የበኣል አምልኮ የእስራኤላውያንን ልብ ለመማረክ የተካሄደ ፍልሚያ
ለአንድ ሺህ ዓመት ያህል የእስራኤላውያንን ብሔር ልብ ለመማረክ የተጧጧፈ ፍልሚያ ተካሄዷል። በአንድ ወገን ከአጉል እምነት የመነጨ ፍርሃትና የፆታ አምልኮታዊ ሥርዓት በሌላ ወገን ደግሞ እምነትና ታማኝነት አንዳቸው ከሌላው ተፋልመዋል። ይህ የሞት ሽረት ትግል የተደረገው በበኣል አምልኮና በይሖዋ አምልኮ መካከል ነው።
የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ነፃ ላወጣው እውነተኛ አምላክ ታማኝ ሆኖ ይቀጥል ይሆን? (ዘጸአት 20:2, 3) ወይስ በኣል ወደሚባለው ምድሪቱን ለም ለማድረግ ቃል ወደገባው የከነዓን ምድር ተወዳጅ አምላክ ይከዱ ይሆን?
ይህ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተካሄደ መንፈሳዊ ፍልሚያ ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። ለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ።” (1 ቆሮንቶስ 10:11) ይህ ታሪካዊ ፍልሚያ የያዘው መሠረታዊ ማስጠንቀቂያ ይበልጥ ትርጉም አዘል የሚሆንልን የበኣልን ማንነትና የበኣል አምልኮ የሚያካትታቸውን ነገሮች ከተገነዘብን ነው።
በኣል ማን ነበር?
እስራኤላውያን ስለ በኣል የሰሙት በ1473 ከዘአበ ገደማ ወደ ከነዓን ምድር በደረሱ ጊዜ ነበር። የከነዓናውያን አማልክት የተለያዩ ስሞችና አንዳንድ ለየት ያሉ ባሕርያት ቢኖሯቸውም እንኳ ከነዓናውያን ከግብፅ አማልክት እምብዛም ያልተለዩ ቁጥር ስፍር የሌላቸው አማልክትን እንደሚያመልኩ እስራኤላውያን ተገንዝበዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በኣል የከነዓናውያን አንጋፋ አምላክ መሆኑን ለይቶ ከመጥቀሱም በላይ አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶችም የእርሱን የበላይነት አረጋግጠዋል። (መሳፍንት 2:11) በኣል የአረማውያን አማልክት ቁንጮ ባይሆንም እንኳ ከነዓናውያን የላቀ ትኩረት የሚሰጡት አምላክ ነበር። በኣል ዝናብን፣ ነፋስንና ደመናን የመቆጣጠር ኃይል እንዳለው እንዲሁም አምላኪዎቹንም ሆነ ከብቶቻቸውንና እርሻቸውን ከድርቅ አልፎ ተርፎም ከሞት ሳይቀር ማስጣል የሚችለው እርሱ ብቻ እንደሆነ ያምኑ ነበር። የበኣል ጥበቃ ባይኖር ኖሮ ሞት የተባለው የከነዓናውያን ቂመኛ አምላክ በእነርሱ ላይ መቅሠፍት እንደሚያወርድ የታወቀ ነው።
የፆታ አምልኮታዊ ሥርዓት ለበኣል የሚቀርብ አምልኮ ዋና ክፍል ነበር። ሌላው ቀርቶ በበኣል ስም የሚቆሙ የማምለኪያ ዓምዶችና ሐውልቶች እንኳ ከፆታ ጋር የተያያዘ ትርጉም ነበራቸው። በኣልን የሚወክሉ ከዓለት ወይም ከድንጋይ ተፈልፍለው የሚሠሩ የአምልኮ ዓምዶች የወንድ ብልት ቅርጽ ያላቸው እንደነበሩ ግልጽ ነው። በሌላ በኩል ሐውልቶቹ የበኣል ተጓዳኝ የሆነችውንና የሴት ብልት የያዘችውን አሼራን የሚወክሉ የእንጨት ዕቃዎችና ዛፎች ነበሩ።—1 ነገሥት 18:19
ሌሎች የበኣል አምልኮ ዐበይት ገጽታዎች በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጸም ግልሙትናና ሕፃናትን መሠዋት ነበር። (1 ነገሥት 14:23, 24፤ 2 ዜና መዋዕል 28:2, 3) ዘ ባይብል ኤንድ አርኪኦሎጂ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በከነዓናውያን ቤተ መቅደሶች ውስጥ ወንድና ሴት ጋለሞታዎች (‘ቅዱስ’ ወንዶችና ሴቶች) የነበሩ ሲሆን ማንኛውም ዓይነት የፆታ ግንኙነት ያለ ገደብ ይፈጸም ነበር። [ከነዓናውያን] እነዚህ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች በሆነ መንገድ እርሻዎችና ከብቶች ፍሬያማ እንዲሆኑ ያስችላሉ የሚል እምነት ነበራቸው።” የሆነ ሆኖ ይህ ሃይማኖታዊ ማሳበቢያ ቢሆንም እንዲህ ያለው የብልግና ድርጊት ለአምላኪዎቹ ሥጋዊ ፍላጎት ማራኪ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ታዲያ በኣል የእስራኤላውያንን ልብ መማረክ የቻለው እንዴት ነበር?
ያን ያህል ማራኪ የሆነበት ምክንያት
አብዛኞቹ እስራኤላውያን ብዙ የማይጠይቅባቸውን ሃይማኖት መከተል የመረጡ ይመስላል። በኣልን በማምለክ ሰንበትንና በርካታ የስነ ምግባር ደንቦች የያዘውን ሕግ ከመከተል ይገላገሉ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:2-30፤ ዘዳግም 5:1-3) ሌሎች ደግሞ የከነዓናውያንን ቁሳዊ ብልጽግና ሲመለከቱ እውነትም በኣል ሊለማመኑት የሚገባ አምላክ ነው የሚል እምነት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል።
ጉብ ባሉና በዛፎች በተሸፈኑ ተራራማ ቦታዎች ላይ የሚገኙትና የኮረብታ መስገጃዎች በመባል የሚታወቁት የከነዓናውያኑ ቅዱስ ስፍራዎች በዚያ ለሚፈጸመው የመራባት ሥርዓተ አምልኮ ከመድረክ ጀርባ እንዳለ ማሳመሪያ ሆነዋል። ብዙም ሳይቆይ እስራኤላውያን ወደ ከነዓናውያን ቅዱስ ስፍራዎች መሄዱ ስላላረካቸው የራሳቸውን የማምለኪያ ቦታዎች ሠሩ። “እነርሱም ደግሞ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፣ ቅጠሉ ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች መስገጃዎችንና ሐውልቶችን የማምለኪያ ዐፀዶችንም ለራሳቸው ሠሩ።”—1 ነገሥት 14:23፤ ሆሴዕ 4:13
ሆኖም ከሁሉም በላይ የበኣል አምልኮ ለሥጋዊ ፍላጎት ማራኪ ነበር። (ገላትያ 5:19-21) ይበልጥ አይሎ የነበረው የተትረፈረፈ እህልና ብዙ የከብት መንጋ የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን የሥጋ ፍላጎት ነበር። ፍትወተ ሥጋ የላቀ ክብር ተሰጥቶት ነበር። ይህ ጉዳይ ፍትወት ቀስቃሽ በሆኑ የተጋነኑ ፆታዊ መግለጫዎችን በያዙ በርካታ የቁፋሮ ግኝት ምስሎች ሊረጋገጥ ችሏል። ድግሱ፣ ጭፈራውና ሙዚቃው መረን የለቀቀ ባሕርይ ለማሳየት ስሜት ያነሳሱ ነበር።
በልግ መግቢያ ላይ ዓይነተኛ የሆነ አንድ ትዕይንት በዓይነ ሕሊናችን ማየት እንችላለን። በዕውን በሚፈጸም አንድ አስገራሚ ሁኔታ አምላኪዎቹ ቁንጣን እስኪይዛቸው በልተውና ሞቅ እስኪላቸው ድረስ ወይን ጠጥተው ይጨፍራሉ። የመራባት ጭፈራቸው ምድሪቱ ዝናብ እንድታገኝ ለማድረግ በኣልን ከበጋ እረፍቱ ለመቀስቀስ የታለመ ነው። የወንድ ብልት ቅርጽ ባላቸው ዓምዶችና ሐውልቶች ዙሪያ ይሽከረከራሉ። በተለይ የቤተ መቅደሱ ጋለሞታዎች የሚያሳዩአቸው እንቅስቃሴዎች ወራዳና የፍትወት ስሜት የሚቀሰቅሱ ናቸው። ሙዚቃውም ሆነ ተመልካቾቹ ጭፈራቸውን እንዲቀጥሉ ኃይል ይጨምሩላቸዋል። ዳንኪራው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ጨፋሪዎቹ ሥነ ምግባር የጎደለው ግንኙነት ለመፈጸም በኣል ቤት ውስጥ ወዳሉት ዕልፍኞች ያመራሉ።—ዘኁልቁ 25:1, 2፤ ከዘጸአት 32:6, 17-19 ጋር አወዳድር፤ አሞጽ 2:8
በማየት እንጂ በእምነት አልተመላለሱም
ብዙዎቹን እስራኤላውያን የማረካቸው ይህ ዓይነቱ ፍትወት የተሞላ አምልኮ ቢሆንም ወደ በኣል አምልኮ ያመራቸው ፍርሃትም ጭምር ነበር። እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት በማጣታቸው የተነሳ ሙታንንና የወደፊቱን ጊዜ መፍራታቸው እንዲሁም ምስጢራዊ ለሆኑ ነገሮች ያሳደሩት ጉጉት መናፍስታዊ ሥራ ለመፈጸም ዳረጋቸው። ይህ ደግሞ እጅግ ርኩስ የሆነ የአምልኮ ሥርዓት ያካትት ነበር። ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክለፒዲያ ከነዓናውያን ከሰው የወጣውን መንፈስ የቀድሞ አባቶች አምልኮ ክፍል አድርገው ያከበሩበትን መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የቤተሰብ መቃብር ወይም የቀብር ጉብታዎች አካባቢ ሙታን ተካፋይ ይሆናሉ ተብሎ በሚታሰብበት፣ ስካርና የፆታ ግንኙነት (በዘመዳሞች መካከል የሚፈጸመውንም ሊያጠቃልል ይችላል) የታከለበት ድግስ . . . ይደረግ ነበር።” በእንዲህ ዓይነቱ ወራዳ መናፍስታዊ ተግባር መካፈላቸው እስራኤላውያንን ከአምላካቸው ከይሖዋ ይበልጥ እያራቃቸው ሄደ።—ዘዳግም 18:9-12
በእምነት ሳይሆን በማየት ለመመላለስ የመረጡ እስራኤላውያንን የማረካቸው ሌላው ነገር ጣዖትና ከጣዖት ጋር ዝምድና ያላቸው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ነበሩ። (2 ቆሮንቶስ 5:7) በዓይን በማይታየው የይሖዋ እጅ አስደናቂ ተአምራትን ከተመለከቱ በኋላ እንኳ ግብፅን ለቅቀው የወጡ በርካታ እስራኤላውያን እርሱን የሚያስታውሳቸው የሚታይ ነገር ፈልገዋል። (ዘጸአት 32:1-4) በተመሳሳይ መንገድ አንዳንድ ዝርያዎቻቸው በዓይን የሚታዩ እንደ በኣል ጣዖታት የመሳሰሉትን ለማምለክ መርጠዋል።—1 ነገሥት 12:25-30
ድል አድራጊው ማን ሆነ?
የእስራኤላውያንን ልብ ለመማረክ የተካሄደው ፍልሚያ እስራኤላውያን ወደ ሞዓብ ሜዳ ከደረሱበት ማለትም ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት አንስቶ ወደ ባቢሎን እስከተጋዙበት ጊዜ ድረስ ለበርካታ መቶ ዓመታት ተጧጡፎ ሲካሄድ ቆይቷል። ድሉ አንዴ ወደ አንዱ አንዴ ደግሞ ወደ ሌላው ይሄድ የነበረ ይመስላል። በአንዳንድ ወቅት አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለይሖዋ ታማኝ የነበሩ ቢሆንም እንኳ ደጋግመው ወደ በኣል ዘወር ብለዋል። ለዚህ ዋናው መንስዔ በዙሪያቸው ከነበሩ አረማውያን ሕዝቦች ጋር ቅርርብ መፍጠራቸው ነበር።
ከነዓናውያን በውጊያ ድል ከተደረጉ በኋላ ትግላቸውን ይበልጥ በረቀቀ ዘዴ ማካሄድ ጀመሩ። ከእስራኤላውያን ጋር ተቀራርበው በመኖር ድል አድራጊዎቻቸው የምድሪቱን አማልክት እንዲቀበሉ ገፋፏቸው። እንደ ጌዴዎንና ሳሙኤል የመሳሰሉ ቆራጥ መሳፍንት ይህን አዝማሚያ ተከላክለዋል። ሳሙኤል እንዲህ በማለት ሕዝቡን በጥብቅ አሳስቧል:- “እንግዶችን አማልክት . . . ከመካከላችሁ አርቁ፣ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፣ እርሱንም ብቻ አምልኩ።” እስራኤላውያን የሳሙኤልን ማሳሰቢያ በመታዘዝ ለተወሰነ ጊዜ “በአሊምንና አስታሮትን አራቁ፣ እግዚአብሔርንም ብቻ አመለኩ።”—1 ሳሙኤል 7:3, 4፤ መሳፍንት 6:25-27
ከሳኦልና ከዳዊት የንግሥና ዘመን በኋላ ሰሎሞን በስተ እርጅናው ለእንግዶች አማልክት መሥዋዕት ያቀርብ ጀመር። (1 ነገሥት 11:4-8) ሌሎች የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታትም ተመሳሳይ ነገር በመፈጸም ለበኣል ተሸነፉ። የሆነ ሆኖ እንደ ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ኢዮስያስ የመሳሰሉ ታማኝ ነቢያትና ነገሥታት የበኣል አምልኮን በመዋጋት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋል። (2 ዜና መዋዕል 34:1-5) ከዚህም በላይ በዚህ የእስራኤላውያን ታሪክ ዘመን በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ግለሰቦች ነበሩ። ሌላው ቀርቶ የበኣል አምልኮ ነግሦ በነበረበት በአክአብና በኤልዛቤል ዘመን እንኳ ‘ጉልበታቸውን ለበኣል ያላንበረከኩ’ ሰባት ሺህ ሰዎች ተገኝተዋል።—1 ነገሥት 19:18
በመጨረሻ አይሁዶች ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ የበኣል አምልኮን በሚመለከት የተጠቀሰ ነገር የለም። ዕዝራ 6:21 ላይ ከተጠቀሱት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሁሉም ‘የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ለመለየት’ ቆርጠው ነበር።
ከበኣል አምልኮ የሚገኝ የማስጠንቀቂያ ትምህርት
ምንም እንኳ የበኣል አምልኮ ከረጅም ጊዜ በፊት የጠፋ ቢሆንም ያ የከነዓናውያን አምልኮና ዛሬ ያለው ኅብረተሰብ ለፍትወተ ሥጋ የሚሰጠው የላቀ ግምት ተመሳሳይ ነው። ዛሬ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ለመፈጸም የሚያነሳሱ ነገሮች የምንተነፍሰውን አየር የበከሉት ያክል ነው። (ኤፌሶን 2:2) ጳውሎስ “የምንጋደለው ይህን ጨለማ ዓለም ከሚገዛው የማይታይ ኃይል እንዲሁም ከክፋት ማዕከል ከሚመነጩ መንፈሳዊ አካሎች ጋር ነው” ሲል አስጠንቅቋል።—ኤፌሶን 6:12 ፊሊፕስ
ይህ ከሰይጣን የሚመነጨው “የማይታይ ኃይል” ሰዎችን በመንፈሳዊ ባሪያ አድርጎ ለመያዝ የፆታ ብልግናን ያስፋፋል። (ዮሐንስ 8:34) ዛሬ ባለው ልቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ለፆታ ስሜት መንበርከክ እንደ ጥንቱ መራባትን በሚመለከት የሚፈጸም አምልኮታዊ ሥርዓት ባይሆንም የግል እርካታ የሚገኝበት መንገድ ወይም አንድ ሰው ያሻውን ማድረግ እንደሚችል ለማሳየት የሚፈጽመው ነገር ነው። ፕሮፓጋንዳውም የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል። በመዝናኛ፣ በሙዚቃና በማስታወቂያዎች አማካኝነት ስለ ወሲብ የሚቀርቡ ነገሮች የሰዎችን አእምሮ ይበክላሉ። የአምላክ ሕዝቦችም ከዚህ ጥቃት ነጻ አይደሉም። እንዲያውም ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገዱት አብዛኞቹ ሰዎች ለእንደዚህ ዓይነት ድርጊት የተሸነፉ ግለሰቦች ናቸው። አንድ ክርስቲያን ንጽሕናውን ጠብቆ መኖር የሚችለው እነዚህን ወደ ብልግና የሚያመሩ ነገሮች ዘወትር የሚጸየፍ ከሆነ ብቻ ነው።—ሮሜ 12:9
በተለይ ወጣት ምሥክሮች ማራኪ ሆነው የሚያገኟቸው አብዛኞቹ ነገሮች የፆታ ስሜት ለማነሳሳት ታቅደው የሚቀርቡ ስለሆነ ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በተጨማሪ ወጣቶች ሌሎች እኩዮቻቸው መጥፎ ነገሮችን እንዲፈጽሙ የሚያሳድሩባቸውን ተጽእኖ መቋቋም ያለባቸው መሆኑ ጉዳዩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። (ከምሳሌ 1:10-15 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ያህል በርከት ያለ ሰው በሚገኝባቸው ግብዣዎች ላይ ብዙ ወጣቶች ፈተና አጋጥሟቸዋል። ጥንት በበኣል አምልኮ እንደነበረው ሁሉ ሙዚቃው፣ ጭፈራውና ፆታዊ መስህቡ አንድ ላይ ተዳምረው አስተሳሰብን ያዛባሉ።—2 ጢሞቴዎስ 2:22
መዝሙራዊው “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል?” ሲል ከጠየቀ በኋላ “ቃልህን በመጠበቅ ነው” የሚል መልስ ሰጥቷል። (መዝሙር 119:9) የአምላክ ሕግ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ እንዳዘዛቸው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተዋል የጎደለው ቅርርብ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ያስጠነቅቀናል። (1 ቆሮንቶስ 15:32, 33) አንድ ወጣት ክርስቲያን ስሜት የሚማርክ ቢሆንም በሥነ ምግባር ጎጂ እንደሆነ የሚያውቀውን ነገር ሲርቅ መጎልመሱን ያሳያል። ታማኙ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር መፍቀድ የለብንም።—1 ነገሥት 18:21፤ ከማቴዎስ 7:13, 14 ጋር አወዳድር።
ሌላው ማስጠንቀቂያ ‘ቶሎ የሚከብበንን ኃጢአት’ ማለትም እምነት ማጣትን የሚመለከት ነው። (ዕብራውያን 12:1) አብዛኞቹ እስራኤላውያን በይሖዋ ያምኑ የነበረ ቢሆንም እርሻቸውን የሚጠብቅላቸውና የዕለት ጉርሳቸውን የሚሰጣቸው በኣል እንደሆነ ማሰብ የጀመሩ ይመስላል። ምናልባትም በኢየሩሳሌም የሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ በጣም ሩቅ እንደሆነና የእርሱን ሕጎች መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። የበኣል አምልኮ ብዙ ልፋት የማይጠይቅና አመቺ ስለነበር ሌላው ቀርቶ በቤታቸው ሰገነት ላይ ሆነው የዕጣን መሥዋዕት ማቅረብ ይችሉ ነበር። (ኤርምያስ 32:29) ምናልባት ወደ በኣል አምልኮ ሸርተት ብለው የገቡት በአንዳንድ ሃይማኖታዊ በዓሎች በመካፈል ብቻ ወይም በይሖዋ ስም ለበኣል መሥዋዕቶችን በማቅረብ ሊሆን ይችላል።
እምነታችንን ልናጣና ውሎ አድሮ ሕያው ከሆነው አምላክ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ዕብራውያን 3:12) በፊት ለጉባኤና ለትልልቅ ስብሰባዎች የነበረንን አድናቆት ቀስ በቀስ ልናጣ እንችላለን። ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ይሖዋ መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ ለማቅረብ በሚጠቀምበት ዝግጅት ላይ ትምክህት እንድናጣ ያደርገናል። (ማቴዎስ 24:45-47) በዚህ መንገድ ከተዳከምን “የሕይወትን ቃል” አጥብቀን ላንይዝ ወይም ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ አሊያም በሥነ ምግባር ብልግና ተጠምደን የተከፋፈለ ልብ ልንይዝ እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 2:16፤ ከመዝሙር 119:113 ጋር አወዳድር።
ጽኑ አቋማችንን አጥብቀን መያዝ
ዛሬ ልብ ለመማረክ ፍልሚያ እየተካሄደ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ለይሖዋ ታማኞች ሆነን እንቀጥል ይሆን ወይስ በዚህ ዓለም ልቅ አኗኗር አቅጣጫችንን እንስታለን? እስራኤላውያን አስነዋሪ በሆኑ የከነዓናውያን ተግባሮች እንደተሳቡ ሁሉ ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች አሳፋሪ የሆኑ ድርጊቶችን ለመፈጸም መማረካቸው ያሳዝናል።—ከምሳሌ 7:7, 21-23 ጋር አወዳድር።
ይህ ዓይነቱን መንፈሳዊ ሽንፈት ማስወገድ የምንችለው ልክ እንደ ሙሴ እኛም ‘የማይታየውን እንደምናየው አድርገን ከጸናን’ ነው። (ዕብራውያን 11:27) በእርግጥም ‘ለእምነት በብርቱ መጋደል’ አለብን። (ይሁዳ 3 የ1980 ትርጉም) በዚህ መንገድ ለአምላካችንና እርሱ ላወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኝ በመሆን የሐሰት አምልኮ ለዘላለም የሚጠፋበትን ጊዜ በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን። የይሖዋ አምልኮ የበኣል አምልኮን እንዳሸነፈ ሁሉ በቅርቡ ‘ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ እንደምትሞላ’ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 11:9
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በገዚር የሚገኙ ለበኣል አምልኮ ያገለግሉ የነበሩ ቅዱስ ዓምዶች ፍርስራሽ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Musèe du Louvre, Paris