ሰባኪዎች ብቻ ሳይሆን አስተማሪዎችም መሆን አለብን
1 “የይሖዋ ምሥክሮች በስብከት ሥራቸው ቃል በቃል ምድርን አዳርሰዋል” ተብሎ ይነገራል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በሰው አቅም ወይም ኃይል ሳይሆን የስብከትና የማስተማር ተልዕኮዋቸውን በተለያዩ መሣሪያዎች እየታገዙ ለማከናወን በሚጥሩት አገልጋዮቹ ላይ በሚሠራው የአምላክ መንፈስ አማካኝነት ነው።—ዘካ. 4:6፤ ሥራ 1:8
2 የስብከት ሥራችንን ለማከናወን የሚረዳን ውጤታማ መሣሪያ ጽሑፍ ነው። ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያውቁ ለመርዳት ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት ዓመታት በቢልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፎችን፣ ቡክሌቶችን፣ ብሮሹሮችን፣ መጽሔቶችንና ትራክቶችን አትመው አሰራጭተዋል። በ1997 የዓመት መጽሐፍ ላይ የወጡት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ መጠን ያለው ጽሑፍ ታትሟል። እስካሁን ድረስ ከ91 ሚልዮን በላይ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ቅጂዎች ታትመዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ የሚታተመው የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ብዛት 7.1 በመቶ ጨምሯል። በጀርመን ደግሞ የሚታተመው የመጽሔት ብዛት 35 በመቶ ጨምሯል። በጀርመን ከሚታተመው ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው መጽሔት በሩስያ ቋንቋ የሚዘጋጅ ነው።
3 ይህን ያህል ጽሑፍ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ እንድንሰብክ ለተሰጠን ማበረታቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ምላሽ በመገኘቱ ነው። ብዙዎቻችን የስብከት ሥራችንን በመዝናኛ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይና በንግድ ቦታዎች በማስፋፋታችን ምክንያት ፍላጎት ለሚያሳዩ ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ ጽሑፍ እየተበረከተ ስላለ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከዚህ ቀደም የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት አጋጣሚ ያላገኙ ናቸው። ሰዎች ያሳዩትን ፍላጎት ለማርካት ጉባኤዎች በማንኛውም የስብከቱ ሥራ ዘርፍ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ዓይነት ጽሑፎች ይይዛሉ።
4 ጽሑፍ ስናበረክት ግባችን ምንድን ነው? ግባችን ጽሑፍ ማበርከት ብቻ አይደለም። ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኳችን ሁለት ገጽታዎችን ያካትታል፤ ይህም መስበክና ማስተማር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ መብት አለን። በዚህም አማካኝነት የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የመንግሥቱ ምሥራች መሆኑን ሰዎች እንዲገነዘቡ እናደርጋለን። (ማቴ. 10:7፤ 24:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተው የሚወጡት ጽሑፎቻችን የሰዎችን ፍላጎት በመቀስቀስና ስለ አምላክ መንግሥት እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ረገድ የተመሰከረላቸው ውጤታማ መሣሪያዎች ናቸው።
5 በሁለተኛ ደረጃ ደቀ መዛሙርት ማፍራት እንድንችል ኢየሱስ ያዘዛቸውን ነገሮች ማስተማር ይኖርብናል። (ማቴ. 11:1፤ 28:19, 20) በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ልብ ውስጥ እውነትን ለመትከልና ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ጽሑፎች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
6 ጽሑፎችን የሚወስዱ ሰዎች ‘የቃሉ ሰሚዎች’ ሊሆኑ ቢችሉም ማንም ሳይረዳቸው የቃሉ አድራጊዎች የመሆናቸው ጉዳይ ግን የማይመስል ነገር ነው። (ያዕ. 1:22-25) ማንም ሳይመራቸው ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ የሉም። (ሥራ 8:30, 31) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለራሳቸው ለማረጋገጥ እንዲችሉ የሚረዳቸው አስተማሪ ያስፈልጋቸዋል። (ሥራ 17:2, 3) ግባችን ራስን ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ እድገት እንዲያደርጉ መርዳትና ሌሎችን ለማስተማር የሚያበቃ በቂ ችሎታ እንዲያገኙ ማሰልጠን ነው።—2 ጢሞ. 2:2
7 ተጨማሪ አስተማሪዎች በጣም ያስፈልጋሉ፦ በምንሰብክበት ጊዜ ምሥራቹን ለሕዝብ ማወጃችን ነው። ማስተማር ግን አንድን ሰው ደረጃ በደረጃ እውቀት እንዲገበይ መርዳትን ያካትታል። ስብከት ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲገነዘቡ የሚያስችል ሲሆን ማስተማር ደግሞ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉና በሥራ እንዲያውሉት ይረዳቸዋል። (ሉቃስ 8:15) አንድ አስተማሪ መልእክቱን ከማወጅ የበለጠ ነገር ያደርጋል፤ ነገሮችን ያብራራል፣ ጥሩ የመከራከሪያ ነጥቦችን እያነሳ በምክንያታዊነት ያስረዳል፣ ማስረጃዎች ያቀርባል እንዲሁም ለተግባር ያነሳሳል።
8 ሰባኪዎች ብቻ ሳንሆን በተቻለ መጠን ሁላችንም አስተማሪዎችም መሆን አለብን። (ዕብ. 5:12) ጽሑፎችን ማሰራጨት የስብከት ሥራችን ዐቢይ ክፍል ነው። ሆኖም ደቀ መዛሙርት የማፍራት ተልዕኮአችን የተመካው በአስተማሪነታችን በምናከናውነው ነገር ነው። ምንም እንኳ ጽሑፍ በማበርከታችን ልንደሰት ብንችልም አገልግሎታችንን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም ከፈለግን ጽሑፍ ማበርከትን የመጨረሻው ግባችን አድርገን መመልከት የለብንም። (2 ጢሞ. 4:5) ጽሑፍ ማበርከት ለሌሎች እውነትን ለማስተማር የሚያስችል ጥርጊያ መንገድ ለመክፈት የሚረዳ ውጤታማ ዘዴ ነው።
9 ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግላቸውን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምራቸው፦ ሁላችንም በርካታ የሆኑ መጽሐፎችን፣ ብሮሹሮችንና መጽሔቶችን አበርክተን ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ብዙ ተመላልሶ መጠየቆች እንዲኖሩን ያስችላል። ተመልሰን ሄደን የሰዎቹን ፍላጎት ለመቀስቀስ ቋሚ የሆነ ፕሮግራም ማውጣት ይኖርብናል። ተመልሰን የምንሄድበት ዋነኛ ምክንያት ተጨማሪ ጽሑፎችን ለማበርከት ብለን ብቻ ሳይሆን አስቀድመው የወሰዱትን ጽሑፍ እንዲያነቡትና ጥቅም እንዲያገኙበት ለማበረታታት ነው። ትክክለኛውን እውቀት እንድናገኝ አንድ ሰው ደጋግሞ እየተመላለሰ ባይረዳን ኖሮ እኛ ራሳችን ምን ያህል መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችል ነበር?—ዮሐ. 17:3
10 ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተከታትለህ በመርዳት አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ብሮሹር ወይም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ተጠቅመህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማስጀመር ግብ ይኑርህ። እነዚህ ሁለት ጽሑፎች የመንግሥቱን መልእክት በቀላሉ መረዳት በሚያስችል መንገድ ያቀርባሉ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር አጠቃላይ የሆነ የጥናት ትምህርት የያዘ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶችን ይሸፍናል። እውቀት የተባለው መጽሐፍ ደግሞ አንድ ሰው ቀላል፣ ግልጽና ቅልጥፍ ባለ ሁኔታ እውነትን በጥልቀት እንዲማር ያስችለዋል።
11 በሰኔ 1996 የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ላይ የተብራራው ቀላል የሆነ የማስተማሪያ ዘዴ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለተማሪውም ሆነ ለአስተማሪው ቀላል ያደርግላቸዋል። ውጤታማ ሆነው የተገኙትን የማስተማሪያ ዘዴዎችና ስልቶች መከለስ እንድትችል የዚህን አባሪ ቅጂ በቀላሉ የምታገኝበት ቦታ አስቀምጠው። ሐሳብ ከተሰጠባቸው ነጥቦች መካከል ለተማሪው በግል ከልብ የመነጨ አሳቢነት እንዴት ማሳየት እንደሚቻል፣ በአንድ የጥናት ክፍለ ጊዜ ምን ያህል ትምህርት መሸፈን እንደሚያስፈልግ፣ ከርዕሱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ጥያቄዎች እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል፣ አስተማሪውም ሆነ ተማሪው ለጥናቱ እንዴት አስቀድመው መዘጋጀት እንደሚችሉና ተማሪውን እንዴት ወደ ይሖዋ ድርጅት መምራት እንደሚቻል ይገኙበታል። የተሰጡትን ሐሳቦች በመከተል አዲሶችን ጨምሮ አብዛኞቻችን እድገት የሚያደርጉ ጥናቶች መምራት እንችላለን።
12 ከመስኩ የተገኙ አመርቂ ሪፖርቶች፦ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹርና እውቀት የተባለው መጽሐፍ ደቀ መዛሙርት የማፍራቱን ሂደት የሚያፋጥኑ ጠቃሚ መሣሪያዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። በቦሊቪያ የሚገኝ አንድ ወንድም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር እንደደረሰው ከአንድ ሰው ጋር ጥናት ለመጀመር ተጠቀመበት። ከአራት ወራት በኋላ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ከተዘጋጁት ደስተኛ ተጠማቂ እጩዎች መካከል ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ይገኝበት ነበር።
13 የእውቀት መጽሐፍን አጥንተው ከጨረሱ በኋላ ብዙዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ ለመወሰን እየተነሳሱ ነው። በአንጎላ የሚገኝ አንድ ጉባኤ በዚያ አካባቢ የእውቀት መጽሐፍን መጠቀም በጀመረ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ አስፋፊዎቹ ይመሩዋቸው የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ከ190 ወደ 260 ያደገ ሲሆን የተሰብሳቢዎች ቁጥር ደግሞ በእጥፍ በመጨመር ከ180 ወደ 360 ከፍ ብሏል። ብዙም ሳይቆይ ሌላ ጉባኤ ማቋቋም ግድ ሆኖ ነበር።
14 በእውቀት መጽሐፍ አማካኝነት የመጀመሪያ ጥናቱን ካስጀመረ በኋላ አንድ ወንድም ጥናት ስለመምራት እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል:- “ጥናቱን የሚመራው ሰው ጥያቄዎቹን ከጠየቀ፣ አንዳንድ ከርዕሱ ጋር የሚሄዱ ጥቅሶችን ካነበበና ተማሪው እንደገባው እርግጠኛ ከሆነ ጥናት መምራት ቀላል ይሆናል።” ምንም እንኳ እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት የሚችሉት ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው አስፋፊዎች ብቻ ናቸው በማለት ጥናት መምራት በጭራሽ ሊሆንለት እንደማይችል ያስብ የነበረ ቢሆንም “እኔ ከቻልኩ ሌላ ማንኛውም ሰው ይችላል” በማለት ጥናት መምራት የሚቻል እንደሆነ ተገንዝቧል።
15 ደቀ መዛሙርት የማፍራት ግብ ላይ መድረስ የምንችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራትን የአገልግሎታችን ክፍል ካደረግነው ነው። በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የመሳተፍን ልማድ ያዳበሩት ጥናት መምራት በእግጥም አርኪ የሆነና አብዝቶ የሚክስ ሆኖ አግኝተውታል። “ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር” የሚለው በእኛም ላይ የሚሠራ እንዲሆን ምኞታችን ነው።—ሥራ 28:31