የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት —አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 በ1895 በጊዜው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ላይ ተሰብስበው የሚያጠኑባቸው ቡድኖች የዶውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክበቦች ይባሉ ነበር። ጥናቱ የሚካሄደውም ሚሌኒያል ዶውን በተባለው መጽሐፍ ተከታታይ ጥራዞች ላይ ተመሥርቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ስብሰባዎች የቤሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክበቦች ተብለው ይጠሩ ጀመር። (ሥራ 17:11) አብዛኛውን ጊዜ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አመቺ በሚሆንላቸው ምሽት በግለሰቦች ቤት ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ስብሰባዎች በዛሬው ጊዜ ለሚደረገው የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ፈር ቀዳጅ ናቸው።
2 ማበረታቻና ድጋፍ ለመስጠት፦ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖች ሆን ተብሎ አነስተኛ ቁጥር እንዲኖራቸው ስለሚደረግ ተሰብሳቢዎቹ ተሳትፎ በማድረግ እምነታቸውን ለመግለጽ ሰፊ አጋጣሚ ያገኛሉ። ይህም ‘በእያንዳንዳቸው እምነት እርስ በርሳቸው ለመበረታታት’ ያስችላቸዋል።—ሮሜ 1:12
3 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ የሚያስተምርበትን መንገድ መመልከት ‘የእውነትን ቃል በትክክል የማስረዳት’ ችሎታችንን ለማዳበር ሊረዳን ይችላል። (2 ጢሞ. 2:15) ትምህርቱ የተመሠረተበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ እንዴት እንደሚያጎላው ልብ ብለህ ተመልከት። እንደሚጠናው ጽሑፍ ዓይነት በጥናቱ መደምደሚያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በመጠቀም ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን መከለስ ይችላል። የእርሱ መልካም ምሳሌነት በክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ላይ የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል ሊረዳን ይችላል።—1 ቆሮ. 11:1
4 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በየሳምንቱ የሚካሄደውን ጥናት ከመምራት በተጨማሪም በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን አለበት። ከአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ጋር በመተባበር ለመስክ አገልግሎት አመቺ የሆኑ ፕሮግራሞችን ያወጣል። ሁሉም የቡድኑ አባላት ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ክርስቲያናዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መርዳት የሚችልበትን ሁኔታ ያመቻቻል።—ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ቆሮ. 9:16
5 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ በቡድኑ ውስጥ ላለው ለእያንዳንዱ አስፋፊ መንፈሳዊ ደኅንነት ያስባል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይና ከሌሎች ጋር በመስክ አገልግሎት አብሮ በሚሠራበት ወቅት ይህን አሳቢነቱን በተግባር ያሳያል። አንዳንድ ጊዜም ወንድሞችን ቤታቸው ሄዶ በመጠየቅ በመንፈሳዊ ያበረታታቸዋል። ሁሉም የቡድኑ አባላት በፈለጉ ጊዜ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹን ቀርበው መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያደርግላቸው ከመጠየቅ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም።—ኢሳ. 32:1, 2
6 እርስ በርስ ለመበረታታት፦ የአምላክ ሕዝቦች እንቅስቃሴ በታገደባቸው አገሮች ወንድሞች ብዙውን ጊዜ የሚሰበሰቡት በትናንሽ ቡድኖች ነው። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻችን የታገዱ ቢሆንም አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ከ10 እስከ 15 እየሆንን በትናንሽ ቡድኖች ሳምንታዊ ስብሰባችንን እናደርግ ነበር። በስብሰባዎቹ ላይ ከሚካሄደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥናትም ሆነ ከስብሰባው በኋላ ከሚደረገው ጭውውት መንፈሳዊ ማበረታቻ እናገኝ ነበር። ተሞክሯችንን የምንለዋወጥ ሲሆን ይህም ሁላችንም በተመሳሳይ ትግል ውስጥ እንዳለን እንድንገነዘብ ረድቶናል።” (1 ጴጥ. 5:9) እኛም እንዲሁ የመጽሐፍ ጥናትን ዝግጅት ሙሉ በሙሉ በመደገፍ እርስ በርስ እንበረታታ።—ኤፌ. 4:16
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መካሄድ የጀመረው እንዴት ነበር?
2. በመጽሐፍ ጥናት ላይ ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እያንዳንዳችን ምን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን?
3, 4. የመጽሐፍ ጥናት ዝግጅት አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚረዳን እንዴት ነው?
5. ከመጽሐፍ ጥናት ዝግጅት በግለሰብ ደረጃ ምን እርዳታ ማግኘት ይቻላል?
6. (ሀ) በአንዳንድ አገሮች ያሉ ወንድሞቻችን በትናንሽ ቡድኖች ሆነው በመሰብሰባቸው የተበረታቱት እንዴት ነው? (ለ) የመጽሐፍ ጥናት ዝግጅት አንተን በግልህ የጠቀመህ እንዴት ነው?