በችግር በተሞላው ዓለም ውስጥ የመጽናናትና የተስፋ ምንጭ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ
1 ይህ ዓለም የሰው ልጆችን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከትቷቸዋል፤ ስለዚህ ማጽናኛና ተስፋ ያስፈልጋቸዋል። የእውነተኛ ተስፋ ብቸኛ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (ሮሜ 15:4፤ 2 ጴጥ. 3:13) ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ በጥራዝ 1 ገጽ 311 ላይ እንዲህ የሚል አስተያየት ይሰጣል:- “ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋንና ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚመጡትን ጥቅሞች አናውቅም ነበር። በአምላክ የጽድቅ መንግሥት ውስጥ ወይም ሥር የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ለመጨበጥ ምን እንደሚፈለግብን አንረዳም ነበር።”
2 ምንም እንኳን መጽሔቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን ብንጠቀምም ሰዎች ከዓለም የሚመጣባቸውን ተጽዕኖ እንዲቋቋሙ በመርዳት ረገድ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሚጫወተው ሚና ላይ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን። ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያደንቁት ምን ልንል እንችላለን?
3 ራስህን ካስተዋወቅህ በኋላ እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል:-
◼ “የአእምሮ ሰላማችንን ሊወስዱ በሚቃጡ ችግሮች ተከበናል ቢባል ሳይስማሙ አይቀሩም። እነዚህን ችግሮች እንዴት መወጣት እንደምንችል የሚያሳየን ተግባራዊ ምክር ከየት ልናገኝ እንችላለን? [መልስ እንዲሰጥ እድል ስጠው።] መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ደስተኛ መሆን እንደምንችል ስለሚያስተምረን ልብን የሚያረጋጋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። [ሉቃስ 11:28ን አንብብ።] የስብከት ሥራችን ዓላማ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡና ከትምህርቱ እንዲጠቀሙ ማበረታታት ነው።”
4 እንዲህ ያለ ቀላል አቀራረብ ትመርጥ ይሆናል:-
◼ “ሰዎች የአምላክ ቃል ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ ካሁኑ የበለጠ አክብሮት እንዲኖራቸው ማበረታታት እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው? የተባለውን ይህን ትራክት ብሰጥዎት ደስ ይለኛል። ስለ ተሻለ ዓለም እርግጠኛ ተስፋ ለማግኘት ለምን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት እንደምንቸል ይገልጻል። [በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን መዝሙር 37:29ን ከመደምደሚያው አንቀጽ ጋር አንብበው።] ይህን ትራክት ያንብቡና በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚሰጠው ተስፋ ምን እንደሚሰማዎት ቢነግሩኝ ደስ ይለኛል።”
5 አንዳንድ አስፋፊዎች ቀጥሎ ያለውን ቀጥተኛ አቀራረብ ተጠቅመው የመጽ ሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ይፈልጉ ይሆናል:-
◼ “የመጣሁት ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደምንሰጥ ለመግለጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ሲሆን ትምህርቶቹም ነገሮችን ለማቅናት ይጠቅማሉ። እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በአጭሩ ላሳይዎት። [መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት 33ለ “የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ምን ታደርግላቸዋለች” በሚል ርዕስ የሰጠውን ሐሳብ ተጠቀም። (በተጨማሪም በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በገጽ 1653 ላይ ይገኛል።) እንደ ሰውዬው ፍላጎት አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶች አንብብና ነጥቡን አብራራ። የቀረቡትን ጥቅሶች ማንበብ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለማከናወን ያሰበውን ለመረዳት እንደሚያስችለን ግለጽ።] ተመልሼ ብመጣና ይበልጥ ስለ መንግሥቱ ተስፋ ባወያይዎት ደስ ይለኛል።”
6 መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት ምንጭ ነው። (ዮሐንስ 17:3, 17) ከሌሎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መካፈላችን ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ፈቃዱ የሆነውን’ ይሖዋን ያስደስተዋል። — 1 ጢሞ. 2:4