‘የሥጋ መውጊያ አለብህን?’
1 ምሥራቹን እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልዕኮ በተቻለን መጠን ለመፈጸም ከልብ እንመኛለን። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የደረሰባቸው ሥር የሰደደ አካላዊ ሕመም ወይም የአካል ጉዳት የሚፈልጉትን ያህል በስብከቱ ሥራ እንዳይካፈሉ እንቅፋት ስለሚሆንባቸው ሙሉ በሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ይቸግራቸዋል። በተለይም ደግሞ ሌሎች በአገልግሎቱ የተሻለ ተሳትፎ እያደረጉ እንዳሉ ሲመለከቱ የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ማሸነፉ ቀላል አይሆንላቸውም።—1 ቆሮ. 9:16
2 ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌ፦ ሐዋርያው ጳውሎስ ከነበረበት ‘የሥጋ መውጊያ’ ጋር መታገል አስፈልጎት ነበር። ያለማቋረጥ የሚጎስመውንና እንደ “ሰይጣን መልእክተኛ” አድርጎ የቆጠረውን ይህን የሚያሠቃይ እንቅፋት እንዲያስወግድለት ይሖዋን ሦስት ጊዜ ተማጽኗል። ሆኖም ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ መከራ ቢኖርበትም በጽናት ወደፊት ገፍቷል። ራሱን እንደ ምስኪን አልቆጠረም ወይም ከመጠን በላይ አላማረረም። ምርጡን ሰጥቷል። ችግሩን በጽናት እንዲወጣ የረዳው ቁልፍ ነገር “ጸጋዬ ይበቃሃል፣ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” በማለት አምላክ የሰጠው ዋስትና ነው። ጳውሎስ ያለበትን ሁኔታ አሜን ብሎ መቀበልንና በይሖዋና በመንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍን ሲማር ድካሙ ጥንካሬ ሆኖለታል።—2 ቆሮ. 12:7-10
3 አንተስ እንዴት መጽናት ትችላለህ? ሰብዓዊ ድካም ለአምላክ የምታቀርበውን አገልግሎት ውስን አድርጎብሃል? ከሆነ የጳውሎስ ዓይነት አመለካከት ይኑርህ። ሕመምህ ወይም ያለብህ የአካል ጉዳት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ምንም መፍትሄ የማይገኝለት ቢሆንም እንኳ ችግርህን በሚረዳልህና “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” በሚሰጥህ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ልትጥል ትችላለህ። (2 ቆሮ. 4:7 NW) ጉባኤው በሚያቀርብልህ እርዳታ ተጠቀም እንጂ ራስህን አታግልል። (ምሳሌ 18:1) በአንዳንድ የአገልግሎታችን ገጽታዎች መካፈል ባትችል መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወይም በስልክ ምስክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራዊ መንገዶችን ፈልግ።
4 ያለብህ የሥጋ መውጊያ በአገልግሎቱ የምትፈልገውን ያክል እንዳትካፈል ቢያግድህም እንኳ ዋጋ ቢስ እንደሆንክ ሊሰማህ አይገባም። እንደ ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን ጸጋ ምሥራች መመስከር ትፈጽም ዘንድ’ ችሎታህና ሁኔታህ በሚፈቅድልህ መጠን መሥራት ትችላለህ። (ሥራ 20:24) አገልግሎትህን ለመፈጸም ጥረት ባደረግህ መጠን ይሖዋ ይበልጥ እንደሚደሰት አትዘንጋ።—ዕብ. 6:10