ክፍል 3—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም
1. ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና በጥቅሶች ላይ ማተኮር ያለብን ለምንድን ነው?
1 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናበት ዓላማ የአምላክን ቃል ተረድተውና ተቀብለው በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ “ደቀ መዛሙርት” እንዲሆኑ ለመርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ተሰ. 2:13) ስለሆነም ጥናቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተደገፈ መሆን አለበት። ጥናት ሲጀምሩ ከግል መጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ እንዴት ጥቅስ ማውጣት እንደሚቻል ማሳየቱ ጠቃሚ ነው። ሆኖም እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ጥቅሶችን መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2. የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መነበብና መብራራት እንዳለባቸው መወሰን የምንችለው እንዴት ነው?
2 የሚነበቡትን ጥቅሶች ምረጥ። በዝግጅትህ ወቅት በትምህርቱ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ጥቅስ ከሚጠናው ነጥብ ጋር ምን ዝምድና እንዳለው በቅድሚያ ካስተዋልክ በኋላ በጥናቱ ወቅት የትኞቹን ጥቅሶች አውጥታችሁ እንደምታነቡና እንደምትወያዩባቸው ወስን። አብዛኛውን ጊዜ ለእምነታችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የሚሆኑትን ጥቅሶች ማንበቡ ተመራጭ ይሆናል። ዋናውን ነጥብ ለማብራራት ሳይሆን ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ብቻ ሲባል የተጠቀሱ ጥቅሶችን ማንበብ ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም። የእያንዳንዱን ተማሪ ፍላጎትና ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገባ።
3. በምናስጠናበት ጊዜ ጥያቄዎችን መጠቀም ምን ጥቅም አለው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
3 በጥያቄዎች ተጠቀም። ለተማሪህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንተ ከምታብራራለት ይልቅ እርሱ ራሱ እንዲያብራራልህ ማድረጉ የተሻለ ነው። በዘዴ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እንዲህ እንዲያደርግ ልትረዳው ትችላለህ። ጥቅሱ የተጠቀሰበት ዓላማ ግልፅ ከሆነ ግን በአንቀጹ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ እንዴት እንደሚደግፈው ልትጠይቀው ትችላለህ። አንዳንዴ ደግሞ ተማሪው ወደ ተገቢው መደምደሚያ እንዲደርስ ለመርዳት ቀጥተኛ ወይም ተከታታይ ጥያቄዎችን መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል። ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ካስፈለገ ተማሪው መልስ ከመለሰ በኋላ ይህን ማድረጉ ይመረጣል።
4. ያነበብነውን ጥቅስ ምን ያህል ማብራራት ያስፈልገናል?
4 አታንዛዛ። ጥሩ ችሎታ ያለው ቀስተኛ ዒላማውን ለመምታት የሚያስፈልገው አንድ ቀስት ብቻ ነው። በተመሳሳይም ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ አንድን ነጥብ ለማስረዳት ቃላት አያበዛም። የፈለገውን ሐሳብ ባልተወሳሰበና ባልተንዛዛ መንገድ በትክክል መግለጽ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አንድን ጥቅስ ለመረዳትና ለተማሪው ለማስረዳት በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። (2 ጢሞ. 2:15) ይሁንና እያንዳንዱን ጥቅስ ከተለያየ አቅጣጫ ለማብራራት መሞከር አይኖርብህም። እየተጠና ያለውን ትምህርት የሚደግፈውን ሐሳብ ብቻ ጥቀስ።
5, 6. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን የአምላክን ቃል በሕይወታቸው እንዲሠሩበት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ሆኖም ምን ከማድረግ መጠንቀቅ አለብን?
5 በሥራ ላይ እንዲያውል እርዳው። ተስማሚ ሆኖ በምታገኝበት ጊዜ ተማሪው የተነበበውን ጥቅስ በራሱ ሕይወት እንዴት ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው። ለምሳሌ ያህል በስብሰባዎች ላይ መገኘት ካልጀመረ ጥናትህ ጋር በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ እየተወያየህ ካለህ ስለ አንዱ ሳምንታዊ ስብሰባ ካብራራህለት በኋላ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ልትጋብዘው ትችላለህ። ተማሪው በአምላክ ቃል ተገፋፍቶ ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስፈልገውን እርምጃ ይውሰድ እንጂ አንተ አትጫነው።—ዕብ. 4:12
6 ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ተልእኮ ስንፈጽም የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ በመጠቀም ሰዎች “አምነው እንዲታዘዙ” እናድርግ።—ሮሜ 16:26