ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ማግኘት
1 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለሌሎች ማስተላለፍ እንችል ዘንድ ‘የማስተማር ችሎታ’ እንዲኖረን በማሰልጠን ረገድ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። (2 ጢሞ. 4:2) በየሳምንቱ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሶች ላይ ጥልቅ የሆነ ማስተዋል እናገኛለን። ይህ ትምህርት ቤት ከሚሰጠው እጅግ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት ሙሉ በሙሉ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በስብሰባው ወቅት ልታገኛቸው ስለምትችላቸው አስደሳች ነጥቦች አንዳንዶቹን በማጉላት የመግቢያ ሐሳቦችን ሲያቀርብ በጥሞና አዳምጥ። እርሱ ስለሚጠይቃቸው ማናቸውም ጥያቄና መልሶቹን በአገልግሎትህ እንዴት ልትሠራባቸው እንደምትችል አስብ።
3 የመምሪያ ንግግሩ እንዲሁ በጽሑፍ ባለ ትምህርት ላይ የሚደረግ ክለሳ አይደለም። የመምሪያ ንግግሩ በትምህርቱ ተግባራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረና አንተን በግል እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል በማስረዳት ላይ ያተኮረ ነው። በቅድሚያ መዘጋጀትህ በዋና ዋና ነጥቦቹ ላይ ይበልጥ እንድታተኩርና ከንግግሩ ቀጥሎ በሚደረገው የክለሳ ጥያቄ ላይ መልስ በመስጠት መካፈል እንድትችል ይረዳሃል።
4 የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አዘውትረህ ማንበብህ ለአምላክ ቃል ጥልቅ አድናቆት እንዲኖርህ ያደርጋል። ተጨማሪ ምርምር ማድረግ አዳዲስና አስደሳች የሆኑ ዝርዝር ሁኔታዎችን ማወቅ ስለሚያስችል እውነትን የበለጠ ለመረዳት ያስችልሃል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የተገኙት ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች የሚቀርቡበት ክፍልም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክን እንዲሁ በመድገም የሚቀርብ አይደለም። ተናጋሪው አጠር ያለ አጠቃላይ ክለሳ ካደረገ በኋላ በተመደበው ክፍል ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ያጎላል። እንዲሁም እነዚህን ነጥቦች በሕይወታችን እንዴት እንደምንሠራባቸውና ከአምልኮአችን ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ያብራራል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ይበልጥ በሥራ ላይ እንዴት እንደምታውለው መማር ትችል ዘንድ በጥሞና አዳምጥ። — መዝ. 119:105
5 የተማሪ ንግግር እንድታቀርብ ክፍል ከተሰጠህ አሁን እየሠራህባቸው ያሉትን የምትመከርባቸው ነጥቦች ማስታወስ አለብህ። እንድትሠራበት የተነገረህን የንግግር ባሕርይ በተመለከተ በትምህርት ቤቱ መመሪያ መጽሐፍ ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች በሙሉ አንብባቸው። የተማሪ ንግግርህን ስታቀርብም ባገኘሃቸው ምክሮች ለመጠቀም ሞክር። ለንግግርህ የሚሆኑ ሐሳቦችን በምትመርጥበት ጊዜ ለመስክ አገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን ለማጉላት ሞክር። — ትመ ጥናት 19
6 እኅት ከሆንሽና ንግግር ቁጥር 3 ወይም ቁጥር 4 እንድታቀርቢ ከተመደብሽ ሊያጋጥም የሚችል ሁኔታን በሚያሳይ ትዕይንት ተጠቅመሽ ትምህርቱን ለማቅረብ ሞክሪ። የምታገኚው ሰው በተናገርሽው ሁሉ ሊስማማ ወይም ላይስማማ ይችላል። ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ በመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ማሰላሰል እንዲችሉ እንዴት እንደምትረጃቸው ለማሳየት ጥረት አድርጊ። (ትመ ጥናት 31) ይህ አቀራረብ አድማጮች በመስክ አገልግሎት ተመሳሳይ መቃወሚያ ሐሳብ ቢያጋጥማቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ በማሳየት ሊረዳቸው ይችላል። ክፍልሽን ከማቅረብሽ በፊት አስቀድመሽ ተዘጋጂ። እንዲሁም ክፍሉን አብራሽ ከምታቀርበው እኅት ጋር ቀደም ብላችሁ በደንብ ተለማመዱ። ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ መለማመድ ተገቢ አይደለም።
7 የተማሪ ንግግር ያላቸው ሁሉ በአዳራሹ ውስጥ ከፊት ባሉት መቀመጫዎች ቢቀመጡ ጥሩ ነው። ይህ ጊዜ ይቆጥባል። እንዲሁም የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በቀጥታ ለተማሪው ምክር መስጠት እንዲችል ያደርገዋል። የበላይ ተመልካቹ በትምህርት ቤቱ መመሪያ መጽሐፍ ላይ ተመርኩዞ በደግነት የሚሰጣቸው ምክሮች ሁሉንም ይጠቀማሉ። ምክር ሲሰጥ በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ ያለውን ቅደም ተከተል ላይከተል ይችላል። አሁን ይበልጥ ማሻሻል በሚያስፈልጋችሁ አንድ ነጥብ ላይ የተመሠረተ ምክር ለመስጠት ይመርጥ ይሆናል።
8 እነዚህ ሁሉ በየሳምንቱ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እንደንገኝና አስቀድመን እንድንዘጋጅ የሚያደርጉን ጥሩ ምክንያቶች ናቸው። የምናገኘው ትምህርት በመስክ አገልግሎታችን ጥበበኛና ጥሩ ችሎታ ያለን እንድንሆን ይረዳናል። — ምሳሌ 1:5