ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ምሩ
1 ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ በተመለከተ አንዲት ሴት እንዲህ በማለት በደስታ ተናገረች:- “ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥሎ ካነበብኳቸው መጻሕፍት ሁሉ በጣም ትክክለኛ የሆነ፣ መንፈስን የሚቀሰቅስና ለሥራ የሚገፋፋ ሆኖ ያገኘሁት ጽሑፍ ይህ ነው!” ይህ መጽሐፍ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባቸውና በተለይም ይሖዋን ለማወደስ በሚደረገው ሥራ በንቃት የሚሳተፉ እንዲሆኑ ለመርዳት እስከ ዛሬ ከታተሙት ጽሑፎች ሁሉ የሚበልጥ እንደሆነ ሁላችንም እንስማማለን።
2 በ1982 ይህ ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ በምሥራቅ አፍሪካ የነበሩ 6,414 አስፋፊዎች 7,228 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመሩ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን 18,603 የሚሆኑት አስፋፊዎች 29,750 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። የዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ እስከ ዛሬ ድረስ በ115 ቋንቋዎች 62 ሚልዮን በሚሆን ቅጂ ታትሟል። ይህ መጽሐፍ ዓለም አቀፉን ሥራችንን እንዴት ባለ አስደናቂ ሁኔታ ነክቶታል!
3 ግቦችን አውጡ፦ ይህ አስደናቂ ዕድገት የተገኘው በይሖዋ በረከትና ሕዝቦቹ ሕይወት አድን በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አማካኝነት ቅን የሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ባላቸው ዝግጁነት ነው። (ሮሜ 10:13–15፤ 1 ጢሞ. 2:4) ጊዜው አጣዳፊ መሆኑንና የአምላክን መንግሥት በማወጅ በኩል ትጋት እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን።
4 ድርጅቱ ወደፊት እየተንቀሳቀሰ ነው። እኛስ በግለሰብ ደረጃ እንዴት ነን? ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተካፋይ ለመሆን ቆርጠናልን? ይህንንም ለመፈጸም በግል ግቦችን ማውጣት ይኖርብናል። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ተከታትለን ለመርዳት ይበልጥ ትጉዎች መሆን እንችላለንን? በየካቲት ወር አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ለምን አታወጡም?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት የሚችለው ማን ነው?፦ የተለያየ ችሎታ ያላቸው ብዙ አስፋፊዎች ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት የሚገኘውን ደስታ አግኝተዋል። መጽሐፉ ቀለል ያለ የአቀራረብ ዘዴ ስላለው ጥናት መምራትን ቀላል ያደርጋል። ይህም አዲስ አስፋፊዎች እንኳን በዚህ አስፈላጊ ሥራ እንዲካፈሉ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ብዙዎቻችን መጽሐፉን በግል ስላጠናነው ከይዘቱ ጋር በደንብ ተዋውቀናል። ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጠንቶ የማያውቅ አንድ አስፋፊ በአድናቆት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሦስት ጥናቶች አሉኝ፤ አራተኛው ደግሞ ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትን ይህን ያህል ቀላል ስላደረጋችሁልኝ ምሥጋናዬ በቃል መግለጽ ከምችለው በላይ ነው።”
6 ወጣቶችም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናቱ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ነው። አንድ ወጣት ወንድም ይህን መጽሐፍ በትምህርት ቤት ጠረጴዛው ላይ ትቶት ሄደ። ይህም ጥሩ ለሆኑ ውይይቶችና በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማግኘት መንገድ ጠርጎለታል። አንዳንድ ወጣቶች ከበር ወደ በር በሚደረገው አገልግሎት ላይ የሚያገኟቸውን ወላጆች ልጆቻችሁን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናላችሁ ብለው በቀጥታ ፈቃድ በመጠየቅ ተጠቅመዋል። ልጆቻችን ይሖዋ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ስለሰጠን ተስፋ ለመናገር ገና ልጆች ናቸው የሚባሉ በፍጹም አይደሉም።
7 ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን አንድ ሰው በአገልግሎቱ ከሚያገኛቸው ታላላቅ ደስታዎች አንዱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት የሚገኘው ደስታ ነው። ስለዚህ እያንዳንዳችን የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት እንጸልይ፤ ተስፋችንን በሕዝብ ፊት ለመግለጽ የሚያስችለንን እያንዳንዱን አጋጣሚ እንጠቀምበት። ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ሌሎችም አምላካችንን ይሖዋን በማወደሱ ተግባር እንዴት ሊካፈሉ እንደሚችሉ እንዲማሩ ለመርዳት ተጠቀሙበት። — መዝ. 148:12, 13