‘ሌላም ጊዜ’ እንዲሰሙ እርዷቸው
1 “ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ሌላ ጊዜ እንሰማለን።” (ሥራ 17:32 የ1980 ትርጉም ) ይህ ጳውሎስ በማርስ ኮረብታ ላይ ላደረገው ዝነኛ ንግግር አንዳንዶች የሰጡት ምላሽ ነበር። በተመሳሳይም ዛሬ እንዳንዶች በመጀመሪያ ጉብኝታችን ወቅት ስላካፈልናቸው የመንግሥቱ መልእክት ይበልጥ ለመስማት ፈቃደኛ ናቸው።
2 በአብዛኛው ትምህርት የምንሰጠው የሰዎችን ፍላጎት ለመኮትኮት ተመልሰን ስንሄድ ነው። ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ዓላማችን እንዲሳካለን ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይረዳናል። የትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ በገጽ 51 ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይሰጣል:- “መጀመሪያ ትምህርቱን በመደገፍ የቀረቡትን ምክንያቶች በግልጽ ተረዳ። ነገሩ ለምን እንደዚያ እንደሆነ ለመረዳት ሞክር። ሐሳቦቹን በራስህ አነጋገር ለመግለጽ ሞክር። የቀረቡት የጥቅስ ማስረጃዎች እንዲገቡህ አድርግ። አንድን ነገር ለማስረዳት በጥቅሶች እንዴት እንደምትጠቀም ተዘጋጅ።”
3 የምታነጋግረው ሰው ጥያቄዎችን ጠይቆህ ጥያቄዎቹን ለመመለስ ተመልሰህ ስትሄድ ይህን አስብ:- ግብህ ልባዊ ፍላጎት ያለው ሰው አግኝተህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ነው። ጥያቄዎቹን ስትመልስ ንግግር አትስጥ። የቤቱን ባለቤት እያመራመሩ ማስረዳት፣ ጥቅሶች ራሳቸው እንዲያናገሩ ማድረግና በጥያቄ እየተጠቀሙ ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት የተሻለ ነው። ለሥራችን ጠቃሚ መሣሪያ ከሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት ወይም ማመራመር (ሪዚኒንግ ) ከተባለው መጽሐፍ ለዚህ የሚሆኑ ተስማሚ ጥቅሶች ሊገኙ ይችላሉ። የምናነጋግራቸው ብዙ ሰዎች በአንድ ወይም በሁለት ጥቅሶች ላይ በተመሠረቱ አጭር መልሶች ይረካሉ፤ እያንዳንዱን ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ማብራራት የግድ አስፈላጊ አይደለም። በተጨማሪም በአንድ ጉብኝት ወቅት ከመጠን በላይ የበዙ ጥያቄዎችን አትመልስ። ለአንድ ጥያቄ ተስማሚ በሆኑ ጽሑፎች መልስ ሰጥቶ ጉብኝቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መለወጡ የተሻለ ነው።
4 “መጽሐፍ ቅዱስን ማመን የሚችሉት ለምንድን ነው?” የተባለውን ትራክት ላበረከትክላቸው ሰዎች እንዲህ ለማለት ልትመርጥ ትችላለህ:-
◼ “ሁላችንም የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንዲሚመጣ ለማወቅ እንጓጓለን። አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ወደፊት ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ሰው ወደፊት ስለሚሆነው ነገር መገመት ብቻ ሲችል አምላክ ምን እንደሚሆን በትክክል ያውቃል። [ኢሳይያስ 46:10ን አንብብ።] መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ በአዲስ ዓለም ገነት ተቋቁማ ብዙ በረከት እንደምናገኝ እንደሚናገር ሲያውቁ ይገረሙ ይሆናል። [በገጽ 4 ላይ ያለውን ሦስተኛ አንቀጽ አንብብ።] ስለዚህ አስደናቂ ተስፋ ይበልጥ ልንገርዎት።”
5 “አዲሲቱ ዓለም ትርጉም” አበርክተህ ከነበረ ምናልባት ቀጥሎ ያለው ሐሳብ ይጠቅምህ ይሆናል:-
◼ “በቅርቡ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ትቼልዎት እንደገና መጥቼ በተሻለ መንገድ እንዲጠቀሙበት እንደምረዳዎት ቃል ገብቼልዎት ነበር። አንዳንዴ ከሰዎች ጋር ያለን ወዳጃዊ ግንኙነት እንዳይበላሽ እንዴት መያዝ እንደምንችል ግራ ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ምክር ይሰጣል፤ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም አስፈላጊውን ነገር ለማግኘት ቀላል ያደርግልናል። [ገጽ 1595 አውጣና “Love(s)” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን ጥቅሶች ተመልከት። እንደ 1 ቆሮ. 13:4፤ ቆላ. 3:14 እና 1 ጴጥ. 4:8 ባሉ ጥቅሶች ላይ አተኩር። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል በአጭሩ መግለጽ ጥሩ ውጤቶችን ያስገኛል።] መጽሐፍ ቅዱስ ለችግሮቻችን እንዴት ተግባራዊ መፍትሔ እንደሚሰጥ የሚያሳይ አንዱ ምሳሌ ይህ ነው። በሚቀጥለው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ደስታና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት እንዴት እንደሚረዳን ላሳይዎት እፈልጋለሁ።”
6 ለሌሎች የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት ከማስተላለፍ የበለጠ ልንሰጣቸው የምንችለው ሀብት የለም። ይህ እውቀት ሰዎችን አምላክን እንዲፈሩና የዘላለም በረከቶች በሚያስገኘው መንገዱ እንዲሄዱ ሊያበረታታቸው ይችላል።— ምሳሌ 2:20, 21