‘ስሙን በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ’
1 መዝሙራዊው “ከእኔ ጋር እግዚአብሔርን አክብሩት፤ ስሙንም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 34:3) በቅርቡ “ከአምላክ ጋር መሄድ” በሚል ጭብጥ የምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ ከተለያዩ ጉባኤዎች ከመጡ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሆነን የይሖዋን ስም በአንድነት ለማወደስ የምንችልበት አጋጣሚ ይሰጠናል። የማረፊያ ቦታን፣ መጓጓዣንና ከሥራ ፈቃድ መጠየቅን ለመሳሰሉት ነገሮች ዝግጅት አድርገሃል? እነዚህን ነገሮች ቀደም ብለን ማመቻቸት አስተዋይነት ነው።—ምሳሌ 21:5
2 ሦስቱንም ቀናት ተገኙ፦ ይሖዋ ሙሴን ‘ይሰሙና ይማሩ ዘንድ ሕዝቡን ሰብስብ’ በማለት አዝዞት ነበር። (ዘዳ. 31:12) ይሖዋ በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት በአውራጃ ስብሰባችን ላይ በሦስቱም ቀናት ልዩ የትምህርት ፕሮግራም አዘጋጅቶልናል። በስብሰባው ላይ የሚያስተምረን ‘የሚበጀንን’ ስለሆነ አንድም ትምህርት እንዲያመልጠን አንፈልግም። (ኢሳ. 48:17) በተቻለ መጠን ጉባኤህ በተመደበበት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጥረት አድርግ። (1 ቆሮ. 14:40) ከአሠሪህ የእረፍት ፈቃድ መጠየቅ የሚያስፈልግህ ከሆነ የደፋሩን የነህምያን ምሳሌ በመኮረጅ አስቀድመህ ለይሖዋ ጸልይና ጥያቄህን አቅርብ። (ነህ. 1:11፤ 2:4) የማያምኑ የቤተሰብ አባሎች ካሉህም በስብሰባው ላይ ለመገኘት እቅድ እንዳለህ አስቀድመህ ብታሳውቃቸው አሳቢነት ይሆናል።
3 በስብሰባው ቦታ ስንደርስ፦ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ስንገኝ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች አሉ። ከቤት በጊዜ መውጣታችን ጉዟችንን የሚያጓትቱ ነገሮች ቢያጋጥሙን እንኳ እንዳናረፍድ የሚረዳን ከመሆኑም በላይ በሰዓቱ ቦታችንን ይዘን በመክፈቻው መዝሙርና ጸሎት ላይ በተረጋጋ ሁኔታ ለመካፈል ያስችለናል። (መዝ. 69:30) ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሊቀ መንበሩ በመድረኩ ላይ ወጥቶ የሚቀመጥ ሲሆን የስብሰባው መክፈቻ ሰዓት መድረሱን የሚጠቁም የመንግሥቱ ሙዚቃ መሰማት ይጀምራል። ፕሮግራሙ ሥርዓት ባለው ሁኔታ እንዲጀምር ሁላችንም በዚህ ወቅት ቦታችንን ይዘን መቀመጥ አለብን።—1 ቆሮ. 14:33, 40
4 የአምላክ ቃል ‘የምናደርገውን ሁሉ በፍቅር እንድናደርግ’ ይመክረናል። (1 ቆሮ. 16:14) ለሌሎች ያለን አሳቢነት ጠዋት በ2:00 ሰዓት የስብሰባው ቦታ በሮች በሚከፈቱበት ወቅት ከሌሎች ቀድመን የምንፈልገውን መቀመጫ ለማግኘት ሌሎችን እየገፈታተርን እንዳንሯሯጥ ያደርገናል። መቀመጫ መያዝ የሚቻለው የቤተሰባችን አባል ለሆኑና አብረውን በመኪና ለሚጓዙ ብቻ ነው።—1 ቆሮ. 13:5፤ ፊልጵ. 2:4
5 እባካችሁ በምሣ እረፍት ወቅት ምግብ ለማግኘት ከስብሰባው ቦታ ውጪ ከምትሄዱ የራሳችሁን ምግብ ከቤት ይዛችሁ ብትመጡ የተሻለ እንደሆነ አስታውሱ። እንዲህ ማድረጋችን ከሌሎች ጋር ለመተናነጽ የሚያስችል ጊዜ ለማግኘትና የከሰዓት በኋላው ስብሰባ ሲጀመር በቦታችን ለመገኘት ይረዳናል። አስፈላጊ ከሆነ በመቀመጫችን ሥር ልናስቀምጠው የምንችለው ምግብን አቀዝቅዞ ለማቆየት የሚችል መጠነኛ የምግብ መያዣ መጠቀም ይቻላል። ሆኖም ትላልቅ የዚህ ዓይነት የምግብ መያዣዎችን፣ ጠርሙሶችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
6 መንፈሳዊ ድግስ ተዘጋጅቶልናል፦ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ እውነተኛውን አምላክ ‘ለመፈለግ ልቡን አዘጋጅቶ’ ነበር። (2 ዜና 19:3) እኛስ ከስብሰባው በፊት ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? በግንቦት 22, 2004 (እንግሊዝኛ) እና ነሐሴ 2004 ንቁ! መጽሔቶች የጀርባ ሽፋን ላይ የወጡት ርዕሶች ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግብዣ እንደተዘጋጀልን ያሳዩናል። ይሖዋ ላዘጋጀልን ለዚህ ድግስ ያለህን አድናቆት ለማሳደግ ለምን ጊዜ ወስደህ በእነዚህ ርዕሶች ላይ አታሰላስልም? ልባችንን ማዘጋጀት በስብሰባው ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በሚገባ ለመረዳትና ተግባራዊ ለማድረግ እንድንችል እንዲረዳን ይሖዋን በጸሎት መጠየቅንም ይጨምራል።—መዝ. 25:4, 5
7 በአምላክ ቃል አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንደምንችል ስለምናውቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመማር የምንችልበትን አጋጣሚ በጉጉት እንጠባበቃለን። (1 ጴጥ. 2:2 የ1954 ትርጉም ) በመሆኑም “ከአምላክ ጋር መሄድ” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተን ‘የይሖዋን ስም በአንድነት ከፍ ከፍ እናድርግ።’—መዝ. 34:3
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. በቅርቡ የአምላክን ስም በአንድነት ለማወደስ የሚያስችል ምን አጋጣሚ ይኖረናል? ከወዲሁ ለመዘጋጀት ምን ማድረግ እንችላለን?
2. በአውራጃ ስብሰባችን ላይ በሦስቱም ቀናት ለመገኘት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ጥረታችን እንዲሳካልን ምን ሊረዳን ይችላል?
3. በስብሰባው ቦታ ቀደም ብሎ ለመድረስ እቅድ ማውጣቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4. መቀመጫ በምንይዝበት ወቅት ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?
5. ለምሳ እረፍት ምን ዝግጅት ማድረግ ይቻላል? ይህስ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
6. በስብሰባው ላይ ለሚቀርበው ትምህርት ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
7. በጉጉት የምንጠብቀው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ?
[ገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ማድረግ የምንችልባቸው መንገዶች
◼ አስቀድመን እቅድ ማውጣት
◼ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት
◼ ልባችንን ማዘጋጀት