ፊልሞና እና አናሲሞስ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተስማሙ
በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት የሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ በሁለት ሰዎች መካከል ስለተነሣው አለመግባባት የሚናገር ነው። አንደኛው ሰው ፊልሞና ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አናሲሞስ ነበር። እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? ጳውሎስ የእነዚህ ሰዎች ጉዳይ አሳስቦት የነበረው ለምንድን ነው?
የደብዳቤው ተቀባይ የሆነው ፊልሞና በትንሿ እስያ በምትገኘው በቆላስይስ ይኖር ነበር። ፊልሞና ምሥራቹን የተቀበለው በሐዋርያው ጳውሎስ ስብከት አማካኝነት ስለሆነ በዚያ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩት ሌሎች በርካታ ክርስቲያኖች ለየት ባለ ሁኔታ ከጳውሎስ ጋር ይግባባ ነበር። (ቆላስይስ 1:1፤ 2:1) ፊልሞና ‘የተወደደና አብሮ የሚሠራ’ ሰው መሆኑን ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ፊልሞና የእምነትና የፍቅር ምሳሌ ነበር። እንግዳ ተቀባይና ለመሰል ክርስቲያኖች የእረፍት ምንጭ ነበር። በተጨማሪም ፊልሞና በከተማው የሚገኘው ጉባኤ የሚያደርጋቸውን ስብሰባዎች ለማስተናገድ የሚያስችል ትልቅ ቤት ስለነበረው ደህና ኑሮ የነበረው ሰው ሳይሆን አይቀርም። በጳውሎስ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሱት ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ማለትም አፍብያና አርክጳ የፊልሞና ሚስትና ወንድ ልጅ ሳይሆኑ አይቀሩም። ከዚህም በላይ ፊልሞና ቢያንስ ቢያንስ አናሲሞስ የተባለ አንድ ባሪያ ነበረው።—ፊልሞና 1, 2, 5, 7, 19, 22
በሮም የሚገኝ ኰብላይ
አናሲሞስ ከቤቱ 1,400 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው፣ በ61 እዘአ ገደማ ለፊልሞና የተላከው ደብዳቤ ወደ ተጻፈበትና ጳውሎስ ወደሚገኝበት ወደ ሮም ለምን እንደሄደ ቅዱሳን ጽሑፎች አይገልጹም። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ለፊልሞና ሲጽፍለት “[አናሲሞስ] በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደ ሆነ፣ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር” ብሎታል። (ፊልሞና 18) እነዚህ ቃላት አናሲሞስ ከጌታው ከፊልሞና ጋር መጣላቱን ያሳያሉ። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ሁለቱን ሰዎች ለማስታረቅ ነበር።
አናሲሞስ የኰበለለው ወደ ሮም ለሚያደርገው ጉዞ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከፊልሞና ከሰረቀ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። በዚያች በጣም ብዙ ሕዝብ በሚኖርባት ከተማ ውስጥ ተሸሽጎ ለመኖር አስቦ ነበር።a በግሪካውያኑና በሮማውያኑ ዓለም ኰብላዮች ለአሳዳሪዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ አስተዳደርም ጭምር ችግር ይፈጥሩ ነበር። የሮም ከተማ ከጌቶቻቸው ለሚኰበልሉ ባሮች “መደበቂያ ዋሻ በመሆን የታወቀች” እንደነበረች ይነገርላታል።
ጳውሎስና አናሲሞስ ሊገናኙ የቻሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ይሁን እንጂ አናሲሞስ ነፃ ሆኖ የመኖሩ ወረት ሲያልፍለት ራሱን አደገኛ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደጣለ ሳያስተውል አይቀርም። በሮም ከተማ ውስጥ ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሮችን እያደነ የሚይዝ የፖሊስ ጓድ ነበረ። በጥንቱ ሕግ መሠረት ባሮች ከጌቶቻቸው መኰብለላቸው እንደ ከባድ ወንጀል ይታይ ነበር። ጌርሃርት ፍሬድሪክ እንዳሉት “ከጌታቸው የኰበለሉ ባሮች ሲያዙ ግንባራቸውን በመተኮስ ምልክት ይደረግባቸው ነበር። ሌሎች ባሮች የእነርሱን አርዓያ እንዳይከተሉ ሲባል ብዙውን ጊዜ ታስረው ይገረፉ፣ . . . በሰርከስ ትርዒቶች ወቅት ለአውሬዎች ይወረወሩ ወይም ተሰቅለው ይገደሉ ነበር።” አናሲሞስ ምናልባት የሰረቀው ገንዘብ ሲያልቅበትና መሸሸጊያ ቦታ ወይም ሥራ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ሲቀር በፊልሞና ቤት ስለ እሱ ሲወራ ይሰማ የነበረውን ጳውሎስን እንዲያስጠጋውና እንዲያስታርቀው ሳይጠይቀው አይቀርም ሲሉ ፍሬድሪክ ተናግረዋል።
ሌሎች ደግሞ አናሲሞስ በሆነ ምክንያት ተቆጥቶ ከነበረው ጌታው ጋር ያስታርቀኝ ይሆናል ብሎ ተስፋ በማድረግ ከጌታው ጓደኞች ወደ አንዱ ሆን ብሎ ሄዷል ይላሉ። የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት እንዲህ ማድረግ “በችግር ላይ ባሉ ባሮች ዘንድ የተለመደና የተስፋፋ” ነበር። ይህ ከሆነ አናሲሞስ የሰረቀው “ለመኰብለል ሳይሆን ሊያስታርቀው ወደሚችለው ወደ ጳውሎስ ለመድረስ የሚያስችለውን ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ መሆን አለበት” ሲሉ ምሁሩ ብራያን ራፕስኪ ተናግረዋል።
ጳውሎስ አናሲሞስን ረድቶታል
አናሲሞስ የኰበለለበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ተቆጥቶ ከነበረው ጌታው ጋር እንዲያስታርቀው የጳውሎስን እርዳታ መፈለጉ የተረጋገጠ ነው። ይህ በጳውሎስ ላይ አንድ ችግር አስከትሎበታል። አብሮት ያለው ሰው ቀደም ሲል የማያምን ባሪያ የነበረና ጌታውን ትቶ የኰበለለ ወንጀለኛ ነው። ታዲያ ጳውሎስ፣ ፊልሞና ሕጋዊ መብቱን ተጠቅሞ በዚህ ባሪያ ላይ ከባድ የቅጣት እርምጃ እንዳይወስድበት ክርስቲያን ጓደኛውን በማሳመን ይህን ባሪያ ሊረዳው ይገባልን? ጳውሎስ ምን ማድረግ ነበረበት?
ጳውሎስ ለፊልሞና በሚጽፍበት ጊዜ ኰብላዩ ባሪያ ከሐዋርያው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሳይኖር አይቀርም። ከጳውሎስ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ በማሳለፉ “የተወደደው ወንድም” ብሎ ሊጠራው ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 4:9) ጳውሎስ ከአናሲሞስ ጋር ስላለው መንፈሳዊ ዝምድና ሲገልጽ “በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ” ብሏል። ፊልሞና ጳውሎስ እጁን ያስገባባቸዋል ብሎ ከሚያስባቸው ጉዳዮች ሁሉ ይህ ፍጹም ያልጠበቀው መሆን አለበት። ሐዋርያው እንዳለው ቀደም ሲል ‘የማይጠቅም’ የነበረው ባሪያ ክርስቲያን ወንድም ሆኖ መመለሱ ነበር። አሁን አናሲሞስ ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ “ጠቃሚ” ወይም “እርዳታ የሚያበረክት” ይሆናል።—ፊልሞና 1, 10-12
አናሲሞስ በእስር ላይ የሚገኘውን ሐዋርያ በጣም ጠቅሞታል። እንዲያውም ጳውሎስ ለራሱ ሊያስቀረው አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ሕግን መጣስ ከመሆኑም በላይ የፊልሞናን መብት መጋፋት ነበር። (ፊልሞና 13, 14) በፊልሞና ቤት ውስጥ ለሚሰበሰበው ጉባኤ በተመሳሳይ ጊዜ በተጻፈ ሌላ ደብዳቤ ላይ ጳውሎስ “ከእናንተ ከሆነውና ከታመነው ከተወደደውም ወንድም” በማለት አናሲሞስን ጠቅሶ ጽፏል። ይህ የሚያመለክተው አናሲሞስ ሊታመን የሚችል ሰው መሆኑን ማስመስከሩን ነው።—ቆላስይስ 4:7-9b
ጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣኑን በመጠቀም አናሲሞስን እንዲቀበለው ወይም በነፃ እንዲለቀው ፊልሞናን ከማዘዝ ይልቅ በደግነት እንዲቀበለው አበረታቶታል። በጓደኝነታቸውና ባላቸው የጋራ ፍቅር ምክንያት ጳውሎስ ፊልሞና ከተጠየቀው ‘አብልጦ’ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነበር። (ፊልሞና 21) ‘አብልጦ’ የሚለው ቃል እስከ ምን ደረጃ እንደሚደርስ አልተገለጸም፤ ምክንያቱም አናሲሞስን በተመለከተ መደረግ ያለበትን በትክክል ሊወስን የሚችለው ፊልሞና ብቻ ነበር። አንዳንዶች የጳውሎስ ቃላት ኮብላዩ ‘ቀደም ሲል ያደርግ እንደነበረው ጳውሎስን መርዳቱን እንዲቀጥል መልሶ ወደ እሱ እንዲልክለት’ በተዘዋዋሪ የሚጠይቁ ናቸው ይላሉ።
ፊልሞና ጳውሎስ ስለ አናሲሞስ ያቀረበውን ልመና ተቀብሎት ይሆን? ባሪያዎቻቸው ፈለጉን እንዳይከተሉ ሲባል ቢቀጣ ይመርጡ የነበሩትን ሌሎች የቆላስይስ የባሪያ አሳዳሪዎችን ባያስደስትም ፊልሞና አናሲሞስን የተቀበለው መሆኑ ምንም አያጠራጥርም።
አናሲሞስ—የተለወጠ ሰው
በዚያም ሆነ በዚህ አናሲሞስ ወደ ቆላስይስ የተመለሰው የባሕርይ ለውጥ አድርጎ ነው። አስተሳሰቡ በምሥራቹ በመለወጡ ምክንያት በዚያ ከተማ ለሚገኘው ጉባኤ የታመነ አባል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። አናሲሞስ ከጊዜ በኋላ ከፊልሞና ነፃ ይውጣ ወይም አይውጣ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጸ ነገር የለም። ከመንፈሳዊ አመለካከት አንፃር ስናየው ግን የቀድሞው ኰብላይ ነፃ ሳይወጣ አይቀርም። (ከ1 ቆሮንቶስ 7:22 ጋር አወዳድር።) በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ የሆነ ለውጥ ይከሰታል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ላይ በሚያውሉበት ጊዜ ሁኔታቸውና ባሕርያቸው ይለወጣል። ቀደም ሲል ለኅብረተሰቡ እንደማይረቡ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ ሰዎች አርዓያ የሚሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ እርዳታ በማግኘት ላይ ናቸው።c
ወደ እውነተኛው እምነት የተደረገ እንዴት ያለ አስደናቂ ለውጥ ነው! የቀድሞው አናሲሞስ ለፊልሞና ‘የማይጠቅም’ የነበረ ቢሆንም አዲሱ አናሲሞስ ግን ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ “እርዳታ የሚያበረክት” ግለሰብ ሆኖ እንደኖረ ምንም አያጠራጥርም። እንዲሁም ፊልሞናና አናሲሞስ በክርስቲያን ወንድማማችነት መስማማታቸው በእርግጥም በረከት ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሮማ ሕግ ሴርቨስ ፉጂቲቨስ (የኰበለለ ባሪያ) የሚለውን ቃል ‘የመመለስ ሐሳብ የሌለው ከጌታው የኰበለለ ባሪያ’ በማለት ይተረጉመዋል።
b አናሲሞስና ቲኪቆስ ወደ ቆላስይስ ባደረጉት በዚህ የመልስ ጉዞ ወቅት ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርገው በሚቆጠሩ መጻሕፍት ውስጥ የተጨመሩትን ሦስቱን የጳውሎስ ደብዳቤዎች በአደራ ተቀብለዋል። እነዚህም ለፊልሞና ከተጻፈው ከዚህ ደብዳቤ በተጨማሪ ለኤፌሶንና ለቆላስይስ ሰዎች የተላኩ የጳውሎስ ደብዳቤዎች ነበሩ።
c ለምሳሌ ያህል የእንግሊዝኛ ንቁ! ሰኔ 22, 1996 ገጽ 18-23፤ መጋቢት 8, 1997 ገጽ 11-13፤ የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ነሐሴ 1, 1989 ገጽ 30-1፤ የካቲት 15, 1997 ገጽ 21-4 ተመልከት።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሮማ ሕግ ሥር የነበሩ ባሮች
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በነበረው የሮማ ሕግ መሠረት አንድ ባሪያ ሙሉ በሙሉ በጌታው ፍላጎት ቁጥጥር ሥር ነበር። ጌርሃርት ፍሬድሪክ የተባሉት ተንታኝ እንዳሉት ከሆነ “በመሠረታዊ ሐሳብ ደረጃም ሆነ በሕግ አንድ ባሪያ ሰው ሳይሆን አሳዳሪው የሚጠቀምበት ዕቃ ነበር። . . . እንደ ቤት እንስሳና ቁሳቁስ ተደርጎ የሚታይና በሰብዓዊ ሕግም ቢሆን ከቁብ የማይቆጠር ነበር።” አንድ ባሪያ ለተፈጸመበት ግፍ አቤት የሚልበትና ካሣ የሚያገኝበት ሕጋዊ ቦታ አልነበረም። በመሠረቱ አንድ ባሪያ ፀጥ ለጥ ብሎ የጌታውን ትእዛዝ መፈጸም ነበረበት። አንድ የተቆጣ ጌታ ለሚወስደው የቅጣት እርምጃ ምንም ገደብ አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ ቀላል ለሆነ ጥፋት ጌታው እስከ መግደል የሚያደርስ የኃይል እርምጃ ሊወስድበት ይችላል።*
ሀብታም የሆኑ ሰዎች በመቶ የሚቆጠሩ ባሮች ሊኖሯቸው ቢችልም ከሌላው ጋር ሲወዳደሩ መጠነኛ ኑሮ ያላቸው ቤተሰቦችም እንኳ ሁለት ወይም ሦስት ባሮች ይኖራቸዋል። ምሁሩ ጆን ባርክሌይ “የቤት ባሮች የሚሠሯቸው ሥራዎች በጣም የተለያዩ ናቸው” ብለዋል። “በትላልቅና በጣም ሀብታም በሆኑ ቤቶች ውስጥ ያሉትን የተለያዩ የሥራ ዓይነቶች ሳንጠቅስ ባሪያዎች ጠራጊዎች፣ ምግብ አብሳዮች፣ አሳላፊዎች፣ ልብስ አጣቢዎች፣ መልእክተኞች፣ ሞግዚቶች፣ ጡት አጥብተው የሚያሳድጉ ሞግዚቶችና የግል ጉዳዮችን የሚከታተሉ አገልጋዮች ሆነው እናገኛቸዋለን። . . . በዚህ መሠረት የአንድ የቤት ባሪያ ሕይወት ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ የተመካው በጌታው ባሕርይ ላይ ሲሆን ይህ ደግሞ ጠቃሚም ጎጂም ሊሆን ይችላል። ጨካኝ በሆነ ጌታ ሥር መሆን ስፍር ቁጥር በሌለው ክፋት መሰቃየትን ሲያስከትል፣ ደግና ለጋስ ጌታ ደግሞ የባሪያውን ሕይወት በአንጻራዊ ሁኔታ ተስማሚና ብሩህ ተስፋ የሚታይበት እንዲሆን ያደርግ ነበር። በጥንቱ የሮምና የግሪክ ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ ስለ ጨካኝ አሳዳሪዎች የሚናገሩ ታዋቂ ምሳሌዎች ቢኖሩም በአሳዳሪዎችና በባሪያዎቻቸው መካከል ሞቅ ያለ የአሳቢነት መንፈስ የነበረ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ጽሑፎችም ይገኛሉ።”
*በጥንት ዘመን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ስለነበረው ባርነት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 977-979 ተመልከት።