የአብርሃም ዓይነት እምነት አላችሁን?
“የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”—ሉቃስ 18:8
1. በዛሬው ጊዜ ጠንካራ እምነት ይዞ መኖር አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ጠንካራ እምነት ይዞ መኖር ቀላል አይደለም። ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዳያተኩሩ ለማድረግ ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። (ሉቃስ 21:34፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16) ብዙዎቹ ጦርነት፣ አሰቃቂ አደጋ፣ በሽታ ወይም ደግሞ ረሃብ ከሚያስከትለው ችግር ጋር እየታገሉ ለመኖር ተገደድዋል። (ሉቃስ 21:10, 11) በበርካታ አገሮች በጣም የሚታመንባቸው ዓለማዊ ባሕሎች ያሉ በመሆኑ በራሳቸው እምነት የሚኖሩ ሰዎች ግትሮችና አልፎ ተርፎም አክራሪዎች ተደርገው ይታያሉ። በተጨማሪም ብዙ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ይሰደዳሉ። (ማቴዎስ 24:9) ኢየሱስ ከ2,000 ዓመት ገደማ በፊት ያነሳው የሚከተለው ጥያቄ በእርግጥም ተስማሚ ነው:- “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”—ሉቃስ 18:8
2. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ጠንካራ እምነት ይዞ መኖሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የማንን የእምነት ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ነው?
2 ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ የተሳካ ሕይወት መምራት የምንችለውና ቃል የተገባውን የዘላለም ሕይወት ልናገኝ የምንችለው ጠንካራ እምነት ካለን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ለዕንባቆም የተናገራቸውን የሚከተሉትን ቃላት በመጥቀስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። . . . ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም።” (ዕብራውያን 10:38–11:6፤ ዕንባቆም 2:4) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎት ነበር:- “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም . . . የዘላለምን ሕይወት ያዝ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:12) ታዲያ ጽኑ እምነት መያዝ የሚቻለው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ በምንመረምርበት ጊዜ ከ4,000 ዓመታት ገደማ በፊት የኖረ ቢሆንም እንኳ እምነቱ አሁንም ድረስ በሦስት ትልልቅ ሃይማኖቶች ማለትም በእስልምና፣ በአይሁድ ሃይማኖትና በክርስትና ከፍ ተደርጎ የሚታይ የአንድ ሰው ታሪክ መመልከታችን ጠቃሚ ነው። ይህ ሰው አብርሃም ነው። የአብርሃምን እምነት ልዩ ያደረገው ምንድን ነው? በዛሬው ጊዜ እሱን መምሰል እንችላለንን?
የአምላክን መመሪያ መታዘዝ
3, 4. ታራ ቤተሰቡን ይዞ ከኡር ወደ ካራን የሄደው ለምንድን ነው?
3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አብርሃም (ቀደም ሲል አብራም ተብሎ ይጠራ ነበር) ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው በመጀመሪያው አካባቢ ነው። ዘፍጥረት 11:26 ላይ “ታራ . . . አብራምንና ናኮርን ሐራንንም ወለደ” የሚል ቃል እናነባለን። ታራና ቤተሰቡ በደቡባዊ ሜሶፖታሚያ በምትገኝ ኡር በተባለች የበለጸገች የከለዳውያን ከተማ ይኖሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህችን ከተማ ለቅቀዋል። “ታራም ልጁን አብራምንና የልጅ ልጁን የሐራንን ልጅ ሎጥን የልጁንም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን [ሣራን] ወሰደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ከነዓን ምድር ይሄዱ ዘንድ ከከለዳውያን ዑር ወጡ፤ ወደ ካራንም መጡ፣ ከዚያም ተቀመጡ።” (ዘፍጥረት 11:31) የአብርሃም ወንድም ናኮርም ቤተሰቡን ይዞ ወደ ካራን መጥቶ ነበር። (ዘፍጥረት 24:10, 15፤ 28:1, 2፤ 29:4) ይሁን እንጂ ታራ የበለጸገችውን ከተማ ኡርን ለቅቆ ሩቅ ወደሚገኘው ወደ ካራን የሄደው ለምንድን ነው?
4 አብርሃም ከኖረበት ዘመን 2,000 ዓመታት ያህል በኋላ ታማኙ ሰው እስጢፋኖስ የታራ ቤተሰብ ያደረገውን ይህን እንግዳ የሆነ የቦታ ለውጥ በአይሁድ ሳንሄድሪን ፊት ገልጾ ነበር። እንዲህ አለ:- “የክብር አምላክ ለአባታችን ለአብርሃም በካራን ሳይቀመጥ ገና በሁለት ወንዝ መካከል ሳለ ታየና:- ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና አለው። በዚያን ጊዜ ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ።” (ሥራ 7:2–4) ታራ ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ ካራን በመሄድ ይሖዋ አብርሃምን በተመለከተ ለነበረው ፈቃድ ተገዝቷል።
5. አብርሃም አባቱ ከሞተ በኋላ ወዴት ሄደ? ለምንስ?
5 የታራ ቤተሰቦች በአዲሱ ከተማቸው ውስጥ መኖር ጀመሩ። ዓመታት ካለፉ በኋላ አብርሃም “አገሬ” ብሎ ሲናገር ስለ ኡር ሳይሆን ስለ ካራን አካባቢ መናገሩ ነበር። (ዘፍጥረት 24:4) ሆኖም ካራን የአብርሃም ቋሚ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ አልነበረም። እስጢፋኖስ እንደገለጸው “አባቱ ከሞተ በኋላ [አምላክ] እናንተ ዛሬ ወደምትኖሩባት ወደዚች አገር አወጣው።” (ሥራ 7:4) አብርሃም የይሖዋን መመሪያ በመታዘዝ ሎጥን ይዞ ከኤፍራጥስ ወንዝ ባሻገር ወዳለው ወደ ከነዓን ምድር ሄደ።a
6. ይሖዋ ለአብርሃም ምን ቃል ገባለት?
6 ይሖዋ አብርሃም ወደ ከነዓን እንዲሄድ ያደረገው ለምንድን ነው? ይህን ያደረገበት ምክንያት አምላክ ለዚህ ታማኝ ሰው ከነበረው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ አብርሃምን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፣ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።” (ዘፍጥረት 12:1–3) አብርሃም የይሖዋን ጥበቃ የሚያገኝና የከነዓንን ምድር የሚወርስ የአንድ ታላቅ ሕዝብ አባት ይሆናል። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነበር! ሆኖም አብርሃም ይህን ምድር መውረስ እንዲችል በሕይወቱ ውስጥ ትልልቅ ለውጦች ማድረግ ነበረበት።
7. አብርሃም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ለመውረስ ምን ለውጦች ለማድረግ መዘጋጀት ነበረበት?
7 አብርሃም ኡርን ለቅቆ ሲወጣ የበለጸገችውን ከተማና አብረውት ይኖሩ የነበሩትን የአባቱን ዘመድ አዝማድ መተው ነበረበት። በዕብራውያን አባቶች ዘመን ደግሞ በዘመድ አዝማድ መካከል መኖር ከፍተኛ የደህንነት ስሜት የሚፈጥር ነገር ነበር። ካራንን ለቅቆ ሲወጣ የወንድሙን የናኮርን ቤተሰብ ጨምሮ ከአባቱ ቤተሰቦች ከመለየቱም በላይ የሄደው ወደማያውቀው አገር ነው። ወደ ከነዓን ምድር ከሄደ በኋላ ደህንነቱ እንዲጠበቅ ሲል በግንቦች በታጠረች ከተማ ለመኖር አልጣረም። ለምን? አብርሃም ወደ ምድሪቱ ከገባ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር:- “በምድር በርዝመትዋም በስፋትዋም ሂድ እርስዋን ለአንተ እሰጣለሁና።” (ዘፍጥረት 13:17) የ75 ዓመቱ አብርሃምና የ65 ዓመቷ ሣራ እነዚህን መመሪያዎች ተከትለዋል። “በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፣ . . . እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ።”—ዕብራውያን 11:9፤ ዘፍጥረት 12:4
በዛሬው ጊዜ የአብርሃም ዓይነት እምነት
8. የአብርሃምንና የሌሎች የጥንት ምሥክሮችን ምሳሌ በመመልከት ምን ማዳበር ይኖርብናል?
8 አብርሃምና ቤተሰቡ በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ውስጥ በተዘረዘሩት በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ‘እንደ ደመና ያሉ ብዙ ምሥክሮች’ መካከል ተጠቅሰዋል። ጳውሎስ የእነዚህን የጥንት የአምላክ አገልጋዮች እምነት ግምት ውስጥ በማስገባት ክርስቲያኖች “ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት [እምነት ማጣት]” እንዲያስወግዱ አበረታቷል። (ዕብራውያን 12:1) አዎን፣ እምነት ማጣት ‘በቀላሉ ሊከበን’ ይችላል። ሆኖም በጳውሎስም ሆነ በእኛ ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአብርሃምና ከሌሎች የጥንት ዘመን አገልጋዮች ጋር የሚወዳደር ጠንካራ እምነት ማዳበር ችለዋል። ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ መሰል ክርስቲያኖች ሲናገር “እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም” ብሏል።—ዕብራውያን 10:39
9, 10. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የአብርሃም ዓይነት እምነት እንዳላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
9 እርግጥ ነው፣ ዓለም በአብርሃም ዘመን ከነበረው በእጅጉ ተለውጧል። ሆኖም አሁንም የምናመልከው ያንኑ የማይለወጠውን ‘የአብርሃም አምላክ’ ነው። (ሥራ 3:13፤ ሚልክያስ 3:6) ይሖዋ በአብርሃም ዘመን ይመለክ እንደነበረ ሁሉ አሁንም ሊመለክ የሚገባው አምላክ ነው። (ራእይ 4:11) ብዙዎች ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ይወስናሉ፤ በተጨማሪም ልክ እንደ አብርሃም የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም በሕይወታቸው ላይ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ሁሉ ያደርጋሉ። ባለፈው ዓመት 316,092 የሚሆኑ ሰዎች “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” በውኃ በመጠመቅ ራሳቸውን መወሰናቸውን በይፋ አሳይተዋል።—ማቴዎስ 28:19
10 ከእነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ ይህን ውሳኔያቸውን ለመፈጸም ሩቅ ወደሆኑ ባዕድ አገሮች መሄድ አያስፈልጋቸውም። ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ሁኔታ ብዙዎቹ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል። ለምሳሌ ያህል በሞሪሽየስ የምትኖረው ኤልሲ አስማተኛ ነበረች። ሰው ሁሉ ይፈራት ነበር። አንዲት ልዩ አቅኚ የኤልሲን ሴት ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት በመጀመሯ ኤልሲ ‘ከጨለማ ወደ ብርሃን ዘወር’ የምትልበት መንገድ ተከፈተ። (ሥራ 26:18) ኤልሲ የልጅዋን ፍላጎት በመመልከት እሷም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ለማጥናት ተስማማች። የማያቋርጥ ማበረታቻ ያስፈልጋት ስለነበር ጥናቷ በሳምንት ሦስት ቀን ይካሄድ ነበር። አስማታዊ ድርጊቷ ምንም ደስታ ያላመጣላት ከመሆኑም በላይ ብዙ የግል ችግሮች ነበሯት። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ረጅሙን ጉዞ አጠናቅቃ ከአጋንንት አምልኮ ወደ እውነተኛ አምልኮ መሸጋገር ቻለች። የእሷን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች በሚመጡበት ጊዜ ከክፉ ሊጠብቃቸው የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ትነግራቸዋለች። በአሁኑ ጊዜ ኤልሲ የተጠመቀች ምሥክር ስትሆን ከቤተሰቧና ከሚያውቋት ሰዎች መካከል 14 የሚሆኑት እውነትን ተቀብለዋል።
11. ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎች ምን ማስተካከያዎች ለማድረግ ፈቃደኞች ሆነዋል?
11 ባለፈው ዓመት አምላክን ለማገልገል ራሳቸውን ከወሰኑት መካከል አብዛኞቹ ይህን የመሰለ ትልቅ ለውጥ ማድረግ አላስፈለጋቸውም። ሆኖም ሁሉም ከመንፈሳዊ ሞት ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተሸጋግረዋል። (ኤፌሶን 2:1) በአካል አሁንም በዓለም ውስጥ ያሉ ቢሆንም የዓለም ክፍል ግን አይደሉም። (ዮሐንስ 17:15, 16) ‘አገራቸው በሰማይ እንደሆነው’ እንደ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “እንግዶችና መጻተኞች” ናቸው። (ፊልጵስዩስ 3:20፤ 1 ጴጥሮስ 2:11) ሕይወታቸውን ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር አስማምተዋል። ከሁሉም በላይ ለዚህ ያነሳሳቸው ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:37–39) ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውን የፍቅረ ነዋይ ግቦች አይከተሉም ወይም ደግሞ በዚህ ዓለም ሰዎች እንደ ስኬት የሚያዩአቸውን ነገሮች ማከናወን እንዳለባቸው ሆኖ አይሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ዓይናቸውን ቃል በተገባው ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ላይ ይተክላሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:18
12. ኢየሱስ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት ጊዜ “በምድር እምነትን” እንዳገኘ የሚያሳየው ባለፈው ዓመት ሪፖርት የተደረገው የትኛው እንቅስቃሴ ነው?
12 አብርሃም ወደ ከነዓን ሲሄድ እሱና ቤተሰቡ ይሖዋ ከሚያደርግላቸው ድጋፍና ጥበቃ በቀር ሌላ ማንም አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ እነዚህ 316,092 የሚሆኑ አዲስ ተጠማቂ ክርስቲያኖች ብቻቸውን አይደሉም። ይሖዋ ልክ ለአብርሃም እንዳደረገው ሁሉ እነሱንም በመንፈሱ እንደሚደግፋቸውና እንደሚጠብቃቸው እሙን ነው። (ምሳሌ 18:10) ሆኖም ከዚህ በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ካሉት አንዳንድ አገሮች የሕዝብ ብዛት የበለጠ ቁጥር ባለው ዓለም አቀፋዊ የሆነ ንቁ “ሕዝብ” አማካኝነት ይደግፋቸዋል። (ኢሳይያስ 66:8) ባለፈው ዓመት 5,888,650 የደረሰ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዚህ ሕዝብ አባላት አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለሰዎች በመንገር ሕያው እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ማርቆስ 13:10) ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በመፈለግ 1,186,666,708 የሚያክል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰዓት አሳልፈዋል። በውጤቱም እምነት ማዳበር ከሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች ጋር 4,302,852 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። ከዚህ “ሕዝብ” መካከል 698,781 የሚሆኑት በሙሉ ጊዜ አለዚያም ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት በአቅኚነት አገልግሎት በመካፈል ቅንዓታቸውን በሌላ ተጨማሪ መንገድ አሳይተዋል። (የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው ዓመት ያደረጉትን እንቅስቃሴ የሚያሳይ መረጃ ከገጽ 12 እስከ 15 ላይ ቀርቧል።) ይህ አስደናቂ ዘገባ “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” ለሚለው የኢየሱስ ጥያቄ ሕያው የሆነ አዎንታዊ መልስ ነው።
ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም ታማኞች ሆነዋል
13, 14. አብርሃምና ቤተሰቡ በከነዓን ሳሉ ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን ግለጽ።
13 አብርሃምና ቤተሰቡ በከነዓን በነበሩ ጊዜ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ በአንድ ወቅት ከባድ ረሃብ በመከሰቱ ከነዓንን ለቅቆ ወደ ግብጽ ለመሰደድ ተገድዶ ነበር። ከዚህም በላይ የግብጽ ገዥም ሆነ የጌራራ (በጋዛ አቅራቢያ) ገዥ የአብርሃምን ሚስት ሣራን ለራሳቸው ለመውሰድ ሞክረው ነበር። (ዘፍጥረት 12:10-20፤ 20:1–18) በተጨማሪም የአብርሃምን መንጎች በሚጠብቁት እረኞችና የሎጥን መንጎች በሚጠብቁት እረኞች መካከል ግጭት መፈጠሩ ለሁለቱ ቤተሰቦች መለያየት ምክንያት ሆኗል። አብርሃም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ሎጥ ይስማማኛል ያለውን አገር መጀመሪያ እንዲመርጥ ያደረገ ሲሆን ሎጥ በልምላሜውና በውበቱ ኤደን ይመስል በነበረው የዮርዳኖስ አውራጃ ለመኖር መርጧል።—ዘፍጥረት 13:5–13
14 ከጊዜ በኋላ በርቀት የምትገኘው የኤላም ንጉሥና ተባባሪዎቹ በሲዲም ሸለቆ ከሚገኙት አምስት ከተሞች ነገሥታት ጋር ያደረጉት ጦርነት ሎጥንም ነክቶት ነበር። ባዕዳን የሆኑት ነገሥታት የአካባቢውን ነገሥታት ድል አድርገው ሎጥንና ንብረቱን ጨምሮ ከፍተኛ ምርኮ ማረኩ። አብርሃም የደረሰውን ሁኔታ በሰማ ጊዜ በድፍረት ባዕዳን ነገሥታቱን ተከታትሎ ሎጥንና ቤተሰቡን እንዲሁም የአካባቢውን ነገሥታት ንብረት ሊያስመልስ ችሏል። (ዘፍጥረት 14:1–16) ይሁን እንጂ ሎጥ በከነዓን ምድር ከዚህም የከፋ ሁኔታ ገጥሞት ነበር። ሰዶም በብልሹ ሥነ ምግባሯ የምትታወቅ ከተማ ብትሆንም እንኳ ሎጥ በሆነ ምክንያት በዚያ መኖር ጀምሮ ነበር።b (2 ጴጥሮስ 2:6–8) ሁለት መላእክት ከተማዋ እንደምትጠፋ ባስጠነቀቁት ጊዜ ሎጥ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ሸሸ። ይሁን እንጂ የሎጥ ሚስት መላእክቱ የሰጧቸውን የማያሻማ መመሪያዎች ችላ በማለቷ በጨው ተቀበረች። ሎጥ ከነበረበት የኑሮ ደረጃ ዝቅ ብሎ ለተወሰነ ጊዜ ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ጋር በዞዓር በአንድ ዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገድዶ ነበር። (ዘፍጥረት 19:1–30) ሎጥ ወደ ከነዓን የመጣው የአብርሃም ቤተሰብ አባል ሆኖ ስለነበር እነዚህ ሁኔታዎች አብርሃምን በጣም ረብሸውት መሆን አለበት።
15. አብርሃም በባዕድ አገር በድንኳን ውስጥ ሲኖር ችግሮች የገጠሙት ቢሆንም እንኳ የትኛውን አፍራሽ አስተሳሰብ እንዳስወገደ የታወቀ ነው?
15 አብርሃም እኔም ሆንኩ ሎጥ በኡር ከተማ ከአባቴ የቅርብ ዘመዶች ጋር ደህንነታችን ተጠብቆ ብንኖር ወይም ደግሞ በካራን ከወንድሜ ከናኮር ጋር ብንኖር ይሻል ነበር እንዴ? ብሎ አስቦ ይሆን? በድንኳን ውስጥ ከምኖር ምነው በግንብ በታጠረች ከተማ ውስጥ ደህንነቴ ተጠብቆ በኖርኩ ኖሮ ብሎ ይሆን? ምናልባትም በማላውቀው አገር እየተቅበዘበዝኩ የምኖር ከሆነ የከፈልኳቸው መሥዋዕትነቶች ከንቱ ናቸው ማለት ነው ብሎ አስቦ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አብርሃምና ስለ ቤተሰቡ ሲናገር “ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ፣ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር” ብሏል። (ዕብራውያን 11:15) ሆኖም አልተመለሱም። የነበሩት ችግሮች ተስፋ ሳያስቆርጧቸው ይሖዋ እንዲኖሩበት በፈለገው ቦታ ኖረዋል።
ጽናት በዛሬው ጊዜ
16, 17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ምን ችግሮች ይገጥሟቸዋል? (ለ) ክርስቲያኖች ምን አዎንታዊ አመለካከት አላቸው? ለምንስ?
16 በዛሬው ጊዜ ያሉትም ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ጽናት እያሳዩ ነው። አምላክን ማገልገላቸው ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝላቸው ቢሆንም በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ኑሮው ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ቀላል አይደለም። በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆንም እንኳ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሱት የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች በእነሱም ላይ ይደርሳሉ። (ኢሳይያስ 11:6-9) ንጹሐን ዜጎች ሆነው ሳለ ብዙዎች ብሔራት በሚያደርጓቸው ጦርነቶች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ያለ ጥፋታቸው በድህነት ለመማቀቅ ተገድደዋል። ከዚህም በተጨማሪ በብዙዎች ዘንድ የሚጠሉ አናሳ ቡድን መሆናቸው ያስከተለባቸውን ችግር በጽናት መቋቋም አስፈልጓቸዋል። በብዙ አገሮች የምሥራቹን የሚሰብኩት አብዛኞቹ ሰዎች የሚያሳዩትን የግድየለሽነት መንፈስ ተቋቁመው ነው። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ‘በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠሩና በንጹሕ ደም ላይ የሚፈርዱ’ ሰዎች የተንኮል ጥቃት ይሰነዝሩባቸዋል። (መዝሙር 94:20, 21) በክርስቲያኖች ላይ ጥቃት በማይሰነዘርባቸውና በሚከተሉት ከፍተኛ የአቋም ደረጃ በሚወደሱባቸው አገሮችም እንኳ፣ በዘመኑ በከተሞች ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ከአብዛኞቹ ሰዎች በተለየ መልኩ በድንኳን ውስጥ ይኖር ከነበረው ከአብርሃም ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ከትምህርት ቤትና ከሥራ ጓደኞቻቸው የተለዩ እንደሆኑ ያውቃሉ። አዎን፣ በዓለም ውስጥ እየኖሩ የዓለም “ክፍል [NW]” አለመሆን ቀላል አይደለም።—ዮሐንስ 17:14
17 ታዲያ ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችን ይጸጽተናልን? ልክ እንደ ማንኛውም ሰው የዓለም ክፍል ሆነን ብንኖር ይሻል ነበር ብለን እናስባለን? ለይሖዋ አገልግሎት ስንል የከፈልናቸው መሥዋዕትነቶች ይቆጩናልን? በፍጹም! የተውነውን ነገር እንደገና ለማግኘት አንጓጓም፤ ከዚህ ይልቅ የከፈልነው ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነት በአሁኑ ጊዜ ካገኘነውና ወደፊት ከምናገኘው በረከት ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር የማይችል እንደሆነ እንገነዘባለን። (ሉቃስ 9:62፤ ፊልጵስዩስ 3:8) ደግሞስ በዓለም ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸውን? ብዙዎቹ ሰዎች እኛ ያገኘናቸውን መልሶች ገና ለማግኘት በመጣር ላይ ናቸው። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ላይ ያሰፈረውን እኛ የምንከተለውን መመሪያ ባለመከተላቸው ለብዙ መከራዎች ተዳርገዋል። (መዝሙር 119:105) በተጨማሪም ብዙዎቹ እኛ ከመሰል አማኞች ጋር ያለንን ዓይነት ክርስቲያናዊ ወዳጅነትና አስደሳች ኅብረት ለማግኘት የሚጓጉ ናቸው።—መዝሙር 133:1፤ ቆላስይስ 3:14
18. ክርስቲያኖች የአብርሃም ዓይነት ድፍረት ሲያሳዩ ምን ውጤት ያገኛሉ?
18 አንዳንድ ጊዜ አብርሃም ሎጥን የማረኩትን ሰዎች ባሳደደበት ጊዜ ያሳየውን ዓይነት ድፍረት ማሳየት እንደሚያስፈልገን አይካድም። ሆኖም እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ ይሖዋ ውጤቱን ይባርከዋል። ለምሳሌ ያህል በሰሜን አየርላንድ በሃይማኖት ወገን ለይቶ በሚካሄደው ዓመፅ ሳቢያ ሥር የሰደደ ጥላቻ ነግሷል፤ በመሆኑም ገለልተኛ ለመሆን ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም ታማኝ ክርስቲያኖች ይሖዋ “በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፣ አይዞህ፤ አትፍራ፣ አትደንግጥ” በማለት ለኢያሱ የተናገረውን ቃል ተከትለዋል። (ኢያሱ 1:9፤ መዝሙር 27:14) ባለፉት ዓመታት ያሳዩት ድፍረት የተሞላበት አቋም አክብሮት ያተረፈላቸው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ባሉት በሁሉም ማኅበረሰቦች መካከል በነፃነት መስበክ ይችላሉ።
19. ክርስቲያኖች ደስተኞች ሊያደርጋቸው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? የይሖዋን መመሪያ ሲከተሉ የትኛውን ውጤት በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ?
19 የይሖዋን መመሪያ የምንከተል እስከሆነ ድረስ ማንኛውም ሁኔታ ቢያጋጥመን በመጨረሻ የምናገኘው ውጤት ለእሱ ክብር የሚያመጣና ለእኛም ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ እንደሆነ ቅንጣት ያህል ልንጠራጠር አይገባም። ፈታኝና መሥዋዕትነት የሚጠይቁ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም እንኳ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር እንድንወዳጅ ካስቻለንና አምላክ ቃል የገባውን የዘላለም ሕይወት በትምክህት እንድንጠባበቅ ከሚያደርገን ከይሖዋ አገልግሎት ሌላ የተሻለ ነገር የለም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የአብርሃም ወንድም የሆነው የሎጥ አባት ሲሞት አብርሃም የወንድሙን ልጅ ሎጥን ልጁ አድርጎ ሳይወስደው አይቀርም።—ዘፍጥረት 11:27, 28፤ 12:5
b አንዳንዶች ሎጥ በከተማዋ መኖር የጀመረው በአራቱ ነገሥታት ከተማረከ በኋላ የተሻለ ደህንነት ለማግኘት በማሰብ ነው የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ።
[ታስታውሳለህ?]
◻ ጠንካራ እምነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ አብርሃም ጠንካራ እምነት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?
◻ አንድ ሰው ራሱን መወሰኑ በሕይወቱ ውስጥ ለውጦች የሚያስከትለው እንዴት ነው?
◻ ማንኛውም ዓይነት ችግር ሊገጥመን ቢችልም እንኳ አምላክን ማገልገል የሚያስደስተን ለምንድን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም የተሰጠውን ተስፋ ለመውረስ በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጦች ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት ጊዜ “በምድር እምነትን” እንዳገኘ ማስረጃዎቹ ያሳያሉ