አምላክ ማንኛውንም ዓይነት አምልኮ ይቀበላልን?
አምላክ ሰውን የፈጠረው መንፈሳዊ ፍላጎት ይኸውም የማምለክ ፍላጎት እንዲኖረው አድርጎ ነው። ይህ ፍላጎት ከጊዜ በኋላ የመጣ አይደለም። ሰው ሲፈጠር ጀምሮ ያለ ነገር ነው።
የሚያሳዝነው ግን ሰዎች ብዛት ያላቸው የተለያዩ የአምልኮ መንገዶች የቀየሱ ሲሆን በጥቅሉ ለመናገር ያህል እነዚህ አምልኮዎች ደስተኛና አንድነት ያለው ሰብዓዊ ቤተሰብ አላስገኙም። ከዚህ ይልቅ በሃይማኖት ስም ደም የሚያፋስሱ ጦርነቶች እየተደረጉ ነው። ይህም አንድ ሰው አምላክን የሚያመልክበት መንገድ ለውጥ ያመጣልን? የሚል አንገብጋቢ ጥያቄ ያስነሳል።
በጥንት ዘመን የነበረ አጠያያቂ አምልኮ
በመካከለኛው ምሥራቅ ይኖሩ የነበሩ የጥንት ሕዝቦች ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚረዳ ታሪክ ትተውልን አልፈዋል። ብዙዎቹ በኣል የተባለ አምላክ ያመልኩ ነበር። በተጨማሪም እንደ አሼራ የመሳሰሉትን የበኣል የሴት ጓደኞች የሆኑትን አማልክት አምልከዋል። የአሼራ አምልኮ የጾታ ምልክት ነው ተብሎ በሚታመን የአምልኮ ዐፀድ መጠቀምን ይጨምር ነበር። አርኪዮሎጂስቶች በዚህ አካባቢ ባደረጉት ቁፋሮ እርቃናቸውን የሆኑ ሴቶች የሚያሳዩ በርካታ ምስሎች አግኝተዋል። እነዚህ ምስሎች “የጾታ ብልቷ ጎላ ብሎ የሚታይና ጡቶችዋን ወደ ላይ የያዘች አንዲት ሴት አምላክ የሚያሳዩ” ሲሆኑ “ይህች ሴት አምላክ አሼራን የምታመለክት ሳትሆን አትቀርም” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን ይናገራል። ይህም ሌላው ቢቀር የበኣል አምልኮ በሥነ ምግባር በጣም የዘቀጠ እንደነበረ ያረጋግጥልናል።
ስለዚህ በበኣል አምልኮ ውስጥ ልቅ የጾታ ብልግና መኖሩ አያስደንቅም። (ዘኁልቁ 25:1-3 የ1980 ትርጉም) ከነዓናዊው ሴኬም ወጣቷን ልጃገረድ ዲናን አስገድዶ ደፍሯታል። ምንም እንኳ ይህን ድርጊት ቢፈጽምም በቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ክብር ያለው ሰው ሆኖ ይታይ ነበር። (ዘፍጥረት 34:1, 2, 19) ከቅርብ የሥጋ ዘመድ፣ ከተመሳሳይ ጾታና ከእንስሳ ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ የተለመደ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:6, 22-24, 27) በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት ለማመልከት የሚያገለግለው “ግብረ ሰዶም” የሚለው ቃል ጥንት በዚህ የዓለም ክፍል ትገኝ ከነበረች የአንድ ከተማ መጠሪያ የተወሰደ ነው። (ዘፍጥረት 19:4, 5, 28) በተጨማሪም በበኣል አምልኮ የተነሳ የብዙ ሰዎች ደም ፈስሷል። እንዲያውም የበኣል አምላኪዎች ልጆቻቸውን በሕይወት እያሉ የሚንቀለቀል እሳት ውስጥ በመጨመር ለአማልክቶቻቸው ይሠዉአቸው ነበር! (ኤርምያስ 19:5) እነዚህ ተግባሮች በሙሉ ከሃይማኖታዊ ትምህርቶች ጋር የተያያዙ ነበሩ። እንዴት?
ዶክተር ሜርል አንገር አርኪዮሎጂ ኤንድ ዘ ኦልድ ቴስታመንት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “በከነዓናውያን አፈ ታሪክ ውስጥ የሚገኘው የጭካኔ ድርጊት፣ ኃይለኛ የጾታ ስሜትና ልቅ አኗኗር በዚያ ዘመን በቅርብ ምሥራቅ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ይደረግ ከነበረው ሁሉ በጣም የከፋ ነበር። የከነዓናውያን አማልክት የነበራቸው አስገራሚ ባሕርይ ይኸውም ጋጠ ወጥ መሆናቸው አምላኪዎቻቸው ብልሹዎች እንዲሆኑ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ለአምልኮ ብሎ የጾታ ብልግና መፈጸምና ልጆችን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ከመሳሰሉት በጊዜው ከነበሩ ብልሹ የአምልኮ ሥርዓቶች አብዛኞቹን እንዲፈጽሙ ይጠይቁባቸው ነበር።”
አምላክ የከነዓናውያንን አምልኮ ተቀብሎት ነበርን? አልተቀበለውም። እስራኤላውያን እርሱን ንጹሕ በሆነ መንገድ ማምለክ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። ከላይ የተጠቀሱትን የአምልኮ ተግባራት በተመለከተ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “በእነዚህ ሁሉ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ ረክሰዋልና በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አትርከሱ። ምድሪቱም ረከሰች፤ ስለዚህ ኃጢአትዋን በእርስዋ ላይ እመልሳለሁ፣ ምድሪቱም የሚኖሩባትን ሰዎች ትተፋለች።”—ዘሌዋውያን 18:24, 25
ንጹሑ አምልኮ ተበከለ
አብዛኞቹ እስራኤላውያን አምላክ ለንጹሕ አምልኮ ያለውን አመለካከት አልተቀበሉም። ከዚህ ይልቅ የበኣል አምልኮ ወደ አገራቸው እንዲገባ ፈቀዱ። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋን አምልኮ ከበኣል አምልኮ ጋር ለመቀላቀል የሞኝነት ሙከራ አደረጉ። አምላክ ይህን ድብልቅ አምልኮ ተቀበለውን? በንጉሥ ምናሴ የግዛት ዘመን የተፈጸመውን ነገር ተመልከት። ንጉሥ ምናሴ ለበኣል መሠዊያ ሠርቷል፣ ወንድ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ አቃጥሏል እንዲሁም የአስማት ድርጊት ፈጽሟል። ‘እግዚአብሔር፦ “ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤት የማምለኪያ ዐፀዶችን [በዕብራይስጥ አሼራ] ሠርቷል።’—2 ነገሥት 21:3-7
የምናሴ ተገዢዎች የንጉሣቸውን ምሳሌ ተከተሉ። እንዲያውም “እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።” (2 ነገሥት 21:9) ምናሴ የአምላክ ነቢያት የሚሰጡትን ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት ኢየሩሳሌም በንጹሐን ደም እስክትጥለቀለቅ ድረስ ብዙ ሰዎች ገደለ። ምናሴ ከጊዜ በኋላ ከዚህ ሥራው ቢገታም በቦታው የተተካው ልጁ ንጉሥ አሞን የበኣል አምልኮ ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል።—2 ነገሥት 21:16, 19, 20 የ1980 ትርጉም
ከጊዜ በኋላ ዝሙት አዳሪ ወንዶች በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ነገር መፈጸም ጀመሩ። አምላክ ይህንን ከበኣል አምልኮ የተቀዳ ድርጊት እንዴት ተመለከተው? በሙሴ አማካኝነት እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን [ከተለምዶ ውጪ የጾታ ግንኙነት የሚያደርግ] ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።”—ዘዳግም 23:17, 18 አዓት የግርጌ ማስታወሻ።
የምናሴ የልጅ ልጅ የሆነው ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን በብልግና ከተሞላው የበኣል አምልኮ አጸዳ። (2 ነገሥት 23:6, 7) ሆኖም ሁኔታው በዚህ መልኩ ብዙም አልቀጠለም። ኢዮስያስ እንደሞተ የጣዖት አምልኮ እንደገና ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ገባ። (ሕዝቅኤል 8:3, 5-17) በዚህ የተነሳ ይሖዋ የባቢሎኑ ንጉሥ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፋ አደረገ። ይህ አሳዛኝ የታሪክ እውነታ በዚያን ጊዜ አምላክ የማይቀበላቸው የአምልኮ ዓይነቶች እንደነበሩ ያረጋግጣል። ስለ ጊዜያችንስ ምን ለማለት ይቻላል?