ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪዎች
1 አንድ ብቃት ያለው ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪ ሆኖ ማገልገሉ ልዩ መብት ነው። በእርሱ ቡድን ውስጥ ያሉት የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ነገር መከታተል ከባድ ኃላፊነት ነው። ኃላፊነቶቹ በሦስት ይከፈላሉ።
2 በጥሩ ችሎታ ማስተማር፦ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪው በየሳምንቱ ቡድኑን እውቀት ለማስጨበጥ ጥልቀት ያለው ዝግጅት ማድረግ ይጠይቅበታል። ወንድሞች እየተጠና ላለው ጽሑፍ ያላቸውን አድናቆት ለማሳደግ ይጥራል። በጥናቱ ወቅት እርሱ ራሱ ብዙ ሐሳብ ከመስጠት ይልቅ አስፈላጊ ሲሆን የትምህርቱ ዐበይት ነጥቦች እንዲተኮርባቸው ለማድረግ ተስማሚ ጥያቄዎች ይጠይቃል። ጥናቱን ማራኪና ትምህርት ሰጪ ማድረግ እንዲሁም ሁሉንም በውይይቱ ማሳተፍ ይኖርበታል። ዓላማው ወንድሞችን በመንፈሳዊ መገንባት፣ የጥናቱን ተግባራዊ ጥቅም ማጉላትና ትምህርቱ አእምሮንም ሆነ ልብን እንዲነካ ማድረግ ነው።—1 ተሰ. 2:13
3 ጠቃሚ እረኝነት ማድረግ፦ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪው “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከአውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ነው። (ኢሳ. 32:2) በቡድኑ ውስጥ ላሉት በሙሉ ያስባል፤ እንዲሁም ከመካከላቸው አንዱ ተስፋ መቁረጥ ሲሰማው መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘቱን ይከታተላል።—ሕዝ. 34:15, 16፤ 1 ተሰ. 2:7, 8
4 በወንጌላዊነቱ ሥራ በቅንዓት መሳተፍ፦ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪው በእርሱ ቡድን ውስጥ ያሉት በሙሉ በመስክ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ያደርጉ ዘንድ ተግባራዊ ዝግጅቶች ለማድረግ ንቁ ነው። በአገልግሎቱ የሚያሳየው አዘውታሪነት፣ ቅንዓትና ግለት በተቀሩት የቡድኑ አባላት ላይ እንደሚንጸባረቅ በማሰብ በወንጌላዊነቱ ሥራ ቀዳሚ ሆኖ ይገኛል። (ቆላ. 4:17፤ 2 ተሰ. 3:9) በየጊዜው ከእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ጋር በአገልግሎት ለመካፈል ይጥራል። በአገልግሎት ያለንን የመስበክና የማስተማር ችሎታ ለማሻሻል ከፈለግን የመጽሐፍ ጥናት መሪው ግባችን ላይ እንድንደርስ ሊረዳን ይችላል።—1 ጢሞ. 4:16፤ 2 ጢሞ. 4:5
5 መንፈሳዊ እርዳታና ፍቅራዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑትን እነዚህን የወንድ ስጦታዎች በማግኘታችን በእርግጥ ተባርከናል። (1 ተሰ. 5:14) በመጽሐፍ ጥናት ቋሚ ተሳትፎ በማድረግና የወንጌላዊነቱን ሥራ ከልብ በመደገፍ ይሖዋ ላቋቋመው ለዚህ ግሩም ዝግጅት ያለንን አድናቆት እናሳይ።—ዕብ. 10:25