ለሰዎች እውነትን ተናገሩ
1 ከሁለቱ ታላላቅ ትእዛዞች አንዱ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” የሚለው ነው። (ማቴ. 22:39) እንዲህ ያለው ፍቅር ያለንን ከሁሉ የተሻለ ነገር ይኸውም በአምላክ ቃል ውስጥ ያገኘነውን እውነት ለሰዎች እንድናካፍል ይገፋፋናል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የእውነት መልእክት ስለሚያብራሩ እነዚህን መጽሔቶች በግንቦት ወር ማሰራጨቱ ‘ከጎረቤቶቻችን ጋር እውነትን ለመነጋገር’ የሚያስችለን አንዱ መንገድ ነው። (ኤፌ. 4:25) ከዚህ ቀጥሎ ውይይት ለመጀመር የሚረዱን ጥቂት ሐሳቦች ቀርበዋል:-
2 ከቤት ወደ ቤት፣ ከሱቅ ወደ ሱቅ፣ በየመሥሪያ ቤቱ እና በመንገድ ላይ ሰዎችን በማነጋገር በተሳካ ሁኔታ መጽሔት ማበርከት እንችላለን። በማንኛውም ጊዜ በቂ መጠን ያላቸው መጽሔቶች መያዝ ያስፈልገናል። ለምናነጋግረው ሰው የሚስማማ አንድ ርዕስ ጎላ አድርገን ከገለጽን በኋላ ሁለት መጽሔቶች አንድ ላይ ብናበረክት የተሻለ ነው። አንድ መጠበቂያ ግንብ እና አንድ ንቁ! ቢሆን ይመረጣል። ወንዶች ብዙውን ጊዜ ኢኮኖሚያዊና ሳይንሳዊ የሆኑ ነገሮችን ወይም ዜናዎችን መከታተል ይወዳሉ። ሴቶች ስለ ቤተሰብና ማኅበራዊ ጉዳዮች ማንበብ ይወዳሉ። ያም ሆነ ይህ አቀራረባችንን አጭር (ከአንድ ደቂቃ የማይበልጥ) ማድረግና መልሱ በመጽሔቱ ውስጥ ሊገኝ የሚችል አንድ ጥያቄ ማንሳት ያስፈልገናል።
3 መጽሔት በማበርከት በኩል የተሳካላቸው ጠንክረው የሚሠሩ አስፋፊዎች ናቸው። ሰዎች ወደ እነርሱ እስኪመጡ ድረስ ቁጭ ብለው አይጠብቁም ወይም መንገድ ላይ አንድ ሰው ካነጋገሩ በኋላ የሚቀጥለውን ሰው እስኪያነጋግሩ በመሐሉ ብዙ ደቂቃዎች አያጠፉም። አንድ ሰው መጽሔት ካልወሰደ ተስፋ አይቆርጡም። ከዚህ ይልቅ እርሱን ከተሰናበቱ በኋላ ማንንም ሳይመርጡ ወዲያውኑ የሚቀጥለውን ሰው ያነጋግራሉ። ስለ ሰዎች አስቀድመው ከመፍረድ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው እውነትን እንዲሰማ መንገድ ይከፍታሉ። አስደሳች የሆኑ ጥቂት መግቢያዎች ከማዘጋጀታቸውም በተጨማሪ ይሆናል የሚል አመለካከት ይይዛሉ። ከዚህ ቀጥሎ ውይይት ለማስጀመር የሚያስችሉ ጥቂት ሐሳቦች ቀርበዋል:-
4 የሚያዝያ— ሰኔ “ንቁ!” መጽሔት በእጅህ ካለ እርሱን ማበርከት አለብህ። እንዲህ ብለህ በመጠየቅ ውይይት መክፈት ትችላለህ:-
◼ “ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣል ሲባል ምን ይሰማዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የዓለም ሃይማኖቶች ጦርነትንና ግድያን እንደሚያበረታቱ ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በተለየ ሁኔታ የአምላክ አገልጋዮች ምን ያደርጋሉ ብሎ እንደሚናገር ልብ ይበሉ።” መጽሔቱን አውጥተህ ገጽ 4 አናት ላይ የሚገኘውን ኢሳይያስ 2:2-4 ካነበብክ በኋላ ገጽ 10 ላይ በሚገኘው “ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሰዎች የቀረበ ጥሪ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ያለውን የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር አንብብ። ከዚያም እንዲህ በማለት ጠይቀው:- “አምላክ ይህንን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ያውቃሉ? መልሱ በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ቅጂ መውሰድ ይችላሉ።” ሁለት መጽሔቶች እንዲወስድና ሌላ ጊዜ ተመልሰህ አሁንም እንኳ ደህንነት የሰፈነበት ሕይወት መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመወያየት ሐሳብ አቅርብለት።
5 አጭር አቀራረብ ለመጠቀም የምትፈልግ ከሆነ የሚከተለውን መሞከር ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ታዋቂ መጽሔቶች ለንግድ፣ ለጾታ ወይም ለዓመፅ ሰፊ ቦታ የሚሰጡ መስሎ ይሰማቸዋል። [መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! አሳየው] እኛ እነዚህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጤናማ ጽሑፎች እያሰራጨን ነው። እነዚህ መጽሔቶች ብዙ አዳዲስ ነገሮች የሚያሳውቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አምላክን እንድናመልክ፣ ጎረቤቶቻችንን እንድንወድና ጥሩ ጠባይ እንዲኖረን ያስተምሩናል። እንደዚህ ያሉ ጽሑፎችን የምትመርጥ ከሆነ በዚህ እትም ውስጥ በምታገኘው ነገር እንደምትደሰት የታወቀ ነው።”
6 ለሰዎች እውነትን በቅንዓት የምንናገር ከሆነ ለብዙዎች ከፍተኛ ደስታ እናስገኝላቸዋለን።— ሥራ 8:4, 8