት” ተብላ ትጠራ ነበር። (ዮሐንስ 4:9) ልድያ “ቀይ ሐር” ወይም ቀይ ቀለም የተነከሩ ጌጣጌጦችን ትሸጥ ነበር። (ሥራ 16:12, 14) በትያጥሮንና በፊልጵስዩስ ቀለም የሚነክሩ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር የከርሰ ምድር ጥናት ተመራማሪዎች በቁፋሮ ባገኟቸው የተቀረጹ ጽሑፎች ተረጋግጧል። ልድያ ወደ ፊልጵስዩስ የመጣችው በሥራዋ ምክንያት ማለትም የራሷን ንግድ ለማካሄድ አሊያም በትያጥሮን የሚገኙ ቀለም ነካሪዎችን ወክላ ለመሥራት ሊሆን ይችላል።
ቀይ ሐር ከተለያዩ ነገሮች ሊገኝ ይችላል። በጣም ውድ የሆነው ሐር የሚገኘው በባሕር ውስጥ ከሚኖሩ አንዳንድ የቀንድ አውጣ ዝርያዎች ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ማርሻል የተባለ አንድ ሮማዊ ባለ ቅኔ በጢሮስ (ቀይ ሐር የሚመረትበት ሌላው ቦታ ነው) የሚገኘው ከሁሉ የተሻለው ቀይ ሐር አንድ የቀን ሠራተኛ 2,500 ቀናት ሠርቶ የሚያገኘውን ደሞዝ የሚያክል 10,000 የሮማ ሳንቲም ወይም 2,500 ዲናሬ ሊያወጣ እንደሚችል ተናግሯል። ከእንዲህ ዓይነቱ ቀይ ሐር የሚሠሩ ልብሶች ጥቂት ሰዎች ብቻ ሊያገኟቸው የሚችሉ የቅንጦት ልብሶች እንደሆኑ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት ልድያ በኑሮዋ የበለጸገች ልትሆን ትችላለች። ኑሮዋ ምንም ይሁን ምን ሐዋርያው ጳውሎስንና የእርሱ የሥራ ባልደረቦች የነበሩትን ሉቃስን፣ ሲላስን፣ ጢሞቴዎስንና ሌሎች ሰዎችን በእንግድነት መቀበል ችላ ነበር።
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ያከናወነው ስብከት
ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓን የረገጠውና በፊልጵስዩስ መስበክ የጀመረው በ50 እዘአ አካባቢ ነበር።a ጳውሎስ ወደ አንድ አዲስ ከተማ በሚደርስበት ጊዜ ለአይሁድና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ሰዎች ለመስበክ በመጀመሪያ ሰዎች ወደሚሰበሰቡበት ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። (ከሥራ 13:4, 5, 13, 14፤ 14:1 ጋር አወዳድር።) ሆኖም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት “ቅዱስ ክልል” ተብላ በምትታወቀው በፊልጵስዩስ አይሁዶች ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን እንዳያከናውኑ የሮም ሕግ ይከለክል ነበር። ስለዚህ ሚስዮናውያኑ “ጥቂት ቀኖች” ካሳለፉ በኋላ በሰንበት ቀን ከከተማው ውጪ ባለው ወንዝ አጠገብ ‘የጸሎት ቦታ ነው ብለው የገመቱትን’ አንድ ቦታ አገኙ። (ሥራ 16:12, 13) ይህ ወንዝ ጋንጊተስ የሚባለው ወንዝ ሳይሆን አይቀርም። እዚያም ሚስዮናውያኑ ያገኙት ሴቶችን ብቻ ነበር። ከእነርሱም መሃል አንዷ ልድያ ነበረች።
“እግዚአብሔርን የምታመልክ”
ልድያ “እግዚአብሔርን የምታመልክ” ነበረች። ምናልባት ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠችው ሃይማኖታዊ እውነትን ፈልጋ ሳይሆን አይቀርም። ልድያ ጥሩ ሥራ የነበራት ቢሆንም ቁሳዊ ሀብት የማሳደድ ምኞት ግን አልነበራትም። ከዚህ ይልቅ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ ትመድብ ነበር። “ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት፤” በዚህም የተነሳ እውነትን ተቀበለች። እንዲያውም ‘እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ተጠመቀች።’—ሥራ 16:14, 15
ሌሎቹ የልድያ ቤተሰቦች እነማን እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ለይቶ አይናገርም። ባል እንዳላት አለመገለጹ ነጠላ ወይም መበለት ስለነበረች ሊሆን ይችላል። “ቤተሰቦችዋ” የሚለው ቃል ዘመዶችዋን ሊያመለክት ቢችልም ቃሉ ባሮችን ወይም አገልጋዮችን ለማመልከት ጭምር ሊሠራበት ይችላል። ያም ሆነ ይህ ልድያ የተማረቻቸውን ነገሮች አብረዋት ይኖሩ ለነበሩት ሰዎች በቅንዓት አካፍላለች። እነርሱም እውነትን ሲቀበሉና እውነተኛውን እምነት ሲይዙ በማየቷ ምን ያህል ተደስታ ይሆን!
“በግድም አለችን”
ሚስዮናውያኑ ከልድያ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በራሳቸው ወጪ ቤት ተከራይተው መኖር ነበረባቸው። ይሁን እንጂ እርሷ የሚያስፈልጋቸውን መጠለያና ምግብ ለማቅረብ ፈቃደኛ ነበረች። እነርሱን የግድ ማለቷ ጳውሎስና ጓደኞቹ ግብዣዋን ላለመቀበል ተግደርድረው እንደነበረ የሚያሳይ ነው። ለምን? ጳውሎስ ‘ባለው መብት አላግባብ ሳይጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ለመናገርና’ በማንም ሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ስለፈለገ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 9:18፤ 2 ቆሮንቶስ 12:14) ሉቃስ “እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፣ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ሥራ 16:15) ልድያ ከሁሉ የበለጠ ያሳሰባት ነገር ለይሖዋ ታማኝ ሆና የመገኘቷ ጉዳይ ስለነበር እነርሱን በእንግድነት ለመቀበል መፈለጓም እምነት እንደነበራት የሚያረጋግጥ ነው። (ከ1 ጴጥሮስ 4:9 ጋር አወዳድር።) እንዴት ያለች ግሩም ምሳሌ ናት! እኛስ ንብረታችንን ምሥራቹ የበለጠ እንዲስፋፋ እንጠቀምበታለንን?
በፊልጵስዩስ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞች
ጳውሎስና ሲላስ በአጋንንት ተይዛ የነበረችውን ሴት ባሪያ በመፈወሳቸው ምክንያት ታስረው ከተፈቱ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ሄደው ጥቂት ወንድሞችን አገኙ። (ሥራ 16:40) አዲስ የተቋቋመው የፊልጵስዩስ ጉባኤ አባል የነበሩት አማኞች ዘወትር ስብሰባ ለማድረግ የልድያን ቤት ሳይጠቀሙ አልቀሩም። ቤቷ በከተማው ውስጥ እየተከናወነ ለነበረው ቲኦክራሲያዊ ሥራ ማዕከል ሆኖ አገልግሏል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።
ልድያ በመጀመሪያ ያሳየችው ሞቅ ያለ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የጠቅላላው ጉባኤ መለያ ምልክት ሆኖ ነበር። ምንም እንኳ በፊልጵስዩስ የሚገኙ ወንድሞች ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም በተለያዩ ወቅቶች ለጳውሎስ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ልከውለት ነበር። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው አመስግኗቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:1, 2፤ 11:9፤ ፊልጵስዩስ 4:10, 15, 16
ጳውሎስ ከ60-61 እዘአ አካባቢ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው ደብዳቤ ላይ ልድያን አልጠቀሳትም። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 16 ላይ ያሉት ክንውኖች ከተተረኩ በኋላ ልድያን ምን እንደገጠማት ቅዱሳን ጽሑፎች ምንም ዓይነት ፍንጭ አይሰጡም። ቢሆንም ስለዚህች ታታሪ ሴት ባጭሩ የተገለጸው ታሪክ ‘የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ’ እንዲኖረን ያደርገናል። (ሮሜ 12:13) ልድያን የመሰሉ ክርስቲያኖች በመካከላችን በመኖራቸው ምንኛ አመስጋኞች ነን! እነሱ የሚያሳዩት መንፈስ በጉባኤ ውስጥ ሞቅ ያለ ወዳጅነት እንዲሰፍን ያደርጋል። ይህም ለይሖዋ አምላክ ክብር ያመጣል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በወታደራዊ ቅኝ ግዛት ሥር የነበረችውና በዩስ ኢታሊከም (በኢጣሊያ ሕግ) የምትተዳደረው ፊልጵስዩስ ከመቄዶንያ ታላላቅ ከተሞች ጋር ስትወዳደር አንጻራዊ ብልጽግና የነበራት ከተማ ነች።—ሥራ 16:9, 12, 21
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በፊልጵስዩስ የነበሩ አይሁዶች አኗኗር
በፊልጵስዩስ የነበረው ኑሮ ለአይሁዶችና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ሰዎች ቀላል እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። በዚህ ከተማ ጸረ-አይሁድ የሆነ አቋም ስለነበረ ጳውሎስ ወደ እዚህ ቦታ ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ከሮም እንዲወጡ አዘዘ።—ከሥራ 18:2 ጋር አወዳድር።
ጳውሎስና ሲላስ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበራትን አንዲት ባሪያ ከፈወሱ በኋላ በባለ ሥልጣኖች ፊት አቀረቧቸው። ጌቶቿ ያገኙት የነበረው ትርፍ አሁን ስለቀረባቸው የአገራቸውን ሰዎች በጥላቻ በማነሳሳት “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ” በማለት ተናገሩ። በመጨረሻም ጳውሎስና ሲላስ በዱላ ተደብድበው እስር ቤት ተጣሉ። (ሥራ 16:16-24፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአይሁዳውያን አምላክ የሆነውን ይሖዋን በግልጽ ማምለክ ድፍረትን የሚጠይቅ ሆነ። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ልድያ የያዘችው ከአካባቢው ሕዝብ የተለየ አቋም ፈጽሞ አላስጨነቃትም።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በፊልጵስዩስ የሚገኝ ፍርስራሽ