ይሖዋን ለማወደስ በአንድነት መሰብሰብ
1. በቅርቡ የምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ ጭብጥ ምንድን ነው? ይሖዋ ክብር የሚገባው ለምንድን ነው?
1 ይሖዋ ታላቅ ኃይል፣ የማይመረመር ጥበብና ፍጹም ፍትሕ ያለው እንዲሁም የፍቅር ተምሳሌት የሆነ አምላክ ነው። ፈጣሪ፣ ሕይወት ሰጪና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ ልናመልከው የሚገባን እርሱን ብቻ ነው። (መዝ. 36:9፤ ራእይ 4:10, 11፤ 15:3, 4) በቅርቡ “ለአምላክ ክብር ስጡት” በሚል ጭብጥ የምናደርገው የአውራጃ ስብሰባ ይሖዋ እውነተኛ አንድ አምላክ እንደመሆኑ መጠን እርሱን ለማክበር ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።—መዝ. 86:8-10
2, 3. አስቀድመን እቅድ ማውጣታችን ከስብሰባው የተሟላ ጥቅም እንድናገኝ የሚረዳን እንዴት ነው?
2 አስቀድሞ እቅድ ማውጣት አስፈላጊ ነው:- ይሖዋ ካዘጋጀልን መንፈሳዊ ድግስ ሙሉ ጥቅም ለማግኘት እንድንችል ጥሩ እቅድ ማውጣት አስፈላጊ ነው። (ኤፌ. 5:15, 16) የምታርፍበትን ቦታና መጓጓዣህን አዘጋጅተሃል? ከሥራ ወይም ከትምህርት ቤት ፈቃድ ጠይቀሃል? እነዚህን አስፈላጊ ጉዳዮች ጊዜው ከመድረሱ በፊት ከወዲሁ ማጠናቀቅ ይኖርብሃል። ፈቃድ ለመጠየቅ ዛሬ ነገ የምትል ከሆነ ይህ አስደሳች ስብሰባ ሊያመልጥህ ይችላል። ሁላችንም ብንሆን የትኛውም የስብሰባ ቀን ሊያመልጠን አይገባም።
3 በሦስቱም ቀናት በስብሰባው ቦታ ቀደም ብለህ ለመገኘት ግብ አውጣ። እንዲህ ማድረግህ ስብሰባው በመዝሙር ከመከፈቱ በፊት ቦታህን እንድትይዝ ከማስቻሉም በላይ አእምሮህን ሰብሰብ አድርገህ የሚቀርበውን ትምህርት ለመከታተል ይረዳሃል። በእያንዳንዱ ቀን በ2:00 ላይ የመሰብሰቢያው ቦታ በር ይከፈታል። እባካችሁ ቦታ መያዝ የሚፈቀደው ለቤተሰቦቻችሁ አባላትና አብረዋችሁ በመኪና ለሚጓዙ ሰዎች ብቻ ነው።
4. ሁላችንም ምሳችንን ይዘን እንድንመጣ ማሳሰቢያ የተሰጠን ለምንድን ነው?
4 በምሳ እረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ከመውጣት ይልቅ ሁሉም የየራሱን ምግብ ይዞ ቢመጣ የተሻለ እንደሆነ ልናሳስባችሁ እንወዳለን። እንዲህ ማድረጉ ግርግር የሚቀንስ ከመሆኑም በላይ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ለመጨዋወት የሚያስችል ሰፋ ያለ ጊዜ እንዲኖረን ያደርጋል። (መዝ. 133:1-3) እባካችሁ ጠርሙሶችንና የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት እንደማይፈቀድ አትርሱ።
5. ልባችንን ለስብሰባው ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
5 በማዳመጥ እውቀት ቅሰሙ:- ዕዝራ የአምላክን ቃል ለመማር ልቡን በጸሎት አዘጋጅቶ ነበር። (ዕዝራ 7:10) ልቡን ወደ ይሖዋ ትምህርቶች አዘንብሎ ነበር። (ምሳሌ 2:2) እኛም ከቤት ከመውጣታችን በፊት በስብሰባው ጭብጥ ላይ በማሰላሰልና ከቤተሰባችን አባላት ጋር በመወያየት ልባችንን ለስብሰባው ማዘጋጀት እንችላለን።
6. ትኩረታችንን አሰባስበን ፕሮግራሙን እንድንከታተል ምን ሊረዳን ይችላል? (ሣጥኑን ተመልከት።)
6 በትልልቅ የስብሰባ ቦታዎች ትኩረታችንን ሊሰርቁ የሚችሉ በርካታ ነገሮች አሉ። እነዚህ ነገሮች ተናጋሪውን በትኩረት እንዳንከታተል ሐሳባችንን ይሰርቁብናል። ይህም ጠቃሚ ትምህርቶች እንዲያመልጡን ያደርጋል። ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የቀረበው ሣጥን ትኩረታችንን ለማሰባሰብ የሚያስችሉንን ነጥቦች ይዟል።
7, 8. ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
7 ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ:- በስብሰባው ወቅት ካሜራና የቪዲዮ መቅረጫ መጠቀም የሚቻል ቢሆንም የሌሎችን ትኩረት ላለመስረቅ ከመቀመጫችን ባንነሳ ጥሩ ነው። ሞባይል ስልክ ወይም ፔጀር የምንይዝ ከሆነ ሌሎችን እንዳይረበሹ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ማንኛውንም የኤሌክትሪክ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለ የኤሌክትሪክ ወይም የድምፅ መሥመር ጋር ማያያዝ አይፈቀድም።
8 በአንድነት ተሰብስበን ይሖዋን የምናወድስበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። በሁሉም የስብሰባው ቀናት በመገኘት፣ በጥሞና በማዳመጥና የተማርነውን በሥራ ላይ በማዋል እርሱን ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ዘዳ. 31:12
[ገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በጥሞና ለማዳመጥ
▪ በንግግሮቹ ርዕስ ላይ አሰላስል
▪ ጥቅሶችን እያወጣህ ተመልከት
▪ አጭር ማስታወሻ ያዝ
▪ ልትሠራባቸው ያሰብካቸውን ነጥቦች ለይተህ ጻፍ
▪ የተማርከውን ከልስ