የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 11/1 ገጽ 7-12
  • መጽናናትን ለማግኘት ይሖዋን ተስፋ አድርግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽናናትን ለማግኘት ይሖዋን ተስፋ አድርግ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አንድ የሚያጽናና ተስፋ ፍጻሜ አገኘ
  • ከኖኅ የሚበልጥ ሰው
  • ማጽናኛ የሚገኘው ከየት ነው?
  • ከባድ ፈተና በሚኖርበት ጊዜ
  • እውነተኛ መጽናኛ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ‘ያዘኑትን አጽናኑ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • አምላክ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት ማጽናኛ ማግኘት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 11/1 ገጽ 7-12

መጽናናትን ለማግኘት ይሖዋን ተስፋ አድርግ

“የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ።”—ሮሜ 15:5

1. እያንዳንዱ ቀን ማጽናኛ የማግኘትን አስፈላጊነት እየጨመረ እንዲሄድ የሚያደርገው ለምንድን ነው?

እያንዳንዱ ቀን ባለፈ መጠን ማጽናኛ የማግኘት አስፈላጊነትም የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከ1,900 ዓመታት በፊት እንዳለው “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ” እየኖረ ነው። (ሮሜ 8:22) በዘመናችን ‘ምጡና ሥቃዩ’ ከምንጊዜውም ይበልጥ የከፋ ሆኗል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ የሰው ልጅ ጦርነት፣ ወንጀል፣ ብዙውን ጊዜ ሰው ምድርን አላግባብ በመጠቀሙ ምክንያት የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች ሲፈራረቁበት ኖረዋል።—ራእይ 11:18

2. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጅ ላይ ለደረሰው ወዮታ ከማንም በላይ ተጠያቂ የሆነው ማን ነው? (ለ) እንድንጽናና የሚያደርገን የትኛው ሐቅ ነው?

2 በጊዜያችን ሥቃይና መከራ ይህን ያህል ሊበዛ የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት በ1914 ከተወለደ በኋላ ሰይጣን ከሰማይ ስለተጣለበት ሁኔታ ሲናገር እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራእይ 12:12) የዚህን ትንቢት ፍጻሜ የሚያሳየው ግልጽ ማስረጃ የሰይጣን ክፉ አገዛዝ በሚያከትምበት የመጨረሻ ጊዜ ላይ እንደደረስን የሚያመለክት ነው። በቅርቡ በምድር ላይ ያለው ሕይወት ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን እንዲያምፁ ከማድረጉ በፊት ወደነበረው ሰላማዊ ሁኔታ የሚመለስ መሆኑን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

3. ሰዎች ማጽናኛ ሳያስፈልጋቸው ይኖሩ የነበረው መቼ ነበር?

3 ቀደም ሲል የሰው ዘር ፈጣሪ ለመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት መኖሪያ የሚሆን አንድ ውብ የአትክልት ሥፍራ አዘጋጅቶ ነበር። ቦታው ይገኝ የነበረው “ደስታ” ወይም “እርካታ” የሚል ትርጉም በነበረው ኤደን ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ነበር። (ዘፍጥረት 2:8 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) ከዚህም በላይ አዳምና ሔዋን ፍጹም ጤና ኖሯቸው ለዘላለም ሳይሞቱ የመኖር ተስፋ ነበራቸው። የአትክልተኝነት፣ የኪነ ጥበብ፣ የግንባታ ሥራ፣ የሙዚቃና የመሳሰሉ ችሎታዎቻቸውን ማዳበር የሚችሉባቸው ምን ያህል የሥራ መስኮች እንደነበሯቸው እስቲ አስበው። ምድርን እንዲገዙና ገነት እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሚፈጽሙበት ጊዜ ምርምር ሊያደርጉባቸው የሚችሉባቸውን የፍጥረት ሥራዎችም እስቲ ቆም ብለህ አስብ። (ዘፍጥረት 1:28) በእርግጥም የአዳምና የሔዋን ሕይወት በሥቃይና በምጥ ሳይሆን በደስታና በእርካታ የተሞላ ይሆን ነበር። ማጽናኛ በሚያስፈልገው ሁኔታ ሥር እንዳልነበሩ ግልጽ ነው።

4, 5. (ሀ) አዳምና ሔዋን የታዛዥነትን ፈተና ሳያልፉ የቀሩት ለምንድን ነው? (ለ) የሰው ልጅ ማጽናኛ በሚያስፈልገው ሁኔታ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው?

4 ሆኖም አዳምና ሔዋን ለደጉ ሰማያዊ አባታቸው የጠለቀ ፍቅርና አድናቆት መኮትኮት ያስፈልጋቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር አምላክን በማንኛውም ሁኔታ ሥር እንዲታዘዙት ይገፋፋቸው ነበር። (ከዮሐንስ 14:31 ጋር አወዳድር።) የሚያሳዝነው ግን ሁለቱም የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ባለመብቱን ሉዓላዊ ጌታቸውን ይሖዋን ሳይታዘዙ ቀሩ። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን ወራዳ ምግባር ለፈጸመው መልአክ ለሰይጣን ዲያብሎስ ክፉ አገዛዝ አሳልፈው ሰጡ። ሔዋንን ኃጢአት እንድትሠራ የፈተናትና የተከለከለውን ፍሬ እንድትበላ ያደረጋት ሰይጣን ነው። አዳምም “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ብሎ አምላክ በግልጽ ካስጠነቀቀው ዛፍ ፍሬ በበላ ጊዜ ኃጢአት ሠራ።—ዘፍጥረት 2:17

5 በዚህ መንገድ ኃጢአተኞቹ ባልና ሚስት ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። አምላክ በአዳም ላይ ሞት በፈረደበት ጊዜ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሮ ነበር፦ “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።” (ዘፍጥረት 3:17, 18) ስለዚህ አዳምና ሔዋን ያልለማውን ምድር ገነት ማድረግ የሚችሉበትን አጋጣሚ አጡ። ከኤደን በመባረራቸው ከተረገመችው ምድር ፍሬ ለማፍራት ጥረውና ግረው ለመሥራት ተገደዱ። ዘሮቻቸው ይህን የኃጢአተኝነትና የሞት ባሕርይ ስለወረሱ ማጽናኛ በሚያስፈልገው አስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ወደቁ።—ሮሜ 5:12

አንድ የሚያጽናና ተስፋ ፍጻሜ አገኘ

6. (ሀ) የሰው ልጅ ኃጢአት ከሠራ በኋላ አምላክ ምን የሚያጽናና ተስፋ ሰጠ? (ለ) ማጽናኛን በተመለከተ ላሜሕ ምን ትንቢት ተናገረ?

6 ይሖዋ የሰው ልጅን ለዓመፅ ባነሣሣው ፍጡር ላይ ፍርድ በሰጠበት ጊዜ ‘ማጽናኛ የሚሰጥ አምላክ’ መሆኑን አረጋግጧል። (ሮሜ 15:5) ይህን ያደረገው የአዳምን ዘሮች የአዳም ዓመፅ ካስከተለባቸው ጠንቅ የሚያላቅቅ “ዘር” እንደሚልክ ቃል በመግባት ነው። (ዘፍጥረት 3:15) ከጊዜ በኋላም አምላክ ነጻ ስለሚያወጣበት መንገድ አንዳንድ ፍንጮች መስጠት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል በአዳም ልጅ በሴት በኩል የአዳም የሩቅ ዘመድ የሆነው ላሜሕ ልጁ ስለሚያደርገው ነገር የሚከተለውን ትንቢት በመንፈስ አነሳሽነት እንዲናገር አድርጎታል፦ “እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል።” (ዘፍጥረት 5:29) ከዚህ ከተሰጠው ተስፋ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ልጁ “ዕረፍት” ወይም “መጽናኛ” የሚል ትርጉም ያለው ኖኅ የሚል ስም ተሰጠው።

7, 8. (ሀ) አምላክ ሰውን በመፍጠሩ እንዲጸጸት ያደረገው ሁኔታ ምን ነበር? በምላሹስ ምን እርምጃ ለመውሰድ ወሰነ? (ለ) ኖኅ ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ሥራ ያከናወነው እንዴት ነው?

7 ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰይጣን ከሰማያዊ መላእክት መካከል አንዳንድ ተከታዮች እያገኘ ነበር። እነዚህ መላእክት የሰው ሥጋ ለብሰው ከአዳም ዘሮች መካከል ቆንጆ ቆንጆ የሆኑትን ሴቶች ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። ይህ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ጥምረት ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ይበልጥ ከማበላሸቱም በላይ ምድርን በዓመፅ እንድትሞላ ያደረጉ ኔፊሊም የሚባሉ “እያነሱ የሚያፈርጡ” አምላክ የለሽ ዘሮች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነ። (ዘፍጥረት 6:1, 2, 4, 11፤ ይሁዳ 6) “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ . . . አየ። እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፣ በልቡም አዘነ።”—ዘፍጥረት 6:5, 6

8 ይሖዋ ያን ክፉ ዓለም ምድር አቀፍ በሆነ የጥፋት ውኃ ለማጥፋት ወሰነ፤ በመጀመሪያ ግን ሕይወትን ለማዳን ሲል ኖኅን መርከብ እንዲሠራ አደረገው። በዚህ መንገድ የሰው ዘርና የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች ከጥፋቱ ሊተርፉ ቻሉ። ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋቱ ውኃ በኋላ ከመርከቡ ውስጥ ወጥተው ወደ ጸዳችው ምድር ሲገቡ እንዴት ያለ እፎይታ ተሰምቷቸው ይሆን! በምድር ላይ ደርሶ የነበረው እርግማን ተወግዶ የእርሻ ሥራ ይበልጥ ቀላል ሆኖ ማግኘት ምንኛ የሚያጽናና ነው! በእርግጥም የላሜሕ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል፤ ኖኅም ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ሥራ ሠርቷል። (ዘፍጥረት 8:21) ኖኅ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን ለሰው ዘር መጠነኛ የሆነ “መጽናኛ” በማምጣት ረገድ የጎላ ሚና ተጫውቷል። ይሁን እንጂ ሰይጣንና አጋንንት መላእክቱ የሚያሳድሩት መጥፎ ተጽዕኖ ከጥፋት ውኃው ጋር አብሮ አልተወገደም፤ የሰው ዘርም በኃጢአት፣ በበሽታና በሞት ቀንበር በመቃተት ላይ ይገኛል።

ከኖኅ የሚበልጥ ሰው

9. ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሐ ለገቡ ሰዎች ረዳትና አጽናኝ መሆኑን ያስመሰከረው እንዴት ነው?

9 በመጨረሻ፣ ወደ 4,000 ዓመት ከሚጠጋ የሰው ልጅ ታሪክ በኋላ ቃል የተገባለት ዘር መጣ። ይሖዋ አምላክ ለሰው ዘር ባለው ከፍተኛ ፍቅር በመገፋፋት ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ቤዛ ሆኖ እንዲሞት አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከው። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕታዊ ሞቱ ለሚያምኑ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ትልቅ እፎይታ አምጥቶላቸዋል። ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑና ተጠምቀው የልጁ ደቀ መዛሙርት የሆኑ ሁሉ ዘላቂ እርካታና ማጽናኛ ያገኛሉ። (ማቴዎስ 11:28-30፤ 16:24) አለፍጽምና ቢኖርባቸውም አምላክን በንጹሕ ሕሊና በማገልገል የጠለቀ ደስታ ያገኛሉ። በኢየሱስ ማመናቸውን ከቀጠሉ የዘላለም ሕይወት በማግኘት እንደሚካሱ ማወቃቸው ምንኛ ያጽናናቸዋል! (ዮሐንስ 3:36፤ ዕብራውያን 5:9) ባለባቸው ድክመት ምክንያት ከባድ ኃጢአት ቢፈጽሙ ከሞት የተነሣው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ረዳት ወይም አጽናኝ ይሆንላቸዋል። (1 ዮሐንስ 2:1, 2 አዓት) እንዲህ ዓይነቱን ኃጢአት በመናዘዝና ኃጢአትን ልማድ ከማድረግ ለመራቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርምጃዎች በመውሰድ እፎይታ ያገኛሉ፤ ምክንያቱም አምላክ ‘ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት የታመነና ጻድቅ እንደሆነ’ ያውቃሉ።—1 ዮሐንስ 1:9፤ 3:6፤ ምሳሌ 28:13

10. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከፈጸማቸው ተአምራት ምን እንማራለን?

10 ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ጋኔን የያዛቸውን በማስለቀቅ፣ ማንኛውንም ዓይነት በሽታ በመፈወስና ውድ የሆኑ የሞቱ ሰዎችን ዳግም ሕያው በማድረግም እፎይታ አስገኝቷል። እርግጥ ነው፣ እነዚህን በረከቶች ያገኙት ሰዎች ከጊዜ በኋላ አርጅተው ስለሞቱ ተአምራቱ ያስገኘላቸው ጥቅም ጊዜያዊ ብቻ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ይህን በማድረግ ወደፊት በሰው ዘሮች ላይ የሚያፈሳቸውን ዘላቂ በረከቶች አመልክቷል። በአሁኑ ጊዜ ኃያል ሰማያዊ ንጉሥ በመሆኑ በቅርቡ አጋንንትን ከማስወጣትም የበለጠ ነገር ያደርጋል። ከእንቅስቃሴ ውጪ በማድረግ ከመሪያቸው ከሰይጣን ጋር ወደ ጥልቁ ይወረውራቸዋል። ከዚያ በኋላ ክብራማው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል።—ሉቃስ 8:30, 31፤ ራእይ 20:1, 2, 6

11. ኢየሱስ ራሱን “የሰንበት ጌታ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

11 ኢየሱስ “የሰንበት ጌታ” እንደሆነ ከመናገሩም በላይ አብዛኛውን ፈውስ የፈጸመው በሰንበት ቀን ነበር። (ማቴዎስ 12:8-13፤ ሉቃስ 13:14-17፤ ዮሐንስ 5:15, 16፤ 9:14) ይህን ያደረገው ለምን ነበር? ሰንበት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ክፍል ነበር፤ በመሆኑም ‘ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር ጥላ’ ሆኖ አገልግሏል። (ዕብራውያን 10:1) ስድስቱ የሥራ ቀናት የሰው ልጅ በሰይጣን የጭቆና አገዛዝ ሥር ያሳለፋቸውን 6,000 የባርነት ዓመታት ያስታውሱናል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያለው የሰንበት ቀን የሰው ዘር በታላቁ ኖኅ በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ዘመን የሚያገኘውን የሚያጽናና ዕረፍት እንድናስብ ያደርገናል።—ከ2 ጴጥሮስ 3:8 ጋር አወዳድር።

12. ወደፊት ምን የሚያጽናኑ ነገሮችን በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን?

12 የክርስቶስ አስተዳደር ምድራዊ ተገዢዎች በመጨረሻ ከሰይጣን መጥፎ ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ሲላቀቁ እንዴት ያለ እፎይታ ይሰማቸው ይሆን! አካላዊ፣ ስሜታዊና አእምሮአዊ ፈውስ ሲያገኙ ደግሞ ይበልጥ ይጽናናሉ። (ኢሳይያስ 65:17) ከዚያ በኋላ ከሞት የሚነሱትን የሚወዷቸውን ሰዎች መቀበል ሲጀምሩ የሚሰማቸውን ደስታ እስቲ አስበው! በእነዚህ መንገዶች አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል።” (ራእይ 21:4) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ቀስ በቀስ መፈጸም ሲጀምሩ ታዛዥ የሆኑት የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች የአዳም ኃጢአት ካስከተለባቸው መጥፎ ውጤት ሙሉ በሙሉ በመላቀቅ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። (ራእይ 22:1-5) ከዚያ በኋላ ሰይጣን “ለጥቂት ጊዜ” ይፈታል። (ራእይ 20:3, 7) የይሖዋን ትክክለኛ ሉዓላዊነት በታማኝነት የደገፉ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ። ሙሉ በሙሉ “ከጥፋት ባርነት ነፃ” መውጣት የሚያስገኘውን ይህ ነው የማይባል ደስታና እፎይታ እስቲ አስበው! በዚህ መንገድ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ‘የእግዚአብሔር ልጆች የሚያገኙትን ክብራማ ነፃነት’ ይጎናጸፋሉ።—ሮሜ 8:21

13. እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ አምላክ የሚሰጠው ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

13 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ እየደረሰ ባለው ሥቃይና ምጥ እየቃተትን እንኖራለን። እየጨመረ የሄደው አካላዊ ሕመምና የስሜት መቃወስ ታማኝ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ያጠቃል። (ፊልጵስዩስ 2:25-27፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ የምንታዘዝ’ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ሰይጣን አግባብ ያልሆነ ብዙ ትችትና ስደት ያደርስብናል። (ሥራ 5:29) ስለዚህ እስከ ሰይጣን ዓለም ፍጻሜ ድረስ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ጸንተን መኖር እንድንችል ይሖዋ የሚሰጠው ማጽናኛ፣ እርዳታና ብርታት ያስፈልገናል።

ማጽናኛ የሚገኘው ከየት ነው?

14. (ሀ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ምን ቃል ገብቷል? (ለ) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ከሚሰጠው ማጽናኛ ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንድንችል ምን ነገር አስፈላጊ ነው?

14 ኢየሱስ ከሞተበት ቀን በፊት በነበረው ምሽት ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚለያቸውና ወደ አባቱ እንደሚመለስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ገልጾላቸው ነበር። ይህን ሲሰሙ በጣም አዝነውና ተረብሸው ነበር። (ዮሐንስ 13:33, 36፤ 14:27-31) የማያቋርጥ ማጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘብ ኢየሱስ “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል” ሲል ቃል ገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 14:16 አዓት የግርጌ ማስታወሻ) ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ከ50 ቀናት በኋላ በደቀ መዛሙርቱ ላይ ስለፈሰሰው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መናገሩ ነበር።a የአምላክ መንፈስ ብዙ ነገሮች አድርጎላቸዋል፤ በፈተናዎች ወቅት አጽናንቷቸዋል፤ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እንዲቀጥሉም አጠንክሯቸዋል። (ሥራ 4:31) ይሁን እንጂ ይህ እርዳታ እንዲሁ የሚገኝ ነገር ተደርጎ መታየት የለበትም። ከዚህ እርዳታ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት እያንዳንዱ ክርስቲያን አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የሚሰጠውን የሚያጽናና እርዳታ ለማግኘት ዘወትር መጸለይ ይኖርበታል።—ሉቃስ 11:13

15. ከይሖዋ ማጽናኛ የምናገኝባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

15 አምላክ ማጽናኛ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) ይህ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ውስጥ የተጻፉትን ነገሮች አዘውትረን ማጥናትና ማሰላሰል እንዳለብን ያሳያል። በተጨማሪም ከአምላክ ቃል የሚያጽናኑ ትምህርቶች በሚሰጥባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር መገኘት አለብን። ከእነዚህ ስብሰባዎች ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል አንዱ እርስ በርስ መበረታታት ነው።—ዕብራውያን 10:25

16. አምላክ ማጽናኛ የሚሰጥባቸው ዝግጅቶች ምን እንድናደርግ ሊገፋፉን ይገባል?

16 ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀጥሎ የገለጸውም ሐሳብ በአምላክ አጽናኝ ዝግጅቶች በሚገባ በመጠቀም የምናገኛቸውን ጥሩ ውጤቶች ይጠቁማል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ልብ ሆናችሁ በአንድ አፍ እግዚአብሔርን፣ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፣ ታከብሩ ዘንድ የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ፈቃድ እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ መሆንን ይስጣችሁ።” (ሮሜ 15:5, 6) አዎን፣ በአምላክ አጽናኝ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ደፋሩን መሪያችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ይበልጥ መምሰል እንችላለን። ይህም አፋችንን በምሥክርነቱ ሥራችን፣ በስብሰባዎቻችን ላይ፣ ከመሰል አማኞች ጋር በምናደርገው የግል ጭውውትና በጸሎታችን አምላክን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንድንጠቀምበት ይገፋፋናል።

ከባድ ፈተና በሚኖርበት ጊዜ

17. ይሖዋ ልጁን ያጽናናው እንዴት ነው? ምን ውጤትስ አስገኘ?

17 ኢየሱስ በከፍተኛ ሁኔታ ተሠቃይቶ ከመሞቱ በፊት በነበረው ሌሊት ‘እጅግ አዝኖና በጣም ተክዞ’ ነበር። (ማቴዎስ 26:37, 38) ስለዚህ ከደቀ መዛሙርቱ ተነጥሎ ትንሽ ራቅ አለና አባቱ እንዲረዳው ጸለየ። “እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።” (ዕብራውያን 5:7) መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ [ለኢየሱስ] ታየው” ሲል ይገልጻል። (ሉቃስ 22:43) ኢየሱስ በድፍረትና በቆራጥነት መንፈስ ተቃዋሚዎቹን የተቋቋመበት መንገድ አምላክ ልጁን ያጽናናበት መንገድ እጅግ ውጤታማ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 18:3-8, 33-38

18. (ሀ) በሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ በተለየ ሁኔታ ፈታኝ ሆኖበት የነበረው ጊዜ የትኛው ነው? (ለ) በትጋት ለሚሠሩ ሩኅሩኅ ሽማግሌዎች የመጽናኛ ምንጭ ልንሆንላቸው የምንችለው እንዴት ነው?

18 ሐዋርያው ጳውሎስም ከባድ ፈተናዎች ያሳለፈባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል በኤፌሶን ያከናወነው አገልግሎት ‘በእንባና ከአይሁድ ሴራ በደረሰበት ፈተና’ የተሞላ ነበር። (ሥራ 20:17-20) በመጨረሻ ጳውሎስ የሴት አምላክ የሆነችው የአርጤምስ ተከታዮች የስብከት ሥራውን በመቃወም ከተማዋን በሁከት ባናወጧት ጊዜ ኤፌሶንን ለቅቆ ወጣ። (ሥራ 19:23-29፤ 20:1) ጳውሎስ በሰሜን በኩል ወደ ጢሮአዳ ባቀናበት ጊዜ አንድ ነገር አእምሮውን በጣም እየረበሸው ነበር። በኤፌሶን ካጋጠመው ሁከት ጥቂት ቀደም ብሎ አንድ የሚረብሽ ሪፖርት ደርሶት ነበር። ከተቋቋመ ብዙም ያልቆየው የቆሮንቶስ ጉባኤ በመካከሉ መከፋፈል ተፈጥሮ የነበረ ከመሆኑም በላይ ዝሙት ሲፈጸም በቸልታ ይታይ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ሁኔታውን ለማረም ሲል ከኤፌሶን ሆኖ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያዘለ ደብዳቤ ጻፈ። ይህን ማድረግ ለእሱ ቀላል አልነበረም። በኋላ በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ “በብዙ መከራና ከልብ ጭንቀት በብዙም እንባ ጽፌላችሁ ነበር” ሲል ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 2:4) ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ ርኅሩኅ የሆኑ ሽማግሌዎችም እርምትና ተግሣጽ የመስጠቱን ጉዳይ ቀላል ሆኖ አያገኙትም፤ ለዚህም አንዱ ምክንያት ራሳቸውም ድክመት እንዳለባቸው የሚያውቁ በመሆኑ ነው። (ገላትያ 6:1) እንግዲያው በፍቅራዊ መንገድ ለሚሰጡን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኃላፊነት ቦታ ለሚሠሩት ወንድሞች ማጽናኛ እንሁናቸው።—ዕብራውያን 13:17

19. ጳውሎስ ከጢሮአዳ ወደ መቄዶንያ የተጓዘው ለምን ነበር? በመጨረሻ እፎይታ ያገኘውስ እንዴት ነው?

19 ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ ለቆሮንቶስ ወንድሞች ደብዳቤ ከመጻፉም በላይ እነርሱን እንዲረዳቸውና ለደብዳቤው የሰጡትን ምላሽ ተመልሶ ሪፖርት እንዲያደርግለት ቲቶን ልኮት ነበር። ጳውሎስ ቲቶን ሲመለስ ጢሮአዳ ላይ አገኘዋለሁ ብሎ አስቦ ነበር። ጳውሎስ በጢሮአዳ ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚችልባቸውን ጥሩ አጋጣሚዎች በማግኘት ተባርኳል። ሆኖም ቲቶ በመዘግየቱ ይህ የጳውሎስን ጭንቀት ሊያቀልለት አልቻለም። (2 ቆሮንቶስ 2:12, 13) ስለዚህ ቲቶን መቄዶንያ ላይ አገኘው ይሆናል ብሎ በማሰብ ወደዚያ ተጓዘ። ጳውሎስ እዚያ ሲያገለግል በገጠመው ኃይለኛ ተቃውሞ ሳቢያ ጭንቀቱ ይበልጥ ተባባሰ። “ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፣” አለ ጳውሎስ፣ “በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም፤ በውጭ ጠብ ነበረ፣ በውስጥ ፍርሃት ነበረ። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን” ሲል ገልጿል። (2 ቆሮንቶስ 7:5, 6) በመጨረሻ ቲቶ መጥቶ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጻፈው ደብዳቤ ጥሩ ምላሽ እንዳሳዩ ሲነግረው ጳውሎስ እንዴት ያለ እፎይታ ተሰምቶት ይሆን!

20. (ሀ) በጳውሎስ ሁኔታ ላይ እንደታየው ይሖዋ ማጽናኛ የሚሰጥበት ሌላው ትልቁ መንገድ ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

20 የጳውሎስ ተሞክሮ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች የሚያጽናና ነው፤ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ‘እንዲያዝኑ’ ወይም ‘እንዲጨነቁ’ የሚያደርጓቸው ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። (ፊሊፕስ) አዎን፣ ‘ማጽናኛ የሚሰጠው አምላክ’ እያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ነገር ያውቃል፤ በተጨማሪም ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የንስሐ ዝንባሌ እንዳሳዩ ቲቶ በነገረው ጊዜ እንደተጽናና ሁሉ እኛም አንዳችን ለሌላው የመጽናኛ ምንጭ እንድንሆን ሊጠቀምብን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 7:11-13) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መልሶ የጻፈውን የሚያበረታታ ደብዳቤና ይህ በዛሬው ጊዜ እኛም አምላክ የሚሰጠውን ማጽናኛ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድናካፍል እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ላይ ካከናወናቸው ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆችና የኢየሱስ ወንድሞች አድርጎ መቀባት ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) ይህ ለ144,000 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ብቻ የተወሰነ ነው። (ራእይ 14:1, 3) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ በደግነት ተሰጥቷቸዋል። ቅቡዓን ባይሆኑም እንኳ እነርሱም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታና ማጽናኛ ያገኛሉ።

ልትመልስ ትችላለህን?

◻ የሰው ልጅ ማጽናኛ በሚያስፈልገው ሁኔታ ሥር የወደቀው እንዴት ነው?

◻ ኢየሱስ ከኖኅ የሚበልጥ መሆኑን ያስመሰከረው እንዴት ነው?

◻ ኢየሱስ ራሱን “የሰንበት ጌታ” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

◻ አምላክ በዛሬው ጊዜ ማጽናኛ የሚሰጠው እንዴት ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጳውሎስ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ቲቶ ባቀረበለት ሪፖርት ትልቅ ማጽናኛ አግኝቷል

መቄዶንያ

ፊልጵስዩስ

ግሪክ

ቆሮንቶስ

እስያ

ጢሮአዳ

ኤፌሶን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ