አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
አካሄዳችሁን ከይሖዋ ጋር በማድረጋችሁ አሁን ምን ተግባራዊ ጥቅሞች ታገኛላችሁ? በሕይወታችሁ ውስጥ የመንግሥቱ ፍላጎት የመጀመሪያውን ቦታ እንዳይዝ የሚያደርጉ ቲኦክራሲያዊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ጣልቃ እንድታስገቡ የሚገጥማችሁን ፈተና እንዴት መቋቋም ትችላላችሁ? (ማቴ. 6:33) ስህተት የሆነውን ትክክል አድርጎ በሚያቀርብ ዓለም ውስጥ መልካሙን ከክፉው መለየት አስቸጋሪ ሆኖባችኋል? (ዕብ. 5:14) እነዚህ ጉዳዮች ከመስከረም 1999 ጀምሮ በሚካሄደው “በአምላክ መንገድ መሄድ በዛሬው ጊዜ የሚያስገኘው ጥቅም” በተባለው የወረዳ ስብሰባ ላይ መልስ ያገኛሉ።—መዝ. 128:1
ቅዳሜ ዕለት የሚኖረው የዚህ የወረዳ ስብሰባ አንድ አዲስ ገጽታ ናሙና የሚሆን የአገልግሎት ስብሰባ አቀራረብ መኖሩ ይሆናል። ሁሉም ከፕሮግራሙ የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ተዘጋጅተው መምጣት እንዲችሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችሁ ለማድረግ የታቀደውን ነገር ለጉባኤዎች ያሳውቃል።
“አቅኚዎች—አካሄዳችሁን ጠብቁ” በሚል ርዕስ የሚቀርበው ክፍል ለአቅኚነት አገልግሎት የሚሆን አመቺ ጊዜ ለማግኘት ጥበብና ምክንያታዊነት መጠቀም የምንችልበትን መንገድ ይገልጽልናል። (ኤፌ. 5:15-17) “ትክክል መስለው ከሚታዩ መንገዶች ተጠበቁ” የሚለው ርዕሰ ጉዳይ በማንኛውም የኑሮ ዘርፍ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ምን እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምንችልበትን መንገድ ያስተምረናል። “ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች በእኛ ላይ የሚኖራቸው ውጤት” የተባለው ንግግር አእምሯችንና ልባችን ለአምላክ ቃል ባለን ፍቅር እንዲሞላ ይረዳናል። “የአምላክ መንገድ ምንኛ ጠቃሚ ነው!” የሚለው የሕዝብ ንግግር ከይሖዋ የጽድቅ ብቃቶች ጋር ተስማምተን በመኖራችን በዛሬው ጊዜ የምናገኛቸውን ተግባራዊ ጥቅሞች ያጎላል።
ራሳቸውን ከወሰኑት የአምላክ አገልጋዮች እንደ አንዱ በመሆን በአምላክ መንገድ መሄድ እንደምትፈልግ በውኃ ጥምቀት አማካኝነት በሕዝብ ፊት ማሳየት ትፈልጋለህ? ከሆነ፣ አስፈላጊ የሆኑትን ዝግጅቶች ማድረግ እንዲቻል ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ አሳውቅ።
ይህ ወቅታዊ የወረዳ ስብሰባ እንዳያመልጣችሁ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። “እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሁሉ፣ በመንገዶቹም የሚሄዱ ምስጉኖች” ናቸውና የሁለቱም ቀን ፕሮግራም አያምልጣችሁ።—መዝ. 128:1