የመንግሥት ስብከታችንን ለማሻሻል የምንችልባቸው መንገዶች
1 የስብከቱ ሥራችን ከመቼውም ይልቅ ዛሬ አጣዳፊ ነው። ሰዎች ሕይወት ማግኘታቸውና ማጣታቸው የሚወሰነው ለዚህ ምሥራች በሚሰጡት ምላሽ መሠረት ነው። (1 ጴጥ. 4:5, 6, 17፤ ራእይ 14:6, 7) ይህም በመሆኑ የመንግሥት ስብከታችንን ለማሻሻል የምንችልባቸውን መንገዶች አዘውትረን መመርመር አለብን። ታዲያ መሻሻል ልናደርግባቸው የሚገቡን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
2 በሚገባ ተዘጋጅ፦ በቅርብ ጊዜ የወጣ የመንግሥት አገልግሎታችንን በመጠቀም በክልልህ ላሉት አብዛኞቹ ሰዎች ይስማማል ብለህ የምታስበውን አቀራረብ ምረጥ። መወያያ ነጥቦችህን ለአካባቢው ሁኔታ እንደሚስማሙ አድርገህ ማቅረብህ አስፈላጊ ነው። ወይም ምናልባት ውጤታማ ሆነው ያገኘሃቸውን ነጥቦችና ጥቅሶች በመጠቀም የራስህ የሆነ አቀራረብ ለማዘጋጀት ትመርጥ ይሆናል። መግቢያዎችህ ግን የመስማት ፍላጎትን የሚቀሰቅሱ መሆን ይኖርባቸዋል። (ማመራመር [ሪዝኒንግ] የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 9–15 ተመልከት።) የቤቱን ባለቤት አእምሮን የሚያመራምሩ ጥያቄዎች ልትጠይቀው ወይም በአካባቢው ትኩረት በተሰጠው አንድ ነገር ላይ የተነገረን ዜና አስመልክቶ አስተያየቱን እንዲሰጥህ ልትጠይቀው ታቅድ ይሆናል። የአቀራረብህ ዘዴ ምን መሆን እንዳለበት ከወሰንክ በኋላ ከቤተሰብህ ወይም የማሻሻያ ሐሳብ ሊሰጥህ ከሚችል ሌላ አስፋፊ ጋር ሆነህ ተለማመደው።
3 የምታወያይ ሁን፦ ዓላማችን አንድን አስፈላጊ የሆነ መልእክት ለሰዎች ማድረስ ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው አድማጫችንን ትርጉም ባለው ውይይት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ነው። የቤቱ ባለቤት የተቃውሞ መልስ ወይም አንድ ዓይነት አስተያየት ከሰጠ የሚናገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠው። የሚሰጥህ አስተያየቶች በአንተ ዘንድ ስላለው ተስፋ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ እንድትሰጥ በር ይከፍትልሃል። (1 ጴጥ. 3:15) አስተያየቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ ከሆነ በዘዴ እንዲህ ልትል ትችል ይሆናል:- “ብዙ ሰዎች ልክ እንደ እርስዎ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም ይህ ጉዳይ ልንመለከተው የሚገባ ሌላ ዓይነት ጎን አለው።” ከዚያም ተስማሚ የሆነ ጥቅስ አንብብና አስተያየቱን አድምጥ።
4 እንደ ሁኔታው ሊስተካከል የሚችል ፕሮግራም ይኑርህ፦ ለሰዎች መልእክቱን ለማድረስ እስካልቻልክ ድረስ በሚገባ መዘጋጀትህ ለፍቶ መና መሆን ነው። በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን ለማግኘት በራቸውን ስናንኳኳ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ማግኘት የተለመደ ሆኗል። በአንተ የአገልግሎት ክልልም ያለው ሁኔታ ይህ ከሆነ ብዙ ሰዎች እቤታቸው በሚገኙበት ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ትችል ዘንድ ፕሮግራምህን ለማስተካከል ሞክር። በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ላይ መሄዱን የተሻለ ሆኖ ታገኘው ይሆናል፤ ሌሎች ደግሞ የሚገኙት በሥራ ቀን ሆኖ ግን አመሻሽ ላይ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ አስፋፊዎች በዓለማዊ የበዓል ቀናት መመሥከርን አመርቂ ሆኖ አግኝተውታል። ይህም የሆነበት ምክንያት በዚህ ሰዓት ብዙ ሰዎች እቤታቸው ስለሚገኙ፣ የተረጋጋ ሁኔታ ስለሚኖራቸውና ለመወያየትም ይበልጥ ፈቃደኛ ስለሚሆኑ ነው። መግቢያህንም ለወቅቱ እንደሚስማማ አድርጎ ማስተካከሉ ጥሩ ነው፤ ከዚያም በአንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕስ ውስጥ የሚካተቱ ሐሳቦችን ስጥ።
5 አቀራረብህ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበር አመዛዝን፦ እያንዳንዱን ቤት አንኳክተህ ከጨረስህ በኋላ ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ:- ‘አቀራረቤ የቤቱን ባለቤት ልብ የሚነካ ነበርን? በልቡ ውስጥ ያለውን እንዲናገር ከጎተጎትኩት በኋላ በጥሞና ተከታትዬዋለሁ? ጥያቄውን የመለስኩለት ቅር በማያሰኘው መንገድ ነውን? እንደ ሁኔታው በተሻሉ አቀራረቦች ተጠቅሜያለሁን?’ በመንግሥቱ አገልግሎት ያለህን ውጤታማነት ማሸሻልን ግብ በማድረግ ተሞክሮ ካለው አስፋፊ ወይም አቅኚ ጋር በየጊዜው አብሮ ማገልገልና አቀራረባቸውን በጥንቃቄ መከታተል ለውጤታማነትህ ይበጃል።
6 በአገልግሎትህ ጥሩ ባለሞያ ከሆንክ የመንግሥቱን እውነት ለሌሎች በማካፈል “ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ።” — 1 ጢሞ. 4:16፤ ምሳሌ 22:29