በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን ስሜት ቀስቃሽ መልእክት አውጅ
1 የራእይ መደምደሚያ የተባለው መጽሐፍ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን ስሜት ቀስቃሽ መልእክት እንድንረዳ አስችሎናል። በአገልግሎትህ ይህንን መጽሐፍ በማበርከት ሌሎች መልእክቱ እነርሱን እንዴት እንደሚነካ እንዲገነዘቡ እርዳቸው። አቀራረብህን በምትዘጋጅበት ጊዜ የሚከተሉትን ሐሳቦች ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ።
2 ተገቢውን ሰላምታ ካቀረብክ በኋላ እንዲህ ለማለት ትችል ይሆናል፦
◼ “በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተጠቀሱት አራት ፈረሰኞች ሰምተው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እነዚህ ፈረሰኞች ምን እንደሚወክሉ የተለያየ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ነገር ግን ምሳሌያዊ የሆነው ግልቢያቸው መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ የተናገረላቸውና በዘመናችን የተከሰቱ ትንቢቶች ክፍል መሆናቸውንና ትንቢቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እኛንም እንደሚነኩን ያውቃሉን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህንን ትንቢት ለመረዳትና ፍጻሜው ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ይፈልጋሉ?” ከዚያም የራእይ መደምደሚያ በሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኘውን ሥዕላዊ መግለጫ ልታሳየውና በትላልቅ ፊደላት ከተጻፉት ጥቅሶች በአንዳንዶቹ ላይ ልታነጋግረው ትችላለህ። ወይም ደግሞ ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን? የሚለውን ትራክት በመጠቀም በራእዩ አንዳንድ ዘርፎች ላይ ሐሳብ ልትሰጥ ትችላለህ። መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘውና ስለ ራእዩና ስለ ትርጉሙ የበለጠ ለመወያየት ተመልሰህ ለመምጣት ዝግጅት አድርግ።
3 ወይም እንደሚከተለው ያለ አቀራረብ ለመሞከር ትፈልግ ይሆናል፦
◼ “ከዚህ በፊት ‘አርማጌዶን’ የሚል ቃል ሰምተው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ብዙ ሰዎች ይህ በጊዜያችን የሚከናወነውን አውዳሚ የኑክሌር ጦርነት ያመለክታል ብለው ያስባሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አርማጌዶን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ አርማጌዶን የተሻለ ነገር ለማምጣት የሚወሰድ ትልቅ የለውጥ እርምጃ ሲሆን ይህም ዘላቂ ሰላም ያለው ዓለም ያስገኛል።” እንደ ራእይ 16:16 ወይም መዝሙር 37:10, 11 ያሉትን ጥቅሶች ልትጠቅስለትና የራእይ መደምደሚያ የሚለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 39 በማሳየት መጽሐፉን እንዲወስድ ልትጋብዘው ትችላለህ። አለበለዚያም ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን? ከሚለው ትራክት ውስጥ ተስማሚ ሐሳቦችን ልታወያየው ትመርጥ ይሆናል።
4 የሚከተለውን ሐሳብ በመጠቀም ፍላጎቱን ልታነሳሳ ትችል ይሆናል፦
◼ “በዚህኛው የዓመቱ ክፍል በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያስባሉ። ከትንሣኤው በኋላ እስካሁን ምን እያደረገ ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ? ዛሬ በጊዜያችን ከሚፈጸሙት አስደናቂ ሁኔታዎች ብዙዎቹ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ዓላማ ውስጥ እየተጫወተ ካለው ሚና ጋር የተያያዙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጸዋል። አምላክ ልጁን ወደ ምድር ስለላከበት ዓላማና ይህ ለእርስዎና ለሚያፈቅሯቸው ሰዎች ምን ትርጉም እንዳለው ለማወቅ ይፈልጋሉ?” የራእይ መደምደሚያ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 41 አንቀጽ 1 እና 2 ላይ ባለው ሐሳብ ላይ እንዲያተኩር ልታደርግ ትችል ይሆናል። ወይም ደግሞ አዲስ በወጣ የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት እትም ላይ ያለውን ተስማሚ ሐሳብ ለማጉላት ትፈልግ ይሆናል። አለበለዚያም ፍላጎቱን ለመቀስቀስ ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት የተባለውን ትራክት ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል።
5 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ አትርሳ። የይሖዋ በረከት ታክሎበት አንድ ሰው ‘የዚህን የትንቢት ቃል እንዲሰማና በውስጡ የተጻፈውንም እንዲጠብቅ’ ልትረዳ ትችል ይሆናል። — ራእይ 1:3