መጨረሻው ሲቃረብ በምሥክርነቱ የምናደርገውን ተሳትፎ ማሳደግ
1 የመከር ወቅት አስደሳች ብቻ ሳይሆን በትጋት የሚሠራበትም ጊዜ ነው። እህል ለመሰብሰብ ያለው ጊዜ በጣም ውስን ነው። ገበሬዎቹ ከሥራ መለገም የለባቸውም።
2 ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያን’ ከመከር ወቅት ጋር አዛምዶ ተናግሯል። (ማቴ. 13:39 NW) የምንኖረው በዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ሲሆን ምሥክርነቱን “በዓለም ሁሉ” ለማዳረስ የቀረን ጊዜ ውስን ነው። (ማቴ. 24:14) መጨረሻው ይበልጥ እየተቃረበ ሲመጣ በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ማሳደግ ይኖርብናል። ለምን? ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” በማለት ምክንያቱን ገልጿል።—ማቴ. 9:37, 38፤ ሮሜ 12:11
3 ሥራውን በጥድፊያ ስሜት አከናውኑ፦ ኢየሱስ ታላቁን የስብከት ሥራውን ሲጀምር የተመደበለትን ሥራ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ነበረበት። “ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል” በማለት ስብከቱን በጥድፊያ ስሜት አከናውኗል።—ሉቃስ 4:43
4 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱም ተመሳሳይ የሆነ የጥድፊያ ስሜት እንዲይዙ አድርጓል። (ማር. 13:32-37) ከዚህ የተነሳ “ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።” (ሥራ 5:42) በሕይወታቸው ውስጥ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዳዮች ቀዳሚውን ቦታ አልያዙም። ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም እንኳ ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በመስበክ ረገድ ተሳክቶላቸዋል።—ቆላ. 1:23
5 በተለይ ዛሬ ‘የነገር ሁሉ መጨረሻ ስለቀረበ’ የጥድፊያ ስሜት የምናዳብርበት የበለጠ ጠንካራ ምክንያት አለን። (1 ጴጥ. 4:7) ይሖዋ ይህ የነገሮች ሥርዓት የሚደመደምበትን ቀንና ሰዓት ቀጥሯል። (ማቴ. 24:36) የስብከቱ ሥራ በቀረው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል። መስካችን ውስጥ አሁንም ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ያላገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ከዚህ የተነሳ ምሥራቹ ለሌሎች ተጨማሪ ሰዎች እንዲዳረስ ጥረታችንን መጨመር አለብን።
6 መጨረሻው እየተቃረበ ሲመጣ በምሥክርነቱ ሥራ የምናደርገውን ተሳትፎ በማሳደግ እኛም እንደ ኢየሱስ ‘ልናደርገው የሰጠኸንን ሥራ ፈጽመናል’ ብለን ለይሖዋ መልስ መስጠትና በዚህ ምክንያት የሚገኘው እርካታ ተካፋዮች መሆን እንችላለን።—ዮሐ. 17:4