እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
1 ሁሉም ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን “ምሥራች” እንዲሰማ ብንፈልግም ሰው ሁሉ መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ እንደማይሆን እናውቃለን። እኛም የግድ እንዲያዳምጡን ለማድረግ አንሞክርም። ሆኖም አስተዋዮች ከሆንን ብዙውን ጊዜ ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ አጋጣሚውን ምክንያታዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ወደሚደረጉ ተጨማሪ ውይይቶች መለወጥ ይቻላል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ውይይት ለማስቆም የሚሰነዝሯቸው ሐሳቦች ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው የነገሯቸውን ነው። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ በለዘበ አንደበት ትኩረታቸውን የአምላክ ቃል ስለ ጉዳዩ ወደሚናገረው ሐሳብ ማዞር እንችላለን።— ምሳሌ 25:15፤ 1 ጴጥ. 3:15
2 ሰዎች ብዙውን ጊዜ “የራሴ ሃይማኖት አለኝ” ይላሉ።
◼ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚቻልበት አንዱ መንገድ የሚከተለው ነው:- “በዚህ ጉዳይ ላይ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት እስማማለሁ፤ ስለዚህ እንዲሰሙ አላስገድድዎትም። ነገር ግን አምላክ ራሱ ሰዎች እውነተኛ አምላኪዎቹ እንዲሆኑ በመፈለግ ላይ እንዳለ ያውቃሉ? ኢየሱስ በዮሐንስ 4:23, 24 ላይ ምን እንዳለ ልብ ይበሉ . . .”
◼ ወይም ለመልሱ የሚከተለውን ጥያቄ ልትጠቀም ትችላለህ:- “የእርስዎ ሃይማኖት ትክክል የሆነውን ነገር የሚወዱ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምር እንደሆነ ሊነግሩኝ ይችላሉ? . . .— መዝ. 37:29”
3 አንዳንዶች ቶሎ ብለው ስለ ማርያም ይጠይቃሉ። “በድንግል ማርያም ታምናላችሁ?” ይሉን ይሆናል።
◼ ለዚህ ቀላሉ ምላሽ የሚከተለው ሊሆን ይችላል:- “በማርያም እንደማናምን የነገረዎት ሰው አለ? መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም ድንግል እንደነበረችና ኢየሱስን እንደወለደች በግልጽ ያሳያል። በሉቃስ 1:26–37 ላይ ከተገለጸው ማርያም የአምላክን መልእክተኞች ለመስማት ካላት ፈቃደኛነት ልንማር እንችላለን።”— ማመራመር ገጽ 254–255 ተመልከት።
[መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማርያም ከሚናገረው ምን ልንማር እንችላለን?
(1) አምላክ በመልእክተኞቹ በኩል የሚነግረን ነገር መጀመሪያ ላይ የሚከብድ ወይም የማይቻል መስሎ ቢታይም ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ ስለመሆኑ ትምህርት እናገኛለን።— ሉቃስ 1:26–37
(2) አንድ ነገር የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ከተነገረን በድፍረትና ሙሉ በሙሉ በአምላክ በመተማመን ያንን ነገር ስለመፈጸም። (ሉቃስ 1:38ን ተመልከት። በዘዳግም 22:23, 24 ላይ እንደተገለጸው አንዲት ያላገባች አይሁዳዊት ልጃገረድ አርግዛ ብትገኝ ከባድ ቅጣት ይደርስባት ነበር።)
(3) አንድ ሰው በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ቦታ ትንሽም ይሁን ትልቅ አምላክ ሊጠቀምበት የሚችል ስለመሆኑ።— ሉቃስ 2:22–24ን ከዘሌዋውያን 12:1–8 ጋር አወዳድር።
(4) ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የላቀ ቦታ ስለ መስጠት። (ሉቃስ 2:41፤ ሥራ 1:14። አይሁዳውያን ሚስቶች ባሎቻቸው ለማለፍ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ረጅም ጉዞ ሲያደርጉ አብረዋቸው የመሄድ ግዴታ አልነበረባቸውም። ማርያም ግን አብራ ሄዳለች።)
(5) የሥነ ምግባር ንጽሕናን ስለመውደድ።— ሉቃስ 1:34
(6) የአምላክን ቃል በትጋት ለልጆች ስለማስተማር። (ይህም ኢየሱስ በ12 ዓመቱ ባደረገው ነገር ታይቷል። ሉቃስ 2:42, 46–49ን ተመልከት።]
4 “አንድ ሰው በፍልሰታ ማርያም ታምናላችሁን?” ብሎ ቢጠይቀን:-
◼ ማርያም አሁን በአምላክ መንግሥት ዝግጅት ውስጥ ድርሻ እንዳላት፣ በሰማይ እንደምትኖርና ልናነጋግረው የምንፈልገውም ስለዚህ መንግሥት እንደሆነ ልንገልጽለት እንችላለን።”
በማርያም አማላጅነት ስለማመን ጥያቄ ከተነሣ የሚከተለውን መልስ መስጠት ትቸላለህ:- ◼ “ኢየሱስ ስለ አማላጅነት እንዲህ ሲል ተናግሯል:- (ዮሐንስ 14:6, 14ን አንብብ።) ለማርያም ተገቢውን አክብሮት እየሰጠን ይህን መመሪያ መከተል ያለብን አይመስልዎትም?”
5 አንዳንዶች “ቤተ ክርስቲያናችሁ የት ነው?” ብለው ይጠይቃሉ።
◼ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት እንዲህ ማለት እንችላለን:- “የአምላክ መንግሥት የሰው ልጆችን ችግሮች እንደምታስወግድ ለማጉላት የመሰብሰቢያ ቦታዎቻችንን የመንግሥት አዳራሽ ብለን እንጠራቸዋለን። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እንደዚህ ዓይነት የመንግሥት አዳራሾች አሉን። በአንዳንድ ስፍራዎች ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚደርስብን ተቃውሞ እንደ ሐዋርያት በግል መኖሪያ ቤቶች እንድንሰበሰብ አስገድዶናል። በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ወደሚደረጉ ስብሰባዎች በመሄዱ ምክንያት ሐዋርያው ጴጥሮስን እንደማይቃወሙት እርግጠኛ ነን። ነገር ግን ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች እየሠራን ነው።”
◼ በተጨማሪም በዋና ከተማው ካሉት የአንዱን የመንግሥት አዳራሽ አድራሻ ልትሰጥና ውይይትህን ልትቀጥል ትችላለህ።
6 ሰዎች ለምን ጽሑፎቻችንን በነፃ እንደማናድል ቢጠይቁ:-
◼ ለምናጠፋው ጊዜ እንደማናስከፍልና በነፃ የምናበረክታቸውን ትራክቶች ወጪ ራሳችን እንደምንሸፍን ልትገልጽላቸው ትችላለህ። ከዚያም በትራክቱ ባለው መልእክት ላይ ለማተኮር ሞክር። ሰውዬው በነፃ መጽሐፍ ማግኘት የሚፈልግ ከሆነ ገንዘብ የምንጠይቀው ለጽሑፎቹ የተደረጉትን ወጪዎች ለመሸፈን ብቻ እንደሆነ ጠቁም።
7 ከእነዚህ መልሶች አብዛኞቹ የተመሠረቱት ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ ነው። ከሌሎች ጋር ሳንከራከር ወይም ውዝግብ ውስጥ ሳንገባ በለዘበ አንደበት በመመለስ ረገድ ይበልጥ ችሎታችንን ለማሻሻል እርስ በርሳችን እንማማር።— 2 ጢሞ. 2:24