“ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው.”
1 ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ሰዎችን ማስተማር ያስፈልጋል። አንድ ግለሰብ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ኢየሱስ ‘ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቅ’ እንድናስተምረው ያስፈልጋል። (ማቴ. 28:19, 20) ይህንን ለመፈጸም ደግሞ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የቤት መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማቋቋም ነው።
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማግኘት በኩል ችግር ካለብህ ተስፋ አትቁረጥ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለማግኘት እንዲሳካልህ እውነትን ለሌሎች ለመንገር መቁረጥንና ይህንንም ለማድረግ ከልብ መፈለግን ይጠይቃል። — ገላ. 6:9
3 ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎትን ማዳበር፦ በመጀመሪያ ላይ ያደረግኸው ውይይት የተወሰነ ፍላጎት ብቻ ያነሳሳ ይሆናል። በሁኔታዎቹ ላይ በመመካት ለቤቱ ባለቤት ትራክት፣ ብሮሹር ወይም መጽሔቶች መተው ይቻላል። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ከእነዚህ በአንዱ ለመጠቀም ትችል ይሆናል። የቤቱ ባለቤት ለመልእክቱ ተጨማሪ ፍላጎት ካሳየ በሚቀጥለው ጉብኝት ተገቢ የሆነ ሌላ ጽሑፍ ሊቀርብለት ይችላል።
4 ዝግጅት ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ቁልፍ የሆነ ነገር ነው። ለቤቱ ባለቤት በተውክለት ትራክት፣ ብሮሹር ወይም መጽሔት ላይ የተጠቀሰ በተመላልሶ መጠየቅህ ወቅት ልትጠቀምበት ያቀድከውን አንድ ጥቅስ ቀደም ብለህ ለምን አትመርጥም? በዚያ መንገድ በውይይትህ ውስጥ በጽሑፉ ላይ ያሉ ሐሳቦችን ለማያያዝ ትችላለህ። በቀጥታ ከጽሑፉ ላይ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን ማንበብም ትችላለህ።
5 እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል፦
◼ “በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ስላለ ስለ አንድ አስደናቂ ትንቢት አንዳንድ ሐሳቦችን ለሰዎች እያካፈልን ነው።” ማቴዎስ 24:3ን አንብብ፤ ከዚያም “እነሆ!” (Look! ) በተባለው ብሮሹር ገጽ 24 ላይ ካለው ስዕልና ሐሳብ ጋር አያይዘህ ግለጽ። ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን? የተባለውን ትራክት በምታስተዋውቅበት ጊዜም በተመሳሳይ አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ።
6 አንድ ጊዜ እውነተኛ የሆነ ፍላጎት እንዳለ ከተረዳን ወዲያውኑ ተከታትለን መርዳት ይገባናል። ያለፈው ውይይታችሁ በቤቱ ባለቤት አእምሮ ውስጥ ገና ትኩስ እያለ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመመለስ ሞክር። እቤቱ በሄድክ ቁጥር ከተውክለት ጽሑፍ ውስጥ ጥቂት አንቀጾችን አወያየው። ከዚያም ተገቢ በሆነ ጊዜ ላይ በዚሁ መንገድ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ልታስተዋውቀው ትችላለህ።
7 በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ በተነበየው ታላቅ የመከር ሥራ ውስጥ ገና ብዙ ሥራ አለ። (ማቴ. 9:37, 38) ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ማስተማራችንን ስንቀጥል ‘እስከዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር እንደሚሆን’ በመግለጽ ኢየሱስ የሰጠን የማጠናከሪያ ዋስትና አለን።