የወረዳና የልዩ ስብሰባዎችን ለመከለስ የተደረገ አዲስ ዝግጅት
የሰይጣን ዓለም በክፋት እየባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት ይሖዋ “በኀጢአት መኖርንና ዓለማዊ ምኞትን ክደን፣ በአሁኑ ዘመን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ፣ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት” ለመኖር እንድንችል በመንፈሳዊ ያጠነክረናል። (ቲቶ 2:12) ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ከሚያደርግልን ዝግጅቶች መካከል ዓመታዊ የሆኑት የወረዳና የልዩ ስብሰባ ፕሮግራሞች ይገኙበታል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም ) እነዚህ መንፈሳዊ ስብሰባዎች ምንኛ የሚያበረታቱና የሚያጠናክሩ ናቸው!
በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት ለማስታወስና በሥራ ላይ ለማዋል እንድንችል ለመርዳት ትምህርቱን ለመከለስ የሚያስችል አዲስ ዝግጅት ከ2005 የአገልግሎት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል። በዚህ የመንግሥት አገልግሎታችን አባሪ ገጽ 3 እና 4 ላይ በስብሰባዎቹ ላይ ከሚቀርቡት ትምህርቶች ቀንጨብ ተደርጎ የተወሰደ ሐሳብና እያንዳንዱን ስብሰባ ለመከለስ የሚያስችሉ ጥያቄዎች ወጥተዋል። ጉባኤዎች ስብሰባዎቹ ከመካሄዳቸው በፊትና ከተካሄዱ በኋላ በአባሪው ላይ የወጡትን ሐሳቦች ይከልሳሉ። እነዚህ ክፍሎች የሚቀርቡት እንዴት ነው?
ጉባኤው የወረዳ ስብሰባ ከማድረጉ አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ አስፋፊዎች ስብሰባውን በጉጉት እንዲጠባበቁት ለማድረግ “አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም” በሚለው ርዕስ ላይ የተመሠረተ የአሥር ደቂቃ ንግግር በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ይቀርባል። ተናጋሪው ወንድም የክለሳ ጥያቄዎቹንም የሚጠቅስ ሲሆን ሁሉም ስብሰባው ከተካሄደ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለሚደረገው ክለሳ እንዲረዳቸው በስብሰባው ላይ ማስታወሻ እንዲይዙ ያበረታታል።
ስብሰባው ከተካሄደ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን በቀረበው ትምህርት ላይ የተመሠረተ የ15 ደቂቃ ክለሳ ይቀርባል። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ በሁለተኛው ቀን የቀረበውን ትምህርት ለመከለስ 15 ደቂቃ ይመደባል። የክለሳ ውይይቶቹ የሚካሄዱት በዚህ የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 3 ላይ በቀረቡት ጥያቄዎች ተመሥርተው ነው። ክለሳው በትምህርቱ ተግባራዊ ጠቀሜታ ላይ የሚያተኩር ይሆናል። ለእነዚህ የክለሳ ውይይቶች የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ሽማግሌዎች ሌሎች የአገልግሎት ስብሰባ ክፍሎችን ለማሳጠር፣ ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ወይም ለማስቀረት ሊወስኑ ይችላሉ።
ለልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራምም ተመሳሳይ ዝግጅት የሚደረግ ሲሆን ከወረዳ ስብሰባ የሚለየው ሙሉው የስብሰባ ፕሮግራም በ15 ደቂቃ ብቻ የሚከለስ መሆኑ ነው። ሁላችንም የዚህን የመንግሥት አገልግሎታችን እትም አባሪ በጥሩ ቦታ አስቀምጠነው ከይሖዋ ከምናገኘው ግሩም ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን ልንገለገልበት እንችላለን።—ኢሳ. 48:17, 18