ከመስክ አገልግሎት ስምሪት ቡድናችሁ ጥቅም ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው?
1. በመጽሐፍ ጥናት አማካኝነት ይገኙ የነበሩትና አሁን በመስክ አገልግሎት ስምሪት ቡድናችን በኩል የምናገኛቸው ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው?
1 የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት የነበሩት አንዳንድ ገጽታዎች ይናፍቋችኋል? በዚያ ፕሮግራም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ዘና ባለ ሁኔታ ይሰበሰቡ ነበር። ይህ ደግሞ በመንፈሳዊ ለመበረታታት የሚያስችለንን ወዳጅነት ለመመሥረት ቀላል ሁኔታ ፈጥሮልን ነበር። (ምሳሌ 18:24) የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች፣ የእያንዳንዳችንን ሁኔታ ለመረዳት ጥሩ አጋጣሚ ስለነበረው በግለሰብ ደረጃ ማበረታቻ ለመስጠት ይቀለው ነበር። (ምሳሌ 27:23፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) እነዚህን ጥቅሞች አሁንም ከመስክ አገልግሎት ስምሪት ቡድናችን ማግኘት እንችላለን።
2. የማበረታቻ ምንጭ በሆነው በስምሪት ቡድናችን ውስጥ ወዳጅነታችንን ለማጠናከር ቅድሚያውን ወስደን ምን ማድረግ እንችላለን?
2 ቅድሚያውን ውሰዱ፦ በአብዛኛው በስምሪት ቡድን ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥር በመጽሐፍ ጥናት ውስጥ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው። ከሌሎች ጋር “አንድ ላይ ሆናችሁ” በምሥራቹ ሥራ መካፈላችሁ እርስ በርስ ይበልጥ እንድትቀራረቡ ያደርጋችኋል። (ፊልጵ. 1:27) በቡድናችሁ ውስጥ ካሉ አስፋፊዎች መካከል ከስንቶቹ ጋር አገልግላችኋል? በዚህ ረገድ “ልባችሁን ወለል” አድርጋችሁ መክፈት ትችላላችሁ? (2 ቆሮ. 6:13) በተጨማሪም ከቡድናችን አባላት ውስጥ አንዱን በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችን ላይ እንዲገኝ ወይም አብሮን እንዲመገብ ልንጋብዘው እንችላለን። በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ የስምሪት ቡድኖች ከሌላ ቦታ ተጋብዘው የሚመጡ ተናጋሪዎችን በየተራ ቤታቸው ተቀብለው የማስተናገድ ልማድ አላቸው። አንድ ቡድን ተረኛ በሚሆንበት ሳምንት፣ ተናጋሪው አብሯቸው መቆየት ባይችልም እንኳ አስፋፊዎቹ አብሮ ለመመገብና ለመጨዋወት ይገናኛሉ።
3. በስምሪት ቡድናችን ውስጥ እረኝነት እንዲደረግልን የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉ?
3 የጉባኤው የስብሰባ ቀናት ከሦስት ወደ ሁለት ዝቅ መደረጉ አስፋፊዎች የሚደረግላቸውን የእረኝነት ጉብኝት ይቀንሰዋል ማለት አይደለም። የቡድን የበላይ ተመልካቾች በቡድናቸው ውስጥ ለሚገኙ አስፋፊዎች በግለሰብ ደረጃ ማበረታቻና ሥልጠና የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። የቡድን የበላይ ተመልካቻችሁ አብሯችሁ አገልግሎ የማያውቅ ከሆነ ለምን አብሯችሁ እንዲያገለግል አትጠይቁትም? በተጨማሪም የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በየወሩ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከአንድ ቡድን ጋር አብሮ ያገለግላል። ጥቂት የስምሪት ቡድኖች ባሉበት አነስተኛ ጉባኤ ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱን ቡድን በዓመት ሁለት ጊዜ ለመጎብኘት ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። ታዲያ ቡድናችሁ በሚጎበኝበት ወቅት አገልግሎት ለመውጣት ፕሮግራማችሁን ታስተካክላላችሁ?
4. (ሀ) የስምሪት ስብሰባዎች የተደራጁት እንዴት ነው? (ለ) ለመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ቤታችንን ስለ መፍቀድ ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
4 አብዛኛውን ጊዜ እያንዳንዱ ቡድን ቅዳሜና እሁድ ለየብቻ የስምሪት ስብሰባ ማድረጉ ጠቃሚ ነው። በተመሳሳይ ሰዓት የሚከናወኑ የተለያዩ ስብሰባዎች መኖራቸው አስፋፊዎች ወደ ስምሪት ስብሰባውም ሆነ ወደ ክልላቸው መሄድ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። አስፋፊዎች ወዲያው ተመድበው በፍጥነት ወደ ክልላቸው መሄድ ይችላሉ። የቡድን የበላይ ተመልካቹም በሥሩ ላሉት አስፋፊዎች በቅርበት እርዳታ መስጠት ይችላል። ያም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቡድኖች በአንድ ላይ የስምሪት ስብሰባ ማድረጋቸው ጥሩ ሊሆን ይችላል። ጉባኤው በወሩ የመጀመሪያ ቅዳሜ ወይም ከመጠበቂያ ግንብ ጥናት በኋላ የስምሪት ስብሰባ የሚያደርገው አንድ ላይ ከሆነ በአብዛኛው እያንዳንዱ ቡድን አብሮ ቢቀመጥና ስብሰባው በጸሎት ከመደምደሙ በፊት የእያንዳንዱ ቡድን የበላይ ተመልካች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የራሱን ቡድን ቢያሰማራ ጠቃሚ ነው።—“ቤትህን ለስምሪት ስብሰባ መፍቀድ ትችላለህ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
5. የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቢቀርም ስለምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
5 የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቢቀርም ይሖዋ ፈቃዱን ለማድረግ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ መስጠቱን አላቋረጠም። (ዕብ. 13:20, 21) በይሖዋ እንክብካቤ ውስጥ እስካለን ድረስ አንዳች አይጎድልብንም። (መዝ. 23:1) በስምሪት ቡድናችን አማካኝነት ብዙ በረከቶችን ማግኘት እንችላለን። ቅድሚያውን ከወሰድን እንዲሁም ‘በብዛት የምንዘራ ከሆነ በብዛት እናጭዳለን።’—2 ቆሮ. 9:6
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቤትህን ለስምሪት ስብሰባ መፍቀድ ትችላለህ?
በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ በርካታ ቡድኖች አንድ ላይ የስምሪት ስብሰባ የሚያደርጉት እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች የሚደረጉባቸው በቂ ቤቶች ስለሌሉ ይሆናል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የጉባኤ ስብሰባ ክፍል ስለሆነ እንዲህ ያለው ዝግጅት ቤታችን ውስጥ መደረጉ ትልቅ መብት ነው። ታዲያ ቤትህን ለስምሪት ስብሰባ መፍቀድ ትችላለህ? ቤትህ አነስተኛ በመሆኑ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አትበል። ሽማግሌዎች ቤትህ የሚገኝበትን አካባቢ እንዲሁም መጽሐፍ ጥናት ይደረግ በነበረበት ጊዜ አንድን ቤት ለመጠቀም ያገናዝቧቸው የነበሩትን ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገቡ ይሆናል። በቤትህ የስምሪት ስብሰባ እንዲደረግ የምትፈልግ ከሆነ ለቡድንህ የበላይ ተመልካች መናገር ትችላለህ።