የተሻለ መንገድ
የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዓለም ውስጥ መንፈሳዊነት ቀስ በቀስ እየጠፋ መሄዱም ሆነ ኅብረተሰቡን ያጥለቀለቀው የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ሃይማኖታዊ ግራ መጋባት ያሳስባቸዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ፋንዳሜንታሊስቶች እየተባሉ ይጠራሉ። ይሁን እንጂ ፋንዳሜንታሊስቶች ናቸውን? አይደሉም። ጠንካራ ሃይማኖታዊ አቋም ቢኖራቸውም ዛሬ ካለው የቃሉ አጠቃቀም አንጻር ግን ፋንዳሜንታሊስቶች ሊባሉ አይገባም። የፖለቲካ መሪዎች የተወሰነ ዓይነት አመለካከት እንዲያራምዱ ተጽእኖ አያደርጉም፤ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የማይስማሙትን ወገኖች በመቃወም ትዕይንተ ሕዝብና ዓመፅ አያካሂዱም። የተሻለ መንገድ አግኝተዋል። መሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስን ይከተላሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እውነት እንዳለና ይህ እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ ያምናሉ። (ዮሐንስ 8:32፤ 17:17) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ክርስቲያኖች ደግ፣ ጥሩ፣ የዋህና ምክንያታዊ ሰዎች እንዲሆኑ ነው፤ እነዚህ ባሕርያት ያሉት ግለሰብ ጭፍን አክራሪ አይሆንም። (ገላትያ 5:22, 23፤ ፊልጵስዩስ 4:5 NW) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የያዕቆብ መጽሐፍ ላይ ክርስቲያኖች ‘በመጀመሪያ ንጽሕት፣ በኋላም ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ የሆነችውን እንዲሁም ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባትን ላይኛይቱን ጥበብ’ እንዲኮተኩቱ ተመክረዋል። ያዕቆብ በመቀጠል “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል” ሲል ተናግሯል።— ያዕቆብ 3:17, 18
የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ለእውነት ይቆረቆር እንደነበር ያስታውሳሉ። ለጴንጤናዊው ጲላጦስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ሲል ነግሮታል። (ዮሐንስ 18:37) ደፋር የእውነት ጠበቃ የነበረ ቢሆንም የእርሱን እምነት ሌሎች እንዲቀበሉት አላስገደደም። ከዚያ ይልቅ አእምሮና ልባቸውን በሚነካ መንገድ እውነትን ገልጾላቸዋል። ሐሰትንና ፍትሕ መጓደልን መቼና እንዴት ከምድር ገጽ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ የሚወስነው ‘ቸርና ቅን’ የሆነው ሰማያዊ አባቱ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 25:8) በመሆኑም ከእርሱ ጋር ያልተስማሙትን ለመደምሰስ አልጣረም። እንዲያውም በተቃራኒው ኢየሱስን ሊያጠፉት የሞከሩት አክራሪ የነበሩት የዘመኑ ሃይማኖታዊ መሪዎች ናቸው።— ዮሐንስ 19:5, 6
የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ ጽኑ እምነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በጥሩ የሥነ ምግባር አቋማቸው የሚታወቁ ናቸው። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ጥምቀት” ብቻ እንዳለ አጥብቀው ያምናሉ። (ኤፌሶን 4:5) ኢየሱስ “ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ሲል የተናገራቸውን ቃላትም አይዘነጉም። (ማቴዎስ 7:13, 14) ያም ሆኖ ግን ሌሎች የእነርሱን እምነት እንዲከተሉ ለማስገደድ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ የጳውሎስን ምሳሌ በመኮረጅ ከአምላክ ጋር ‘ለመታረቅ’ ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ ‘ይለምናሉ።’ (2 ቆሮንቶስ 5:20) የተሻለው መንገድ ይህ ነው። አምላክ የሚፈልገውም ይኸንኑ ነው።
ሃይማኖታዊ አክራሪነት ዛሬ ካለው የቃሉ አጠቃቀም ረገድ ከዚህ በጣም ይለያል። ሃይማኖታዊ አክራሪዎች የእነርሱን መሠረታዊ ሥርዓቶች ኅብረተሰቡ እንዲቀበል ለማስገደድ ዓመፅን ጨምሮ የራሳቸውን የተለያዩ ስልቶች ይጠቀማሉ። ይህንንም በማድረግ ከፖለቲካው ሥርዓት ጋር የጠበቀ ጥምረት ይፈጥራሉ። ይሁንና ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል’ መሆን እንደማይገባቸው ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16፤ ያዕቆብ 4:4) የይሖዋ ምሥክሮች ከእነዚህ ቃላት ጋር በመስማማት ከፖለቲካ ውዝግቦች ፍጹም ገለልተኞች ናቸው። ፉዎሪፓጂና የተባለው የኢጣሊያ ጋዜጣ እንዳለው ምሥክሮቹ “ማንም ሰው ምን ነገር አምኖ እንዲቀበል አያስገድዱም፤ እያንዳንዱ ሰው እነርሱ የሚናገሩትን ነገር ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል ነፃ ነው።” ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? ምሥክሮቹ የሚያዳርሱት ሰላማዊ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ አክራሪ የነበሩትን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የሚማርክ ሆኗል።— ኢሳይያስ 2:2, 3
የማይናጉ የሥነ ምግባር ደንቦች ያሉት ዓለም
የይሖዋ ምሥክሮች ዛሬ ሃይማኖታዊ አክራሪዎችን የሚያሳስቧቸውን ችግሮች ሰዎች ሊፈቷቸው እንደማይችሉ ያውቃሉ። አንድን ሰው በአምላክ እንዲያምን ወይም የግል ሃይማኖታዊ እምነትህን እንዲቀበል ልታስገድደው አትችልም። ይህን ማድረግ ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ በታሪክ ውስጥ እንደ መስቀል ጦርነት፣ በመካከለኛው ዘመን የተደረጉትን ኢንኪዊዚሽኖች እንዲሁም የአሜሪካ ሕንዳውያን ‘ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ’ የተደረገውን እንቅስቃሴ የመሳሰሉ አንዳንድ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ከፍቷል። ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ የምትታመን ከሆነ ነገሮችን ለእርሱ ለመተው ፈቃደኛ ትሆናለህ።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ ሰዎች ሕጉን በመጣስ መከራና ሥቃይ ሲያስከትሉ እያየ የሚታገሠው እስከተወሰነ ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ አልቋል ማለት ይቻላል። ኢየሱስ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛቱን ጀምሯል፤ በቅርቡም ሰብዓዊ መንግሥታትን በማስወገድ የሰው ልጆችን ማስተዳደር ይጀምራል። (ማቴዎስ 24:3-14፤ ራእይ 11:15, 18) ይህም ሰላምና ጽድቅ የሚያብብበት ምድር አቀፍ ገነት ያስገኛል። በዚያን ጊዜ እውነተኛው አምላክ እንዴት መመለክ እንደሚገባው ምንም ግራ የሚያጋባ ነገር አይኖርም። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝሙር 37:29) እንደ ፍቅራዊ ደግነት፣ እውነት፣ ፍትሕና ጥሩነት የመሳሰሉት ዘላለማዊ ባህርያት በምድር ላይ ድል በማድረግ ለመላው ታዛዥ የሰው ልጆች በረከት ያስገኛሉ።
መዝሙራዊው ያንን ጊዜ አሻግሮ በመመልከት በግጥም መልክ እንደሚከተለው ብሏል:- “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ። እውነት ከምድር በቀለች፣ ጽድቅም ከሰማይ ተመለከተች። እግዚአብሔርም በጎ ነገርን ይሰጣል፣ ምድራችንም ፍሬዋን ትሰጣለች። ጽድቅ በፊቱ ይሄዳል፣ ፍለጋውንም በመንገድ ውስጥ ያኖራል።”— መዝሙር 85:10-13
ዛሬም ቢሆን ዓለምን መለወጥ ባንችልም በግለሰብ ደረጃ አምላካዊ ባሕርያትን ማፍራት እንችላለን። በዚህ መንገድ አምላክ በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲያገለግሉት የሚመርጣቸውን ዓይነት ሰዎች ሆነን ለመገኘት ልንጥር እንችላለን። ያን ጊዜ መዝሙራዊው “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” በማለት ከገለጻቸው ሰዎች መካከል እንሆናለን። (መዝሙር 37:11) አምላክ ፈቃዱን የሚያደርጉትን ሰዎች ይደግፋቸዋል፣ ይባርካቸውማል፤ ወደፊትም ግሩም የሆኑ ነገሮችን እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ብሏል።— 1 ዮሐንስ 2:17
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲያውቁ ለሁሉም ሰዎች ግብዣ ያቀርባሉ
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
በገጽ 3, 4, 5 እና 6 ላይ የሚገኘው መቅረዝ:- Printers Ornaments/by Carol Belanger Grafton/Dover Publications Inc.