መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ተጠቀሙበት
1 በአገልግሎት ላይ ልናበረክተው ያሰብነው የትኛውንም ጽሑፍ ቢሆን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ልናነብ የምንችለው ትኩረታቸውን የሚስብ ጥቅስ ማዘጋጀታችን ጠቃሚ ነው። (ዕብ. 4:12) በምታበረክተው ጽሑፍ ላይ የሚገኝ ጥቅስ መርጠህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማንበብህ ጽሑፉን ለማስተዋወቅ ቀላል ያደርግልሃል። በአንዳንድ አካባቢዎች አስፋፊዎች በመንገድ ላይ ወይም ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በእጃቸው መያዙን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።
2 ውይይቱን በጥቅስ ጀምር፦ አንዳንድ አስፋፊዎች ቀጥለው ሊያነቡት ባሰቡት ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ቀለል ያለ የአመለካከት ጥያቄ ለሚያነጋግሩት ሰው በማቅረብ ውይይቱን ይጀምራሉ። እንዲህ ማድረጉ የሰውየውን ትኩረት ወዲያውኑ ወደ አምላክ ቃል ለማዞር ይረዳል። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን የመግቢያ ሐሳቦች አንተ ባለህበት ክልል ውስጥ ልትጠቀምባቸው ትችል ይሆን?
◼ “ኃይል ቢኖርዎት ኖሮ በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹትን ለውጦች ያመጡ ነበር?” ራእይ 21:4ን አንብብ።
◼ “የምንኖርበት ዘመን ይህን ያህል አስጨናቂ የሆነው ለምንድን ነው?” 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብብ።
◼ “ሁሉም ሰው በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ቢያደርግ የተሻለ ኅብረተሰብ የሚኖር ይመስልዎታል?” ማቴዎስ 7:12ን አንብብ።
◼ “ልጆችዎ በዚህ ጥቅስ ላይ የሰፈረው ሁኔታ ሲፈጸም መመልከት የሚችሉ ይመስልዎታል?” መዝሙር 37:10, 11ን አንብብ።
◼ “እነዚህ ቃላት የሚፈጸሙበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ?” ኢሳይያስ 33:24ን አንብብ።
◼ “በዚህ ጥቅስ ላይ ስለተገለጸው የመንግሥት ለውጥ ከዚህ በፊት ሰምተው ያውቃሉ?” ዳንኤል 2:44ን አንብብ።
◼ “አምላክን እንደሚከተለው ብለው ለመጠየቅ አስበው ያውቃሉ?” ኢዮብ 21:7ን አንብብ።
◼ “በሞት የተለዩንን የምንወዳቸው ሰዎች እንደገና ማግኘት የምንችል ይመስልዎታል?” ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።
◼ “የሞቱ ሰዎች ስለ እኛ ማወቅ ይችላሉ?” መክብብ 9:5ን አንብብ።
3 ጥቅሱን ማብራራት፣ በምሳሌ ማስረዳትና ከምታወያየው ነጥብ ጋር ማዛመድ፦ ለመወያየት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ስታገኝ ውይይቱን በአጭሩ ከመቋጨት ይልቅ ጊዜ ወስደህ ያነበብክለትን ጥቅስ በማብራራት፣ በምሳሌ በማስረዳትና ከምትወያዩበት ነጥብ ጋር በማዛመድ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንለት እርዳው። (ነህ. 8:8) ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት ሲረዱትና ሲቀበሉት በሕይወታቸው ውስጥ አስደናቂ ለውጦች እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።—1 ተሰ. 2:13
4 የግለሰቡን ፍላጎት ለማሳደግ እየጣርክ በመጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ መጠቀምህን ቀጥል። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግም ከላይ በተገለጸው መንገድ መጠቀም ትችላለህ። ይኸውም (1) ተስማሚ የሆነ ጥቅስ ምረጥ። (2) ጥቅሱን በተመለከተ ቀለል ያለ የአመለካከት ጥያቄ ካቀረብህለት በኋላ ጥቅሱን አንብበው። (3) ጥቅሱን በማብራራት፣ በምሳሌ በማስረዳትና ከምትወያዩበት ጉዳይ ጋር በማዛመድ ነጥቡ እንዲገባው አድርግ። ተመላልሶ መጠየቅ ባደረግህለት ቁጥር ግለሰቡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እውቀት ለማሳደግ ጥረት አድርግ። ብዙም ሳይቆይ ጥናት ልታስጀምረው ትችል ይሆናል!
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
1. ለመስክ አገልግሎት ስትዘጋጅ ምን ማድረግ ትችላለህ?
2. (ሀ) ውይይቱን በጥቅስ መጀመር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንተ ባለህበት ክልል ውስጥ ሰዎችን የሚያሳስቧቸው የትኞቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦች ናቸው?
3. ሰዎች የምናነብላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዲረዱት ምን ማድረግ እንችላለን?
4. ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?