የቤተሰብ አባላት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ የሚችሉበት መንገድ—በአገልግሎት
1 ባልና ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች በሕዝብ ፊት የይሖዋን ስም በማወደስ አንድ ላይ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሲካፈሉ ከማየት የበለጠ የሚያስደስት ምን ነገር ሊኖር ይችላል? (መዝ. 148:12, 13) ሁሉም ቤተሰቦች ዘወትር በመስክ አገልግሎት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ጥሩ ልማድ ሊኖራቸው ይገባል። ቤተሰባችሁ በየሳምንቱ በአገልግሎት የሚሳተፍበት የተወሰነ ቀን አለው? ከሆነ እያንዳንዱ ሰው ምን ማቀድ እንዳለበት በትክክል ስለሚያውቅ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይችላል።—ምሳሌ 21:5
2 ቤተሰባችሁ አገልግሎት ከሚወጣበት ቀን ቀደም ብሎ ሁላችሁም የምትጠቀሙባቸውን አቀራረቦች ለምን በጋራ አትዘጋጁም? በልምምድ የምታሳልፏቸው ጊዜያት እጅግ ጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ በቤተሰቡ መካከል እውነተኛ የትብብር መንፈስ ሊፈጥሩ ይችላሉ። የመስክ አገልግሎት ቤተሰቡን የሚያነጋግር ጉዳይ መሆኑና የቤተሰቡ አባላት በሙሉ በደንብ መዘጋጀታቸው ምንኛ ጠቃሚ ነው!
3 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመጽሔት ቀን ከአንድ ቤተሰብ ጋር ወደ አገልግሎት ወጥቶ ከአንደኛዋ ልጅ ጋር ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ ልጅትዋ “አብረኸኝ የምትቆየው ለምን ያህል ሰዓት ነው?” ስትል ጠየቀችው። ከእርሱ ጋር ስትጨርስ ከአባቷ ጋር ማገልገል እንደምትፈልግ ገለጸችለት። በእርግጥም እርስዋና አባትዋ አንድ ላይ ሆነው ማገልገል እንደሚያስደስታቸው ግልጽ ነው። እንዴት ግሩም የሆነ የቤተሰብ መንፈስ ነው!
4 አንዳንድ ቤተሰቦች በዓመቱ ውስጥ ሁሉም ለአንድ ወር ረዳት አቅኚ መሆን ይችሉ ይሆናል። ወይም ቢያንስ አንደኛው የቤተሰብ አባል ሳያቋርጥ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል አልፎ ተርፎም የዘወትር አቅኚ መሆን ይችል ይሆናል። በጥሩ ሁኔታ በመደራጀትና በመተባበር ምናልባትም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በአገልግሎት ላይ ያላቸውን የግል ተሳትፎ በማሳደግ አቅኚ ሆኖ ለሚያገለግለው ሰው ድጋፍ መስጠት ይችሉ ይሆናል። የቤተሰቡ አባላት በዚህ መንገድ ተሳትፏቸውን በማሳደጋቸውና አገልግሎት ላይ በሚያገኟቸው ጥሩ ተሞክሮዎች አማካኝነት እንደሚባረኩ የተረጋገጠ ነው።—ሚል. 3:10
5 ቤተሰቦች በወንጌላዊነቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረጋቸው እርስ በእርስ እንዲቀራረቡ፣ በአገልግሎት ቅንዓት እንዲኖራቸው፣ ፍሬ እንዲያፈሩና በይሖዋ አገልግሎት ደስታ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል!—ከፊልጵስዩስ 2:1, 2 ጋር አወዳድር።