የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w14 9/15 ገጽ 23-27
  • የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ
  • በሰው ልጆች ላይ ሞት የመጣው እንዴት ነው?
  • ከአዳም የወረስነው ኃጢአትና ሞት ይደመሰሳል
  • የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
  • ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
w14 9/15 ገጽ 23-27
አዳምና ሔዋን ልጃቸው አቤል በመሞቱ ሲያዝኑ
አዳምና ሔዋን ልጃቸው አቤል በመሞቱ ሲያዝኑ

የመጨረሻው ጠላት ሞት ይደመሰሳል

“የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።”—1 ቆሮ. 15:26

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ይሖዋ ለአዳም ፍቅር የተንጸባረቀበት ሆኖም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባ ምን ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር?

  • በሰው ልጆች ላይ ሞት የመጣው እንዴት ነው?

  • ‘የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት የሚደመሰሰው’ መቼ ነው?

1, 2. አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ ምን ዓይነት ሕይወት ነበራቸው? የትኞቹ ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ ጠላት የሚባል ነገር አልነበራቸውም። ፍጹም ሆነው በገነት ውስጥ ይኖሩ ነበር። የፈጣሪያቸው ልጆች በመሆናቸው ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ነበራቸው። (ዘፍ. 2:7-9፤ ሉቃስ 3:38) አምላክ የሰጣቸው ተልእኮ ወደፊት ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል የሚጠቁም ነበር። (ዘፍጥረት 1:28⁠ን አንብብ።) “ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” የሚለውን ትእዛዝ ለመፈጸም ያን ያህል ብዙ ጊዜ አይወስድባቸውም። ይሁንና አዳምና ሔዋን “በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” የሚለውን ትእዛዝ ሁልጊዜ ለመፈጸም ለዘላለም መኖር ያስፈልጋቸዋል፤ አዳም ከሞተ ደግሞ ይህንን ኃላፊነቱን መፈጸም አይችልም።

2 ታዲያ አሁን የሰው ልጆች ያሉበት ሁኔታ አምላክ ካሰበው በጣም የተለየ የሆነው ለምንድን ነው? የሰው ልጆች በሕይወታቸው ተደስተው እንዳይኖሩ የሚያደርጓቸው በርካታ ጠላቶች ያሏቸው ለምንድን ነው? ከሁሉ የከፋ ጠላት የሆነው ሞት የመጣባቸውስ እንዴት ነው? አምላክ እነዚህን ጠላቶች ለመደምሰስ ምን ያደርጋል? የእነዚህም ሆነ ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጥያቄዎች መልስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይገኛል። እስቲ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እንመርምር።

ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ

3, 4. (ሀ) አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ምን ትእዛዝ ሰጣቸው? (ለ) ይህንን መመሪያ መታዘዛቸው ምን ያህል አስፈላጊ ነበር?

3 አዳምና ሔዋን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ቢዘረጋላቸውም የማይሞት ሕይወት አልነበራቸውም። በሕይወት ለመኖር መተንፈስ፣ መብላትና መጠጣት እንዲሁም መተኛት ነበረባቸው። ከሁሉ በላይ ግን በሕይወት መኖራቸው የተመካው ሕይወት ከሰጣቸው አካል ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ ነበር። (ዘዳ. 8:3) ሕይወትን ማጣጣማቸውን እንዲቀጥሉ የአምላክን መመሪያ የግድ መከተል ነበረባቸው። ይሖዋ፣ ሔዋን ከመፈጠሯ በፊት እንኳ ይህንን ለአዳም ግልጽ አድርጎለታል። እንዴት? “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።’”—ዘፍ. 2:16, 17

4 ‘መልካምና ክፉን የሚያሳውቀው ዛፍ’ የሚያመለክተው አምላክ፣ መልካም ወይም ክፉ የሚባለው ምን እንደሆነ ለመወሰን ያለውን መብት ነው። እርግጥ ነው፣ አዳም ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባለው ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ምክንያቱም በአምላክ መልክ የተፈጠረ ከመሆኑም ሌላ ሕሊና አለው። ዛፉ፣ አዳምና ሔዋን ምንጊዜም የይሖዋን መመሪያ ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቁማል። ከዛፉ መብላታቸው ግን ራሳቸውን መምራት እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ነው፤ ይህ ድርጊታቸው በራሳቸውም ሆነ በዘሮቻቸው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ የሚያስከትል ነው። አምላክ የሰጣቸውን ትእዛዝ መጣስ የሚያስከትለው ቅጣት የጉዳዩን ክብደት የሚጠቁም ነው።

በሰው ልጆች ላይ ሞት የመጣው እንዴት ነው?

5. አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

5 አዳም፣ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ሔዋን ከተፈጠረች በኋላ ነግሯታል። እሷም ትእዛዙን በደንብ ታውቀው ነበር፤ እንዲያውም ቃል በቃል ትእዛዙን መድገም ችላለች። (ዘፍ. 3:1-3) የአምላክን ትእዛዝ ደግማ የተናገረችው ተንኰለኛ በተባለው በእባብ ተመስሎ ላነጋገራት አካል ነበር። ከእባቡ በስተጀርባ የነበረው የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው፤ ዲያብሎስ በራሱ የመመራትና ሥልጣን የማግኘት ምኞት ነበረው። (ከያዕቆብ 1:14, 15 ጋር አወዳድር።) ይህን የክፋት ምኞቱን ለማሳካት ሲል አምላክን ውሸታም እንደሆነ አድርጎ ከሰሰው። ሔዋን ራሷን ለመምራት የምታደርገው ጥረት ሞት እንደማያስከትልባት እንዲያውም እንደ አምላክ ለመሆን እንደሚያስችላት ገለጸ። (ዘፍ. 3:4, 5) ሔዋንም እሱ የነገራትን ስላመነች ፍሬውን በመብላት በራሷ መመራት እንደምትፈልግ አሳየች፤ አዳምንም በድርጊቷ እንዲተባበራት አግባባችው። (ዘፍ. 3:6, 17) ይሁንና ዲያብሎስ የተናገረው ነገር ውሸት ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 2:14⁠ን አንብብ።) ያም ሆኖ አዳም ‘የሚስቱን ቃል ሰማ።’ እባቡ ሔዋንን የቀረባት ወዳጅ መስሎ ነበር፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ለሔዋን የሰጣት ሐሳብ የሚያስከትለውን ከባድ መዘዝ አሳምሮ የሚያውቅ ጨካኝ ጠላት ነው።

6, 7. ይሖዋ በኃጢአተኞቹ ላይ ምን ዓይነት ፍርድ አስተላለፈ?

6 አዳምና ሔዋን ራስ ወዳድ በመሆናቸው፣ ሕይወትንና ያሏቸውን ሌሎች ነገሮች ሁሉ በሰጣቸው ፈጣሪያቸው ላይ ዓመፁ። ይሖዋ ያደረጉትን ሁሉ ተመልክቶ ነበር። (1 ዜና 28:9፤ ምሳሌ 15:3⁠ን አንብብ።) በእሱ ላይ ያመፁት ሦስቱ አካላት ለእሱ ያላቸውን አመለካከት ለማሳየት እንዲችሉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ፣ አባታቸው እንደመሆኑ መጠን በድርጊታቸው በጣም እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። (ከዘፍጥረት 6:6 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ትእዛዙን መጣስ ስለሚያስከትለው መዘዝ የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ በማድረግ እንደ ዳኛ ሆኖ ፍርድ መስጠት ነበረበት።

7 አምላክ ለአዳም “[መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ] በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር። አዳም ይህ “ቀን” የ24 ሰዓት ርዝመት እንዳለው አስቦ ይሆናል። በመሆኑም የአምላክን ትእዛዝ ከጣሰ በኋላ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ይሖዋ እርምጃ እንደሚወስድበት ጠብቆ ሊሆን ይችላል። “ቀኑ መሸትሸት ሲል” ይሖዋ አዳምና ሔዋንን አነጋገራቸው። (ዘፍ. 3:8) በዚህ ጊዜ ችሎት የተሰየመ ያህል ነበር፤ አምላክ ጻድቅ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን መጀመሪያ አዳምና ሔዋን የሰጡትን ምላሽ አዳመጠ። (ዘፍ. 3:9-13) ከዚያም በኃጢአተኞቹ ላይ ፍርድ አስተላለፈ። (ዘፍ. 3:14-19) ይሖዋ፣ አዳምንና ሔዋንን ወዲያውኑ ቢያጠፋቸው ኖሮ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ አይፈጸምም ነበር። (ኢሳ. 55:11) በሞት እንደሚቀጡ የነገራቸው ሲሆን ኃጢአት ወዲያውኑ በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀመረ፤ ያም ቢሆን ይሖዋ ከሚያደርጋቸው ሌሎች ዝግጅቶች የሚጠቀሙ ልጆች እንዲወልዱ ፈቀደላቸው። ከአምላክ አመለካከት አንጻር አዳምና ሔዋን የሞቱት ኃጢአት በሠሩበት ቀን ነው፤ ደግሞም በእሱ ፊት አንድ “ቀን” እንደ 1,000 ዓመት ስለሆነ በዚያው ዕለት ሞተዋል ማለት ይቻላል።—2 ጴጥ. 3:8

8, 9. አዳም የሠራው ኃጢአት በዘሮቹ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 አዳምና ሔዋን ያደረጉት ነገር በልጆቻቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን? በሚገባ። ሮም 5:12 “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” ይላል። መጀመሪያ የሞተው፣ ታማኝ የነበረው አቤል ነው። (ዘፍ. 4:8) ከዚያም ሌሎቹ የአዳም ዘሮች ማርጀትና መሞት ጀመሩ። ይሁንና የአዳም ዘሮች የወረሱት ሞትን ብቻ ነው? ወይስ ኃጢአትንም ጭምር? ሐዋርያው ጳውሎስ መልሱን ሲሰጥ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ” ገልጿል። (ሮም 5:19) ከአዳም የተወረሱት ኃጢአትና ሞት፣ ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ሊያመልጧቸው የማይችሉ ምሕረት የለሽ ጠላቶቻቸው ሆኑ። ኃጢአትና ሞት ወደ አዳም ልጆችም ሆነ ወደ ዘሮቻቸው የተላለፉት እንዴት እንደሆነ በትክክል መናገር ባንችልም ይህ መሆኑን ግን እርግጠኞች ነን።

9 መጽሐፍ ቅዱስ፣ የወረስነውን ኃጢአትና ሞት ‘በሕዝብ ሁሉ ላይ የተጣለው መጋረጃ፣ በመንግሥታት ላይ የተዘረጋው መሸፈኛ’ ብሎ መግለጹ ተስማሚ ነው። (ኢሳ. 25:7) ይህ ፍርድ፣ ትንፋሽ እንደሚያሳጣ መሸፈኛ ወይም መጋረጃ ሕዝቦችን ተብትቦ ይዟል። በመሆኑም ‘ሁሉም በአዳም ምክንያት ይሞታሉ።’ (1 ቆሮ. 15:22) አሁን የሚነሳው ጥያቄ፣ ጳውሎስ ካነሳው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሐዋርያው “እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?” ብሎ ነበር። ታዲያ ሊታደገን የሚችል ይኖር ይሆን?a—ሮም 7:24

ከአዳም የወረስነው ኃጢአትና ሞት ይደመሰሳል

10. (ሀ) ይሖዋ፣ በአዳም ምክንያት የመጣውን ኃጢአት እንደሚደመስስ የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) እነዚህ ጥቅሶች ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ ምን ያስተምሩናል?

10 ይሖዋ፣ ጳውሎስን ሊታደገው ይችላል። ኢሳይያስ ስለ ‘መጋረጃው’ ከተናገረ በኋላ “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” ሲል ጽፏል። (ኢሳ. 25:8) ለልጆቹ ሥቃይ መንስኤ የሆነውን ነገር በማስወገድ እንባቸውን እንደሚያብስ አባት ሁሉ ይሖዋም በአዳም ምክንያት የመጣውን ሞት ለማስወገድ ይጓጓል! ይህንንም ሲያደርግ የሚተባበረው አካል አለ። 1 ቆሮንቶስ 15:22 “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ” ይላል። በተመሳሳይም ጳውሎስ “ማን ይታደገኛል?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” ብሏል። (ሮም 7:25) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የሰው ልጆችን እንዲፈጥር ያነሳሳው ፍቅር፣ አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላም አልቀዘቀዘም። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ሲፈጥር በሥራው የተባበረው ኢየሱስም ለሰው ልጆች ያለው ልዩ ፍቅር አልቀነሰም። (ምሳሌ 8:30, 31) ይሁንና የሰው ልጆችን መታደግ የሚቻለው እንዴት ነው?

11. ይሖዋ የሰው ልጆችን ለመርዳት ምን ዝግጅት አደረገ?

11 የሰው ልጆች ፍጽምና የጎደላቸው የሆኑት ብሎም የሚሞቱት አዳም በፈጸመው ኃጢአትና ይሖዋ በሰጠው ጻድቅ ፍርድ የተነሳ ነው። (ሮም 5:12, 16) መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ በደል ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲኮነኑ [አደረገ]” ይላል። (ሮም 5:18) ታዲያ ይሖዋ፣ የራሱን መሥፈርቶች ሳይሽር ይህንን ኩነኔ ማስወገድ የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ‘የሰው ልጅ የመጣው በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ነው’ በማለት መልሱን ተናግሯል። (ማቴ. 20:28) መንፈሳዊ ፍጥረት የሆነው የይሖዋ የበኩር ልጅ፣ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ በመወለድ ቤዛ እንደሚሆን በግልጽ ተናግሯል። ይህ ቤዛ ፍትሕ እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት ነው?—1 ጢሞ. 2:5, 6

12. ፍትሕ እንዲፈጸም ያደረገው ተመጣጣኝ ቤዛ ምንድን ነው?

12 ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት የተሰጠው ዓይነት ሕይወት ነበረው። የይሖዋ ዓላማ ፍጹም በሆኑ የአዳም ዘሮች ምድርን መሙላት ነበር። ኢየሱስ ለአባቱና ለአዳም ዘሮች ጥልቅ ፍቅር ስላለው ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አደረገ። አዎን፣ ኢየሱስ አዳም ካጣው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ የሆነውን ሕይወቱን ሰጠ። ከዚያም ይሖዋ ለልጁ መንፈሳዊ ሕይወት ሰጠው። (1 ጴጥ. 3:18) ይሖዋ፣ ፍጹም ሰው የሆነውን የኢየሱስን መሥዋዕት ቤዛ ወይም ካሳ አድርጎ በመቀበል ከፍትሕ መሥፈርቱ ጋር በሚስማማ መንገድ የአዳምን ቤተሰብ የዋጃቸው ሲሆን አዳም ያሳጣቸውን ሕይወት እንዲያገኙ አድርጓል። ኢየሱስ የአዳምን ቦታ የወሰደ ያህል ነው። ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “‘የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ’ ተብሎ ተጽፏል። የኋለኛው አዳም ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።”—1 ቆሮ. 15:45

አቤል ልክ ከሞት እንደተነሳ

በሞት ያንቀላፋው የመጀመሪያው ሰው ማለትም አቤል ከኢየሱስ ቤዛ ተጠቃሚ ይሆናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

አቤል ልክ ከሞት እንደተነሳ

በሞት ያንቀላፋው የመጀመሪያው ሰው ማለትም አቤል ከኢየሱስ ቤዛ ተጠቃሚ ይሆናል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. “የኋለኛው አዳም” የሞቱ ሰዎችን የሚጠቅም ምን እርምጃ ይወስዳል?

13 “የኋለኛው አዳም” ለሰው ዘር በሙሉ “ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ” የሚሆንበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ሕይወት ከሚሰጣቸው መካከል በሞት ያንቀላፉ በርካታ የአዳም ዘሮች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው በምድር ላይ ይኖራሉ።—ዮሐ. 5:28, 29

14. አዳም ለዘሮቹ ያወረሰውን አለፍጽምና ለማስወገድ ይሖዋ ምን ዝግጅት አድርጓል?

14 የሰው ዘር ከወረሰው አለፍጽምና ጋር የሚያደርገውን ትግል ማሸነፍ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ ‘የኋለኛውን አዳም’ እና ከሰው ዘር መካከል የተመረጡ ተባባሪ ገዢዎችን ያቀፈ መንግሥት አቋቁሟል። (ራእይ 5:9, 10⁠ን አንብብ።) ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት ሰዎች አለፍጽምና ምን እንደሆነ ያውቃሉ። ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ አንድ ሺህ ዓመት በሚዘልቀው የግዛት ዘመናቸው ምድር ላይ ያሉ ሰዎችን ከአለፍጽምና ነፃ እንዲሆኑ ይረዷቸዋል፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ከአለፍጽምና መላቀቅ አይችሉም።—ራእይ 20:6

15, 16. (ሀ) “የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት” የሚለው አገላለጽ ምንን ያመለክታል? ይህ ጠላት የሚደመሰሰውስ መቼ ነው? (ለ) 1 ቆሮንቶስ 15:28 እንደሚገልጸው ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ምን ያደርጋል?

15 የመንግሥቱ የሺህ ዓመት ግዛት ሲያበቃ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች፣ በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ከመጡት ጠላቶች በሙሉ ነፃ ይወጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ። ሆኖም እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት [ተባባሪ ገዢዎቹ] ሕያዋን ይሆናሉ። ከዚያም መንግሥትን ሁሉ እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ በሚያስረክብበት ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና። የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮ. 15:22-26) አዎን፣ ከአዳም የተወረሰው ሞት በመጨረሻ ይወገዳል። መላውን የሰው ዘር የሸፈነው “መጋረጃ” ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋል።—ኢሳ. 25:7, 8

16 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር መሆን ይችል ዘንድ ነው።” (1 ቆሮ. 15:28) በዚህ ጊዜ የወልድ አገዛዝ የታሰበለትን ዓላማ ያሳካል። ከዚያም ወልድ ሥልጣኑን በደስታ ለይሖዋ ይመልሳል፤ እንዲሁም ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ቤተሰብ ለይሖዋ ያስረክባል።

17. ሰይጣን ምን ይጠብቀዋል?

17 በሰው ልጆች ላይ ለደረሰው መከራ ሁሉ ዋነኛ መንስኤ የሆነው ሰይጣንስ ምን ይጠብቀዋል? ራእይ 20:7-15 መልሱን ይሰጠናል። ሰይጣን ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆችን በሙሉ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈትን ይፈቀድለታል። ዲያብሎስና እሱን የሚከተሉ ሁሉ ‘በሁለተኛው ሞት’ ለዘላለም ይጠፋሉ። (ራእይ 21:8) ‘በሁለተኛው ሞት’ የጠፉ ሁሉ መቼም ቢሆን ወደ ሕልውና ስለማይመለሱ ይህ ሞት ፈጽሞ አይደመሰስም። ይሁንና ፈጣሪያቸውን ለሚወድዱና ለሚያገለግሉ ሰዎች “ሁለተኛው ሞት” ጠላት አይሆንባቸውም።

18. አምላክ ለአዳም የሰጠው ተልእኮ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

18 በዚህ ጊዜ፣ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ በይሖዋ ፊት የሚኖራቸው አቋም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችላቸው ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ አንድም ጠላት አይኖራቸውም። ለአዳም ተሰጥቶት የነበረው ተልእኮ እሱ በሌለበት ፍጻሜውን ያገኛል። ምድር በእሱ ዘሮች ትሞላለች፤ እነሱም ሕያዋን ፍጥረታትን በመግዛትና በመንከባከብ ይደሰታሉ። እንግዲያው ይሖዋ የመጨረሻው ጠላት የሆነውን ሞት ለመደምሰስ ላደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ያለን አድናቆት ምንጊዜም እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ!

a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ የሳይንስ ሊቃውንት የእርጅናን እና የሞትን መንስኤ ለማወቅ ስላደረጉት ጥረት ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “የሳይንስ ሊቃውንት፣ በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ላይ የሞትን ፍርድ ያስተላለፈው ፈጣሪ ራሱ እንደሆነና ይህን ፍርድ ተግባራዊ ያደረገው የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ ሊረዱት በማይችሉት መንገድ እንደሆነ ይዘነጋሉ።”—ጥራዝ 2 ገጽ 247

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ