ለዘመናችን የሚሆን መልእክት የያዘ የጥበብ መጽሐፍ
ከጥንቶቹ አበውና በጊዜው ከነበሩት በጣም ሀብታም ሰዎች አንዱ የነበረው ኢዮብ “ከአንድ ከረጢት ሙሉ ዕንቁ የአንድ ከረጢት ሙሉ ጥበብ ዋጋ ይበልጣል” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 1:3፤ 28:18 NW፤ 42:12) በእርግጥም አንድ ሰው ሕይወቱ የተሳካ እንዲሆን በመርዳት ረገድ ጥበብ ያለው ዋጋ ቁሳዊ ሀብት ካለው ዋጋ እጅግ የላቀ ነው። “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው” በማለት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ተናግሯል።—መክብብ 7:12
ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ እንዲህ የመሰለውን ጥበብ ከየት ማግኘት ይቻላል? ሰዎች ለችግሮቻቸው መፍትሄ ለማግኘት ሲሉ የምክር አምድ አዘጋጆችን፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎችን፣ የስነ አእምሮ ባለሙያዎችን ሌላው ቀርቶ ፀጉር ሠሪዎችንና የታክሲ ሾፌሮችን ያማክራሉ። ገንዘብ ይከፈላቸው እንጂ በየትኛውም ጉዳይ ላይ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ባለሙያዎች አሉ። ሆኖም እነዚህ “የጥበብ” ቃላት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ብስጭት አልፎ ተርፎም ወደ ጥፋት ከመምራት በቀር ምንም የፈየዱት ነገር የለም። ታዲያ እውነተኛ ጥበብ እንዴት ልናገኝ እንችላለን?
ስለ ሰው ልጅ ጉዳዮች ጥልቅ ማስተዋል ያለው ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት “የጥበብ ትክክለኛነት በሥራዋ ይገለጣል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:19 የ1980 ትርጉም) እስቲ ሰዎች በኑሯቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አንዳንድ የተለመዱ ችግሮች እንዳስስና የትኞቹ የጥበብ ቃላት እንደረዷቸው እንዲሁም እነዚህ የጥበብ ቃላት በእርግጥም ‘ከከረጢት ሙሉ ዕንቁ’ የላቀ ዋጋ ያላቸው መሆኑን እንመልከት። አንተም ይህን “ከረጢት ሙሉ ጥበብ” ማግኘትና መጠቀም ትችላለህ።
የመንፈስ ጭንቀት አለብህን?
“ከጅምሩ አንስቶ በጭንቀት የተሞላው 20ኛው መቶ ዘመን መደምደሚያውም ሐዘንና ትካዜ የነገሠበት ይሆናል” በማለት የለንደኑ ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን ይናገራል። አክሎም “በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ላይ የተደረገው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጥናት በሽታው በዓለም ዙሪያ በመስፋፋት ላይ መሆኑን አመልክቷል። እንደ ታይዋን፣ ሊባኖስ እና ኒው ዚላንድ የመሳሰሉ የተለያየ ድብልቅ ሕዝብ የሚኖሩባቸው አገሮች አንድ ትውልድ አልፎ ሌላኛው እየተተካ በሄደ መጠን በበሽታው የሚጠቁት ሰዎች ቁጥር ይበልጥ እያደገ መጥቷል።” ከ1955 በኋላ የተወለዱ ሰዎች በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት እድላቸው ከአያቶቻቸው ይልቅ በሦስት እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ይታመናል።
በከባድ የመንፈስ ጭንቀት እየተሠቃየች አብዛኛውን ጊዜዋን በመኝታ ታሳልፍ የነበረችው የቶሞኢ ሁኔታ ይህ ነበር። የሁለት ዓመት ወንድ ልጅዋን ተንከባክባ ማሳደግ ስላቃታት ተመልሳ ወደ ወላጆቿ ቤት ገባች። የቶሞኢ ልጅ እኩያ የሆነች ሴት ልጅ ያለቻት አንዲት የጎረቤት ሴት ቶሞኢን ጓደኛ አደረገቻት። ቶሞኢ የሚሰማትን የዋጋቢስነት ስሜት ስትነግራት ጎረቤቷ ከአንድ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ጥቅስ አነበበችላት። ጥቅሱ “ዓይን እጅን:- አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፣ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን:- አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው” የሚል ነበር።a ማንኛውም ሰው በዚህ ዓለም ላይ የራሱ የሆነ ቦታ እንዳለውና ተፈላጊም እንደሆነ በተረዳች ጊዜ ቶሞኢ እንባዋ በዓይኖቿ ግጥም አለ።
እነዚህ ቃላት የሚገኙበትን መጽሐፍ እንድትመረምር ጎረቤቷ ሐሳብ አቀረበችላት። ቶሞኢ እስከ እዚህ ጊዜ ድረስ ምንም ነገር ማከናወን የማትችልና ሌላው ቀርቶ በጣም ቀላል ነገር እንኳ አደርጋለሁ ብላ ቃል ገብታ የማታውቅ ብትሆንም ጎረቤቷ ባቀረበችላት ሐሳብ በመስማማት ራሷን ነቀነቀች። በተጨማሪም ጎረቤቷ አብራት ታገበያያትና በየቀኑ ምግብ በማዘጋጀት ትረዳት ነበር። ከአንድ ወር በኋላ ቶሞኢ ልክ እንደ ሌሎች የቤት እመቤቶች ሁሉ እሷም በየቀኑ ጠዋት እየተነሳች ልብስ ማጠብ፣ ቤት ማጽዳትና ምግብ ማዘጋጀት ጀመረች። ብዙ ችግሮችን ማሸነፍ የነበረባት ቢሆንም “ባገኘኋቸው የጥበብ ቃላት መሠረት ከኖርኩ ደህና እንደምሆን ትምክህት ነበረኝ” ስትል ተናግራለች።
ቶሞኢ ያገኘችውን ጥበብ በሕይወቷ ላይ በመተግበር በመንፈስ ጭንቀት ያሳለፈቻቸውን የሐዘን ጊዜያት አሸንፋለች። ቶሞኢ የነበሩባትን ችግሮች ተቋቁማ እንድታሸንፍ የረዷትን እነዚያን ቃላት ሌሎች ሰዎችም በሥራ ላይ እንዲያውሉ ለመርዳት ሙሉ ጊዜ ታገለግላለች። እነዚህ የጥበብ ቃላት ዛሬ ላሉ ሰዎች ሁሉ የሚሆን መልእክት በያዘ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ።
በቤተሰባችሁ ውስጥ ችግሮች አሉባችሁ?
በዓለም ዙሪያ የፍቺ ቁጥር እያሻቀበ በመሄድ ላይ ይገኛል። በቤተሰብ መካከል የሚነሱ ችግሮች በአንድ ወቅት በነበራቸው የጠበቀ የቤተሰብ ትስስር ይኩራሩ በነበሩት በሩቅ ምሥራቅ አገሮችም እንኳን ሳይቀር እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ታዲያ ትዳርን በሚመለከት ሊሠራ የሚችል ጥበብ የሞላበት መመሪያ ከየት ልናገኝ እንችላለን?
በትዳራቸው ውስጥ ችግር ጠፍቶ የማያውቀውን ሹጎንና ሚሆኮን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በረባ ባልረባው ይጣሉ ነበር። ሹጎ ግልፍተኛ ሲሆን ሚሆኮ ደግሞ ባሏ ስህተት ባገኘባት ቁጥር አጸፋውን ትመልስ ነበር። እንዲያውም ሚሆኮ ‘በምንም ነገር ልንስማማ አንችልም’ ብላ እስከማሰብ ደርሳ ነበር።
አንድ ቀን አንዲት ሴት ሚሆኮ ወደምትኖርበት ቤት ሄደችና ከአንድ መጽሐፍ ላይ የሚከተሉትን ቃላት አነበበችላት:- “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው።”b ምንም እንኳ ሚሆኮ ለሃይማኖት ግድ ያልነበራት ብትሆንም እነዚህ ቃላት የሰፈሩበትን መጽሐፍ ለማጥናት ተስማማች። የቤተሰቧ ሕይወት እንዲሻሻል የማድረግ ፍላጎት ነበራት። ስለሆነም የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የተባለው መጽሐፍ በሚጠናበት ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ግብዣ ሲቀርብላት ግብዣውን በደስታ ተቀበለች።c ባሏም እንደዚሁ ግብዣውን ተቀበለ።
ሹጎ በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ የሚያውሉና ደስተኞች መሆናቸውን ተገነዘበ። ሚስቱ እያጠናች ያለችውን መጽሐፍ ለማንበብ ወሰነ። መጽሐፉን በሚያነብበት ጊዜ “ለትዕግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል” የሚለው አረፍተ ነገር ወዲያው ትኩረቱን ሳበው።d ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በሕይወቱ ላይ ለመተግበር ጊዜ የወሰደበት ቢሆንም እንኳ ቀስ በቀስ ያደርግ የነበረውን ለውጥ ባለቤቱን ጨምሮ በአካባቢው ባሉ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታይ ነበር።
ሚሆኮ ባሏ ያደረገውን ለውጥ በመመልከቷ እርሷም የምትማረውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል ጀመረች። ሌላው በተለይ በጣም የረዳቸው “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፣ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ነው።e ስለዚህ ሚሆኮ እና ባለቤቷ ስለ መልካም ጎኖቻቸው ለማውራትና አንዳቸው የሌላውን ስህተት ከመለቃቀም ይልቅ እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ ለመነጋገር ወሰኑ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሚሆኮ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በእርግጥም ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል። ሁልጊዜ ማታ ማታ እራት እየበላን መወያየት ከጀመርን ሰነባብተናል። የሦስት ዓመት ወንድ ልጃችንም ሳይቀር በውይይታችን ውስጥ ይካፈላል። በእርግጥም ማነቃቂያ ሰጥቶናል!”
ይህ ቤተሰብ ያገኘውን ትርጉም ያዘለ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር የጋብቻ ዝምድናቸውን ወደ መበጠስ አድርሰውት የነበሩትን ችግሮች እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል። ታዲያ እነዚህ ባልና ሚስት ያገኙት የጥበብ ምክር ዕንቁ ከሞላው ከረጢት የተሻለ ጥቅም አላስገኘላቸውም?
ሕይወትህ ስኬታማ እንዲሆን ትፈልጋለህ?
በዛሬው ጊዜ የአብዛኞቹ ሰዎች ዋነኛ የሕይወት ግብ ሀብት ማካበት ነው። ሆኖም በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ለበጎ አድራጎት የለገሰ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ነጋዴ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር:- “ገንዘብ አንዳንድ ሰዎችን ያማልል ይሆናል። ይሁን እንጂ በአንድ ጊዜ ሁለት ጥንድ ጫማ ሊያደርግ የሚችል ማንም ሰው የለም።” ይህን ሐቅ የተቀበሉ ጥቂት ሰዎች ሲሆኑ ሀብትን መከታተል ያቆሙ ግን ከዚያ በጣም ያነሱ ናቸው።
ሂቶሺ ያደገው በድህነት ስለነበር ሀብታም የመሆን ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። አበዳሪዎች በዕዳ ውስጥ ተዘፍቀው የሚገኙ ተበዳሪዎችን ምን ያህል እንደፈለጉ እንደሚጫወቱባቸው በተመለከተ ጊዜ “ብዙ ገንዘብ የሰበሰበ አሸናፊ ይሆናል” ወደሚለው መደምደሚያ ደረሰ። ሂቶሺ ገንዘብ ከፍተኛ ኃይል አለው ብሎ ከማመኑ የተነሳ የሰው ሕይወት እንኳ ሳይቀር በገንዘብ ይገዛል ወደሚል አስተሳሰብ ደረሰ። ሀብት ለማካበት ሲል ዓመቱን ሙሉ አንዲት ቀን እንኳ ሳያርፍ በቧንቧ ሥራው ተጠመደ። የመለስተኛ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት የሆነው ሂቶሺ ምንም ያክል ትጉ ሠራተኛ ቢሆን ኮንትራት የሚሰጡትን የሥራ ተቋራጮች ያክል ኃይል ሊኖረው እንደማይችል ወዲያው ተገነዘበ። ብስጭትና ከአሁን አሁን እከስር ይሆናል የሚለው ፍርሃት የዕለት ተዕለት ዕጣው ሆነ።
ከዚያም አንድ ሰው የሂቶሺን ቤት አንኳኳና ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርሱ እንደሞተለት ያውቅ እንደሆነ ጠየቀው። ሂቶሺ እንደ እርሱ ላለው ሰው የሚሞት ሰው ይኖራል ብሎ ስላልገመተ በከፍተኛ ጉጉት ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ፈለገ። በቀጣዩ ሳምንት በተደረገ በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ በሰማው ንግግር ውስጥ ‘ዓይናችሁ ቀና ይሁን’ የሚለውን ምክር ሲሰማ በጣም ተገረመ። ተናጋሪው “ቀና” ዓይን አርቆ የሚመለከትና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩር እንደሆነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ክፉ” ወይም “ምቀኛ” ዓይን ጊዜያዊ በሆኑ ሥጋዊ ምኞቶች ላይ የሚያተኩር አርቆ የማይመለከት መሆኑን አብራራ። “መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና” የሚለው ምክር በጣም ነካው።f ሀብት ከማካበት የሚበልጥ አንድ ነገር መኖር አለበት! ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ሰምቶ አያውቅም።
በተማራቸው ነገሮች በጣም ስለተነካ የተማረውን በሕይወቱ ላይ መተግበር ጀመረ። ገንዘብ ለማግኘት ብቻ ከመባዘን ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በሕይወቱ ውስጥ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጥ ጀመረ። ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰቡን መንፈሳዊነት ለመንከባከብ ጊዜ መደበ። እንዲህ ማድረጉ ለሥራ የሚያውለውን ጊዜ እንደሚሻማበት የታወቀ ቢሆንም ሥራው ጥሩ ውጤት አስገኝቶለታል። ለምን?
የተሰጠውን ምክር በሥራ ላይ እያዋለ ሲሄድ የጠበኝነት ባሕርዩ ተለውጦ ገርና ሰላማዊ እንዲሆን አደረገው። በተለይ “ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፣ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፣ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፣ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል” የሚለው ምክር በጣም ነካው።g ይህን ምክር መከተሉ ባለጠጋ እንዲሆን አልረዳውም። ይሁን እንጂ ‘የለበሰው አዲስ ሰውነት’ በደንበኞቹ ዘንድ ጥሩ ስም እንዲኖረውና በእነርሱ ዘንድ እምነትና ትምክህት አተረፈለት። አዎን፣ ያገኛቸው የጥበብ ቃላት ኑሮው እንዲሰምርለት ረድተውታል። ቃል በቃል ከከረጢት ሙሉ ዕንቁ ወይም ገንዘብ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ሆነውለታል።
ከረጢቱን ለመፍታት ትፈልጋለህን?
ከላይ እንደ ምሳሌ ሆነው ለቀረቡት ግለሰቦች ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው ጥበብ የሞላበት ከረጢት ምንድን ነው? ይህ ጥበብ በምድር ላይ በስፋት በመሰራጨትም ሆነ በየትኛውም አካባቢ እንደ ልብ በመገኘት ረገድ አቻ በማይገኝለት መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ ምናልባት ቀደም ብሎም ይኖርህ ይሆናል፤ ከሌለህ ደግሞ በቀላሉ እንዲኖርህ ማድረግ ትችላለህ። አንድ ከረጢት ሙሉ ውድ ዕንቁዎች ያሉት አንድ ሰው ዕንቁዎቹን ጥቅም ላይ እስካላዋላቸው ድረስ ምንም የሚፈይዱለት ነገር እንደማይኖር ሁሉ አንድ ሰውም መጽሐፍ ቅዱስ ስላለው ብቻ ጥቅም ያገኛል ማለት አይደለም። ስለዚህ በምሳሌያዊ አባባል ከረጢቱን ከፍተህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያለባቸውን ምክሮችና ወቅታዊ ሐሳቦች ተግባር ላይ አውላቸው፤ እንዲሁም በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተሳካ መንገድ ለመወጣት እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል ተመልከት።
አንድ ከረጢት ሙሉ ዕንቁ ቢሰጥህ በጣም አትደሰትም? ደግሞስ ምስጋናህን ለመግለጽ ማን እንደሰጠህ ለማወቅ አትፈልግም? መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከትስ ሰጪው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” ብሎ ሲናገር በውስጡ ለሚገኘው ጥበብ ምንጩ ማን መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) በተጨማሪም “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ” እንደሆነ ይነግረናል። (ዕብራውያን 4:12 የ1980 ትርጉም) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የጥበብ ቃላት ለጊዜያችን ወቅታዊና ውጤታማ የሆኑት በዚህ ምክንያት ነው። በዛሬው ጊዜ ላሉ ሰዎች የሚሆን መልእክት በያዘው የጥበብ መጽሐፍ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ‘ጥበብ የተሞላ ከረጢት’ ተጠቃሚ መሆን ትችል ዘንድ ለጋስ ሰጪ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ እንድትማር የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጥቅሱ የተወሰደው ከ1 ቆሮንቶስ 12:21, 22 ነው።
c በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ።
f ማቴዎስ 6:21-23፤ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ስሜታዊ ሚዛንን ለመጠበቅ የሚረዱ የጥበብ ቃላት
“ኃጢአታችንን ብትከታተል፣ ማን ከፍርድ ሊያመልጥ ይችላል? ነገር ግን አንተን በማክበር እንድንታዘዝህ ይቅር ትለናለህ።”—መዝሙር 130:3, 4 የ1980 ትርጉም
“ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፤ በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች።”—ምሳሌ 15:13
“እጅግ ጻድቅ አትሁን፣ እጅግ ጠቢብም አትሁን፣ እንዳትጠፋ።”—መክብብ 7:16
“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—ሥራ 20:35
“ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።”—ኤፌሶን 4:26
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ለማድረግ የሚረዱ የጥበብ ቃላት
“ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል።”—ምሳሌ 15:22
“አስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፣ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች።”—ምሳሌ 18:15
“የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው።”—ምሳሌ 25:11
“እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ [“ይሖዋ፣” NW] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቆላስይስ 3:13, 14
“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ ይሁን።”—ያዕቆብ 1:19
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሕይወትን የተሳካ ለማድረግ የሚረዱ የጥበብ ቃላት
“አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 11:1
“ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።”—ምሳሌ 16:18
“ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፣ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።”—ምሳሌ 25:28
“በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፣ ቁጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።”—መክብብ 7:9
“እንጀራህን በውኃ ፊት ላይ ጣለው፣ ከብዙ ቀን በኋላ ታገኘዋለህና።”—መክብብ 11:1
“ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።”—ኤፌሶን 4:29
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ‘ጥበብ ከተሞላው ከረጢት’ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያበቃ የመጀመሪያ እርምጃ ነው