የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 1/1 ገጽ 3-5
  • ለቤተሰብ ችግር ተግባራዊ መፍትሄ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለቤተሰብ ችግር ተግባራዊ መፍትሄ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፍቺን ማስቀረት
  • የሃይማኖት ልዩነቶች
  • አባት ኃላፊነቶቹን ችላ ሲል
  • ሰላማዊ መንፈስ
  • ክፉ ባልንጀሮች
  • የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ይኖራልን?
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የቤተሰብን ኑሮ የተሳካ ማድረግ
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • አምላክን የሚያስደስት የቤተሰብ ሕይወት
    አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
  • በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አድርጉ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 1/1 ገጽ 3-5

ለቤተሰብ ችግር ተግባራዊ መፍትሄ

“አሜሪካ ውስጥ የቤተሰብ ሕይወት ተቃውሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም። የፍቺውን መጠን፣ ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ልጆችን አኃዝ፣ [እና] በልጆችም ሆነ በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸመውን በደል ስንመለከት ከዚህ የተለየ መደምደሚያ ላይ ልንደርስ አንችልም።”

በዩናይትድ ስቴትስ የቴሌቪዥን ዘጋቢ የሆነው የቶም ብሮኮ አነጋገር ለአብዛኞቹ አገሮች ይሠራል። ይህ ቀውስ ምንድን ነው?

በብዙ አቅጣጫዎች ሲታይ ቤተሰብ የኅብረተሰብ ዋና መሠረት ነው። ቤተሰብ ከተናጋ ኅብረተሰብም ይናጋል። በተጨማሪም ለልጆች ስሜታዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ የሚሰጠው ቤተሰብ ነው። ለሕይወት የሚጠቅሟቸውን የመጀመሪያዎቹንና እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ትምህርቶች የሚቀስሙበት ቦታ ነው። ቤተሰብ ውስጥ ብጥብጥ ካለ ልጆች ምን ይማራሉ? ከየትስ ጥበቃ ያገኛሉ? ሲያድጉስ ምን ዓይነት ሰዎች ይሆናሉ?

ቤተሰብ ለገጠመው ለዚህ ቀውስ በእርግጥ መፍትሄ ይኖራልን? አዎን፣ ይኖራል። ቤተሰብ አምላክ ራሱ ያቋቋመው ተቋም ነው። (ዘፍጥረት 1:​27, 28) እንዲሁም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ የቤተሰብ መመሪያ አስፍሯል። (ቆላስይስ 3:​18–21) እርግጥ ነው፣ በአጠቃላይ ኅብረተሰብን መለወጥ አንችልም፤ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በየቤተሰባችን ሕይወት ውስጥ በሥራ ማዋል እንችላለን። ይህን ተግባራዊ ስላደረጉና ጥሩ ውጤት ስላገኙ አንዳንድ ሰዎች ልንነግራችሁ እንፈልጋለን።

ፍቺን ማስቀረት

በበርካታ አገሮች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ጋብቻዎች በፍቺ ያከትማሉ። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ውድቀት ነው! በዚህ ምክንያት ነጠላ ወላጅ የሆኑ ብዙዎች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ የሚደነቅ ሥራ ማከናወናቸው የማይካድ ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ባልና ሚስቶች ቅራኔዎቻቸው ተፈትተው አብረው መኖር ቢችሉ የተሻለ መሆኑን እንደሚስማሙበት ምንም ጥርጥር የለውም።

በሰሎሞን ደሴቶች የሚኖሩ የአንድ ባልና ሚስት ትዳር ሊፈርስ ተቃርቦ ነበር። የአካባቢው አለቃ ልጅ የሆነው ባልየው ጠበኛ ከመሆኑም በላይ ብዙ መጥፎ ልማዶች ነበሩት። ሚስትየው ሕይወት በጣም ስላንገፈገፋት ራስዋን ለመግደል ሁሉ ሞክራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ባልየው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። አምላክን ማስደሰት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ስህተት የሆነውን ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን ‘ክፋትንም መጥላት’ እንዳለበት ተማረ። (መዝሙር 97:​10) ይህ ደግሞ እንደ መዋሸት፣ መስረቅ፣ ጠበኝነትና ስካር የመሳሰሉትን ነገሮች መጥላት ይጨምራል። ይህን ምክር በመከተሉ ብዙም ሳይቆይ መጥፎ ልማዶቹንና የግልፍተኝነት ባሕርይውን ማሸነፍ ቻለ። የአምላክ ቃል ባሳደረበት በጎ ተጽእኖ የተነሳ ባደረገው ለውጥ ሚስቱ የተገረመች ሲሆን ትዳራቸውም ከፍተኛ መሻሻል አሳየ።

በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር አሠሪዋ ከባልዋ ለመፋታት በዕቅድ ላይ መሆኗን ሰማች። ምሥክርዋ አምላክ ስለ ጋብቻ ያለውን አመለካከት ለአለቃዋ ከነገረቻት በኋላ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አሳየቻት። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ከጋብቻ ጋር የተያያዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚያጎላ ሲሆን በተለይ ደግሞ ባለ ትዳሮች ቅራኔዎቻቸውን ለመፍታት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል አበክሮ ይገልጻል። አሠሪዋና ባልዋ መጽሐፉን ከማንበባቸውም በላይ በውስጡ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ከልብ ጥረት አደረጉ። ከዚህ የተነሳ ላለመፋታት ወሰኑ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል ሊተርፍ የቻለ አንድ ሌላ ትዳር ነው።

የሃይማኖት ልዩነቶች

የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ ባልና ሚስት ስላቀፈ ትዳር ምን ለማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘በጌታ ብቻ’ እንዲያገቡ ምክንያታዊ የሆነ ምክር ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 7:​39) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሃይማኖቱን ይቀይር ይሆናል። ይህ የትዳሩ ማክተሚያ ሊሆን ይገባዋልን? በጭራሽ።

በቦትስዋና የምትኖር በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት ሴት አዲሱ እምነቷ ምን ለውጥ እንድታደርግ እንዳስቻላት ተጠይቃ ነበር። ባልዋ ስለ እርስዋ ሆኖ እንዲመልስላት ስትጠይቀው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሚስቴ የይሖዋ ምሥክር ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ገንቢ ለውጦች አይቼባታለሁ። ባሁኑ ጊዜ ቀድሞ ያልነበራት ከፍተኛ ማስተዋል የሚንጸባረቅበት የሰከነ መንፈስ ይታይባታል። እኔ እስካሁን ድረስ ላሸንፈው ያልቻልኩትን የማጨስ ሱስ ለማቆም የሚያስችል ጥንካሬና ቆራጥነት አዳብራለች። ሚስቴ ለልጆቼም ሆነ ለእኔ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ከበፊቱ የላቀ ፍቅርና ርኅራሄ የምታሳይ ሆናለች። በተለይ ከልጆቹ ጋር ባላት ግንኙነት በጣም ትዕግሥተኛ ሆናለች። ሌሎች የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲችሉ ለመርዳት በመጣር በአገልግሎት እንደምትካፈል ተመልክቻለሁ። በእኔ በራሴ ላይ እንኳ ጥሩ ለውጦች ተመልክቻለሁ። እንዲህ ዓይነት ለውጥ ላደርግ የቻልኩት እርሷ በምታሳየው ጥሩ ምሳሌነት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምናለሁ።” በዚህ ትዳር ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ምንኛ መልካም ውጤት አስገኝቷል! የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ብዙዎች ምሥክር ስለሆኑት የትዳር ጓደኞቻቸው ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል።

አባት ኃላፊነቶቹን ችላ ሲል

በአባትና በልጆች መካከል ያለው ዝምድና ጠንካራ ቤተሰቦችን ለመገንባት የሚያስችል ቁልፍ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ሲል መክሯል። (ኤፌሶን 6:​4) በመሆኑም ዘ ዊልሰን ኳርተርሊ ባወጣው አንድ ርዕስ ለአብዛኞቹ ማኅበራዊ ቀውሶች ተጠያቂዎች ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አባቶች መሆናቸውን መግለጹ ምንም አያስደንቅም። ጽሑፉ እንዲህ ብሏል:- “በ1960 እና በ1990 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ያለ ወላጅ አባት የሚያድጉ ልጆች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። . . . ብዙዎቹን የአሜሪካ ኅብረተሰብ በእጅጉ እያመሱት ላሉት ችግሮች ዋናው መንስዔ የአባትነት ሚና መቀነሱ ነው።”

ታዲያ እንዲህ ሲባል አባቶቻቸው አመራር የማይሰጧቸው ልጆች ሕይወታቸው ሰንካላ ሆኖ ይቀራል ማለት ነውን? አይደለም። በጥንት ጊዜ የኖረው መዝሙራዊ “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 27:​10) በታይላንድ የሚኖር አንድ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ይህ እውነት መሆኑን ተገንዝቧል። ገና ሕፃን እያለ እናቱን በሞት አጣ። አባቱ ደግሞ እሱን ማሳደግ ስላልፈለገ ወስዶ ለሴት አያቱ ሰጠው። ይህ ልጅ የተጣለና የማይፈለግ እንደሆነ ስለተሰማው የዓመፀኝነት ባሕርይ በማዳበሩ ረብሸኛ እንደሆነ ይነገርለት ነበር። ይባስ ብሎም አያቱ ላይ ይዝትባቸው ነበር። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢው ካለው የመንግሥት አዳራሽ አቅራቢያ እንደሚቆም ስላስተዋሉ አንድ ቀን ቤታቸው ጋበዙት።

አምላክ ልክ እንደ አንድ አባት ልጆቹን እንደሚያፈቅር ነገሩት። በተጨማሪም አምላክ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ለመስጠት ቃል ስለገባው ምድራዊ ገነት ነገሩት። (ራእይ 21:​3, 4) ልጁ የነገሩት ነገር ስለማረከው ይበልጥ ለማወቅ በየቀኑ ይመጣ ጀመር። አምላክ አባት እንዲሆነው ከልቡ የሚፈልግ ከሆነ ረብሸኛነቱን መተው እንዳለበት ምሥክሮቹ ገለጹለት። ይህ ሐሳብ ጳውሎስ ለሮማውያን ክርስቲያኖች “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ሲል ከጻፈላቸው ጋር የሚስማማ ነው። (ሮሜ 12:​18) በተጨማሪም አያቱን በደግነት መያዝ ይኖርበታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​1, 2) ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሥራ ላይ ማዋል ጀመረ። እንዲህ ማድረጉ ከአያቱ ጋር የሚያሳልፈውን የቤተሰብ ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሻሻለለት አያጠራጥርም። (ገላትያ 5:​22, 23) ጎረቤቶቹ በእርሱ ላይ በተመለከቱት ለውጥ በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ ልጆቻቸው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ፈልገዋል!

ሰላማዊ መንፈስ

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች “የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። . . . የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ” ሲል ጽፎላቸዋል። (ቆላስይስ 3:​14, 15) ሰላማዊ መንፈስና ልባዊ ፍቅር ቤተሰብን አንድ ላይ እንደሚያስተሳስሩ የታወቀ ነው። እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የዘለቁ የቤተሰብ አለመግባባቶችን ሊያስወግዱ ይችላሉ። በአልባኒያ የምትኖረው ሩኪያ በቤተሰቡ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ከ17 ዓመት በላይ ከወንድሟ ጋር ተነጋግራ አታውቅም ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ስታጠና እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሰላም መኖር እንደሚጠበቅበት ተማረች። “ሰላምን ይሻ ይከተለውም።”​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​11

ሩኪያ ከወንድሟ ጋር ሰላም መመስረት እንዳለባት ተገነዘበች። ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ ካደረች በኋላ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት፣ ልቧ ድው ድው እያለ ወደ ወን​ድሟ ቤት ሄደች። የወንድሟ ልጅ በሩን ከፈተችላትና በመደነቅ “ምን ልትሠሪ መጣሽ?” ስትል ጠየቀቻት። ሩኪያ ረጋ ባለ መንፈስ ከወንድሟ ጋር መታረቅ እንደምትፈልግ ከገለጸችላት በኋላ እንድትጠራላት ጠየቀቻት። እንዲህ ያደረገችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስለተገነዘበች ነው። ወንድሟ ጥሩ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ተቃቅፈው የደስታ እንባ አነቡ። ይህ ቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ በመደረጋቸው እርቅ አግኝቷል።

ክፉ ባልንጀሮች

“ዛሬ አንድ ልጅ በአማካይ በቀን ለሰባት ሰዓት ያህል ቴሌቪዥን ይመለከታል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ከስምንት ሺህ በላይ ግድያዎችንና ከመቶ ሺህ የሚበልጡ የዓመፅ ድርጊቶችን ይመለከታል።” ይህን የገለጸው ዘ 7 ሀቢትስ ኦቭ ሐይሊ ኢፌክቲቭ ፋሚሊስ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ነው። ይህ በአንድ ልጅ ላይ ምን ተጽእኖ ያሳድራል? “ባለሙያዎች” በሚያስከትለው ውጤት ረገድ አንድ አቋም የላቸውም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ ባልንጀርነት ጎጂ መሆኑን አጥብቆ ያስጠነቅቃል። ለምሳሌ ያህል “የሰነፎች ባልንጀራ . . . ክፉ መከራን ይቀበላል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:​20) በተጨማሪም “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) ከክፉ ባልንጀሮች ጋር በመግጠምም ሆነ በቴሌቪዥን ፕሮግራም አማካኝነት፣ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የሚሠራ መሆኑን አምነን በጥበብ ከተከተልን የቤተሰብ ሕይወታችን ሊሻሻል ይችላል።

በሉክሰምበርግ የምትኖር አንዲት እናት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ነበር። አንድ ቀን እናትየው ለአስጠኚዋ የሰባትና የስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ሴት ልጆችዋ ማታ ማታ በጣም እንደሚጣሉና ነጭናጫ እንደሚሆኑ ነገረቻት። ምሥክሯ ልጆቹ ማታ ምን እንደሚያደርጉ ጠየቀቻት። እናትየው ማድቤት በምትሠራበት ጊዜ እነሱ ቴሌቪዥን እንደሚመለከቱ ነገረቻት። የሚከታተሉት ፕሮግራም ምንድን ነው? “የሆነ የአሻንጉሊት ፊልም ነው” ስትል እናትየው መለሰች። አስጠኚዋ እንዲህ ባሉ ፕሮግራሞች አብዛኛውን ጊዜ የዓመፅ ድርጊቶች እንደሚቀርቡ ስትጠቅስላት እናትየው ክትትል ለማድረግ ወሰነች።

በሚቀጥለው ቀን እናትየው ልጆችዋ የሚከታተሉትን የአሻንጉሊት ፊልም በማየቷ በጣም መሰቀቅዋን ነገረቻት። ፊልሙ ከሌላ ኅዋ የመጡ ጭራቆች ያገኙትን ነገር ሁሉ ያለ ምንም ርኅራኄ ሲጨፈጭፉ የሚያሳይ ነበር። እናትየው ይሖዋ ዓመፅ እንደሚጠላና ይህ ዓይነቱን የጭካኔ ድርጊት ስንመለከት እንደማይደሰት ለልጆችዋ አስረዳቻቸው። (መዝሙር 11:​5) ልጆቹ ይሖዋን ለማ​ስደሰት ስለፈለጉ ቴሌቪዥን ከመመልከት ይልቅ አንዳንድ ሥዕሎች ለመሳል ተስማሙ። ወዲያውኑ የጠበኝነት ባሕሪያቸውን በመተዋቸው የቤተሰቡ መንፈስ ተሻሻለ።

እነዚህ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል የተሻለ የቤተሰብ ሕይወት እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ምክር ሁሉንም ዓይነት ሁኔታዎች ያካትታል። መጽሐፉ እምነት የሚጣልበት ከመሆኑም በላይ ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ኃይለኛ ግፊት ያሳድራል። (ዕብራውያን 4:​12) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው በውስጡ የያዘውን ትምህርት ለመከተል ከልብ ሲጥሩ የቤተሰብ ሕይወት ይጠናከራል፣ ጥሩ የባሕርይ ለውጥ ይታያል እንዲሁም ስህተቶችን ማስቀረት ይቻላል። አምላክ የሚሰጠውን ምክር በሥራ የሚያውለው አንደኛው የቤተሰቡ አባል ብቻ ቢሆንም እንኳ ሁኔታዎች ይሻሻላሉ። በእርግጥም በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ መዝሙራዊው “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብሎ ሲጽፍ ለአምላክ ቃል የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል።​—⁠መዝሙር 119:​105

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በተግባር በማዋል የቤተሰብ ቅራኔዎች መፍትሔ አግኝተዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ