መልእክቱን ተቀብለው እርምጃ እንዲወስዱ እርዳቸው
1 የስብከት ሥራችን ሰዎች ‘በራእይ መጽሐፍ ላይ ያለውን የትንቢት ቃል እንዲሰሙ’ አጋጣሚውን ይከፍትላቸዋል። (ራእይ 1:3) ‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት እንዲያልፉ ከተፈለገ ግን በሰሙት ነገር መሠረት እርምጃ መውሰድ አለባቸው። (ራእይ 7:14) ይህ የሕይወት ጉዳይ ነው! ለዚህ ወር ከቀረቡት መግቢያዎች በአንደኛው ተጠቅመህ ስታነጋግራቸው በመጀመሪያው ቀን ውይይታችሁ ላይ ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተመልሰህ መጠየቅ አትርሳ።
2 “የራእይ መደምደሚያ” የተባለውን መጽሐፍ ሰጥተኸው ከነበረ እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል፦
◼ “እንደገና በመገናኘታችን በጣም ደስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ ስንነጋገር በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት ትንቢቶች መካከል በአንዱ ላይ ተወያይተን ያንን የሚያብራራ ጽሑፍ ሰጥቼዎት ነበር። ምንም እንኳን የራእይ መጽሐፍ በጣም ጥልቀት ያለው ቢሆንም በብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውነቶች በመጠቀምና ዛሬ በሚከናወኑት ነገሮች ብርሃን መጽሐፉን ለመረዳት እንደሚቻል ሳያስተውሉ እንዳልቀሩ እገምታለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስላለንበት ጊዜ የሚነግረንን አንዳንድ ነገሮች ለማጉላት ለጥቂት ደቂቃዎች ባነጋግርዎ ደስ ይለኛል።” ከዚያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ወደሚያስችልህ ተስማሚ ጽሑፍ ተሸጋገር።
3 በመጀመሪያው ዕለት ውይይታችሁ “ይህ ዓለም ከመጥፋት ይተርፍ ይሆን?” የሚለውን ትራክት ሰጥተኸው ከነበረ እንደሚከተለው ለማለት ትችል ይሆናል፦
◼ “ዛሬ እርስዎን እቤት ለማግኘት በመቻሌ ደስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ ስመጣ የዓለም መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት የሚፈጸመው ምልክት ክፍል ስለሆኑት አንዳንድ ክንውኖች ተነጋግረን ነበር። [በማቴዎስ 24:3–14 ላይ ካሉት ተስማሚ የሆኑትን የምልክቱን አንዳንድ ዘርፎች ከልስ።] የዚህ ምልክት ክፍል ፍጻሜ ነው ብለው የሚያስቡት በዓለም ላይ ወይም በአካባቢያችን በቅርቡ ሲፈጸም ያስተዋሉት ነገር አለ?” የራእይ መደምደሚያ በሚለው መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ላይ ያለውን ሥዕላዊ መግለጫ በመጠቀም ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንዳንዶቹ እንዴት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ አስረዳ። በጉብኝትህ መደምደሚያ ላይ በዚያ ሳምንት የሚሰጠውን የሕዝብ ንግግር ርዕስ ጥቀስና በመንግሥት አዳራሹ አብሮህ እንዲገኝ ግብዣ አቅርብ።
4 የቤቱን ባለቤት በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኝ ጋብዘኸው ከነበረ እንዲህ በል፦
◼ “ባለፈው ጊዜ መጥቼ ሳለ የኢየሱስ ሞት ለሰው ዘር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተነጋግረን ነበር። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች መጋቢት 26 በሚያከብሩት የሞቱ መታሰቢያ በዓል ላይም እንዲገኙ ጋብዤዎት ነበር። ዛሬም የመጣሁት በዚህ ጠቃሚ የሆነ ወቅት ላይ እንዲገኙ እንደተጋበዙ ላስታውስዎት ነው። [በዓሉ የሚከበርበትን ቦታና ሰዓት ንገረው።] ኢየሱስ ለሰው ዘር ባደረገው ነገር አሁን ስላገኘናቸውና ወደፊትም ስለምናገኛቸው አንዳንድ በረከቶች ብንወያይ የዚህን ልዩ በዓል አስፈላጊነት እንዲያደንቁ ሊያደርግዎት ይችላል።” ከዚያ በኋላ በቅርብ ጊዜ ከወጡት መጽሔቶች ወይም የራእይ መደምደሚያ ከተባለው መጽሐፍ በምዕራፍ 41 ውስጥ ተስማሚ በሆኑት ነጥቦች ላይ ለመወያየት ሞክር። በገጽ 294, 299, እና 308 ላይ ያሉትን ሥዕላዊ መግለጫዎች ሐሳብ ጎላ አድርገህ ልትገልጽ ትችላለህ። የሚቻል ከሆነ ፍላጎት ያሳየውን ሰው በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኝ ለመርዳት ዝግጅት አድርግ።
5 ሰውዬው እንዲሁ የማይቃወም አድማጭ ብቻ ከሆነ እንዲህ ማለቱ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፦
◼ “በቀደም ዕለት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባደረግነው ውይይት በጣም ተደስቻለሁ። ዛሬ ተመልሼ የመጣሁት አምላክ ስለ እርሱ የበለጠ ለመማር ለሚፈልጉ ሰዎች የገባው ቃል ሲፈጸም በዚያ ተገኝተው ሲደሰቱ ለማየት ስለምፈልግ ነው።” ዮሐንስ 17:3ን አንብብና ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ሕይወት ከሚለው ትራክት እየጠቀስህ አወያየው።
6 ለሕይወት ያለህ ፍቅርና ለቤዛው ያለህ አድናቆት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሰህ ለመጎብኘት የሚያነሳሳህ ይሁን። በራእይ ውስጥ በሚገኘው ስሜት ቀስቃሽ መልእክት እርምጃ እንዲወስዱ እርዳቸው። ‘ዘመኑ እንደቀረበ’ አስታውስ! — ራእይ 1:3